Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለም​​​​​​​የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት መታሰር የቀሰቀሰው ተቃውሞ

​​​​​​​የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት መታሰር የቀሰቀሰው ተቃውሞ

ቀን:

የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፣ በሥልጣን ዘመናቸው ፈጽመውታል ለተባለው ሙስና ፍርድ ቤት ቀርበው ቃል እንዲሰጡ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ባለመፈጸማቸው ለ15 ወራት እንዲታሰሩ የተደረገው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡

ችሎት በመድፈር ካለፈው ረቡዕ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለ15 ወራት ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ሕገመንግሥታዊ ፍርድ ቤት የወሰነባቸው በመሆኑም፣ እዚያው በሚኖሩበት ካዋዙሉ ናታል ከተማ ከሚገኝ እስር ቤት እንዲያርፉ ተደርገዋል፡፡

  ፍርድ ቤት በተጠሩበት ቀን ለመቅረብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለእስር የተዳረጉት ሚስተር ዙማ፣ እ.ኤ.አ. ከ2009 እስከ 2018 ደቡብ አፍሪካን መርተዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካውያንን ከአፓርታይድ ግዞት ለማላቀቅ ከታገሉት የአገሪቱ ዜጎችም ከቀዳሚዎቹ የሚሠለፉ ናቸው፡፡

በሥልጣን ዘመናቸው በሙስና ወንጀል ይታሙ የነበሩት እኚህ ሰው፣ ከሥልጣናቸውና ከፓርቲያቸው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ኃላፊነት ለመውረድ ያበቃቸው ይኸው ሙስና ውስጥ ተዘፍቀዋል ተብሎ በተቀሰቀሰባቸው ተቃውሞ ነበር፡፡

ዙማ አሁን ላይ የተከናነቡት የ15 ወራት እስር ችሎት ከመድፈር ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ ዋናው ለችሎት እንዲያስረዱ የተፈለገው የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በነበሩበት በ1999 ከፈረንሣይ የመከላከያ ድርጅት ታለስ የመሣሪያ ግዥ ስምምነት ጋር በተያያዘ ተፈጽሟል በተባለ ሙስና ነው፡፡

የ79 ዓመቱ ዙማ ስለዚሁ ጉዳይ እንዲያብራሩ በተጠሩበት ችሎት ባለመገኘታቸው የተላለፈባቸውና ተፈጻሚ መደረግ የጀመረው እስር ደግሞ ተቃውሞ ይዞ መጥቷል፡፡

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ባልደረባ የደርባን የገበያ ማዕከልን ከዘራፊዎች ለመታደግ ሲጥር

የእርሳቸው ደጋፊዎች መታሰር የለባቸውም በሚል ተቃውሞ አድርገዋል፡፡ አልጀዚራ እንደዘገበው፣ በጆሃንስበርግ ለተቃውሞ በመጡ ሰዎች ሱቆች ተዘርፈዋል፣ ጎዳናዎች ተዘግተዋል፣ ንብረቶች ተቃጥለዋል፡፡

በሁለት የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ማለትም በካዋዙሉ ናታል እና ጉተንግ ከተሞች ባለፈው ሳምንት የተጀመረው ተቃውሞ አሁን ላይ ጆሃንስበርግን አዳርሷል፡፡ ተቃውሞው ግን እንዲሁ ተቃውሞ በመግለጹ ብቻ የተወሰነ ባለመሆኑ፣ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲረል ራማፎዛ፣ ተቃዋሚዎች የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከሚያደቁ፣ በሰላም ተቃውሟቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ንብረቶች መዘረፋቸውን፣ መቃጠላቸውን ድርጊቱም በአሌክሳንደሪያ እንዲሁም ጆሃንስበርግ አቅራቢያ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ መፈጸሙን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ተናግሯል፡፡ ተቃውሞ ባለባቸው አካባቢዎች ባንኮች፣ የንግድ ተቋማትና ሌሎች አገልግሎቶች ተዘግተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ራማፎዛ እንዳሉት ደግሞ፣ ሰዎች ላይ ጉዳት ከመድረሱም ባለፈ የሞቱም አሉ፡፡ እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ፣ ሦስት የፖሊስ አባላት ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ተቃውሞ አድራጊዎችም እየታሰሩ ነው፡፡  

የጭነት መኪኖች ከደርባን 150 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ሞይ ወንዝ አቅራቢያ እንዲቆሙም ተደርጓል፡፡ ሰዎችን ማስፈራራት፣ መፈረጅና መጉዳት መስተዋሉን የገለጹት ራማፎዛ፣ ተቃዋሚዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና የኮቪድ-19 መርህን እንዲያከብሩ ጠይቀዋል፡፡

እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ እስከ ማክሰኞ ሐምሌ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ዝርፊያውና ተቃውሞው አልቆመም፡፡ በዙማ መንደር ካዋ ዙሉ ናታል እና ጉተንግ አካባቢዎችም ሱቆች እንደተዘጉ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡

ከአሥር በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎም የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ተቃውሞው በፀናበት አካባቢ ወታደሮችን አሰማርቷል፡፡ የአገሪቱ መከላከያ እንዳለው በኢኮኖሚ እምብርትነቷ በምትታወቀው ጆሃንስበርግና በሌሎች ከተሞች ወታደሮች እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡ ከ750 ሰዎች በላይ ከዘረፋና ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ የታሰሩ መሆኑንም ፖሊስ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...