Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገት​​​​​​​አገራችን እንዴት ሰነበተች?!

​​​​​​​አገራችን እንዴት ሰነበተች?!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የኢትዮጵያን ሕዝቦች አባልቶ አገር የለሽና ሰላም የለሽ ገሃነም ውስጥ የመክተት ከፍ ያለ አደጋ ባንዣበበበት፣ ውስብሰብ ሴራ በተፈተለበት የከፋ ጊዜ ውስጥ አንዱን ሕመም አልፈን፣ አሳልፈን ተንፈስ አልን ከማለታችን፣ ሌላው ብቅና ከተፍ ብሎ አንድነታችንን፣ ቁርጠኝነታችንን፣ እምነታችንን፣ ወዘተ ሲፈታተኑ እናያለን፡፡ እንደምን ሰንብተናል? እንዴት ውለን አድረናል? ብለን አጥብቀን የምንጠይቀውና የምንጠያየቀው ከሁሉም በላይ ሕመማችንና በሽታችንን ይበልጥ ለይተን አውቀን በእሱው ላይ ለመረባረብ በዚሁ ግብ ላይ የተመጠነና ያነጣጠረ ኅብረታችንንና ትግላችንን ለማስተባበርና ለማጠናከር ነው፡፡

ብዙ ግርግርና ግብግብ፣ አለመግባባትና ተቃውሞ፣ ከዚያም ይበልጥ የለየለት ፀበኝነትና ቅራኔ የገጠመውና ያጋጠመው የምርጫ ጉዳይ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ፣ ‹‹ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ›› ሆኖ የተካሄደው የሰኔ 14 ምርጫ ከሞላ ጎደል በድል ተጠናቋል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ምርጫው ያለ አደጋ ተጠናቋል፡፡ አሁን የምንገኘው የምርጫ 2013 የድምፅ መስጫ ዋነኛው ቀን ተግባር ከተከናወነ በኋላ ባሉትና በሕግም የምርጫ ውጤት መግለጫ ጊዜ ተብሎ በተወሰነው ጊዜ መጨረሻ ላይ ቢሆንም፣ ይህንን ጽሑፍ ስጀምር እስካሁን ያገኘሁት የለየለት ነገር የሚናገር ውጤት አልሰማሁም፡፡ ያም ቢሆን ግን አሁን ከዚህ በላይ እንደገለጽኩት ምርጫው በሰላም መጠናቀቁ በራሱ ትልቅ ድል ነው፡፡ ትርጉም የሌለው ምርጫ ነው፣ አገር፣ መንግሥት፣ ተፎካካሪና ተሳታፊ ፓርቲዎች ማፈሪያ ይሆኑበታል ተብሎ ‹‹ሲጠበቅ›› እና ‹‹ሲናፈቅ›› የምርጫው የሕዝብ ተሳትፎ በራሱ ‹ዓይናቸው ደም የለበሰ› የውጭ አገርና ‹‹አጋር›› ሰዎችን ሳይቀር ኩም አደረገ፡፡

ምርጫው ይህን ያህል በስኬት የተከናወነው እንደተፈለገውና እንደተገመተው ብቻ ሳይሆን፣ ሲሠራበትና ሲሴርበት እንደቆየው መሳቂያና መሳለቂያ ባለመሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያም በፊትና እስከ ምርጫው የድምፅ መስጫ ቀን ድረስ ምርጫውንና የምርጫውን ሒደት እያንዳንዱን መረማመጃ እንዳይሆን አድርጎ፣ ሕዝብንና መንግሥትን የትርምስ አዙሪት ውስጥ ለመክተት በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች የጥፋት ኃይሎች የደገሱልን የትኛው ደባ ከፀጥታና ሕግ አስከባሪ ኃይሎች ቅድሚያ መከላከል አምልጦ ዕውን ይሆን ይሆን ከሚለው ሥጋታችን ተገላግለናል፡፡ ዕፎይ ብለናል፡፡ እግዜር ሳይደግስ ስለማይጣላ ነው እንጂ፣ የዚሁ የአዲስ አበባው ተራና የዘወትር የመብት ጥያቄ ወይም አቤቱታ ብቻ መስሎ ብቅ ያለው የመስቀል አደባባይ ነገር በ‹‹ኪነ ጥበቡ›› ያመለጥነው አደጋ አንድ ምሳሌ ነው፡፡ በአደባባዩ የተነሳውን የ‹‹መብት››፣ የ‹‹ተቃውሞ›› ጥያቄ መነሻ ያደረገ ግርግር ቢፈጠርና ቢፋፋም፣ ይህም ለአሸባሪዎች መሹለክለኪያ ሽፋን ሆኖ ቢያገለግል ለከፋ ጥቃት መጋለጥና ይህም ሳይበቃ መዓት ‹‹ተቃውሞ›› የበዛበትን ምርጫ ላይ ሌላ ተጨማሪ የማሰናከያ ሰበብ በፈጠረ ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን ምርጫውን በሰላምና በሚገርም የሕዝብ ተሳትፎ አጠናቀናል፡፡

