በመስፍን ሀብቱ
ሰኞ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማው ባደረጉት ንግግር ውስጥ ካነሷቸው ነጥቦች አንደኛው የዲፕሎማሲው ጉዳይ ነው። አንዳንድ ሰዎች በዲፕሎማሲው መስክ ወያኔ እንደ በለጠን አርገው የሚያቀርቡ አሉ። ይኼ ጨርሶ የተሳሳተ ነው፡፡ የመንግሥትን ዲፕሎማሲ ስኬታማ እንዳይሆን ያደረገው ወያኔ በሚሊዮን ብር የቀጠራቸው ሎቢስቶች ናቸው እንጂ ወያኔ ራሱ በሠራው ሥራ አይደለም። ችሎታውም ስለሌለው። ወያኔ ገና ከድሮ ጀምሮ ዘለዓለም ዲፕሎማሲውን በተወሰኑ ፈረንጆች እያሠራ የኖረ ነው።
የሚደንቀን ግን የራሳችን መንግሥት ዲፕሎማሲ እንዲህ የሚፈለገውን ውጤት ሳያመጣ ሲቀር ነው። ለነገሩ የውጭ ዲፕሎማሲ እንዲሠራ ለማድረግ የሚፈለገው ሥራ በመሠረቱ በቀጥታ ከውጭ መንግሥታት ጋር ያለው በይነ ግብር ብቻ አይደለም። ዋናው ጉዳይ የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታት ፖሊሲን ለማውጣትና ለማስፈጸም ውሳኔ ላይ የሚደርሱት እንዴት እንደሆነ ማወቁ ላይ ነው። ይህን ጥያቄ በትክክል መመለስ ዲፕሎማሲያችን የት ላይ እንደ ደከመ ለመረዳት ያስችለናል። ይህን ስንመልስ ነው በዲፕሎማሲው ረገድ በውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊ (በስህተት “ዳያስፖራ” የሚባለው) ምን ያህል ወሳኝ ሚና ሊጫወት እንደሚችል መረዳት የምንችለው።
ውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊ በእጅጉ አብዛኛው በራሱ ጥረት ተፍጨርጭሮ የተማረና ሥራ የያዘ ነው። በዚህ ረገድ ያለ ምንም ማጋነን በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጠንካራ ሠራተኞች፣ በተሰማሩበት ሥራም ሆነ ትምህርት እጅግ የተመሠገኑ ናቸው። አገራቸውንም በመውደዳቸው ስለአገራቸው ዘለዓለም እንደ ተጨነቁና እንዳሰቡ ነው። የአገራቸውንም ችግር በሚመለከት ሠልፍ ሲጠራ እንደ ጎርፍ የሚወጡትም፣ መዋጮም የሚያዋጡት ለአገራቸውና ለወገናቸው ባላቸው ፍቅር ነው። ብዙዎቹ አገራቸው እያሉ ያጡትን ዕድል በቀላሉ ሲያገኙ ወደ ትምህርት በመግባት እስከ ከፍተኛ ደረጃ ድረስ ሊማሩ ችለዋል። በአሁኑ ጊዜ በተለይም በዩናይትድ ስቴትስና ካናዳ በየዩኒቨርሲቲው በማስተማር ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ቁጥር እጅግ ብዙ ነው። ችሎታቸውም የተመሰከረለት ነው። ከዚህ አንፃር ካየነው በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ዕምቅ ችሎታና ሙያዊ ልምድ (ኤክስፐርቲዝ) ለአገራቸው ቢያውሉት ኖሮ፣ በኢትዮጵያ ሊኖር የሚችለውን ለውጥ መገመት አይከብድም።
በአሁኑ ወቅት በተለይ ተነጥሎ ለአገራችን ኋላቀርነት ተጠያቂ የሆነው በመንግሥትም ሆነ በክልሉ ሴክተር ገንኖ ያለው ከፍተኛ የችሎታ ማነስ ጉዳይ ነው። በውጭ አገር ያለው የተማረው ክፍል በአገራችን ለሚያስፈልገው በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በትምህርት፣ በሕክምና፣ ወዘተ. አመራር በመስጠት ቢሳተፍ ሊገኝ የሚችለውን ውጤት በቀላሉ ማሥላት ይቻላል። ታዲያ በአገራችን በሚካሄደው የለውጥና የልማት ሒደት ውስጥ ይህን ክፍል ማሳተፍ የሚቻለው እንዴት ነው የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል። ምን ቢደረግ ነው ይኼ አገሩን በተቻለው አቅሙ ሊረዳ የሚችለውን/የሚፈልገውን ክፍል ማሳተፍ የሚቻለው? እስካሁንስ በሚፈለገው መጠን ሊሳተፍ ያልቻለው ለምንድነው ብለን መጠየቅ ይኖርብናል።
