Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየሰኔ አሥራ አራቱ ምርጫ ምልከታ

የሰኔ አሥራ አራቱ ምርጫ ምልከታ

ቀን:

በተስፋዬ ጎይቴ

የዘንድሮው የሰኔ አሥራ አራት ምርጫ በጣም ተፈርቶ እንዳልነበር የጎላ የፀጥታ ችግር ሳያስከትል በአንፃራዊ ሁኔታ በሰላም ሊባል በሚችል ደረጃ ተካሂዷል። የመራጩ ሕዝብ ተሳትፎ ዕፁብ ድንቅ ነበር ማለት ይቻላል። የምርጫ ቦርዱም ገለልተኛነትና ብቃት ያለው አመራር ከእነ ችግሮቹ ድንቅ ሆኖ ታቷል። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከሞላ ጎደል ሸጋ ሥነ ምግባር አሳይተዋል። ክረምት ቢሆንም አየሩ በጣም የከፋ አልነበረም። ሰማዩ እንኳን “በዝናብ አልረብሻችሁም፣ ሁከት አልፈጥርም” ብሎ በብዙ ቦታዎች ዝናቡን በተቻለው መጠን ዋጥ አድርጎ አቆይቶልናል። እግዜር እንደ ሰው ክፉ አይደለማ። የሚሠራውን ያውቃል።

ከዚህ አንፃር ዘንድሮ በቅድመ ምርጫው፣ በምርጫው ዕለትና በድኅረ ምርጫው ወቅቶች ምን በጎ አካሄዶች ታይተዋል? ለወደፊቱስ ሊታረሙ የሚገባቸው አፈጻጸሞች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን መዳሰሱ ተገቢ ነው። አገር፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ መንግሥትና ፓርቲ ቀርቶ ቤተሰብና ግለሰብ እንኳን በተወሰነ ጊዜ ቆም ብሎ ራሱን መገምገም አለበት፡፡ ያለዚያ በወደፊት ዕርምጃው ላይ ጥላ ያጠላበታል። አይመስላችሁም አንባቢያን?

- Advertisement -

የዚህ አስተያየት አቅራቢ ቀደም ባሉት ዓመታት ለረዥም ጊዜ በምርጫ አመራር ላይ የቆየ ሰው በመሆኑ፣ የአንድን የምርጫ ሒደት አዎንታዊና አሉታዊ ገጽታዎች በተሻለ መንገድ ማየት ይችላል። ከዚህም በላይ በገለልተኛ አመለካከቱ ላይ ጥያቄ የማይነሳበት፣ ከምንም በላይ ለአገሩ ሰላምና ለሕዝቡ ደኅንነት ብዙ የሚጨነቅ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ሐሳቡን በግልጽ ቢያስቀምጥ፣ ‹‹የዚህ›› ወይም ‹‹የዚያ›› ወገን ተብሎ ሊፈረጅ አይገባውም። የግድ ፀጉር ካልሰነጠቅኩ የሚል ካለ ግን የሚከለክለው የለም። በማናቸውም የአገር ጉዳይ ላይ የሚሰጡትን ሚዛናዊ አስተያየቶች እንደ መብት መውሰድን ባህል ማድረግ ግን ይገባል። በሆነ አገራዊ ጉዳይ ላይ ወደ መግባባት ሊያመሩን የሚችሉ ሐሳቦች ሲመጡ እንደ ቀንዳም በሬ ከመዋጋት ይልቅ፣ ‹‹ይኼ ሐሳብ ትውልዱን ያስተምራል፣ ይገራናል፣ ይገነባናል፣ መንገድ ያሳየናል›› ብሎ መውሰድ ጤናማነት ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን የሚጎረብጡና ለአገርና ለሕዝብ የማይበጁ ሐሳቦችን በተሻለ ሐሳብ መመከትና ተነጋግሮ ወደ ጋራ መፍትሔ መድረስም የሥልጣኔ ምልክት ነው።

ዋና ዋና ጠንካራ ጎኖች

ከፍ ብሎ በመንደርደሪያው ላይ እንደ ተጠቀሰው በቅርብ ዓመታት ካሳለፍናቸው አስከፊ የፀጥታ መናጋት ወቅቶች አንፃር የዘንድሮ ምርጫ እንደዚህ በሰላም ይከናወናል ተብሎ አልተገመተም ነበር። ከመንግሥት ሲሰጡ የነበሩ መግለጫዎች ድንገት ያልተጠበቁ የጥፋት ሙከራዎች ቢቃጡ በሚል ሲደረጉ የቆዩት ዝግጅቶች ያስጨንቁም ያረጋጉም ነበር። ከዚህ አንፃር መንግሥት የሠራው ብርቱ ሥራ የዚህን ጽሑፍ አቅራቢ በእጅጉ አስደስቶታል። እንደ ጤነኛ ዜጋ በፀጥታና በደኅንነት ኃይሉ ኩራትም ተሰምቶታል። ከመራጮች ምዝገባ ወቅት አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ የተሠራው የፀጥታ ሥራ ውጤቱ አመርቂ ነው ማለት ያስደፍራል። በተለይ በሰኔ 14 ዋዜማና ማግሥት የተካሄደው ጠንካራ ጥበቃ ይበል የሚያሰኝ ነበር። የትም ቦታ ምንም ዓይነት የጥፋት ኃይሎች ሙከራ አልነበረም ማለት አይደለም። ነገር ግን የመከላከያ ሠራዊታችን፣ የፖሊስ መዋቅሩ፣ የደኅንነት ኃይሉ፣ ሚሊሻው፣ ልዩ ኃይሉ፣ ወዘተ. የፌዴራሉ ከየክልሉ ኃይሎች ጋር የከፋ ጉዳት እንዳይደርስና ትርምስ እንዳይፈጠር በቅንጅት ለሠሩት አርኪ ሥራ ብድግ ብሎ ማመሥገንና ማወደስ ያስፈልጋል።