የምርጫ 2013 ጥቂት ክንዋኔ ወደ ጳግሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. (ያን ዕለት ለሚደረገው የድምፅ መስጫ ቀን) ቢራዘምም፣ ከራሱ ከሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የድምፅ መስጫ ዕለት ለሐሙስ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በቀጠሮ ያደሩ የጥቂት የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ መስጠት ውዝፍ ሥራን የመሰለ ውዥቀት (Anomaly) መኖሩ ባይቀርም፣ ገና ውጤቱ ሙሉ በሙሉ ሳይገለጽ፣ እንዲያውም ከመገለጹ በፊት ምርጫው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሪፈረንደም እስከመባል የዘለቀና የከበደ ክብርና ሞገስ አግኝቷል፡፡ ምርጫውን ሪፈረንደም ወይም ውሳኔ ሕዝብ (ሕዝበ ውሳኔም ይባላል) እስከመባል የገዘፈ ስም አግኝቷል፡፡ ምርጫው ይህን ያህል ክብር አግኝቷል፣ ይህን የመሰለ ስምም አግኝቷል የምለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ሰኞ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በተሰበሰበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ፣ ደጋግመውና አጽንኦት ሰጥተው ሪፈረንደም ሲሉ ስለሰማሁ አይደለም፡፡ በእሳቸው ደረጃ፣ በእሳቸውም አማካይነትና በእሳቸውም በኩል መንግሥታቸውና ፓርቲያቸው ምርጫውን ሪፈረንደም የማለት ያህል ከፍ አድርገው መግለጻቸውና ማክበራቸው በእኔ በኩል ደስ የሚያሰኝ ቢሆንም፣ የስያሜውን መስተጋባት (መስተጋባት የሚባል ከሆነ) የሰማነው ግን ከእሳቸው ንግግር በፊትና ከዚያ አስቀድሞ ገና የምርጫው ዓላማ ሲገለጽና አልገባ ብሎም ብዙዎችን ሲያስቸግርና ሲያወዛውዝ ነው፡፡

ምርጫውን ሪፈረንደም (ውሳኔ ሕዝብ) ለምን እንለዋለን? ውሳኔ ሕዝብ (ሪፈረንደም) ማለትስ ምን ማለት ነው? ከሚለው እንጀምር፡፡ በአገራችን የቅርብ ጊዜና አሁን በሥራ ላይ ባሉ የምርጫ ሕጎች መሠረት ውሳኔ ሕዝብ ማለት ‹‹የሕዝብ ፍላጎትን ለመለካትና የሕዝብን ውሳኔ ለማወቅ ድምፅ የሚጥበት ሥርዓት ነው፡፡ አሁን ያለው የምርጫ ሕግ ይህንን አሁን እዚህ እንዳለ ቃል በቃል የጠቀስኩትን ትርጉም ‹‹…የሕዝብ ፍላጎትን ለመለካት ወይም የሕዝብን ውሳኔ ለማወቅ የሚደረግ የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት ነው›› ይላል፡፡ እዚህ የሕግ ትርጉም ልዩነትና ተመሳሳይነት ውስጥ አልገባም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ጉዳይ ሕዝብ ሪፈረንደም ሰጠ ሲባል ትርጉሙ ከዚህ ውጪ ያለውን የዘወትር ኑሮ የ‹‹አባባል›› ፍቺ የሚመለከት በመሆኑ ነው፡፡ ሕዝብ ምን አለ? ሕዝብ በድርጊቱ፣ በተግባሩ፣ በሁኔታው፣ በዝምታው፣ ወይም በሌላ ዓይነት አኳኃኑ ምን አለ? ማለት ነው፡፡ ‹‹ምን አለ? ሕዝቡ ምን አለ? አገሬን ለሰው ዕንቢ – አልሰጥም አለ…›› እየተባለ በዜማ፣ በሽለላና በፉከራ መልክ ከሚባለው በላይ ነው፡፡ ሕዝብ ተናገረ ማለት ነው፡፡

