Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርይድረስ አዙሮ ማየት ላቃተን በሙሉ!

ይድረስ አዙሮ ማየት ላቃተን በሙሉ!

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ

በአንድ ወቅት ዓለምን ተቆጣጥረው የገዙ ሁሉ የዓለም ወዳጅ ሆነው ሳይሆን፣ ቀድመው በመንቃታቸውና የበታች ሆነው መገዛት ያለባቸውን በቁጥጥራቸው ሥር አውለው በማሠራት የበላይና የበታችነትን ፈጥረው በመጨረሻም ወደ ባርነት አሸጋገሯቸው። ማነው የጀመረው? ከሁሉ በፊት ሮማውያን እንደ ጀመሩት ይታወቃል። በዓለም ዙሪያ ባርነት በቀለም ወይም በመልክ በማበላለጥ ሳይሆን፣ አቅም ያለው የሌለውን በመደፍጠጥ ነው የተጀመረው።

ለምሳሌ ግሪኮች ነጮች ናቸው፡፡ በሮማውያንም የተገዙ ነበሩ፡፡ ግን ጥቁር ወይም ጠይም ስለሆኑ ሳይሆን፣ አቅም ያለውና ብልጣ ብልጡ በመቅደም ሊያሸንፍ የሚችለውን እያሰረ፣ እየጎተተ፣ እንዲሁም እየገደለ ጭምር ባሪያ የሚባለውን ይሸጣል፣ ይለውጣል። በዘመኑ የማረሻና የመጫኛ መሣሪያ ስላልነበረ የቻለው ያልቻለውን ስለሚሸጥና ሕጉ ለጉልበተኛው ስለሚያዳላ ነበር ባርነት የተጀመረው። ይህ የጥንቱ ሁኔታ ሲሆን፣ ነጮቹ እየተሻሻሉ ሲመጡ ወገናቸውን ከመሸጥና ከመለወጥ ነጭ ወዳልሆኑት ሱሉሱን አዞሩና ወደ እስያና አፍሪካ ተላለፉ፡፡ የጥቁር ታላቅ ነን ባዮችም በተዘጋጀው መስመር ውስጥ ገብተው፣ የራሳቸውን ወገን አሳልፈው ከመሸጥ ከመለወጥ አልፈው ራሳቸውም ባለባሪያ ሆኑ።

ይህ እንግዲህ የጥንቱን ስንመለከትና ታሪክን ስናገላብጥ የምናገኘው እውነታ ነው። ዛሬ አውሮፓና አሜሪካ ሠለጠንን በሚሉበት ዘመን በመላው ዓለም ከ40 ሚሊዮን  በላይ ሰዎች በዘመናዊ ባርነት (Modern Slavery) መከራቸውን ያያሉ። በእርግጥ እንደ ጥንቱ አይገረፉም፣ በፈለገው ጊዜ ስንብት ጠይቀው ይሄዳሉ፣ ጌታቸውን ባያሸንፉም መክሰስ ይችላሉ፡፡ ግን በዚህ ውስጥ የሚያልፉ ኑሯቸው የተለያየ ነው። ነጮቹም ቢሆኑ፣ ዘራቸውን እምብዛም አያንከራትቱም፡፡ የሲቪል ነፃነት የሚሉትን ለመተግበር ይሞክራሉ። ለምንስ ብለው ወገናቸውን ይጎዳሉ? ከደቡብ አሜሪካ፣ ከህንድ፣ ከአፍሪካና ከመሳሰሉት እየጎረፈላቸው።                                            

በአፍሪካና በእስያ የወጣት ዘመናዊ ባርነት የተለመደ ነው። እርግጥ ነው ባሪያ አይባሉም፡፡ ነገር ግን የባሪያ ሥራ ይሠራሉ፡፡ አንድ ሕፃን በገዛ አገሩና ወገኑ መሀል ተቀምጦ የመማር ዕድል ሳያገኝ፣ የዕለት ጉርስ አጥቶ ሲንከራተት፣ የአንዷን ወይዘሮ ዕቃ ተሸክሞ ለተሸከመበት ተገቢ ዋጋ ሳይከፈለው የፈለጉትን ጉርሻ ሰጥተው የሚባረርበት ዘመን በመሆኑ፣ ከእኩያ ጓዶቹ እኩል የመማር ዕድል ከሌለውና በተገኘው ሁሉ ማገልገል ከዘመናዊ ባርነት አንዱ ነው፡፡ የአፍሪካ ወጣቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ በዘመናዊ ባርነት ዛሬ ጊዜ ለሰጣቸውና ላለፈላቸው የዓረብ ሀብታሞች ለማገልገል፣ በሕግም ይሁን ከሕግ ውጪ በመጓዝ ስንቱ የዓሳ ነባሪ እራት እንደሆነ ቤት ይቁጠረው።                                                                          