በምርጫው የተሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያዩዋቸውን አንዳንድ ጉድፎች እንኳን በጣም ሳያጋንኑ፣ ሰክነውና ችግሮቹን ዋጥ አድርገው፣ ሳያላዝኑ፣ በመቻቻል ለምርጫው መሳካት ያሳዩት ፅናት ለወደፊቱ የአገራችን ፖለቲካ ተስፋ ፈንጣቂ ሆኗል ማለት ይቻላል። ለአገር ፀጥታና ደኅንነት፣ ለሕዝቡ መረጋጋት፣ ግጭቶች እንዳይነሱ ለመከላከል የድርሻን መወጣት ማለት ትርጉሙ ይኼው ነው። ከድምፅ ቆጠራው በኋላ የቀረቡትም እጅግ በርካታ ቅሬታዎች በምርጫ ወቅት የማይጠበቁ አይደሉምና በሕጉ መሠረት በአግባቡ መፈታት አለባቸው።

የምርጫ አስተዳደር ሥራው ባለቤት ከሆነው ተቋም በተጨማሪ የበርካታ ወገኖች ድርሻ ያለበት ነው። በመሆኑም የምርጫ ቦርድ አመራር በግራም በቀኝም፣ በላይም በታችም፣ በገጠርም በከተማም የገጠሙትን ልዩ ልዩ ጋሬጣዎችና ጣልቃ ገብነቶች ተቋቁሞ በእውነት የተሳካ ሥራ ሠርቷል። እንደ ቅኝት አድራጊው የቆየ ተሞክሮ ከሆነ፣ በተለይ በምርጫ ወቅቶች የምርጫ አመራሩና ሠራተኛው ለበርካታ ቀናት ያለ ዕንቅልፍ እንደሚያድር ያውቃል። ይመሰክራልም። ስለሆነም ሒደቱ እጅግ ፈታኝ ከመሆኑም እንፃር የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በተለይ የላይኛው ሠራዊት ጥሩ አድርጎ ተዋግቷል። የማይናቅ ድልም አጎናፅፎናል። በተለይ የምርጫ ቁሳቁሶች ዘመናዊነት፣ ጥያቄዎች ሲነሱ ፈጣን ምላሽ የመስጠት ብቃት፣ ጉዳዮችን በሰከነ መንገድ የማየት ትዕግሥት፣ ወዘተ. የቦርዱ ጥንካሬ መገለጫዎች ሆነው ተገኝተዋል። በአጠቃላይ የምርጫ ቦርዱ መዋቅር ከላይ እስከ ታች ገለልተኛነቱ (Impartiality) ካለፉት አምስት ምርጫዎች ሁሉ በፍፁም የተሻለ ነበር። እንደ ቀድሞዎቹ እዚህና እዚያ የሚያሯሩጥ የድምፅ ስርቆትም ጎልቶ አልታየም።

በምርጫ ቦርዱ ዝግጅትና አፈጻጸም ውስጥ ከሁሉም ሰፊና ከባድ የነበረው የምርጫ ሎጂስቲክስ ሥራ ነው። የመዛግብቱ፣ የቁሳቁሶቹ፣ የፖስተሮቹ፣ የድምፅ መስጫ ወረቀቶቹና የድምፅ መስጫ ሳጥኑ (Ballot Box)፣ የማይለቅ የጥፍር ቀለሙ (Indelible ink)፣ የዩኒፎርሞቹ፣ የጽሕፈት መሣሪያዎቹ፣ ወዘተ. ዝግጅትና ሥርጭት አብዛኛውን ጊዜ ገንዘብ፣ ጉልበትና ዕውቀት የጠየቀ ነበር። አንዳንዱ ትልልቅ የዝግጅት ሥራ ምናልባት በቅድመ ኮቪድ ወቅት (በ2012 ዓ.ም.) ባይጀመር ኖሮ በዚህ መልኩ ሊሳካ ይችል ነበር ወይ? የሚል ጥያቄም ያጭራል። ከዚህ አንፃር ትልቅ ውጤት የታየበት ዋናው እዚህ ዘርፍ ላይ ነው ማለት ይቻላል። ክፍተቶቹን ግን በኋላ እናያቸዋለን።

መራጩ ሕዝብስ የተባለ እንደሆነ ከሁሉም በላይ መብትና ግዴታውን የተረዳ ቀልቡ ለወደደው ፓርቲ ድምፁን ሳይሰጥ ወደ ቤቱ ላለመመለስ እነዚያን ረዣዥም የሚለው ቃል የማይገልጻቸው ግዙፍና አሰልቺ ሠልፎች፣ ብርዱንና ፀሐዩን ሁሉ ተቋቁሞ በፅናት፣ በቁርጠኝነት፣ በእልክ ጭምር የሠራው ሥራ እጅግ የሚያኮራ ነበር።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከማኅበራዊ ድረ ገጾች ውስጥ በተለይ ‹‹የበሬ ወለደ›› ተረት መርዝ ቀማሚዎች በዘንድሮው ምርጫ አልተሳካላቸውም ማለት ይቻላል። ይኼም ሌላው ድል ነው። የአገራችን መገናኛ ብዙኃን (አንዳንዶቹ ከእነ ክፍተቶቻቸውም ቢሆን) ስለምርጫው ሒደት ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሕዝቡ ተገቢውን ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኝ፣ በመላ አገሪቱ ተሰማርተው ፀሐይ፣ ዝናብና ብርድ ሳይበግራቸው ለሠሩት ሥራም ትልቅ ምሥጋና ይገባቸዋል።

ውዳሴዎቹ እነዚህ ብቻ አይደሉም። ሌሎችም በርካታ በጎ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል። ነገር ግን የጋዜጣው ገጽ ወሰን አለውና ከጥንካሬዎች ጎን ክፍተቶችስ አልታዩም ወይ? በሚለው ላይ አስተማሪ የሆኑ ጥቂት ምሳሌዎችን ማንሳቱ ምልከታውን ሚዛናዊ ያደርገዋል። ሲክቡንና ሲያወድሱን ብቻ ሳይሆን፣ ክፍተቶቻችንንም ሲነግሩን በአክብሮትና በምሥጋና ተቀብለን የጳጉሜን ጨምሮ ለቀጣይ ምርጫዎች ማስተካከያ ማድረግ ለሁሉም ይጠቅማል።

