Monday, March 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ዋጋ ግሽበት ምን አሉ?

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ዘለግ ያለውን ጊዜ የወሰዱት ደግሞ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ይበልጥ ደግሞ ከወቅታዊ የዋጋ ግሽበት አንፃር የሰጡት ማብራሪያ ሰፋ ያለውን ጊዜ ወስዷል፡፡  

እሳቸው እንዳመለከቱትም፣ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ጊዜ መውሰዱ የሚሻል ነው፡፡ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ መንግሥታቸው እየሠራ ያለውን ሥራ፣ ከኢኮኖሚ ጉዳዮች አንፃር የነበሩ ተግዳሮቶችን እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተገኙ መልካም ውጤቶችንም በዝርዝር ያቀረቡበት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ብትሆንም ጥሩ የሚባል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚጠበቅ ስለመሆኑም አመልክተዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ከፓርላማ አባላት ጭምር በተለያየ መንገድ በጥያቄ የቀረበበት ዋነኛ ጉዳይ ወቅታዊው የዋጋ ንረት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ የችግሩን መንስዔና አዲሱ መንግሥት ሊወስድ ያሰበውን ዕርምጃ በዝርዝር ያቀረቡበትና እንደ አገር ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነ የጠቀሱበት ነው፡፡

የዋጋ ንረቱ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም የራሱን ተፅዕኖ ማሳረፉንም ከገለጻቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ይህንንም ‹‹በአብዛኛው ዘርፎች ያመጣናቸውን ለውጦች በኢኮኖሚ ልናመጣ ያልቻልንበት አንዱ የዋጋ ንረት ነው፤›› ማለታቸው ማሳያ ይሆናል፡፡ ‹‹የእኛም የቆየ ችግር አለ፡፡ ዓለም ላይ የተፈጠረው አጠቃላይ የዋጋ ንረት የሚፈጥረው ጫና አለ፡፡ እሱ ላይ እንዳናተኩር ደግሞ ግራና ቀኝ የያዙን በጣም በርካታ ምክንያቶች አሉ፤›› በማለት ከዋጋ ንረቱ ጋር የነበረውን ችግር አመላክተዋል፡፡

የዋጋ ግሽበትና መንስዔዎች

በዋጋ ግሽበት ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት አንድ ያለመሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ አንደኛው ሌላኛውን ያባብሰዋልም በማለት ከገለጹ በኋላ፣ የኑሮ ውድነቱ ላለፉት 16 ዓመታት ነበር ብለው የዋጋ ንረቱ አሁን የመጣ ስላለመሆኑ አመላክተዋል፡፡ አንደኛው በሌላው ላይ እየተደመረ የመጣ ግሽበት ስለመሆኑ በመጥቀስም፣ ለሸማቾች ሸምቶ ማደር በጣም ፈታኝ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ ጥረት ልማትን በማፋጠን የሕዝብን ገቢ በማሳደግ ምርትን ማሳደግ፣ ግሽበት የሚያመጡ ዕቃዎችን ለይቶ በተቻለ መጠን ገበያውን ማረጋጋትና የገበያ ሥርዓቱ ያለበትን ጫና መፍታት ይጠይቃልም ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለተከሰተው የዋጋ ንረት በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዋናው መንስዔ የአቅርቦትና ፍላጎት ያለመመጣጠን ነው፣ የሰው ቁጥርና ፍላጎት እያደገ በዚያ ልክ ምርት ማደግ የማይችል ከሆነ በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት ዋጋን እንዲያሻቅብ ማድረጉንና ሌሎች መንስዔ ያሏቸውን ጉዳዮች አብራርተዋል፡፡

የምርት ዕጥረት ብቻ ሳይሆን ምርቱም እያለ የንግድ ሰንሰለቱ የሚያስከትላቸው ሳንካዎች በራሱ ሊታዩ እንደሚገባቸው በማመልከትም፣ በዚህ ጉዳይ በጣም ብዙ ችግሮች እየተፈጠሩ ነው ብለዋል፡፡ ሌላው ለዋጋ ንረት እንደ ምክንያት ያነሱት የፊሲካልና የገንዘብ ቁጥጥሩ ክፍተት ያለበት መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ወደ ገበያ የሚፈሰው ገንዘብ ኢንፍሌሽን የሚያጣ መሆኑን የምንቆጣጠርበት መንገድም መፈተሽ ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡

ከወቅታዊው የዓለም ሁኔታ ጋር ተያይዞ በዓለም ላይ የነበረው የዋጋ ግሽበት የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱም ሌላው መታየት ያለበት ጉዳይ ነው ያሉት ዶ/ር ዓብይ፣ በጣም ብዙ ምርት ከውጭ የሚገባ በመሆኑ ወደ አገር የሚገቡት ላይ የዋጋ ንረት መኖር ለአገር ውስጥ የዋጋ ዕድገት አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