በቀላሉ በአሜሪካ ስላለንና ከውጭ ስለመጣን ጥቁርና ጠያይም ሰዎች ትንሽ ላንሳና ልናገር፡፡ አንድ ጥቁር ሰው ምንም አዋቂ ሆኖ ለአንድ ዓይነት ሥራ ከአገሬው ነጭ ጋር ቢወዳደርና ሥራ ቢጀምሩ፣ ጥቁሩ ሰው ግን ማንነቱን በሥራ መስክ ለማስታወቅ ጥሮና ግሮ ብልጫ የማሳየት ኃይሉ ከሌለው መቀደሙ የማይቀር ሀቅ ነበር፡፡ የአሁኑን እንጃ፡፡ ራሳችንን ካላታለልን በስተቀር ተለውጧል ለማለት ያዳግተኛል።                                                   

ብዙ ጊዜ በአሜሪካን ፖለቲካ ውስጥ በመምረጥም በማስመረጥም የተሳፈ አንድ ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ አንድ ቀን የቢል ክሊንተን ምርጫ በሚካሄድበት እራት ግብዣ ላይ ጥሩ ሥራ ሠራ ተብሎ በጣም ተመሠገነ፡፡ አንዱ ከመሀላቸው ብድግ ብሎ፣ “አቶ እገሌ እኮ መልኩ ነው እንጂ ልክ እንደ እኛ ነው ሁለንተናው” አለ። ይህ ታዲያ ምሥጋና ወይስ ስድብ? ከዚያች ቀን ጀምሮ ሰውዬው ቢለመንም ገደል ግቡ ብሎ ትቷቸው ከመሀላቸው ወጣ። ይውጣ እንጂ ስለመቀየሙ ስላልነገራቸው ስለአገሩ ጉዳይ ሊጠቀምባቸው ሲል ሳያስቀይማቸው በዝምታ አልፎታል።                                                                                

ይህን ሁሉ ያመጣሁትና የቆጥ የባጡን የምቀባጥርበት ምክንያት ወገኖቼ በመልክ የማይለያዩ፣ በፍቅርና በሰላም ለሺሕ ዓመታት አብረውና ተባብረው የኖሩ፣ በማያጣላና በማያስፈልግ ጉዳይ በቀዬ ወይም በጎጥ እንለያይ ብለው ሌሎች ከመቶ ዓመታት በላይ ያቀዱልንን የተንኮል መርዝ ሳይገባቸው ይዘው መዘመራቸው አሳስቦኝ ነው።

ሠለጠንን ያሉት ዛሬ ጠፈር ላይ ቦታ ለመመራት በሚሽቀዳደሙበት ዘመን ወጣት ሴት ልጆቻችን ሕፃን አዝለው በየመንገዱ ለልጄ ቁራሽ መፅውቱኝ ብለው ሲለምኑ እነሱን እንኳ መታደግ ያልቻልን፣ በየባህሩ የዓሳ ነባሪ እራት በመሆን ላይ የሚገኙትን ወጣት ወገኖቻችንን ከመከራና ከሥቃይ ማዳን የተሳነን፣ ለሙ አፈራችንን ለልማት ያላበቃን፣ ወራጅ  ወንዞቻችንን ለመስኖ ይቅርና በየከተማው ያሉትን ነዋሪዎች በቂ ውኃ ማደል ያልጀመርን፣ ለአገሩ ሠርቶና አገልግሎ ለጡረታ የደረሰንና በየዳር ድንበሩ ወሰን ጠብቆ ክብርና ነፃነታችንን ያስጠበቀልንን ሠራዊት በጡረታው ዘመን በልቶ፣ ጠጥቶና ለብሶ በክብር እንዲኖር ማድረግ ያቃተን፣ ዘመኑ የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ እንደ መሆኑ መጠን አገራችንን በዚያ መስመር ማስያዝና ሕዝባችንን ከዘመናዊ ባርነት ነፃ ለማውጣት ያልቻልን፣ በተለይም አዳዲስ የፖለቲካ ወጣት ተፎካካሪዎች ምን ሠርታችሁ ነው አገር ለመምራት የምትሽቀዳደሙት? ሊያፈርሱን ሲያደቡ ለኖሩት ባላንጣዎቻችን መሣሪያ እንዳትሆኑ፣ አገራችንን በታሪኳ ዓይታ ወደ የማታውቀው ዘመናዊ ቅኝ ግዛት ውስጥ እንዳታስገቧትና የታሪክ ጠባሳ በፊታችሁ ላይ ለጥፋችሁ የዘለዓለም ባሪያ እንዳትሆኑ አስቡበት፡፡