ጎልተው የታዩ ክፍተቶች

ቦርዱም በግልጽ እንዳመነው ከምርጫ ሰነዶች ዝግጅትና ሥርጭት አንፃር የድምፅ መስጫ ወረቀቶች መቀያየር፣ እጥረት፣ ብልሽት፣ የሥርጭት መዛባት፣ የምርጫ ቁሳቁሶች መዘግየት፣ የድምፅ ቆጠራና የድምር ስህተት ወይም መምታታት፣ ወዘተ. በተደጋጋሚ አጋጥሟል። በዚህ ረገድ በርካታ ችግሮች ታይተዋል። በ160 የምርጫ ክልሎች ላይ ቅሬታዎች እንደቀረቡ ከምርጫ ቦርድ እየተነገረ ይገኛል። ይህም አኃዝ በጣም አስደንጋጭ ይመስላል። ከዚህ አንፃር ሚፈጠሩትን ችግሮች ተቀብሎ ‹‹ችግሮቹ ነበሩ፣ ግን ተምረንባቸዋል፣ ወደፊት እናስተካክላለን፤›› ቢባል ያስደስታል። ድካም ሲበዛና እንቅልፍ ሲያንገላጅጅም ስህተት ሊፈጠር ይችላል። በሌላ በኩል አዲስ ከመሆናቸውም ጋር ተያይዞ በሠራተኞችና በአስፈጻሚዎች በኩል አንዳንድ የግንዛቤ ማነስ፣ ግዴለሽነትና ስልቹነት፣ የሥነ ምግባር ችግሮች ጭምር መታየታቸውን ሚዲያዎችም ደጋግመው ስለዘገቡት የችግሩን መነሻ ምክንያቶች አጥንቶ በየቦታው ቅሬታ ያስነሳውን ይህንን ችግር ወደፊት እንዳይደገም ማድረግ ተገቢ ነው። ከዚህም በላይ መዘንጋት የሌለበት ሌሎች በምርጫው ያልተሳተፉ ፓርቲዎች ቢሳተፉ ኖሮ የመራጮች ሠልፎች ከዚህም በላይ ሊረዝሙና የድምፅ አሰጣጡ እስከ ንጋቱ ሊቀጥል፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የድምፅ መስጫ ወረቀቱም ጋዜጣ ሊያክል፣ በተወሰኑ ክልሎች የፉክክሩ ባህሪ ከዚህ በላይ በጣም የጠነከረ ሊሆን ይችል እንደነበር መገመት ያስፈልጋል።

በመራጮች ምዝገባ ወቅት ከተገኙ መራጮች ቁጥር በመነሳት የድምፅ መስጫ ካርዶችን አመጣጥኖ ማሳተም ይቻልና ይገባም ነበርና ብንማማርበት መልካም ነው። የመራጮች ምዝገባ በጣም ቀድሞ የሚካሄደው ምን ያህል መራጮች በየምርጫ ክልሉና በየምርጫ ጣቢያው እንዳሉት ትክክለኛ የመራጭ ቁጥር ለማግኘትና የሚታተሙትን የድምፅ መስጫ ካርዶች ብዛት ለመወሰን እንዲያግዝ መሆኑ ይታወቃል። ካርድ ባነሰባቸው ጣቢያዎች ይህን ያህል መራጭ እንደሚመጣ አላወቅንም ነበር የሚለው ሰበብ ቦታ የለውም።

በከተማም በገጠርም በበርካታ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች በሕጉ መሠረት በሰዓቱ ድምፅ መስጠት ባለመጀመሩና አንዳንዱጋም ሰዓቱ በጣም ገፍቶ በመጀመሩ የተነሳ፣ እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ ያልተቋረጡ ሠልፎች ተከስተዋል። አንዳንድ ቦታ ሦስት ሰዓት አልፎም መራጮች ድምፃችንን ሳንሰጥ አንወጣም ያሉበት ሁኔታ ታይቷል። የመራጩ መብዛት አንድ ነገር ሆኖ ይህንን ያመጣው የመራጮች መብዛት ብቻ ነው ብሎ መከራከር ግን ችግሩን በመቅረፍ ፋንታ ለወደፊቱም እንዲቀጥል ማድረግ ስለሚሆን፣ ሰበቦችን መደርደሩ ቀርቶ የችግሩ መንስዔ ምን እንደሆነ ነቅሶ አውጥቶ ለወደፊቱ ማሻሻያ ማድረግ ይገባል። ይኼኛው ችግር ትንሽ ካለፉት ምርጫዎችም የባሰ ነበርና በደንብ ቢታይ።