አነስተኛ ድርሻ ያለው ቢሆንም ዋጋ ሊጨምር ይችላል ብለው ምርታቸውን የሚይዙ አካላትም እንዳሉ በመጥቀስ፣ ለዋጋ ንረት ምክንያት ናቸው ያሏቸውን አንዳንድ ሁኔታዎች ያመላከቱበት ነበር፡፡ የዋጋ ንረትን በማስከተሉ ረገድ ሸማቾችም ራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው ሳይጠቅሱ ያላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሸማቾችም በኋላ ሊወደድ ይችላል ብለው አሁን ገዝተን እናከማች፣ እናስቀምጥ ካሉ አርቴፊሻል የሆነ ዋጋ ሊያጋንን ስለሚችል እንደ መንስዔ የዋጋ ግሽበት ሊያመጣ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

የዋጋ ግሽበትና የመንግሥት ዕርምጃ

ወቅታዊውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ መንግሥት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን እንደቆየ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይ መንግሥት ምግብ ነክ ምርቶች በርከት ብለው እንዲገቡ ለማድረግ ጥረት አድርጓል፡፡ ብዙ ቢሊዮን ብር መድበው ለማስገባት መሞከራቸውን፣ ለዚሁ ጉዳይ የሚውል ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ግማሽ ቢሊዮን ብር ገደማ ተጨማሪ ብድር እንዲያገኙና ሸቀጣ ሸቀጦች እንዲያከፋፍሉ መሞከሩን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ አካባቢ እንዲሠራ የተፈለገውም አንዱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲጠቀሙ ነው፡፡ የአቅርቦት ሰንሰለቱም ሳንካ በመሆኑ፣ የገበያ ማዕከላት በአዲስ አበባና በተለያዩ ቦታዎች ለመገንባት ጥረት ስለመደረጉም አመልክተዋል፡፡ የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስ መንግሥት ሠርቷል ብለው የጠቀሱት ሌላው ክንዋኔ የግሉ ዘርፍ በፍራንኮ ቫሉታ ተጨማሪ ታክስ ሳይከፍል ስንዴ፣ ስኳር፣ ዘይት፣ ሩዝና የሕፃናት ዱቄት እንዲያስገባ መፈቀዱን ነው፡፡ ነገር ግን በፍራንኮ ቫሉታ የተፈቀደው በቂ ስላልሆነ መንግሥት ስንዴ፣ ዘይትና ስኳር ላይ ተጨማሪ ሀብት መድቦ እያስገባ መገኘቱ ነው፡፡

ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ሙከራዎች የዋጋ ንረቱን መፈጠር የለበትም በሚባለው ልክ ባይቀንሱም በተወሰነ ደረጃ እንደገዛ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ፈተና አንፃር መቀነስ ባይችልም፣ የተደረጉት ሙከራዎች ብዙ መሆናቸውን በመጥቀስ እንደ አንድ ምሳሌ ነዳጅን አንስተዋል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከውጭ በምንገዛው መጠን ከሸጥን የኑሮ ውድነትን ያባብሳል ተብሎ 47.8 ቢሊዮን ብር መከሰሩን ወይም ከዋጋ በታች መሸጡን አስታውሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ነዳጅ ከየትኛውም አካባቢያዊ አገር ባነሰ ዋጋ የሚሸጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ነዳጅ በጨመረ ልክ እንዳይጨምር በመንግሥት የተወሰደው ዕርምጃ ተገቢ ቢሆንም፣ ትልቁ ስህተት ግን ማንን ነው እየደጎምን ያለነው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት ብለዋል፡፡ በነዳጅ ዙሪያ መደጎም ያለበት ኅብረተሰብን የሚመለከት ሥራ የሚሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሕገወጥ ነጋዴዎች

የዋጋ ንረት በተነሳ ቁጥር አንዱ ተግዳሮት ሕገወጥ ነጋዴዎች ይፈጽማሉ የተባለው ሸፍጥ ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ውስጥ ሕገወጥ ነጋዴዎች የንግድ ሰንሰለቱ እንዲበላሽ፣ እንዳንዶቹ ደግሞ ሆን ብለው እንዲበላሽ ሰፊ ጥረት አድርገዋል፡፡ ለዚህም ዕርምጃ የተወሰደባቸው እንዳሉ፣ የታሸገባቸው፣ ንግድ ፈቃድ የተሰረዘባቸውና በክስ ሒደት ላይ ያሉም አሉ፡፡ ይህ የንግድ ሥርዓቱን ለማስተካከል በእጅጉ እንደሚያግዝ ይጠበቃል፡፡ ነጋዴዎች ሥርዓት ብቻ ተከትለው እንዲሠሩ ማድረግ የራሱ የሆነ ትርጉም እንደሚኖረው በማስረዳት በዚህ ረገድ መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ስለመዘጋጀቱ ከገለጻቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡  