ያለውን በማጥፋት ሳይሆን በምክርና በአስተያየት መስመር በማስያዝ መጓዝ እንጂ፣ ሲያዩት እንደሚያምር ሲይዙት ግን ችግር ማምጣቱን በመገንዘብ አገራችሁን አሳልፋችሁ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን እንዳታስረክቡ ተጠንቀቁ፡፡ ታሪክ ይወቅሳችኋልና። አገርን ለማልማት፣ ወገንን ለማሳደግ የሚደረግ እሽቅድምድም መልካም ነው፡፡ መሠረት ይዞ መሄድም አለበት። ወገኖቼ እስቲ ራሳችሁን ጠይቁ፣ ተመራመሩ፣ እስከ ዛሬ ድረስ ምን ሠርተን አገርን ጠቅመን እናውቃለን ብላችሁ ራስችሁን ጠይቁ፣ ተመካከሩ። አሜሪካኖች ለሥልጣን በሚወዳደሩበት ጊዜ መጀመሪያ ሠርተው፣ ብዙ ልምድ አካብተው፣ ማንነታቸውን አስመስክረው፣ ራሳቸውን በኑሮ አበልፅገው፣ ለቤተሰባቸው ተርፈው አሁን በሄድኩበት መንገድ አገሬን ልርዳ፣ ወገኔን ልጥቀም ብለው ብዙ አስበውበት፣ አለ የተባለ አማካሪ ቀጥረው አማክረው፣ ከሁሉም ወገን አዎንታ ካገኙ በኋላ ወደ ውድድሩ ይገባሉ፡፡ ካሸነፉ ሥራቸውን በገቡት ቃል መሠረት ይጀምራሉ፡፡ ከተሸነፉም በደስታ ተቀብለው ወገናቸውን ይረዳሉ እንጂ ሞቼ ካልተገኘሁ ብለው ቀውስ ለመፍጠር አይነሱም።

እኛም መጀመሪያ የሥራ ልምድና እርግጠኛ የሆነ የአገር ፍቅር እንዲኖረን ያሻል። ፖለቲካ ውስጥ የምንገባው ራስን ከፍ ለማድረግ፣ የራስን የቅርብ ወገንን ብቻ ይዞ ለመጠቃቀም ከሆነ ዋጋ የለውምና ይታሰብበት። “ከበሮ በሰው እጅ…” ይባል የለ?                                                                      ማንም ይሁን ማን ለአገር የሚጠቅምና የሚሠራ ከሆነ እስከቻለ ይሥራ፡፡ ከመንገድ ከወጣና ለአገር የማይበጅ ሥራ ላይ የሚሰማራ ከሆነ በግልጽ ለውይይት ይቅረብ፣ ብሎም ከቦታው ይነሳ፡፡ ይህም ሲባል ለዘለዓለም ይንገሥ ማለቴ ሳይሆን፣ በተወሰነለት ጊዜ ብዙም አናውከው፡፡ ሰው መሆኑን አንርሳ፡፡ ምክር የማይቀበል ከሆነ ዘዴ ይፈለጋል እንጂ፣ ያ ሰው ያሳየውን ያህል ያልሞከሩ ግራ ሊያጋቡት አይገባምና ይታሰብበት።

ዛሬ ኢትዮጵያን ሊያጠፉ የገዛ ንብረታችንን ለመውሰድ ሲያቆበቁቡ የሚተባበሩ ኢትዮጵያዊያን፣ አገር እንደ ሸጡ እንደሚቆጠር ምንም አልጠራጠርም። በአንድነት መቆምና ነባር ታሪካችንን በድጋሚ ማሳየት ያለብን ጊዜ ነውና በአንድነት እንቁም። ምንም ይሁን ምንም የአገራችንን ክብር ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ሁሉ መተባበር ስላለብን በአንድነት እንቁም።                                                                           

የታላቁን የአፄ ምኒልክን ምሳሌ እንከተል። “ጉልበትህ ያለህ በጉልበትህ የሌለ በፀሎትህ፣ ይህን የማታደርግ ከሆነ ማሪያምን አልምርህም” ያሉትን እናስታውስ፡፡ በአገር ቀልድ የለምና፡፡ አገር ሲኖር ነው ሥልጣን የሚገኘው፣ አገር ሲኖር ነው ታላቅነት የሚኖረው። ምንም ብናገኝ የሰው አገር የሰው ነውና አገርን ለባዕድ አሳልፎ ለመስጠት አንብለጥለጥ፡፡ ብዙ ቢናገሩ ሆድ ባዶ ይቀራልና እዚህ አብቅቼ እናንተ ደግሞ የራሳችሁን አስተያየት ጨምሩበት።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...