በአንዳንድ ጣቢያዎች ውስጥ ስለድምፅ አሰጣጡ ይሰጡ የነበሩት መግለጫዎች በአስመራጮች ገለልተኛነት ላይ ጥያቄና አላስፈላጊ ጭቅጭቅም ያስነሱ ነበሩ። ቤት ለቤት እየዞሩ “እገሌ የተባለውን ፓርቲ ምረጡ” እያሉ ሲቀሰቅሱ የነበሩ ሰዎች ገለልተኛ አስመራጮች ተብለው ተመድበዋል። በአቅመ ደካሞች አሳበው ጎረቤቶቻቸውንና ዘመዶቻቸውን ባሻቸው ሰዓት ሲመጡ ከፊት አሠልፈው፣ በሠልፉ ላይ ያለውን ሕዝብ ትዝብት ሳይፈሩ እየተጮኸባቸውም ቅድሚያ ሲሰጡ የታየበት ሁኔታ አለ። ‹‹ተው እንጂ ነውር ሥራ አትሥሩ›› ሲባሉ መራጮችን ሲያንጓጥጡና ሲቆጡ የነበሩ አስፈጻሚዎችም አልጠፉም። ጣልቃ ገብነቶችና ጫናዎች ባለፉት ምርጫዎችም በስድስተኛው ምርጫም ነበሩ። አስመራጭና ታዛቢዎች አንዳንድ ቦታ ግንዛቤያቸው በቂ እንዳልነበረና በድምፅ አሰጣጡ ሒደት ላይ በተገነዘቡት ልክ ለመራጮች ፍፁም አሳሳች መረጃ ይሰጡ እንደነበርም ተስተውሏል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ጣቢያው ከተከፈተ በኋላ፣ ‹‹አስመራጮች አርፍደውብን ነው፣ ታዛቢዎች ቀርተውብን ነው›› እየተባለ ሕዝብ ከ11 ሰዓት ጀምሮ ብርድ ላይ ተሠልፎ በጣም ዘግይቶ ሥራ የተጀመረባቸው ጣቢያዎች በርካታዎች ነበሩ ብለናል። ይሁንና ሕዝቡ በመረጋጋት ለአገሩም፣ ለመረጠውም ፓርቲ ያለውን ፍቅርና አክብሮት አሳይቷል። ይሁንና የእነዚህ ሁሉ ክፍተቶች ድምር ውጤት በምርጫው አካሄድ ላይ ትንሽም ቢሆን፣ አሉታዊ ተፅዕኖ አላሳደረም ማለት ግን አይቻልም። ይህንን ችግር ለመፍታት በአስመራጮችና በታዛቢዎች አመላመል/አመራረጥ ላይ የበለጠ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ፣ ለአስመራጩም ለመራጩም በቂ ሥልጠናና መግለጫ መስጠት፣ መራጮች በበዙባቸው ሥፍራዎች በምርጫው ዕለት ሳይሆን፣ ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ ተጨማሪ ጣቢያዎችን ማቋቋም፣ በቂ ቁሳቁሶችን መመደብ፣ ለጥርጣሬ ቀዳዳ የሚከፍቱ አሠራሮችን መድፈን፣ ወዘተ. እንደ መፍትሔ ሊወሰዱ ይችላሉ። አንዳንድ ነገሮች ላይ መኮነን ብቻ ሳይሆን፣ ካለፉት ምርጫዎችም ቢሆን ጥቂት በጎ ልምዶች ካሉ መውሰድ አይከፋም። አብዛኞቹ ክፍተቶች ባለፉት ምርጫዎችም የነበሩ ስለሆኑ ተጠንተው ሊታረሙ ይችሉ ነበር።

ከሕዝባችን የትምህርት ደረጃና የምርጫ ግንዛቤ አንፃር፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የክልል ምክር ቤቶች አባላት ድምፅ መስጫ ወረቀት የያዘው ዕጩ ቁጥር እጅግ ከፍተኛና አደናጋሪ መሆኑ ሌላው ችግር ነበር። በተለይ ማንበብ መጻፍ ለማይችሉ፣ ለአረጋውያን፣ ወዘተ. የግድ የሌሎችን ድጋፍ እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል። ያልተማረ ኅብረተሰብ በበዛበት አገር ውስጥ የምርጫውን አፈጻጸም ቀለል ማድረግ የምርጫውን ተዓማኒነትና ቅቡልነት ከፍ ያደርገዋል። በዚህ መካከል እንዳንድ ቦታዎች ላይ አስመራጮች ያገኙትን የማገዝ ዕድል ባልሆነ መንገድ እንደተጠቀሙበትም ታይቷል። ይህም ችግር ከሌሎች አገሮች ልምድ ተወስዶ ለወደፊቱ ሳይንሳዊ መፍትሔ ይሻል።

የዘንድሮ የዕጩዎች የትምህርት ደረጃ ፉክክር አስገራሚ ነበር። በአደባባይ ፖስተሮች ላይ አንዱ ፕሮፌሰር፣ ተባባሪ፣ ረዳት፣ ዶ/ር፣ ማስተርስ፣ ዲግሪ ማለት ሲጀምር ሌላውም፣ ሌላውም ቀጠለ። ዕጩዎቹ ለሕዝቡ ከሰጡት ምሥጉን አገልግሎት ከጨዋነታቸው፣ ከተወዳጅነታቸው፣ በመራጩ ሕዝብ ከመታወቃቸው ይልቅ በትምህርት ደረጃቸው ትልቅነት ባላቸው ብልጫ ጎልተው ለመታየት ሞከሩ። የምርጫው ውጤት ግን በአብዛኛው በትምህርት ደረጃ ላይ አልተንጠለጠለም። በትምህርት ደረጃዬና በሙያዬ “እኔ እበልጣለሁ” የሚለው ፉከራ እምብዛም አልሠራም። በበርካታ ምርጫ ክልሎች ላይ ከፕሮፌሰሮቹና ከዶክተሮቹ ባለማስተርሶቹ የበለጡበት ሁኔታ በግልጽ በመስተዋሉ አመለካከቶቹን ማስተካከል ይገባል።

ምርጫው በክረምት ለመካሄዱ በቂ ምክንያት አለው። ግን ዝናብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ጭምር ገና በመጭው ጳጉሜን ድምፅ የሚሰጥባቸው የምርጫ ጣቢያዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ባለፉት ምርጫዎች ያልተለመደ ቢሆንም፣ ዘንድሮ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በክረምት ሊካሄድ ችሏል። ይሁንና የምርጫው በክረምት መካሄድ የፈጠራቸውና የሚፈጥራቸው ችግሮች በግልጽ የታዩ ስለሆነ፣ ለወደፊቱ ልንማርባቸው ይገባል። ዝናቡ በአንዳንድ ሥፍራዎች እንቅስቃሴን አውኳል። ገናም ማወኩ አይቀርም። “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” እንዲሉ በደሃ አገር ኢኮኖሚ ለአላስፈላጊ ተጨማሪ ወጪዎችስ ቢሆን ለምን እንዳርጋለን?