የዚህን ቃል ትርጉም በአገራችን ሥነ ቃል ወይም ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ጠፍጥፎ የሠራውና ከሞላ ጎደል ሕዝብ ‹‹አፍ›› ውስጥ ያስገባው ምርጫ 97 ነው፡፡ ምርጫ 97 በማራኪ የመድረክ ሙግቶቹ ለተቃዋሚ አገር ያካለለ ድጋፍና ወዶ ገብ ካድሬ ያሳፈሰበት የምርጫ ሒደት ነበር፡፡ የ97 ቅስቀሳና ሙግት ተስፋ በሚጭሩ መፈክሮች ሕዝብን ከዳር ዳር ያነሳሳና ያሟሟቀ ብቻ ሳይሆን፣ ጠርንፎና አፍኖ ይገዛ የነበረውን ኢሕአዴግን ያሳጣና በግልጽ ያስጠላም ነበር፡፡ በድምፅ መስጫው ዕለት በመላው ኢትዮጵያ የታየው 24 ሰዓት ውስጥ ሊገባ የተቃረበ የድምፅ መስጠት ሠልፍና ውሎ ማደር፣ እንዲሁም በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የተመሰከረው (ኢሕአዴግም ራሱ ያመነው) ሽንፈት ምክንያት የተቃዋሚዎች ‹‹ጥሩነት›› ወይም የተሻለነት ሳይሆን የኢሕአዴግ ጥላቻ ነበር፡፡ ሕዝብ ኢሕአዴግን ጠላና፣ ኢሕአዴግን አልፈልግህም አለና ተቃዋሚዎችን መረጠ፡፡ ተቃዋሚዎችን ሕዝብ የመረጠው እነሱን አውቆ አማራጮቹን ወዶ ሳይሆን፣ ከኢሕአዴግስ የማይሻል የለም ብሎ ነው፡፡ ሕዝብ ወሰነ፣ ሪፈረንደም ሰጠ ማለት የመጣው ከዚህ አኳያ ነው፡፡

የአሁኑን ምርጫ፣ ምርጫ 2013ን ሕዝብ ሪፈረንደም የሰጠበት ምርጫ ነው የምንለው ዓብይ አህመድ ስላሉት፣ ከእሳቸውም ሰምተን ሳይሆን እንዲያውም ከእሳቸውም ቀድመን ሕዝብ፣ ከዚህ የበለጠ አደራና ግዳጅ የለም ብሎ በአንድ ቃል የሚናገርበት ግዴታው ነው ብለን ነው፡፡ የዚህ ምክንያት መጀመርያ አገር ብዙ ጣጣና ወከባ ባጋጠመው ለውጥና ሽግግር ውስጥ በመሆኗ ነው፡፡ ለውጡንና ሽግግሩን ዘላቂ የማድረግ፣ ዴሞክራሲን የማደላደል፣ የዴሞክራሲ አውታራትን ገለልተኛ አድርጎ የማንጠፍ ከሁሉም በፊት የሚመጣው አጣዳፊ ተግባር፣ ለውጡንና ሽግግሩን ከክሽፈት ከማዳን መጀመር ከዚህ መነሳት ስላለበት ነው፡፡ የምርጫውም ዓላማ በዚህ ግብ ላይ የተመጠነና የተወሰነ ነው፡፡

