Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ26 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው ኩባንያ በፍራፍሬዎች ውህድ የተሠሩ መጠጦች ለገበያ አቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአንድ ኢትዮጵያዊና በሦስት የውጭ አገር ባለሀብቶች ጥምረት በ26 ሚሊዮን ዶላር ተመሥርቶ ባለፈው ዓመት ዕውን ሊሆን ተቃርቦ ሳለ፣ በዓለም አቀፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተስተጓጉሎ የነበረው የኮማሪ ቤቬሬጅስ ምርቶች በይፋ ለገበያ መቅረባቸው ተገለጸ፡፡

‹‹በኢትዮጵያውያን የተጠመቁ መጠጦች ለኢትዮጵያውያን ይዳረሱ›› በሚል ዕሳቤ ወደ ገበያ እንደመጣ ያስታወቀው የአራዳ መጠጦች አምራች ኩባንያ ኮማሪ ቤቬሬጅስ፣ ከበርካታ ውጣ ውረዶች በኋላ አምስት በመቶ የአልኮል መጠን ያላቸው ሦስት ዓይነት ከስኳር ነፃ (Sugar Free) የሆኑ ምርቶች ለገበያ ማዋሉን አስታውቋል፡፡

ኩባንያው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳመላከተው፣ ከአራት ዓመታት በፊት ዕውን የሆነውና የኢትዮጵያ፣ የአሜሪካ፣ የብሪታንያና፣ እንዲሁም የደች ዜግነት ያላቸው የሥራ ፈጣሪዎች የተጠነሰሰው ሲሆን፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ ባሉ የፋይናንስ አጋሮች ለአብነትም ከጀርመን ፋሚሊ ፈንድና ከዳሽን ባንክ 26 ሚሊዮን ዶላር አግኝቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

ኩባንያው በአማራ ክልላዊ መንግሥት ደብረ ብርሃን ከተማ መዳረሻ ጫጫ ከተማ ጮቄ በሚባለው አካባቢ ፋብሪካ የገነባ ሲሆን፣ በ132 ሠራተኞች በመታገዝ 27,000 ጠርሙስ የኮክቴል መጠጦችን በሰዓት የማምረት አቅም ይዞ ወደ ሥራ እንደገባ ተገልጿል፡፡

በ2012 ዓ.ም. ምርቱን ለገበያ የማቅረብ ዕቅድ ይዞ ተንቀሳቅሶ እንደነበረ ያስታወቀው ኩባንያው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በታሰበላቸው ጊዜ እንዲገቡ የተፈለጉትን ከውጭ የሚገቡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች በወቅቱ እንዳይገቡ እንቅፋት እንደነበረና በታሰበው ጊዜም ምርቶቹ ለገበያ እንዳይቀርቡ ሳንካ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

ኩባንያው በሎሚ፣ በአፕልና በአናናስ ካቀረባቸው የአራዳ የኮክቴል አልኮል መጠጦች በተጨማሪ ሌሎች የጣዕም ይዘት ያላቸውን ምርቶች በመጪው የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት ለገበያ እንደሚያቀርብ ገልጿል፡፡ “አራዳ” የሚለው ስያሜን ለምርቶቹ መጠሪያነት የመረጠው፣ ጣዕሙን በሚሞክሩ ሰዎች ዘንድ የንቃትና የብርታት ስሜትን ለማንፀባረቅ በማሰብ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት የኮክቴል አልኮል መጠጦችን ለኢትዮጵያ ገበያ ለማቅረብ የተጠነሰሰው ኩባን፣ ከደብረ ብርሃን ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ጫጫ ከተማ ጮቄ ቀበሌ አራት ሔክታር መሬት አግኝቶ ወደ ሥራ እንደገባ ይታወሳል፡፡

በየካቲት 2010 ዓ.ም. 11ኛው የአልኮል መጠጥ አምራች ኩባንያ በመሆን የንግድ ፈቃድ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አግኝቶ ወደ ገበያ የተቀላቀለው ኮማሪ የመጠጦች አምራች ድርጅት፣ ከአዲስ አበባ ከተማና ከኦሮሚያ ክልል ውጪ በአልኮል መጠጦች ዘርፍ በአማራ ክልል የተቋቋመ ድርጀት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች