Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ወቅታዊውን የአገራችንን ሁኔታ ከአንድ መሠረታዊ ጉዳይ በመነሳት ስቃኘው፣ የሰሞኑ ገጠመኛችን እኔን ወደኋላ በርካታ ዓመታት መልሶኛል፡፡ ከዚያ ትውስታ ተነስቼ ወደ ሰሞኑ ጉዳይ እመለሳለሁ፡፡ ፈረንጆቹ ‹‹ማርጀትህን የምታውቀው በተስፋ መኖር ትተህ በትዝታ መኖር ስትጀምር ነው›› የሚሉት ብሂል ለጊዜው ባይመለከተኝም፣ አንዳንድ ትዝታዎች ግን የግድ መነሳት አለባቸው እላለሁ፡፡ ለነገሩ አብዛኛዎቹ የትዝታ ዘፈኖቻችን የአድማጭን ቀልብ ይሰርቁ የለ? ስለዚህ ትዝታን ማንጎራጎር ባልችልም አንድ ሁላችንም የምናስታውሰውን ትዝታ ላካፍላችሁ፡፡

የኤርትራ መንግሥት በድንገት ባድመን መውረሩ የተነገረ ዕለት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት ተነቃንቆ እንደተነሳ አይረሳንም፡፡ ምንም እንኳ ወረራው በምሽት ዜና ከመታወጁ ሰዓታት በፊት፣ ለፓርላማው በቀረበው ሪፖርት የአገሪቱ ወታደራዊ ቁመና አስተማማኝና ጠላትን በብቃት መመከት የሚያስችል ነው ቢባልም፣ ባድመ ላይ ወረራ ያካሄደውን የኤርትራ መንግሥት ጦር ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ገትሮ የያዘው የአካባቢው ሚሊሻ እንደነበር ሰምተናል፡፡ ከዚያ በኋላ የዛጉ ታንኮችና መድፎች ዕድሳት እየተደረገላቸው ወደ ባድመ ሲንቀሳቀሱና ልምድ ያላቸው የቀድሞ ጦር አባላት ለዘመቻ ሲጠሩ ዓይተናል፡፡ ከዚያም የአገሪቱ ወጣቶች ከዳር እስከዳር ዘምተው የፈጸሙትን ገድልም እናስታውሳለን፡፡

በዚያን ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ከነበሩት ተቋማት መካከል ከፍተኛ ክብርና ሞገስ የተጎናጸፈ አንድ መሥርያ ቤት ነበር፡፡ በአንዲት ታዋቂ ኢትዮጵያዊት ይመራ የነበረው ‹‹የመንግሥት ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት›› ሁሌም የማልረሳው ተቋም ነው፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነትን የየቀኑን ሪፖርት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ ሚዲያዎች በኩል ያሠራጭ የነበረው ይህ ተቋም፣ እስካሁን ድረስ መንግሥት አሉኝ ከሚላቸው እጅግ በጣም ጥቂት መንግሥታዊ ተቋማት በቁንጮነት ይጠቀሳል፡፡ እንደ ዛሬው ሳይሆን ሁሉም ነገር ‹‹ሚስጥርና ድብቅ›› በሆነበት በዚያን ጊዜ፣ ይህ የመንግሥት ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት በኢትዮ-ኤርትራ የጦርነት ግንባሮች የተከናወኑትን ድርጊቶች እግር በእግር እየተከታተለ ይነግረን ነበር፡፡ ከአንዳንድ ለብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ከሆኑ ጉዳዮች በቀር ብዙዎችን ክስተቶች በትኩሱ እንድናውቅ ረድቶናል፡፡ ይህንን ተቋም ይመሩ የነበሩት እመቤት በሠሩት ሥራ በበኩሌ ዛሬም ድረስ አመሠግናቸዋለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የላቀ ተግባር እያስታወስን የማመስገን ባህል ቢኖረን ኖሮ እያልኩም እቆጫለሁ፡፡ ለማንኛውም በአጭሩ ትዝታዬ ይኼ ሆኖ ወደ ሰሞኑ ገጠመኝ ልመለስ፡፡

ዘመኑ የመረጃ ነው፡፡ መረጃ በተቀላጠፈ መንገድ ከአንዱ ሥፍራ ወደ ሌላው እንዲተላለፍ ደግሞ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ ረቀቅ ያሉ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች በየቀኑ እየተፈበረኩ ነው፡፡ የሞባይልና የኢንተርኔት የመገናኛ ዘዴዎች በተራቀቁ የቴክኖሎጂ ምርቶች እየተደገፉ፣ ዘመናችን በኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ታላቅ ግስጋሴ እያደረገ ነው፡፡ ይህንን አመቺ ሁኔታ በመጠቀም መረጃን በአግባቡ መለዋወጥ ካልቻልን፣ ማዘን ያለብን በራሳችን እንጂ በማንም ሊሆን አይገባም፡፡ ይህ ዘመን ለማመን እስከሚያዳግት ድረስ የተለመደውን የሚዲያ ተፅዕኖ የሚገዳደሩ የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን እያስተዋወቀ ነው፡፡ ዩቲዩብ፣ ፌስቡክና ትዊተር… የሚባሉት ገጾች በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመረጃ ልውውጥ እያሳተፉ ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅና በሰሜን አፍሪካ የተካሄዱት የፀደይ አብዮቶች ሳይቀሩ በቀዳሚነት መሠረት ያደረጉት እነዚህን ነበር፡፡ በአገራችንም በተለይ የዩቲዩብና የፌስቡክ ተገልጋዮች ቁጥር በጣም እየጨመረ ሲሆን፣ የትዊተር ተገልጋዮች ቁጥርም እያሻቀበ ነው፡፡