ምርጫው የሚካሄድበት ጊዜ ራሱ ለውጡንና ሽግግሩን ማገዝና ወደፊት ማራመድ ቀርቶ ሊያወሳስብና ሊያሰናክል በሚችልበት ሁኔታ የፀብ፣ የጭቅጭቅ፣ የተቃውሞና የመከፋፈል ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ምን ምን/የትኞቹን ዝግጅቶችን አድርገን ምርጫ እንግባ በማለት ፈንታ የለውጡ ቀንደኛ ተቃዋሚዎችና ሳያውቁ ደግሞ፣ ለውጡን የሚጎዱ ወገኖች በቀደዱት የምርጫ ሕገ መንግሥታዊ የጊዜ ገደብ ማለፍ አለማለፍ ላይ አተካራ ውስጥ ገባን፡፡ ይህ ራሱ ብዙ ጊዜ ፈጀ፡፡ ብዙ ያልተገባና የማያዋጣ መንገድ ውስጥ የዕውር ድንብር ጉዞ አስከተለ፡፡ ዛሬም ድረስ ፀፀት ያላስከተለ መንግሥትን በሕገወጥነት መከሰስን፣ ሥልጣን የለህም ማለትን፣ በእሳት መጫወትን፣ የፌዴራላዊ ሥርዓቱን ሕግ መጣስን፣ የገዛ ራስ፣ የእኔ የብቻዬ ‹‹ምርጫ›› ማለትን፣ ‹‹ሠራዊት›› የመገንባትን፣ የአስተዳደር ክልልን፣ የገዛ ራስ የቅርጫ መሬት ማድረግ መድረስ የዘለቀ ውዝብግ፣ ጣጣና ጦርነት አመጣ፡፡ ምን ዓይነት ቅድመ ሁኔታ አሟልተን፣ እንዴት ያለ ቅድመ ዝግጅት አድርገን ምርጫ እናካሂድ የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ የሆነው ዝም ብሎ በትናንትናው ዓይነትና ሁኔታ የሚካሄድ ምርጫ የሕዝብን ሉዓላዊነት መወከል የሚያስችል ሪፐብሊክ ማቋቋም ስለማይቻል ነው፡፡ ትናንት በኢሕአዴግ ጊዜ የማይቻለውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድና ሪፐብሊክ የማቋቋም ትልቅ ግዳጅ ዛሬ ማከናወን የማንችለው ኢሕአዴግ ክፉና መጥፎ ስለነበር ብቻ ሳይሆን፣ ምርጫ የማካሄድ ሥራ ከደግነትና ከጥሩነት በላይ መንግሥታዊ አውታራትን ገለልተኛ አድርጎ ማደላደልንና ማዋቀርን ስለሚጠይቅ ጭምር ነው፡፡

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ምርጫው 2013 ላይ እንዲደረግ የተወሰነው፣ የተባለውና የሚፈለገው ቅድሚያ መሰናዶ ተሟልቶና ተጠናቅቆ ሳይሆን ምርጫውም ራሱ ይህንን ዴሞክራሲን የማደላደል፣ መንግሥታዊ አውታራትን ገለልተኛነትን የማነፅ የለውጡንና የሽግግሩን ተግባር የሚያግዝ ሚና ይጫወት ተብሎ ነው፡፡

ይህ ግን ብቻውን የሚስተናገድ የአገር የቤት ሥራ አልሆነም፡፡ ለውጡን የሚፃረሩ፣ ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ሽግግር የሚጠናወቱ ኃይሎች በፈጠሩት ሁኔታና አጋጣሚ ውስጥ ሌሎችም አደጋዎችና ትንኮሳዎች ተግተልትለው መጡ፡፡ ኢትዮጵያ በውኃ ሀብቷ በተለይም በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብቷን በጭራሽ አይቻልም የሚለው የግብፅና የሱዳን የቆየ ፖሊሲ በግርግር መሬት ከመቦጨቅ የሱዳን ፍላጎት ጋር ተወሳስቦ መጣ፡፡ የኢትዮጵያ በገዛ ራሷ የውኃ ሀብት መጠቀም፣ የኢትዮጵያ ልማት በጠቅላላው፣ ለህልውና አደጋ ነው የሚሉ የጎረቤቶቻችን ፍላጎት ኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ ጦርነት ከመክፈት ጀምሮ በእጅ አዙር በታጠቁ የውስጥ ትግል ሽፋን እስከማመስ ተግባራዊ መሆን አልበቃ ብሎት፣ ትናንት በገፍ የተሰደዱ ‹‹ምድረ ጎስቋሎች›› መጠጊያ የሆነው የውጭ አገር ዛሬ የነፃ አውጪ ሠራዊት ጠቅላይ መምርያ ሆኖ እስኪዘገብ ድረስ ‹‹መጫወቻ›› ሆነን አርፈናል፡፡ ምዕራባዊ ጫናም በዚህ ሁሉ ውስብስቦሽ ውስጥ ዓይን አውጥቶ ከእነ ሙሉ ሠራዊት (ሚዲያው፣ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና ግሎባል ገቨርናንስ ተቋማት ጋር – ተመድ፣ ሴኪዩሪቲ ካውንስል፣ ጂ7፣ ወዘተ) ኢትዮጵያ ውስጥ ስውር እጅ ከመስደድ ጀምሮ በማዕቀብ የማፈን ተጨማሪ የጎረቤት ባላጋራ በመግዛትና በሚዲያ የተቀናበረ ሴራ ስም በማጠልሸት ቅንብር ውስጥ ገብቶ ይፋዊ ‹‹ጦርነት›› ውስጥ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሪፈረንደም የሰጠው፣ ውሳኔ ሕዝቡን በአንድ ድምፅ  የገለጸው የተመዘገበውን ያህል በዚህ ቀውጢ ጊዜ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ተምሞ በመሄድ ነው፡፡

የአገራችን መራጭ ሕዝብ ይህን ያደረገው በዴሞክራሲ ውስጥ እየኖረ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መኗኗሪያው አድርጎ አይደለም፡፡ እነዚህ መብቶች ሥልጣን ላይ ካለው መንግሥትና ባለሥልጣናት ችሮታ ውጪ መኗኗሪያ የሚሆኑት፣ ቢጣሱ፣ ቢገሰሱ በሕግ የሚጠበቁትና የሕግ መቃኛ የሚበጅላቸው፣ ወዘተ ኢትዮጵያ የጎደላት ከፓርቲ ወገንተኛነት ነፃ ሆኖ የታነፀ ዓምደ መንግሥት ሲኖር ነው፡፡ ይህን የማበጃጀት ሥራ ተጀማምሯል፡፡ ጥቃትም የደረሰበት፣ የውስጥ ወረራ መባል የሚችል፣ አገር የማወራረድ ያህል አደጋ የመጣውም በጭራሽ ይህ አይሆንም፣ ለውጥና ሽግግሩ መቀጠል የለበትም ተብሎ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ በምርጫ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ማቋቋም የማይቻል ነገር የሆነበት ምክንያት ዴሞክራሲዊ መብቶች ገና መኗኗሪያ ስላልሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ በዚሁ ጎዶሏችን ጭምር የኢትዮጵያ ሕዝብ የፓርቲ አማራጮችን፣ አማራጭ የፖለቲካ መስመሮችን ያንተረከከ ቀርቶ እነዚህ በነፃነት ብቅ እንዲሉ፣ አብረውም ተቻችለውና ተፎካክረው እንዲሠሩ ያደረገ ሕይወት ውስጥ አልገባንም፡፡ ምርጫ 2013 እየተጣደፈና ‹‹ሳይታወቅ››ም እየገሰገሰ የመጣው ገና በዚህ ረገድ ተገቢውን መሰናዶ ሳናደርግና ከሁሉም በላይ ደግሞ በለውጡና በሽግግሩ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰላማችን፣ በአገራችን ህልውና ላይ እየተግተለተለ እየጠነከረ የመጣው ከበባና ጥቃት በፀናበት ወቅት ነው፡፡

የአገራችን ሕዝብ በምርጫው ዕለት ድምፅ የሰጠው ከእያንዳንዱ ፓርቲ ወይም ድርጅት ማሸነፍና የፖለቲካ ትርፍ በላይ የሚበልጥብኝ ሌላ ነገር አለ ብሎ ነው፡፡ አገርን የማትረፍና የለውጡን ዘላቂነት የማረጋገጥ ተግባር በልጦ ያፈጠጠበት ወቅት ነው ብሎ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መራጭ ሕዝብ በዚህ አንድ አዳራሽ ውስጥ ከቶ አንድ ላይ ተገናኝቶ ባልመከረበት ድርጊቱ ምርጫው፣ የድምፅ መስጫው ዕለት ድርጊትና ውሎ የፀብ ደጋሾች መጫወቻ እንዳይሆን፣ ወደ የባላንጣዎች ግብግብ እንዳይለወጥ፣ ሰላማዊነቱ፣ ተዓማኒነቱና ዴሞክራሲያዊነቱም በራሱ በሕዝቡና በተወዳዳሪ ፓርቲዎች ፊት መዘባበቻ እንዳይሆን አድርጓል፡፡ የአውሮፓና የአሜሪካ ታዛቢ በሌለበት የአውሮፓና የአሜሪካን ‹‹አጋር›› አገሮች ዕውቅናና ክብር አግኝቷል (የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትና የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ የ13 አውሮፓ አገሮች ኤምባሲዎች ያወጡትን መግለጫ ይመለከታል)፡፡

የልማት አጋሮቻችንና ለጋሾቻችን በግልጽ የሚናገሩትን፣ ፖሊሲያቸውና አቋማቸው ያደረጉትን፣ ውስጣቸውም ጭምር የሚተናነቃቸውን አካትተው በገለጹበት በዚህ የጁን 25 መግለጫቸው ሁለቱም ወገኖች የኢትዮጵያን ሕዝብ ድምፅ በመስጠት መብቱ መገልገሉን ከማድነቅ ሊሸሹና ሊያፍሩ (እፍርታም ሊሆኑ) አልቻሉም፡፡

ምርጫውን በተለይም የድምፅ መስጫውን ዕለት በዚህ ሁኔታ አጠናቅቀን፣ ተቃዋሚዎቻችን፣ ተቀናቃኞቻችን በአጠቃላይ ጠላት ያለው ቀርቶ የኢትዮጵያ መራጭ ሕዝብ ሰኔ 14 ቀን ያለው ከሆነ በኋላና እየሆነ ባለበት ጊዜ፣ በተለይም በሕግ የተወሰኑትን ከምርጫው ቀን ቀጥሎ ያሉትን የምርጫ ውጤት የሚገለጽባቸውን አሥር ቀናት በመቁጠርና በመኖር ላይ እያለን ገና በሰባተኛው ቀን (ልክ በሳምንቱ ሰኞ) ነበር የኢትዮጵያን የመከላከያ ሠራዊት ከትግራይ/ከመቀሌ መውጣት በድንገትና በከፍተኛ ድንጋጤ የሰማነው፡፡ ይህ ልክ እንደ ብራ መብረቅ ድንገት የወደቀወን ዜና የሰማነው ‹‹ሰበር›› የሚባል ቅጽል እንኳን ሳይሰጠው ነው፡፡ በዚህ ላይ በኋላ ቀስ እያልን በተረጋጋ ስሜት የተረዳነው መግለጫ ‹‹… ይህ የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ ያለ ቅድመ ሁኔታ በሰብዓዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም ከዛሬ ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት አውጇል›› የሚል ቢሆንም፣ የመንግሥት ቴሌቪዥን የዚህ ዜና ርዕስና መሪ መግቢያ፣ ‹‹የትግራይ ጊዜዊ አስተዳደር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ አቀረበ፡፡ የፌዴራል መንግሥትም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተኩስ አቁም ስምምነት ጥያቄን በአዎንታዊነት እንደተቀበለው አስታወቀ›› እያለ አሳሳነን፣ አደናገረን፡፡ ዛሬም ድረስ ከሳምንት በኋላ የአንድ ወገን የተናጠል ዕርምጃና ከአንድ በላይ የሆኑ ወገኖች ስምምነት ልዩነት አልገባ ብሎን ማኖ በማኖ የሆንን ብዙዎች ነን፡፡

በዚህ ላይ አማፂውና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የሰየመው ቡድን ፕሮፓጋንዳ የብራ መብረቅ ሆኖ የወደቀብንና ገላችንንም ህሊናችንንም ክፉኛ ባደማው ቁስላችን ላይ ጨው ነሰነሰብን፡፡ ማክሰኞ መጥቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የ‹‹አሳቻ›› ቦታ መግለጫ መደበኛ ባልሆኑ የዜና ምንጮች በኩል ሰማን፡፡ በመደበኛው ኑሮ ውስጥና ሁሌም የሚከነክነን፣ የሚያቃጥለንና የሚያንገበግበን ሕገ መንግሥታዊው የመንግሥት የአሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ነገር የምንነጋገርበት ጉዳይ በቀረበበት መልክና ማዕቀፍ ውስጥ ቢቆረቁረንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰጡት የተባለውን መግለጫ ምንጭ ተዓማኒነት ካረጋገጥን በኋላ አሞን አድሮ፣ አሞን ከዋለው ሕመማችን ዳንን፡፡ ጥርጣሬያችንን እየሞገትን ሰንብተን በሳምንቱ የሰኞ የፓርላማው ውሎ ላይ ብዙውን የተብራራ እውነት ሰማን፡፡

የአገራችን ሰው የሆነ፣ የሚያገባው ነገር ተደበቀብኝ ብሎ ሲያምን ወይም ሲጠረጥርና ‹‹ተከዳሁ›› ባለ ጊዜ ‹‹በዚህ በዚህ አይደል ሰው የሚተማማ፣ ሞተችልህ አሉኝ ሕመሟን ሳልሰማ›› ብሎ ያንጎራጉራል፡፡ ገና እንደዚህ ዓይነት መጠያየቅ፣ መወቃቀስ ውስጥ መግባት አልቻልንም፡፡ እኔ እምለው ገና እንደዚህ ዓይነት መወቃቀስ ውስጥ አልገባንም አይደለም፡፡ መግባት አልቻልንም ነው፡፡ አሁንም በላይ በላዩ እየተከታተለ የሚሰነዘርብን ጥቃት መጠያየቃችንን ‹‹መተማማታችንን›› አጣዳፊ የማያደርግ እየሆኑብን ነው፡፡

እንደ ጂ ሰባት ሁሉ፣ እንደ አሥራ ሦስቱ ኤምባሲዎች ‹‹አድማ›› ሁሉ ዓረብ ሊግ ውስጥ ጭምር የገባው፣ በ‹‹ኢትዮጵያን አትንኩ›› ምትክ በ‹‹ኢትዮጵያን እንደምን እናጥቃት›› የተለወጠው መመርያ በተግባር ሲተረጎም ቀን ተቀን እያየን ነው፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ወገኖቻችን ሕጋውያንና የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ጭምር፣ ‹‹የዓይናችሁ ቀለም አላማረንም›› ተብለው በገፍ እየተባረሩና መቀጣጫ እየሆኑ ነው፡፡

በዚህ ብቻ ሳይወሰን በእውነትና በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ያልተመሠረተውን የሳዑዲ አድሏዊና ወገንተኛ የ‹‹የአብዬን ለእምዬ›› ፍርደ ገምድል አቋም በአደባባይ ሰምተናል፡፡

ሌሎችም በሳምንቱ መጨረሻ ውስጥ ማስፈራሪያ ሲልኩብን፣ ማስጠንቀቂያ ሲያከታትሉብን፣ የ‹‹ጭቃ ሹማቸው›› ያህል እነሱ የዓለሙ ጌታ ሆነው ከላይ ከፍ ዝቅ አድርገው ሲያዩንና ሲይዙን ታዝበናል፡፡ ኢትዮጵያን ከተቃጣባትና ካነጣጠረባት የህልውና አደጋ ልናድናት የምንችለው ሰላሟን፣ የዴሞክራሲ ግንባታዋን የምንከላከለው፣ ለውጡንና ሽግግሯን ይበልጥ ዕውንና ድርስ እየሆነ ከመጣ ክሽፈት የምናድነው በምርጫው ውስጥ እንዳደረግነው፣ በተለይም በድምፅ መስጫው ቀን እንዳረጋገጥነው አንድ ላይ ሆነን ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› ብለን የምርጫውን ውጤት በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ስናስተናግድ ነው፡፡ በውጤቱ ላይ ልዩነት ሊኖረን ይችላል፡፡ ልዩነት የሚስተናግደው ግን ዴሞክራሲያዊነት ጭምር የሚረጋገጠው በዴሞክራሲ መብቶችና መቻቻል ውስጥ መኗኗርን መሠረት በማስያዝ ላይ በመረባረብና ችግሮች ሲመጡም በሰላማዊ፣ በሕጋዊና በዴሞክራሲያዊ መንገዶች ለመፍታትና ውጤቱንም ለመቀበል በመቻል ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...