ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የአምስተኛው ምክር ቤት ስድስተኛ ዓመት የምክር ቤት ዘመናቸውን ያጠናቀቁት የፓርላማ አባላት፣ አዲስ መጪዎቹ የሕዝብ ተወካዮች የአገርንና የሕዝብን ጥቅም እንዲያስቀድሙ አሳሰቡ፡፡
በቀድሞው ኢሕአዴግ በአሁኑ ብልፅግና ፓርቲ በበላይነት የተያዘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተወካዮች፣ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በአዲስ ዕጩ ተመራጮች ተተክተዋል፡፡
ለዚህም ከመጪዎች ሁለት ወራት የክረምት እረፍት በኋላ ሥልጣናቸው የሚጠናቀቀው የምክር ቤት አባላት በመስከረም 2014 ዓ.ም. መጨረሻ ሳምንት ሥራ የሚጀምረው አዲሱ ፓርላማ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ አገር ጠንካራ ሰዎችን የምትፈልግበት ጊዜ በመሆኑ፣ ለአገርና ለሕዝብ ቅድሚያ በመስጠት በምክር ቤቱ ውይይቶችና ክርክሮች ሊካሄዱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በምክር ቤቱ የመጨረሻ ስብሰባ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ አባላት፣ ፓርላማው በውጭ አንዳንዶች እንደሚሉት የተኛ ወይም እንቅልፋም ያልነበረ፣ ነገር ግን በከባድ ፈተና ውስጥ ሆኖ አገርን ያስቀጠለ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በምክር ቤቱ ላለፉት 16 ዓመታት አባል የነበሩት አቶ ዘለቀ መሐሪ እንደሚሉት፣ ለበርካታ ጊዜያት የምክር ቤቱ ሚና ግልጽ ሆኖ በአደባባይ ባይወጣም፣ በተዘጉ አዳራሾች ውስጥ ጠንከር ያሉ የሐሳብ ግጭቶችና ፍጭቶች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ በዚያው ልክ አንዳንድ ውይይቶችና ክርክሮች ወደ ድርጅት አጀንዳነት ተቀይረው ለሕዝብ ይፋ አይደረጉም ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ፓርላማው ይህችን አገር ከውድቀት የታደገ መሆኑን በመጥቀስ፣ በአዲስ የሚተካው ፓርላማ አባላት ከብሔርተኝነት አስተሳሰብ በመውጣት በአዳራሽ ውስጥ የሚከራከሩባቸውና የሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች የአገሪቱን ሰላምና አብሮነት፣ እንዲሁም አንድነትን ለሚያስቀጥሉ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡
‹‹ቀጣዩ ምክር ቤት የልዩነት ሐሳቦች የሚራመዱበት ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች በመኖራቸው፣ መጪው ምክር ቤት እነዚህን ችግሮች ሊፈታ ይገባዋል፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ፓርላማው ከዚህ ቀደም በነበሩት ጊዜያት ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ አስፈላጊ እንደነበር፣ በዋነኛነት ከሕገ መንግሥት ውጪ የሚመጣ መንግሥትና ሥልጣን አካሄድ አደገኛ በመሆኑ አነሰም በዛም በሕጉ መሠረት የመንግሥት ሽግግር ሲደረግ ልማዱም፣ ሒደቱም ከእነ ድክመቱ አስተማሪ ስለሚሆን፣ በዚያ ሁኔታ እንዲሄድ ከማሰብ የመነጨ መሆኑን አቶ ዘለቀ ገልጸዋል፡፡
ሻምበል ጀምበር አስማማው የተባሉ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው፣ ሕዝብ መርጦና ወክሎ ሲልክ ቀላል አለመሆኑን በማስታወስ፣ በ16 ዓመታት የምክር ቤት ቆይታ የነበሩ ውይይቶችና ክርክሮች ቃለ ጉባዔ ወጥተው ቢታዩ ፓርላማው በውጭ እንደሚታየው እንቅልፋም አለመሆኑን መረዳት ይቻላል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ተተኪው ፓርላማ አገርና ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ የሐሳብ ልዩነቶች የሚንፀባርቁበትና የሚዘወሩበት እንዲሆን አሳስበዋል፡፡
አዲሶቹ የፓርላማው አባላት ፓርቲያቸው ሲመረጥ ቃል የገባውን ጉዳይ ስለመፈጸሙ መከታተል፣ ባልተፈጸመው ላይ ይቅርታ መጠየቅና አስፈጻሚውን ወጥረው የሚይዙና የሚከራከሩ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ላለፉት ስድስት ዓመታት የፓርላማው አባል የነበሩት አቶ መሐመድ ሐሰን ደግሞ፣ የፓርላማ አባላት ምንጊዜም ቢሆን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መያዝ እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡
የተሰናባቹ የምክር ቤት አባላት በውጭ የሚሰጠው ስምና ፓርላማው የሚሣልበት መንገድ ጥሩ እንዳልነበር፣ ነገር ግን የፓርላማው አባላት እንደ አስፈጻሚ ወይም እንደ ብሔርተኛ ጫፍና ጫፍ ይዞ የሚከራከር ከሆነ፣ መጀመሪያ ፓርላማው ከዚያም መንግሥት ሊፈርስ የሚችልበት አደጋ መኖሩ መዘንጋት እንደሌለበት አቶ መሐመድ ጠቁመዋል፡፡
ለአብነት የትግራይ ክልል የምክር ቤት አባላት በያዙት ጽንፍ የወጣ አቋም ምክንያት፣ አሁን በክልሉና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለውን ሁኔታ አውስተዋል፡፡
በመሆኑም በተለያዩ አገሮች የሚሰማውን ወይም የሚጫነውን፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ ማንኛውም ግለሰብ የሚያነሳውን ሐሳብ ሁሉ ምክር ቤት አምጥቶ የሚያራግፍ ከሆነ እንደ ምክር ቤትም ሆነ እንደ አገር መቀጠል እንደማይቻል አቶ መሐመድ ተናግረዋል፡፡
‹‹እኛ በቆይታችን ችግር ውስጥ ሆነን ሚሊዮኖች እየተፈናቀሉና ብዙዎች እየሞቱ ችለን የኖርነው፣ አገርን የግድ ማስቀጠል ስለነበረብንና ለአገር ቅድሚያ በመስጠት ነው፤›› ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ክርክር በሚደረግበት ወቅት በሚዲያ እንዳይገለጽ በማድረግና ጫፍ የረገጡ ሐሳቦች አዳራሽ ውስጥ ላይ አልቀው ለሕዝብ ይቀርቡ እንደነበር የገለጹት፣ ወ/ሮ ሥራ አቢ የተባሉ የተሰናባች ምክር ቤት አባል ናቸው፡፡
‹‹በአገሪቱ መፈናቀልና ሞት ሲከሰቱ ብዙ ስሜት ውስጥ የሚያስገቡና አንዳንዴም የሚያስለቅሱ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ያን የውስጥ ስሜት ይዞ ሌላ ውሳኔ ውስጥ መግባት አገርን ማስቀጠል ከባድ በመሆኑ፣ መጪዎቹ አዲስ ተወካዮችም በዚያው ልክ አገርን ሊያስቀድሙ ይገባል፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