የዋጋ ንረትና የቀጣዩ ዓመት ወሳኝ ዕርምጃ

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰፊ ማብራራያ የተሰጠበት ወቅታዊው የዋጋ ንረት የተለያዩ መፍትሔዎች የሚፈለግለት ስለመሆኑ፣ በሚቀጥለው ዓመት ዋና ጉዳይ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ ቁጥጥር እንደሚጠናከር ጠቁመዋል፡፡ በመንግሥትና ከመንግሥት ውጪ በሚሠሩ ሥራዎች የሚያስፈልጉ የምግብ ሸቀጦች ማምረት፣ የማይቻሉትን በማስገባት ለማስተካከል ጥረት ይደረጋል፡፡ ለዓመታት እየተከማቸ የመጣውን ኢንፍሌሽን ገትቶ የተሻለ ውጤት ለማምጣት  መሬት ፆም ማደር የለበትም ተብሎ ዓምና የተጀመረው ሥራ ይገኝበታል፡፡ በየትኛውም ቦታ ማምረት እንደሚያስፈልግ በተለይ የበጋ ስንዴ ማምረትን ማጠናከርና ሌሎች ምርት ሊያሳድጉ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን ግድ ስለመሆኑ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራያ መሠረት፣ ለዋጋ ንረት እንደ መፍትሔ መወሰድ አለበት ብለው ከጠቀሷቸው የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦች ውስጥ አንዱ ባንኮችን የሚያመለክት ነው፡፡ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምርታማነት ያስፈልጋል ከተባለ ምርታማነትን ለማሳደግ የባንኮች ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ጠቆም አድርገዋል፡፡ ይህንንም ምርታማነት ለመጨመር ግብርናው ላይ በይበልጥ መሠራት ካለበት በፋይናንስ መደገፍ እንደሚኖርበት አመልክተው፣ እስካሁን ባንኮች ለዘርፉ እየሰጡ ያሉት ብድር አነስተኛ መሆኑንም አኃዝ ጠቅሰው ተናግረዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ከምታወጣው ወጪና ብድር አንፃር ለግብርና ዘርፍ እየወጣ ያለው በተለይ አነስተኛ ማሳ ላላቸው ሰዎች እየቀረበ ያለው ብድር ከአምስት በመቶ አይበልጥም፣ ይህ መስተካከል አለበት፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሀብት ወደ ግብርና ከፍ ባለ ደረጃ ማፍሰስ ካልቻልን የምንፈልገውን ውጤት ለማምጣት እንቸገራለን፤›› በማለትም የማክሮ ፋይናንስ ተቋማትም ወደ ባንክ የሚያድጉበት አንዱ ምክንያት ለአርሶ አደሩ የቀረቡ ስለሆኑ ለግብርና ዘርፍ ብድር እንዲያቀርቡ መሆኑን አክለዋል፡፡

የግብይት ሰንሰለትና መርካቶ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ብለው ካስቀመጡዋቸው ነጥቦች ውስጥ ከግብይት ሰንሰለት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ማስተካከል  ይገኝበታል፡፡

በጥቂት ሰዎች የተያዘውን ሲፈልጉ ያዝ፣ ሲፈልጉ ለቀቅ የሚያደርጉትን ገበያ ማስተካከል ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ዓብይ፣ መርካቶ ተገብቶ ጭምር በርካታ ማስተካከያ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡

ይህንም ሲያብራሩ ሆን ብለው የደሃውን ኑሮ የሚያመሰቃቅሉ ነጋዴዎች ያሉ በመሆኑ፣ ይህንን መስተካከል አለበት በማለት መንግሥት ከዚህ አንፃር ሊወስድ ያቀደውን ዕርምጃ ጠቁመዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሁሉ ተደርገው በአዲሱ ዓመት የዋጋ ግሽበቱን በተቻለ መጠን ዕድገቱን እንዲቀንስ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ሰዎች በልተው የማደር ጫና እንዲቀንስ ከበጀትም፣ ከበጀት ውጪም ጥረት ይደረጋል፡፡ መንግሥት ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጥረቱ በውጤት እንዲቀየር ሌሎች ሰፋፊ ሥራዎች እንደሚሠሩና ሊሠሩ ይገባል ያሉትንም አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው ከገለጹት ነጥብ ውስጥ ደሃው እንዲያማርጥ ሳይሆን ገዝቶ እንዲበላ የሚያስችል አቅም መፍጠርና በሚቀጥለው ዓመት የማክሮ ትኩረት አቅጣጫ በዚህ ጉዳይ ላይ መሥራት ይሆናል የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የዋጋ ንረትን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቃቸው የኢኮኖሚ ባለሙያ ስለዋጋ ንረቱ ይደረጋል ተብሎ የታሰቡት ተግባራት በተወሰነ ደረጃ መፍትሔ ሊያመጡ ቢችሉም የተባለውን ለመተግበር ግን ምን ያህል አቅም ይኖራል የሚለው ጉዳይ ያሳስበኛል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች