ጉዳያችን ነውና ዛሬም መነጋገሪያችን የዋጋ ንረቱን ይመለከታል፡፡ የኑሮን ክብደት እኛ በደንብ ብናውቀውም የኑሯችሁ ሸክምና ክብደት ይህንን ይመስላል በሚል በአኃዝ የተደገፈ መረጃ ሲቀርብ ድንጋጤያችን ይጨምራል፡፡
የሰሞኑን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሰኔ ወር የዋጋ ንረት አኃዛዊ መረጃን ለተመለከተ፣ ‹‹ጎበዝ ጉዟችን ወዴት ነው?›› የሚል ጥያቄ ደግሞ ደጋግሞ እንዲያነሳ ያደርገዋል፡፡ ይህ መረጃ የሰኔ ወር የዋጋ ንረት መጠን 24.5 በመቶ፣ በተለይ ምግብ ነክ ምርቶች የዋጋ ንረቱ ዕድገት ወደ 28.7 በመቶ ስለመድረሱ ያሳያል፡፡
ለዋጋ ንረቱ በዚህን ያህል ማደግ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ እንደ ገብስና በቆሎ ያሉ ምርቶች ዋጋቸው በዕጥፍ ጨምሮ መገኘት ነው፡፡ ዳቦ፣ ስንዴ፣ ዘይትና የመሳሰሉ ምርቶችም ከሌላው ጊዜ በተለየ ዋጋቸው መቆለሉ የሰኔ ወር የዋጋ ንረት በአገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ ቁጥር ይዞ ብቅ እንዲል አድርጓል፡፡ ስለዚህ የዘንድሮ ኑሮ በአኃዝ ጭምር ሲገለጽ ያስደነግጠን ጀምሯል የምንለው ለዚህ ነው፡፡ በኤጀንሲው ታሪክም የምግብ ነክ ምርቶች 28.7 በመቶ የዋጋ ንረት የተፈጠረበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም፡፡
በየዕለቱ የሚያስፈልጉን ምግብ ነክ ምርቶች በሙሉ ዋጋቸው እንዲህ ተሰቅሎ ያየንበት ጊዜ ያለመኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ በዓመቱ መጀመርያ ላይ የነበረውን አሁን ካለው ጋር በንፅፅር ስናስቀምጠው የዋጋ ንረቱ ፍጥነት አስደንጋጭ የሚባል መሆኑን ነው፡፡
ይህ የሰኔ ወር የዋጋ ንረትን የሚገልጸው የኤጀንሲው መረጃ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በፓርላማ በዋጋ ንረቱ ዙሪያ ያለውን ችግርና የታሰበውን መፍትሔ በነገሩን ማግሥት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ነገሩን ስንፈትሸው ይህ ጉዳይ የአገር ፈተና ሆኖ ሊቀጥል ይችል ይሆን? ብለን እንድንሠጋ ያደርገናል፡፡
በእርግጥም አሁን ያለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት የአገርም የሕዝብም ፈተና ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ ከወቅታዊው አገራዊና ውጫዊ ቀውሶቻችን ጋር ተደማምሮ ሌላ ራስ ምታት የሆነ አሳሳቢ ጉዳያችን ሆኖ ቀርቧል፡፡
አሁን ለደረሰው ከፍተኛ የዋጋ ንረት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ እርግጥ ቢሆንም፣ ለዚህም መንግሥት እተገብረዋለሁ ብሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገለጹ የመፍትሔ ሐሳቦች በቲዎሪ ደረጃ በእርግጥም ለመፍትሔው መባል ያለባቸው ሐሳቦች ናቸው፡፡
ችግሩ ግን ይህንን የመፍትሔ ሐሳብ ወደ መሬት ለማውረድ ያለን አቅምና ተነሳሽነት ምን ያህል ነው? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ እንደተመለከትነው አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የዋጋ ንረቱ በእጅጉ እየጨመረ ያለበትን ፍጥነት ለመያዝ መፍትሔውም የዚያኑ ያህል መሆን ካልቻለ ሊከተል የሚችለው ቀውስ ቀላል አይሆንም፡፡
ዓመቱ መጀመርያ ላይ የዋጋ ንረቱ 20 በመቶ እንዳይደርስ ይሠራል ተብሎ፣ ዓመቱ ሳይጠናቀቅ ጭራሽ ወደ 30 በመቶ የተጠጋው የምግብ ነክ ምርቶች ችግሩ ፈጣን መፍትሔ እንደሚያሻው ያመላክታል፡፡ በዚህ ፍጥነት ማደጉ ብቻ ሳይሆን ነገሩ በዚሁ ከቀጠለ ሸማቾች የመሸመት አቅማቸው ሳይታሰብ የሆነ ቦታ ላይ ሊቆም ወይም በእጅጉ ተገዳድሮ አቅምን የሚበላ ሊሆን ይችላል፡፡
በመሆኑም ከሁኔታው አሳሳቢነት አንፃር በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዘረዘሩ ዕርምጃዎችን ወደ መሬት አውርዶ ለውጥ ማምጣት ከባድ ቢሆንም፣ የግድ መተግበር አለበት፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት ለብቻው የሚሠራው ባለመሆኑ የሁሉንም ርብርብ ይሻል ብለን እንሞግታለን፡፡
መብላትና ማጠጣት ያልቻለ ኅብረተሰቡ ቆይቶም ቢሆን የሚያቀርበው ጥያቄ ቀላል ስለማይሆን በምሥጋና የሚሰናበተው የፓርላማ አባላትም፣ የመጨረሻውን የፓርላማ ቆይታው በዋጋ ንረቱ ዙሪያ ጠንከር ያለ ጥያቄ የማቅረባቸው ነገርም ከፖለቲካ ሕመሙ ባሻገር የመብላትና የመጠጣት ጉዳይም የአገሪቱ አንገብጋቢ አጀንዳ መሆኑን ያሳያል፡፡
የአዲሱ መንግሥትና የአዲሱ ፓርላማ አባላት የመጀመርያው ሥራቸው ከዚሁ የዋጋ ንረት ጋር የተያያዘ ጉዳይ መሆን ይኖርበታል፡፡ በዘንድሮ ምርጫ እስከ ሌሊት ድረስ ጠብቆ የመረጣቸው ዕጩዎችም የሕዝቡን የኑሮ ሸክም የሚያቃልል መፍትሔ መፈለጉ ላይ ማተኮር አለባቸው፡፡
እንዲህ ያሉ የዋጋ ንረቶችን ለመቆጣጠርም ለየት ያለ እንቅስቃሴ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በተለይ የንግድ ኅብረተሰቡ ሚና በቀዳሚነት ሊቀመጥ ይገባል፡፡ አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ መተሳሰብና መደጋገፍን የምናጎለብትበት ጊዜ በመሆኑ እንደ ከዚህ ቀደሙ በተጋነነ ትርፍ ገበያው ውስጥ እንደፈለጉ ከመሆን ቆጠብ ማለትን ይጠይቃል፡፡ አጋጣሚ ተገኘ ተብሎ የሚበሉና የሚጠጡ ምርቶችን ሸሽጎ ከልክ በላይ ለማትረፍ መሞከር አደጋው የከፋ ብቻ ሳይሆን፣ አገርን መግደል መሆኑን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡
የትርፍን መጠን ብቻ ሳይሆን ዋጋን ለማውረድ የሚረዱ ሐሳቦችን ለመንግሥት በማቅረብ መንግሥት ያልታየውን መንገድ ማሳየትና ይህቺን ጊዜ ለመሻገር የሚቻልበት ሁኔታ በመፍጠር፣ ባለውለታ መሆንም ይቻላልና የንግዱ ኅብረተሰብ ‹‹እኔም ተወዶብኝ ነው›› ብሎ ዋጋ ከመቆለል ወገን ላግዝና የዋጋ ግሽበት እንዳይባባስ ማድረግ እችላለሁ ብሎ መነሳት ትልቅ ጀግንነት ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ከሌሎች አጀንዳዎቻቸው በላይ ሸምቶ ለማደር እየከበደው የመጣውን ኅብረተሰብ ለማገዝ የሚረዱ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ በማተኮር ከአባሎቻቸውም ጋር በመምከር የተወሰነ አስተዋጽኦ ለማበርት ዕድሉ አላቸው፡፡
ሁሉም እንዲሁ ቢያደርግ ንረቱ ቢያንስ ከዚህ በላይ እንዳይሄድ በማድረግ ዘላቂ መፍትሔው እስኪያገኝ ሊያግዝ ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ግን እንደ መፍትሔ የተቀመጡ ዕርምጃዎች በንፁህ ልብና በንፁህ እጅ በአግባቡ እንዲተገበር መፍጠን የግድ ነው፡፡