አብዛኛው ውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊ ወደ ውጭ አገር በገፍ የወጣው በደርግ ጊዜ ነው። ታዲያ እንዲህ አገሩንና ወገኑን የሚወደው ኢትዮጵያዊ እንዴት ነው ደርግ ከወረደ በኋላ በአገሩ ጉዳይ በቀጥታ ሊሳተፍ ያልቻለው? መልሱ ቀላል ነው። ወያኔ የተማረ ኢትዮጵያዊ እንደ ጦር ይፈራ ስለነበር ውጭ አገርም ያለው ኢትዮጵያዊ በነፃነትና በቀጥታ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚው እንዳይሳተፍ ለማገድ ዓላማው ስለነበር ውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊ አገሩ መጥቶ ከፖለቲካና መከላከያ/ፀጥታ በስተቀር መሳተፍ ይችላል አለ። በሕገ መንግሥቱም ውስጥ ኢትዮጵያውያን የሁለት አገር ዜግነት ሊኖራቸው አይችልም ብሎ ደነገገ። ስለዚህ ውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተሳትፎ መብት ሳይኖራቸው፣ ወያኔ በጀመረው የከይሲዎች አገዛዝ ዝም ብለው አንገታቸውን ደፍተው እንዲኖሩ ደነገገ። ውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከሁሉ አስቀድሞ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት በአገራቸው እንዲኖር ይፈልጋሉ። እንዲህ ያለ መብት በሌለበት ምን ይበጀኝ ብለው ወደ አገራቸው ሊመለሱ ይችላሉ? ወያኔ ውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን በራሱ የጨዋታ ሕግ ተሸብበው ስለሰብዓዊ መብትና ስለዴሞክራሲያዊ መብት ሳይጠይቁ አንገታቸውን ደፍተው እንዲገዙ ፈለገ። ይኼ ሊሆን ስለማይችል በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን እጅግ ብዙዎቹ ወደ አገራቸው ተመልሰው ማገልገል ቢፈልጉም ሳይመለሱ ቀሩ። ምንም ቢሆን የሚያስቡትን ሳይገላመጡ እንደ ልባቸው በሚናገሩበትና የሕይወት ዋስትና ባለበት በውጭ አገር ለመቆየት ወሰኑ።
ከሦስት ዓመት በፊት የወያኔ አገዛዝ መጀመርያ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሠልፍ ተደፍሮ ሲገዘገዝ ቆይቶ፣ በኦሮሞና በአማራ ወጣቶች ትግል ሥልጣኑን ለመልቀቅ ሲገደድና አዲስ መንግሥት ሲቋቋም የሕዝቡ ተስፋ ከፍ እንዳለው ሁሉ ውጭ አገር የሚኖረውም ኢትዮጵያዊ ተስፋው እንደገና ብድግ አለ። የወያኔ አገዛዝ ያብቃ እንጂ ውጭ አገር አንድም ቀን ማደር የማንፈልገው ለውጡ ልባችንን ቢሰቅለውም፣ በአንድ በኩል ደግሞ አገራችን ተመልሰን ባለን ችሎታ አገራችንን ለማገልገል ይህ ወያኔ የደነገገው ሕግ ካልተቀየረ ምን ያህል አስተዋጽኦ ይኖረናል የሚለው ፍርኃት ቀፍድዶ ያዘን። ዓብይ በመጀመርያው የፓርላማ ንግግራቸው ብንደመምም በተጨባጭ ግን ያ ከይሲ ሕግ እስካልተቀየረ ድረስ ተሳትፏችን ውሱን መሆኑ እንደማይቀር ታየን። ስለሆነም እስከ ዛሬ ድረስ እንዲህ ያለ ጽሑፍ መጻፍ ከመሰለ ተሳትፎ የዘለለ ሚና ሊኖረን አልቻለም። በአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዝብረቃ፣ በሚዲያ ሰዎች አሳፋሪ ድክመት፣ በአንዳንድ የክልል ባለሥልጣናትና ሠራተኞች ችሎታ ማነስ፣ በዲፕሎማሲው ድክመት እንዲሁም በሌላውም ድክመትና ስህተት ሁሉ እየተሳቀቅን መኖር ተገደናል።
ገና ያልተመለሰውና ይህንን ሁሉ ጉድ ያላየውስ ውጭ አገር ያለ ኢትዮጵያዊ ምንም ለማድረግ የፖለቲካ መብት ከሌለው ምን ሊያደርግ ይመለስ? ይኼ ኢትዮጵያዊ እኮ የውጭ አገር ዜግነት የወሰደው ወዶ አይደለም፣ ለሕይወት ዋስትና እንጂ። ከቀይ ሽብር የተረፈ፣ ከወያኔ የከይሲ አገዛዝም የተረፈው እኮ ከሁሉ አስቀድሞ የሕይወት ዋስትና ይፈልጋል። የውጭ አገር ዜግነት የሚሰጠው ይኼን የደኅንነት ዋስትና ነው። ይህ ደኅንነት ፖለቲካዊ ብቻ አይደለም። አንደ ሰው ሥራ ካጣ ለኑሮው የሚያስፈልገው ድጎማ ሁሉ ይደረግለታል። ውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊ እንዲህ ያለውን የደኅንነት ዋስትና ለምዶ የኖረ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያለ የተሟላ ዋስትና እንደሌለ የታወቀ ቢሆንም የፖለቲካ ዋስትና ግን ሊኖር ይችላል። ሕግን የመደንገግ ጉዳይ ስለሆነ። መንግሥት ፖሊሲውን ማስተካከል ብቻ ነው የሚጠበቅበት። ስለሆነም ውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እንዲህ ዋስትና በሌለበት ሁኔታ ለመሥራት አይፈልግም። አንዳንዱም ልጆቹን ጥሎ፣ ሴቷም የምትወደውን ባሏን፣ ወንዱም የሚወዳትን ሚስቱን ትቶ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የደኅንነት ዋስትና ሁኔታ አስተማማኝ መሆን አለበት። ከዚህም ዋናው የፖለቲካ ነፃነት ነው።
እንዲያው ምንም ቢሆን አገሬ ብሎ ከላይ የጠቀስነው ዋስትና ባይረጋገጥም፣ ለውጡ ከወያኔ አገዛዝ ይሻላል ብሎ ለመመለስ ቢፈልግም አሁንም አንዳንድ እንከኖች አሉ ብሎ ስለሚያምን ተመልሶ አገሩን ለማገልገል አይቻለውም። ይህንን ለማድረግ ግን ይህ ክፍል ምን ይፈልጋል? ሰላም፣ መረጋጋት፣ የብሔር ፖለቲካ አምልኮ ቆሞ አገልግሎት ሰጪዎች ቀልጣፋና ትክክለኛ አሠራር መከተላቸው፣ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ሙሉ ለሙሉ መከበር፣ የመንግሥት ሚዲያ አገልግሎት ለሕዝብ እንጂ ለመንግሥት አለመሆኑ፣ ወዘተ የአንድ ብሔር የበላይነት አለ ለሚለው ፍርኃቱ የማያወላዳ መልስ መስጠት፣ በተለያዩ ደረጃዎች የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች ሊጀምር ቢፈልግ ሊያገኝ ስለሚችለው የመንግሥት ትብብር እርግጠኛ አለመሆን፣ ወዘተ. አገር አደጋ ላይ ስትሆን ያሳየው መተባበር ያሉትን ጥርጣሬዎችና ጥያቄዎች አስወግዷል ማለት አይደለም። “ዳያስፖራው” በዲፕሎማሲው ሊካፈል ይገባል እየተባለ ስለ“ዳያስፖራው” የፖለቲካ መብት ግን ምንም አለመነሳቱ ዋና እንቅፋት ሆኖበታል። ስለሆነም ከሁሉ በፊት ፖለቲካዊ መልስ ይፈልጋል።
ውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊ ለአገሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ያለው አቅም ከፍተኛ ነው። እንደ አውሮፓዊ ወይም አሜሪካዊ ዜጋ ያለው የዜግነት መብት ከፍተኛ ስለሆነ ያለበት አገር መንግሥት የሚከተለውን የውጭ ፖሊሲ የመጠየቅ ሲልም የመቃወም መብቱ የተጠበቀ ከመሆኑም በላይ፣ በፓርላማ ባልተወሰኑ ግን መንግሥት በራሱ በሚወስዳቸው ፖሊሲዎች አንድ ዜጋ የፓርላማ አባላትንና ሌሎች ፖለቲከኞችን እየነዘነዘና ለሚዲያም መረጃ እየሰጠ ፖሊሲው እንዲቀየር ወይም እንዳይሳካ ማድረግ ይችላል። ይኼ እንግዲህ በግለሰብ ደረጃ አንድ ሰው ሊያደርገው የሚችለው ነው። እዚህ ላይ ደግሞ መደራጀትና መቀናጀት ሲታከልበት ውጤቱም ይበልጥ ስኬት ሊያሳይ ይችላል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ስለዲፕሎማሲው ካነሱት ጉዳይ አንዱ ኤምባሲዎችን የመቀነስና ውጭ ያለውን ኢትዮጵያዊ ትብብር መሻት ያሉት ጥሩ ሐሳብ ነው። ቢሆንም ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ቢደረግለት ስለሚፈልገው ደግሞ ግልጽ መሆን ያስፈልጋል። መብትና ነፃነትን ያላዘለ ጥሪ የደርጉን “የእናት አገር ጥሪ” እንዳይመስል መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ኤምባሲ መቀነስ ሐሳቡ ጥሩ ቢሆንም ሊያስከትል የሚችለውን የአሠራር ምስቅልቅል በቅጡ አጢኖ መዘጋጀትን ይጠይቃል። ውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊ ከኤምባሲው ሥራ ሊሸፍን የሚችለው ውትወታና ማግባባቱን (አድቮኬሲና ሎቢውን) ብቻ ይመስለኛል። ሌሎች “ክኖትራክቹዋል” የሆኑ ጉዳዮችን ሊሸፍን አይችልም። ይህን የመሳሰሉት ሥራዎች እንዴት እንደሚሠሩ በቅጡ መጤን አለበት። በእርግጥ እንደ ቪዛ ያሉት ጉዳዮች ከአዲስ አበባ ሆኖ በኦንላይን ሊሠሩ ይችላሉ። ሌሎች በኦንላይን ሊሠሩ የማይችሉ ጉዳዮች እንዳሉም የታወቀ ነው። የሆነው ሆኖ ግን ውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊ በአድቮኬሲና ሎቢ ብዙ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። ከሁሉ አስቀድሞ ግን የሚገባውን የፖለቲካ መብቱን ማክበር ያስፈልጋል። ውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁለት ዓይነት ዜግነት ሊኖራቸው እንደሚችልና በፖለቲካውም ለመሳተፍ እንደሚችሉ በሕግ መደንገግ አለበት።
በእርግጥ የሁለት አገር ዜግነት ጉዳይ በኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ የሌሎቹንም አገሮች ሕግ የሚመለከት ነው። በሽብርተኞች ምክንያት አንዳንድ አገሮች የሁለት አገር ዜጋነት የሚለውን በሕግ ሰርዘዋል። እንዲህ ባለው ሁኔታ ውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው የፖለቲካ ሒደት ውስጥ የመሳተፍ መብታቸው ግን ሊደነገግ ይችላል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሒደት ውስጥ ወደ ዴሞክራሲ በሚደረገው ሽግግር፣ ብሎም በኢኮኖሚውም፣ በትምህርትና በሕክምና ረድፍ በመሳተፍ ውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ የፖለቲካ መብታቸው ከታወቀና ከላይ የጠቀስናቸው የፖለቲካና የአሠራር እንቅፋቶች ከተነሱ ማለት ነው።
ከአዘጋጁ፡– ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