መረጃዎች ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው በፍጥነት በሚተላለፉበት በአሁኑ ዘመን፣ ገጠር ውስጥ አንድ ነገር ኮሽ ሲል አዲስ አበባ በደቂቃዎች ውስጥ ይሰማል፡፡ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች የሚተላለፉት መረጃዎች እንደወረዱ ስለሆኑና ብዙውን ጊዜ ግራና ቀኝ በማየት ሚዛናዊነት ስለማይታይባቸው፣ አንድ ጉዳይ አፈትልኮ ከወጣ በብዙዎቻችን ዘንድ እንደ እውነት ይቆጠራል፡፡ በብዙ አገሮች ከግላዊ ሚስጥሮች ማፈትለክ እስከ ብሔራዊ ደኅንነት አደጋዎች ድረስ የደረሱትን ችግሮች እናውቃለን፡፡ ይህ ደግሞ በእያንዳንዳችን ላይ ሳይቀር ሊያጋጥም የሚችል አሰቃቂ ነገር ነው፡፡ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ያላቸውን ከፍተኛ  ጠቀሜታ ያህል አደጋውም የዚያን ያህል ነው፡፡

ከተነሳሁበት ትዝታ አንፃር ትዝብቴን ላቅርብ፡፡ መንግሥትን የሚያህል ትልቅ አቅም ያለው አካል በፖለቲካው፣ በዲፕሎማሲውና በተለያዩ ጉዳዮች አሉ የሚባሉ የአገሪቱን ዜጎች ማንቀሳቀስ ሲያቅተው ይነደኝ ነበር፡፡ በአገር ላይ ጦርነት አውጆ የመከላከያ ሠራዊቱን የወረረና አሰቃቂ ዕልቂት የፈጸመ፣ በማይካድራ በጀሌዎቹ አማካይነት በማንነታቸው ምክንያት ንፁኃንን የጨፈጨፈ፣ ለትግራይ ክልል ሕዝብ ዕልቂት የደገሰ፣ የአገሪቱን አንጡራ ሀብት ለውድመት የዳረገና ኢትዮጵያ ተዳክማ ለጠላት ቀላል ዒላማ እንድትሆን ያሴረ የወንበዴዎች ጥርቅም በውሸት ፕሮፓጋንዳ የምዕራቡን ዓለም ሲቆጣጠር ያበሳጫል፡፡ ትናንት ለመብታቸው የቆሙ ወገኖችን ሲገድልና በየእስር ቤቱ ሲያጉር የነበረ የአምባገነኖች ስብስብ በለኮሰው ጦርነት አከርካሪው ከተመታ በኋላ፣ እንደገና እንዲያንሰራራ ዕድል ሲሰጠውም ያስቆጫል፡፡ በሐሰት ፕሮፓጋንዳው የዓለምን ጆሮ ማግኘቱ ያበግናል፡፡

 ለአገሪቱ እንደ ‹‹ቃል አቀባይ›› ሆኖ ወጣ ብሎ ያለውን እውነታ ማስረዳት የሚችል ቋሚ መንግሥታዊ አካል አለመኖሩ የሚያሳዝን ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ማድረግ ሲያቅተውና የኢትዮጵያዊያንን ዕምቅ አቅም መጠቀም ተስኖት ይህ ሁሉ ትርምስ ቢፈጠር ምን ይገርማል? በቀደም ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን የውጭ ዲፕሎማሲ ሚሲዮኖች ቁጥር በግማሽ መቀነስ አለባቸው ሲሉ በጣም ነበረ ደስ ያለኝ፡፡ ዲፕሎማሲው ከተወሰኑ ቦታዎች በስተቀር የጡረተኞችና የባለውለታዎች፣ እንዲሁም የዚህ ግፈኛ ቡድን ግብረ በላዎች የነበሩ ተላላኪዎች መፈንጫ ስለሆነ፣ ለአገር አሳቢ የሆኑ ምሁራንና ልሂቃን ለየት ባለ መንገድ ቢሳተፉበት የተሸለ ውጤት ይገኝበታል፡፡ በበርካታ መስኮች የመንግሥት ግልጽነትና ተዓማኒነት እየወረደ የሐሰተኞች ውሸት የሚገዝፈው፣ መንግሥት ሁነኛ ቃል አቀባይ አካል ስለሌለው ነው፡፡ በተግባቦት (ኮሙዩኒኬሽን) ሙያ ከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ዜጎች ከአገር ውስጥም ከውጭም ተመርጠው ቢሰማሩ፣ እንኳን ለዚህ ኋላቀር ጦር ጠማኝ ጠባብ ስብስብ ቀርቶ ግብፅን በቀላሉ ማንበርከክ ይቻል ነበር፡፡ ማንቀላፋት ይብቃ፡፡

(ነቢያት ባዚን፣ ከዓድዋ ድልድይ)

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...