የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው የ2013 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 735 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉንና ከታክስ በፊት 20.3 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 735 ቢሊዮን ብር ማድረስ የቻለው፣ በበጀት ዓመቱ ብቻ ተጨማሪ 140 ቢሊዮን ብር አዲስ የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ በመቻሉ ነው፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንዳመለከቱትም፣ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ማሰባሰብ የቻለው ተቀማጭ ገንዘብ በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ረገድ ካስመዘገበው አዲስ ታሪክ ባሻገር፣ በባንኩ ከፍተኛ ትርፍ ያስመዘገበበት ነው፡፡
በባንኩ መረጃ መሠረት በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው የ20.3 ቢሊዮን ብር ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ ከ5.5 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባንኩ በቀዳሚው ዓመት ከታክስ በፊት አስመዝግቦት የነበረው የትርፍ መጠን 14.9 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከባንኩ የተከታታይ ዓመት መረጃ መገንዘብ እንደተቻለው፣ በ2010 ሒሳብ ዓመት የትርፍ ምጣኔው ቀንሶ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የትርፍ ምጣኔውን እያሳደገ መጥቷል፡፡ ባንኩ የትርፍ ምጣኔው በቀነሰበት በ2010 አትርፎ የነበረው 10.4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2009 ሒሳብ ዓመት ግን ትርፉ 14.7 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህም የ4.3 ቢሊዮን ብር ቅናሽ ማሳየቱን ያመላክት ነበር፡፡ የባንኩን ዓመታዊ ትርፍ ምጣኔ የሚያሳዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በ2006 ሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ 9.7 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በ2007 ዓ.ም. ደግሞ ወደ 12.3 ቢሊዮን ብር ደርሶ ነበር፡፡
ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት ይህንን ትርፍ በማሳደግ 20.3 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ከቻለባቸው ምክንያቶች ውስጥ ከወለድ የሚያገኘውን ገቢ ማሳደጉ ይጠቀሳል፡፡ ተቀማጭ ገንዘብና ከትርፍ ዕድገቱ ባሻገር ለተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች የሰጠውን ብድር በተመለከተም ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት ብቻ በብድርና በቦንድ ሽያጭ 107 ቢሊዮን ብር ማቅረቡን አስታውቋል፡፡ ከብድር አመላለስ ጋር በተያያዘም በበጀት ዓመቱ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን አቶ አቤ ገልጸዋል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠንም 999 ቢሊዮን ብር መድረሱንም አመልክተዋል፡፡
ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንፃር ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ 2.56 ቢሊዮን ዶላር ከተለያዩ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች አግኝቷል፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ግን ባንኩ ከዚህ ቀደም ያስገኝ ከነበረው አንፃር ሲታይ አሁንም ዝቅተኛ ስለመሆኑ የሚያሳይ ነው፡፡ ከባንኩ ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርቶች መረዳት እንደሚቻለው፣ ባንኩ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ለአብነት የሚጠቀሰው በ2007 የሒሳብ ዓመት ከተለያዩ ምንጮች አግኝቶት የነበረው የውጭ ምንዛሪ 5.6 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ባሉት ተከታታይ ዓመታት ግን ይህ መጠን እየቀነሰ ሄዷል፡፡ ቀደም ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም፣ ባንኩ በ2003 ዓ.ም. ከሁሉም የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ዘርፎች 4.1 ቢሊዮን ዶላር ያገኘ ሲሆን፣ በ2008 የሒሳብ ዓመትም የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ወደ 4.7 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ በ2009 የሒሳብ ዓመት የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንደ ቀደመው ዓመታት ዕድገት የታየበት ሳይሆን ቀርቶ ወደ 4.5 ቢሊዮን ዶላር፣ በኋላም በ2013 የሒሳብ ዓመት ወደ 2.56 ቢሊዮን ዶላር ወርዷል፡፡
ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ በዚህን ያህል ደረጃ እየቀነሰ ለመምጣቱ የተለያዩ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በተለይ ሌሎች ተፎካካሪ ባንኮች ደንበኞችን ለመሳብ የሚጠቀሙበት መንገድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞችን ለመውሰድ ስላስቻላቸው እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይጠቁማሉ፡፡
ከውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ዝቅተኛ ሆኖ ከመገኘቱ ውጪ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ጥሩ አፈጻጸም ነበረው፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት እንደገለጹትም፣ ተደራሽነቱን በማስፋት ጥራት ያለውና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለደንበኞቹ ለማድረስ የሚያደረገው ጥረትም በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ስኬት አስመዝግቧል፡፡ የባንኩ ቅርንጫፎች ቁጥርም ከ1,700 በላይ መድረሱን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የባንኩ የአስቀማጭ ደንበኞች ብዛት 31.4 ሚሊዮን እንደደረሰ አስታውቀዋል፡፡
ባንኩ በአስቀማጮች ቁጥር ብዛት በኢትዮጵያ ካሉ ባንኮች አንፃር ሲታይ ወደ ግማሽ የሚሆነውን የያዘ ነው፡፡ በ2013 የሒሳብ ዓመት 18ቱ ባንኮች ያስመዘገቡ የአስቀማጮች ቁጥር (አንዳንድ ደንበኞች ሁለት ሦስት ደብተሮች እንዳሏቸው ታሳቢ ተደርጎ) ከ66 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ ከዚህ አንፃር ወደ 31.4 ሚሊዮን የሚሆኑት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስቀማጮች ናቸው፡፡
በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ ስኬት አግኝቼበታለሁ ብሎ ያመላከተው፣ የኤቲኤም ካርድ ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት 6.7 ሚሊዮን በላይ ማድረስ መቻሉን ነው፡፡ በመላ አገሪቱም ከ3,091 በላይ የኤቲኤም ማሽኖችና ከ4,350 በላይ የፖስ ተርሚናሎችን ለተገልጋዮቹ ምቹ በሆኑ ቦታዎች ማስቀመጥ ተችሏል፡፡
አቶ አቤ አክለው ደንበኞች ወደ ቅርንጫፍ ሳይሄዱ ባሉበት ሆነው የባንክ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚሠሩ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የአገሪቱን የክፍያ ሥርዓት በማዘመን ዓለም ወደ ደረሰበት ጥሬ ገንዘብ አልባ የክፍያ ሥርዓት ለመግባት በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስተዋጽኦ እያደረገ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት የባንኩ የዲጂታል ባንኪንግ ዓመታዊ ዕድገት ከፍተኛ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ በባንኩ የዲጂታል ባንኪንግ አማካይነት ከ529 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማዘዋወር መቻሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተደረሰበት ያለውን ደረጃ ያመላክታል ተብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአንድ ወር የሚቆይ ‹‹ሃጂ ለሁሉም›› የተሰኘ የቁጠባ ንቅናቄ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. አስጀምሯል፡፡ ይህንን ንቅናቄ በባንኩ በመገኘት ያስጀመሩት የባንኩ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር እንድሪስ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በቁጠባ ንቅንቄ ወር የ‹‹ለበይክ›› ከወለድ ነፃ የቁጠባ አገልግሎትን በኅብረተሰቡ ዘንድ በሰፊው በማስተዋወቅ በሕይወት ዘመን አንድ ጊዜ ሃጅ የማድረግ ዕቅዶቻቸውን ለማሳካት የሚያስችላቸውን ቁጠባ እንዲጀምሩ ለማበረታታት ያለመ ንቅናቄ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ሃጅ›› ከእስልምና የእምነት መሠረቶች አንዱ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አቤ፣ አንድ ጤናማና የገንዘብ አቅም ያለው ሙስሊም በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ ለአንድ ጊዜ መካ በመሄድ የሃጅ ሥነ ሥርዓትን መፈጸም ግዴታን ለመወጣት ብዙዎች ጥረት የሚያደርጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሆኖም በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ይህን የሕይወት ዘመን ምኞታቸውን ማሳካት አቅቷቸው እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ አሁን ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የእስልምና እምነት ተከታዮች በረዥም ጊዜ ቁጠባ ይህን ምኞታቸውን የሚያሳኩበት ‘‘ለበይክ’’ የተሰኘውን የቁጠባ ሒሳብ አገልግሎት ባለፉት ሁለት ዓመታት ሥራ ላይ ማዋሉን አስታውቀዋል፡፡
የእስልምና እምነት ተከታዮች የእምነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል የተዘጋጀው ከወለድ ነፃ የተቀማጭ ሒሳብ አገልግሎት በኅብረተሰቡ ዘንድ እየታወቀ ስለመምጣቱ የገለጹት አቶ አቤ፣ በ2013 የበጀት ዓመት ማጠቃላያ ላይ 11,500 ደንበኞች ለበይክ የቁጠባ ተቀማጭ ሒሳብ መከፈታቸውንና ከ75 ሚሊዮን ብር በላይም መቆጠባቸውን አክለዋል፡፡
አገልግሎቱ ለበርካታ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ በሰፊው ለማስተዋወቅ የሚያስችል ለአንድ ወር የሚቆይ ‹‹ሃጅ ለሁሉም›› የተሰኘ የቁጠባ ንቅናቄ በይፋ ሊጀመር መቻሉንም አቶ አቤ አስታውቀዋል፡፡
በ‹‹ሃጅ ለሁሉም›› ንቅናቄ ኅብረተሰቡ የቁጠባ ባህሉን እንዲያዳብርና የሲቢኢ ኑር የባንክ አገልግሎትን በሰፊው ለማስተዋወቅ የሚረዱ መርሐ ግብሮች እንደሚከናወኑም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ከተሰጠው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ የሚባል ቁጠባ ማሰባሰብ ችሏል፡፡ ባንኩ በሁሉም ቅርንጫፎች ለአገልግሎቱ ተለይተው በተዘጋጁ መስኮቶች እንዲሁም ለዚሁ አገልግሎት ብቻ በተከፈቱት 75 ቅርንጫፎች አገልግሎቱን እየሰጠ ሲሆን፣ ‹‹ሲቢኢ ኑር›› በሚል አዲስ ስያሜና መለያ አገልግሎት እየሰጠ ባለው አገልግሎት 4.2 ሚሊዮን ደንበኞች ሒሳብ መክፈት ችለዋል፡፡ ከእነዚሁ ደንበኞችም የተሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ 52 ቢሊዮን ብር መድረሱ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እያሳየ ያለውን ዕድገት ያመለክታል ተብሏል፡፡