የምርጫ መፈክሮችና የተላለፉ መልዕክቶች ባለፉት ምርጫዎች ቅስቀሳዎች ወቅት በጥቅም ላይ ከዋሉት፣ በተለይም በምርጫ ’97 ከታየው ይልቅ በጣም ጥሩ ሥነ ምግባር የሠፈነባቸው ቢሆንም አልፎ አልፎ ውረፋዎችና አሽሙሮች አልነበሩም ማለት ግን አይቻልም። እዚህ ላይ የፓርቲዎቹን ስም ላለማንሳት ሲባል በምሳሌ ማስረዳት አልተፈለገም። ይሁንና መልዕክቶቹ ግን እምብዛም ወደ አተካራና ያለ መግባባት የሚመሩ አልነበሩም።

ገዥውን ፓርቲ በሚፎካከሩት ፓርቲዎች ትኩረት ሊሰጠው ሲገባ ባለመሰጠቱ የተነሳ፣ ራሳቸውንም ደጋፊዎቻቸውንም የጎዱትን ነገር እዚህ ላይ አጠንክሮ ማንሳቱ ተገቢ ነው። በተለይ በከተሞች በእያንዳንዱ ምርጫ ክልል ሥር በሚገኙ ጣቢያዎች ተወዳዳሪዎች ያገኙት ድምፅ ተለጥፎ ሲታይ፣ በፕሮግራሞቻቸው የሚቀራረቡ ሁለት ወይም ሦስት ተፎካካሪዎች ተዋህደው ቢቀርቡ (ቢወዳደሩ) ኖሮ በድምሩ ውጤታቸው በጥቂት ቦታዎች ላይም ቢሆን ገዥውን ፓርቲ ሊበልጡት (ሊያሸንፉ) የሚችሉበት ዕድል ነበራቸው። ነገር ግን ልክ እንደ ቀደሙት ምርጫዎች ይህንን ባለማድረጋቸው ድምፃቸው ሊያንስ ወይም ሊበልጡ ችለዋል። እንደ በጋ ደመና ሳይዘንቡ ብን ብለው ጠፍተዋል። አወሩ እንጂ አልሠሩም። ይህ ደግሞ የምንጊዜም ክፍተታቸው ነው።

በበጎ አልታየላቸውም እንጂ ገዥው ፓርቲ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲዎቹ እንዲዋሀዱ/እንዲጣመሩ/እና ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ሲመክሩ ቆይተዋል፡፡ “እንዳታሸንፉኝ ተበታትናችሁ ቅረቡ” አላሉም። ፓርቲዎቹ በሌሎች ጉዳዮች እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ ከባድ ጋሬጣም አልነበረባቸውም። ይልቁንም የፓርቲዎቹ መብዛት በምርጫ ቦርድ መዋቅር፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በምርጫ ካርድ ዝግጅትና ኅትመት ላይ አላስፈላጊ ጫና ከመፍጠር በቀር አሸናፊ ከመሆን አንፃር አንዳች ፋይዳ አልነበረውም። ስለዚህ አሁን የፓርላማ መቀመጫ ያጡት ፓርቲዎች ለወደፊቱ ከክፍተታቸው ሊማሩ ይገባል። ያለበለዚያ ትናንት ከትናንት ወዲያም ሯጭ ሳይሆኑ አሯሯጭ፣ ተጋጣሚ ሳይሆኑ ጥሩ ተመልካች፣ ተመራጭ ሳይሆኑ የአሸናፊዎች አጃቢ ሆነው እንደኖሩት ነገም ዕጣ ፈንታቸው ተመሳሳይ መሆኑ አይቀርም።

በፖስተር፣ በቢልቦርድና በባነር የተደረገው የመብራትና የስልክ ምሰሶዎችን፣ አጥሮችን፣ ግንቦችን ያለበሰው የዘንድሮ ቅስቀሳ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ትንግርት የሚያሰኝ ነበር። ለመሆኑ የንግድ ማስታወቂያዎች ቢሆኑ ኖሮ ምን ያህል ወጪ ይጠይቁ ነበር? የፋብሪካዎች ሸራ፣ ጨርቅና ብረታ ብረት ምንም የተረፈ አይመስልም። የቅስቀሳዎቹ ስፋት ግን እንደ የገንዘብና የዕውቀት አቅማቸው ከፓርቲ ፓርቲ በጣም የተለያየ ነበር። ይህም ሆኖ ግን የፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ፣ የመገናኛ ብዙኃንና የራሱ የምርጫ ቦርዱ ትምህርትና ቅስቀሳም ቢሆን በአጠቃላይ እምብዛም አጓጊና ማራኪ ነበር ለማለት ያስቸግራል።

እስቲ የምርጫ 1997 ሁለንተናዊ ገጽታ ትዝ ይበላችሁ አንባብያን። የነበረው የጦፈ ፉክክርና ክርክር፣ ሦስተኛው ምርጫ ሥጋንም ነፍስንም ያስደሰተ፣ ማንም ያሸንፍ ማን፣ የኋላ ኋላ ምንም ችግር ይፈጠር ከእነ ችግሩ ማራኪ የሆነ ምርጫ ነበር። አንዳንዶች የዘንድሮውን ምርጫ ከምርጫ 1997 ዓ.ም. ጋር ያነፃፅሩታል። አዎን። ስድስተኛው ምርጫ በጣም በርካታ መልካም ነገሮች (መሠረታዊ ለውጦች) ታይተውበታል። ጅምሮቹ ተስፋ ሰጪ እንደሆኑ ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ያለፉት ምርጫዎች በጅምላ ሊወገዙ በፍፁም አይገባም። የዘንድሮውም ምርጫ ጥንካሬዎቹም ችግሮቹም ቢሆኑ በጥንቃቄ ተለይተው ለነገው ትምህርት ካልተወሰደባቸው፣ በተመሳሳይ ተሞክሮዎቹ ሞተው ተቀብረውና ተረስተው በየአምስት ዓመቱ ብቻ ድንጋያቸውን ፈንቅለን ከተቀበሩበት የምናወጣቸው እንዳይሆኑ፣ የጋራ ቢደረጉና መተማመን ላይ ቢደረስባቸው ይጠቅማል። ጥሩ ሠራሁ ለማለት የውጤት አመልካቾቹ ከበፊት ሥራዎች ጋር ማነፃፀር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች አገሮች ተሞክሮዎች፣ አገሪቱ ከደረሰችበት የኢኮኖሚና የዕውቀት ደረጃ፣ ከተፈጠሩት ምቹ ሁኔታዎች ጋር ጭምር መሆን ይኖርበታል።

ከምርጫው ሒደት ጋር ተያይዞ ከላይ እስከ ታች ባሉ ባለሥልጣናት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ የሚድያ ባለሙያዎች፣ ወዘተ. ይተላለፉ የነበሩ መልዕክቶች የእንግሊዝኛ ቃላት በጣም የበዙባቸው ነበሩ። አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን፣ አረጋውያንን፣ ወዛደሮችን እንኳን በእንግሊዝኛ በአማርኛም የምርጫ መልዕክቶችን ለመገንዘብ የሚቸገሩትን ዜጎቻችንን ለማስተማር እንግሊዝኛ እንዴት እንጠቀማለን? ሐሳባችንን ለመግለጽ አማርኛችን አቅም አንሶት ወይም ለተከታታይ ዓመታት እንግሊዝኛ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች ውስጥ ኖረን አማርኛው ስለጠፋን አይደለም። እንግሊዝኛ አዋቂ ወይም ምሁር ለመባል ሕዝቡን አናደናግር። በሚገባው ቋንቋ እንንገረው።

በተለያዩ መንገዶች መልካቸውን ቀይረው እስከ ሰኔ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የተካሄዱትን የፓርቲ ቅስቀሳዎች፣ ጉዳዩ ድፍረት መሆኑ እያወቀ ምርጫ ቦርድ በዝምታ አልፏቸዋል። ምክንያቱን ተቋሙ ራሱ ያውቀዋል። ግን ሕጋዊና ፍትሐዊ ነበር ወይ ብሎ መጠየቅ ይገባል። ሕገወጥነትንና ሕጋዊነትንስ እየቀላቀሉ እስከ መቼ መጓዝ ይቻላል?

ከምርጫ 2013 አፈጻጸም ቀልብ ተሰጥቷቸው ሊሻሻሉ ከሚገባቸው ሌሎች ጉድለቶች መካከል፣ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ መደጋገፍ በጣም ፈጦ የወጣበት ነበር። “አሁንስ የሚመክራቸው አጡ እንዴ?” እስከሚባል ድረስ የትናንቱ ዛሬም ተባብሶ ቀጥሏል። መቼ ሊሻሻል እንደሚችልም ሥጋት ያጭራል። “አወይ የእኛ ነገር”ም ያሰኛል። የመንግሥት ተሽከርካሪዎች በጀትቁሳቁስሠራተኛወዘተ. ከልክ በላይ በዚያው መልኩ ለፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ሲውሉ ማየት ይከብዳል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ በጋራ አገራችን ሀብቶች ለምርጫው እኩል የመጠቀም ፍትሐዊ አሠራርና መብት መፈጠር ይኖርበት ነበር። ግን ይህንን አላየንም። ታዲያ በአውሮፕላንና በመኪና፣ በመኪናና በፈረስ፣ በፈረስና በእግር፣ በገደላ ገደልና በሜዳ እንዴት እኩል መሮጥ ይቻላል?

የሰኔ 14 ምርጫ ኮቪድ-19 መኖሩ የተዘነጋበት ነበር። ኳስ ለመመልከት እንኳን ምንም ሰው እንዳይገባ ገደብ ተደርጎ ሳለ በአዲስ አበባ ስታዲየም በመጨረሻው ቀናት የተካሄደው መርሐ ግብር፣ የድጋፍ ሠልፎችና ሌሎች አብዛኛው ሕዝብ ያለማስክ የተሳተፈባቸው ሁነቶች በምርጫው ስለማሸነፋችን እንጂ ስለኮቪድ ማንኛችንም ምንም ያህል እንዳልተጨነቅን ያሳያል። ከምርጫ ቅስቀሳ እኮ የሕዝቡ ደኅንነት ይበልጣል ጎበዝ! ሕዝብ ከሌለ አገርም፣ ክልልም፣ ምርጫም፣ መንግሥትም የለም። “እንቆረቆርልሃለን” ለምንለው ሕዝባችን በሁሉም አቅጣጫ የምር እንቆርቆርለት። ለኮቪድ ግብርና ቀለብነት አንዳርገው። ከእነ ችግሮቻችን ጳጉሜን እየደረሰ መሆኑን አንዘንጋ።

ባለፉት የምርጫ ዋዜማ ወራት ቴሌቪዥኖቻችሁን በከፈታችሁ ቁጥር የተቋማት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ፣ ምርቃት፣ ጉብኝት፣ ወዘተ. በገፍ ሲታይ ቆይቷል። በጤነኛ አዕምሮ ከተወሰደ ጥሩ ነው። ልማት ነው። ዕድገት ነው። ድህነት ማሸነፊያ መንገድም ነው። ነገር ግን በሦስት የለውጡ ዓመታት ያላየናቸውን አፈጻጸሞች በሁለትና በሦስት ወራት ውስጥ እጅግ ገዝፈው ዓይተናል። ጨለምተኛ አስተሳሰብ ነው የሚሉ ካሉ ወደፊት በተጨባጭ የሚያዩት ይሆናል። እስከ ዛሬ በሦስት ወራት የታዩት አፈጻጸሞች ሲመዘኑ የተመረቁት መንገዶች አስፋልታቸው፣ ድልድዮቻቸው፣ የእግረኛ መገልገያዎችና ፉካዎቻቸው፣ ትምህርት ቤቶችም የማስተማሪያ፣ የቤተ መጻሕፍትና የመምህራን ማረፊያ፣ መፀዳጃ ቤቶቻቸው፣ የአይቲ ክፍሎች ሁሉ ተጠናቀው ከሆነ የተመረቁት ጥሩ ነው። ያለዚያ ለምርጫ ፍጆታ ነው እየተባለ ለትርጉም እንዳንጋለጥና ትዝብት ውስጥ እንዳንወድቅ መጠንቀቅ ያሻል። ነገሮቻችን ሁሉ የአንድ ወቅት ሆይ ሆይታ አይሁኑ። ብልጭ ብሎ ድርግም ማለት ይቅር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራ እየታየ ነው። ከሥራ ዕድል ፈጠራው ጋር ተያይዞ በመንግሥት የተመደበው በጀት ክፍፍል ፍትሐዊነት ጉዳይ በእጅጉ ያነጋገረ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁን ግን ምርጫው የተጠናቀቀ ስለሆነ ‹‹እንደ ስሟም አበባ እናደርጋታለን›› እያልን በየዕለቱና በየሰዓቱ የምንዘምርላትን በላስቲክ ዳሶች የተንቆጠቆጠችውን ከተማችንን ወደ እውነተኛ አበባነቷ እንመልሳት። በአንድ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትራችን በ‹‹ገበታ ለአገር›› ኢትዮጵያን ሙሽራ ለማድረግ እየለፉ ባሉበት ወቅት፣ በሌላ በኩል ግን አዲስ አበባን ከእንጦጦ፣ ከአንድነትና ከወዳጅነት ፓርኮች ውበት ጎን ለጎን የላስቲክ ዳስ መንደሮች እየፈጠርንላት መሄዳችን ትክክል ነው ተብሎ ሊወሰድ አይችልም። ጉራማይሌ ውበት የለም። የሥራ ዕድል ፈጠራው የአዲስ አበባ ከተማን ውበት የሚጋፋ መሆን የለበትም። የነዋሪዎችም የእግረኞች መተላለፊያዎች በአግባቡ ሊከበሩና ሊጠበቁ ይገባልና ይህንን ጉዳይ እንደገና እናስብበት።

ባለፉት ጊዜያት መሬትና ቤት እንዴትና ለእነማን ነበር የሚሰጠው? በአንዳንዱ አካባቢ አምባገንንነት እያቆጠቆጠ፣ ሙስናና መጠቃቀም እውነትንና ፍትሕን እየተጫነው እየሄደ ነው። በተለያዩ ቆሻሻ ተግባራት ውስጥ ተዘፈቁ እየተባለ ስማቸው በመጥፎ የሚነሱ ጥቂት ሰዎችም ሰኔ 14 ተመርጠዋል። ከዚህ አንፃር የወደፊቱ የሕዝባችን አስተዳደር ባለፈው ዓይነት እንዳይቀጥል አሸናፊው ፓርቲም መንግሥትም ሊያስቡበት ይገባል። የለውጡ መንግሥት የወያኔን ጉድ እስካወጣው ድረስ በወቅቱ የባለሥልጣናት ስም በሙስና ሲነሳ ‹‹አሉባልታ ነው›› ይባል ነበር። የዛሬውም ጉድ እንዲወጣ የግድ ሌላ መንግሥት መምጣት የለበትም። በኢትዮጵያ ጥላ ሥር ራሱን በራሱ የሚያርም ሥርዓት መፍጠር አለብን።

ሰሞኑን የታላቋ ወዳጃችንና አጋራችን የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ 100ኛ ዓመቱን ሲያከብር፣ በአገሪቱ ውስጥ ያመጣውን ለውጥና ቻይናን በዓለም ላይ የት እንዳደረሳት እናስብ። በዚህ ሒደት ውስጥ ቻይናዎች በምን ዓይነት ልባዊ መግባባት፣ መተሳሰብና መከባበር አገራቸውን የት እንዳደረሷት እናስብ፡፡ ፓርቲው የሕዝቡን ሕይወት ለመቀየር የሄደባቸውን መንገዶች በአብዛኛው ለፕሮፓጋንዳ አልተጠቀመባቸውም። ለዚህም ነው ቻይና እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰችው። እኛ ግን እንደዚህ እየተነዳደፍንና እየተነቋቆርን፣ የፓርቲ የበላይነትን በተዛባ መንገድ ለማንገስ እየሞከርን መጨረሻችን ያሳስባል። ስለዚህ ኢትዮጵያ በውስጧና በዙሪያዋ እንዲሁም በርቀት ጭምር ያንዣበቡባትን ብቻ ሳይሆን፣ እያቃጠሏት ያሉትን የእናት ጡት ነካሾችና አጋሮቻቸው መክተን ብቻ ሳይሆን፣ ሴራቸውን አክሽፈንና የኢትዮጵያ ሕዝብ አሸናፊ ሆኖ ከምንፈልገው ግብ ላይ እንድንደርስ ውሸት፣ ሸፍጥ፣ ቅጥፈት፣ ራስ ወዳድነት፣ ዕብሪት፣ ምቀኝነት፣ ትምክህት፣ መታበይ፣ ከፋፋይነት፣ ጎሰኝነትና ጠባብ የሃይማኖት አመለካከት፣ ወዘተ. እንደገና ትንሳዔ እንዳያገኙ ተደርጎ ቀብራቸው መፈጸም አለበት።

ሌላው ጉዳይ ምግብና አልባሳት ያላቸው ለሌላቸው እንደሚያጋሩት ሁሉ፣ አገር ሰላም እንድትሆን ‹‹እኔ ብቻ ነኝ የምወሰንልህ አንተ ዝም ብለህ ተቀበል›› ከሚል የቆየ አባዜ ለመላቀቅ፣ ከብጥብጥና ከሁከት የፀዳች አገር እንድትኖረንና ሁሉም ዓይነት ሐሳቦች በምክክር ያለ ልዩነት እንዲስተናገዱ ለማድረግ፣ ሥልጣንን ለሌሎች የማጋራትም ጉዳይ ቢታይ ክፉ አይደለም። ባለፉት ሦስት ዓመታት አልፎ  አልፎ የታዩት ወጣ ያሉ የሥልጣን አሳታፊነት በጎ ጅምሮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። ደመወዝ ከሚከፈላቸው አማካሪዎች በተጨማሪ የሕዝቡንም ምክር ማዳመጥ ያሻል። በየሙያ ዘርፉ ከመንግሥት ሰዎች ውጪ የሚሰጡ አስተያየቶችም በሙያው ላይ ተመሥርተው እስከሆነ ድረስ አክብሮ መቀበሉ አይጎዳም። እርስ በርስ መጠራጠር ክፉኛ ጎድቶናል። ለአገራቸው ተገቢው ዕውቀትና መታመን ያላቸው የፓርቲ አባላት ብቻ አይደሉም። ‹‹መደመር›› ማለት አንዱ ገጽታው አሳታፊነትና ከግለኝነት መላቀቅ ነው። ለራስ አገር እንጂ ለራስ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ መንደር፣ ፓርቲ ብቻ ታስቦ የትም አይደረስም።

ከሌሎች መልካም ነገሮችን ስንጠብቅ እኛም መልካም እንሁን። መልካም መልካሙን ዘርተን እንጨድ። የራሳችንን ጉድፍ ሳናወጣ፣ እንደ ጉድፍም ሳይቆረቁረን የሌሎችን  ጉድፍ  ብቻ አንይ፡፡ ሁላችንም እንደ ዘመን መለወጫ ውኃ ወንዝ ወርደን አብረን እንታጠብ፡፡ ውስጣችንም ይፅዳና እስቲ አዲሱን ዓመት ከልባችን ፅዱ በፅዱ ሆነን እንቀበለው። የዘንድሮ ምርጫ በጎ ጎኑ እጅግ ከፍተኛ እንደነበር መውሰድም ጤናማ አተያይ ነው።

ስለምርጫ የሚያውቅም  ምንም  የማያውቅም በጅምላ፣ ‹‹የዘንድሮ ምርጫ ብቻ ነው ምርጫ የሚባለው፡፡ ከቀደምት ምርጫዎችምንም አላገኝንም›› በሚል መታበይ ተገቢ አይሆንም። በዚህ ላይ የየወቅቶቹን የዓለምና የአፍሪካ የሥልጣኔዎች ደረጃ ልዩነት አንመልከት፡፡ የምርጫ ተሞክሯቸውን በበጎ የወሰድንላቸው ስዊድን፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉት እንኳን የዛሬ 30 እና 50 ዓመታት ካካሄዷቸው ምርጫዎች  እያሻሻሉ  መጥተዋል።  ያለፈውን  ነገር  ሁሉ ዝም ብሎ በጅምላ የመኮነን አባዜ መቼ እንደሚለቀን አሳሳቢ ነው። ሌላው ቢቀር  ምርጫ 1997 ትውልዱን ያነቃነቀ ምርጫ መሆኑን አንካድ። በሚሊዮን ብሮች የተካሄደውን ምርጫ በቢሊዮን ብሮች ከተካሄደው ጋርም አናነፃፅረው። ከዚህ አንፃር የሰኔ 14 ምርጫ የማይናቁ  ክፍተቶች  የታዩበት ቢሆንም፣ ምርጫ ቦርድ ግን አሁንም ቢሆን የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ስለሆነ ሊመሠገን ይገባዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን ግን የማያምንበትን መርህ የጣሰ አካሄድ ማንም ይሁን ማን ‹‹አይሆንም›› ማለትን እንደ አቋም በፅናት መያዝ አለበት።

በተረፈ ዛሬም እንደ ትናንቱ ካልታመንን ስለተመረጥን ብቻ ዋጋ የለውም። ከሁሉም መታመን፣ ፍቅርና ከበሬታ ይበልጣል። የመፎጋገር፣ የመወራረፍ፣ የመፈራረጅ ፖለቲካ አይረባንም። በጎ አስተሳሰብ ከራሳችን ይጀመር። በሕዝባችን ልብ ውስጥ  በፍቅር እንንገሥ። ተፈርተንና ተጠልተን ሳይሆን ተወደን እንከበር። ከኢትዮጵያና ከሕዝቦቿ የሥልጣን  ወንበር  አይበልጥብንም፡፡ ኢትዮጵያ ለከፈልንላት እውነተኛ መስዋዕትነት ነገ እንደ እናት ዋጋችንን ትከፍለናለች፡፡ ያለዚያ ደግሞ ትፋረደናለች፡፡ ከዚህ በኋላ በሚረቡም ሆነ በማይረቡ የተለያዩ ሰበቦች የተነሳ መናቆሩን ትተን  ፊታችንን  ሕዝባችንን  አጥግበን ወደ ማኖር እናዙር። ተፎካካሪዎችም ብትሆኑ ምንም ይሁን ምን አሁንም አታኩርፉ። እንቅስቃሴያችሁ በዕውቀትና በእውነት ላይ የተመሠረተ ይሁን። ከጋራ አገራችን ውጪ የትም አይደረስምና በጉዟችሁ ሁሉ አገራችሁንና ሕዝባችሁን አስቀድሙ፡፡ አንዴ ወይም ሁለቴ ብትመረጡ እንጂ ሰማይና ምድር እስኪያልፉ ድረስ ለዘለዓለም ተመርጣችሁ በሥልጣን ወንበር ላይ ልትኖሩ እንደማትችሉ ተገንዘቡ። ሰላምና ደኅንነት ለአገራችንና ለሕዝባችን ይሁን።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሽግግሩ ወቅት የምርጫ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሥራችና ለስድስት ዓመታትም የመጀመርያው ምክትል ዋና ኃላፊ በመሆን በአገር ውስጥም በውጭም ተሞክሮ ያላቸው ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...