Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር​​​​​​​አገር ከሚያተራምስ ከንቱ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንላቀቅ!

​​​​​​​አገር ከሚያተራምስ ከንቱ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንላቀቅ!

ቀን:

በሁነኛው አርዓያ ሥላሴ

በአንድ ወቅት የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮኑ፣ እንዲሁም የበርካታ ክብረ ወሰኖች ባለቤት ዝነኛው ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ‹‹ተናገረው›› የተባለና በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ሲመላላስ ያገኘሁትን ሐሳብ የጽሑፌ መግቢያ ማድረግ እሻለሁ፡፡ ‹‹እኔ እንግዲህ ከአገሬ አልፌ በመላው ዓለም በደንብ የታወቅሁ ሰው ነኝ፡፡ በዓለም ደረጃም ዝነኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን ከአገሬ ወጥቼ ወደ ሰው አገር ስሄድና አውሮፕላን ላይ ልሳፈር ስሠለፍኢትዮጵያየሚለውን ፓስፖርቴን ሳሳይ፣ ወደ ኋላ ረድፍ እንድሠለፍ ነው የምደረገው፡፡ መጀመርያ አሜሪካዊያን፣ እንግሊዞችና ሌሎች የበለፀጉት ይቀድማሉከአገር ስንወጣ ሁላችንም ያው የዚህችው የደሃ አገር ዜጎች ነን የእኛ አማራ ነኝ፣ ኦሮሞ ነኝ፣ ወላይታ ነኝፉክክር ምንም አይፈይድልንም፡፡ ይህን የሚያውቅልንም የለም፡፡ ይልቅ ቶሎ ቶሎ በርትተን ሠርተን ተለውጠንዓለም ፊት የቆሸሸውን የአገራቸንን ስም ብናፀዳ ነው የሚጠቅመን፤›› ነበር ያለው የተባለው፡፡

ይህ ነባራዊ ሀቅ የብዙዎቹ አገር ወዳዶችና የጽንፈኛ ብሔርተኝነትን መሸከም የማይፈልጉ ወገኖች ሐሳብ መሆኑ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁንም ድረስ ከዓለም  ደሃ አገሮች ተርታ ተሠልፋ፣ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለዕለት ዕርዳታ የሚጋለጡ ሚሊዮኖች ባሉበት ጊዜ፣ እንዲሁም ዜጎች በኢኮኖሚ ስደት ከአገር አገር በሚባዙንበትና ዓለምን በደረሱበት ሁኔታ፣ በዘር እየተቧደኑ መነታረክ እጅግ አሳፋሪና አሳዛኝ ገጽታችን መሆኑ ሊሸሸግ አይችልም፡፡ ከዚህ ብልሽት ቀስ በቀስ ካልተወጣም ፈተናው መክበዱ አይቀርም፡፡      

ከዚህም በላይ ዓለምን በተለያዩ ጊዜያት ከሚያጋጥሟት ፈተናዎች ዋነኛው የሰው ልጅ የሚያካሂደው የእርስ በርስ ጦርነትና ግጭት መነሻው ነጣጣይ አስተሳሰብ መሆኑን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ አገሮች በተናጠል ወይም በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች እርስ በርስ የሚያደርጉት አለመግባባትና ጥላቻ የሚቀሰቅሰው ጦርነት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕዝቦችን አስተላልቋል፡፡ ከዚያም በላይ የዓለም አገሮች ጎራ ለይተው የተጠዛጠዙባቸው እንደ አንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ያሉ ክስተቶች  በአውዳሚነታቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ለእነዚህ ጦርነቶች መቀስቀስ በርካታ ምክንያቶች በየታሪክ ድርሳናቱ ቢጠቀሱም፣ በአብዛኛው ከመሪዎችና ፖለቲከኞች አምባገነናዊ፣ ዘረኛና ዘራፊ አስተሳሰብ የሚመነጨው የተሳሳተ አመለካከት ከፍ ያለውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በተለይ ሕዝባችንን ባልተገባ የጥላቻና የቂም በቀል መንገድ በመንዳት በትንንሽ ምክንያቶች (በዘረኝነት፣ በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ፣ እንዲሁም በድንበር፣ በጋራ ሀብት፣ በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም…) ሰበብ የሚለኮስ እሳት በቀላሉ ሳይበርድ እስከ ትውልድ የሚተርፍ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል፡፡

ይህ ችግር በሠለጠነው ዓለምዳት ካደረሰ በኋላ በይቅርታና ወቅቱ በሚጠይቀው የጠንካራ አገረ መንግሥት ግንባታሳቤ እየተሠራ ሲመጣ መቆየቱ ግን ይታወቃል፡፡ በሦስተኛው ዓለም በተለይ በአፍሪካ ግን ቅኝ ገዥዎችና የተዛባ አስተሳሰብ አራማጆች በቀደዱት ቦይ በመፍሰስ እስካሁንም ድረስ ጥላቻ፣ ቂመኝነት፣ ግጭትና መለያየት  ተባብሶ የቀጠለባቸው አገሮች ትንሽ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያም ብትሆን በዚሁ ድርና ማግ ተተብትባ የምትገኝ ነች፡፡

አገራችን እንደ ብዙ ሰፋፊ አገሮች ብዝኃነት የሞላባት፣ የተፈጥሮ ባለፀጋና የታሪክ ምሰሶ ብትሆንም በውስጥም ሆነ በውጭ ኃይሎች የግጭትና የጦርነት ሰለባ ሆና ነበር የቆየችው፡፡ አሳዛኙ ነገር ደግሞ የእነዚያ ዘመናት ቅሪት አስተሳሰቦች በአሁኑ ትውልድ አዕምሮ ውስጥም እንዲመላለሱ እየተደረጉ፣ ከአብሮነት ይልቅ ልዩነትና መነጣጠል እያንዣበበ መሄዱ ነው፡፡ አገራችን ምንም እንኳን በሕዝቦቿ ጥንካሬና በፈጣሪም ረዳትነት ሳትጠፋ እዚህ ብትደርስም በየዘመናቱ ያለቀባት ሕዝብ፣ ምሁርና አምራች ኃይል ግን ለኋላ ቀርነትና ድህነት መባባስ የራሱ ድርሻ እንደነበረው ይኼ ትውልድ መገንዘብና መገመት አለበት፡፡ ዛሬም የኦሮሞና የትግራይ አንዳንድ ጠርዘኞች አካሄድ ከዚሁ አዙሪት እንዳንወጣ የሚያደርግ ነው፡፡

ካለፉት የታሪክ ዝንፈቶችና የተሳሳቱ የጥላቻ መንገዶች ዓለም እየወጣ ወደ ሥልጣኔና ትብብር ቢመጣም፣ በእኛ አገር በዛሬዋ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ለምን  የመራራቅ የመገፋፋት ዕሳቤ አረበበ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የተቃርኖ አስተሳሰብስ እስከ የት ድረስ ሊወስደን ይችላል ብሎ ማውጠንጠንም ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች የዚህ ሁሉ መዘዝ መነሻ የጎሳ ፌዴራሊዝም መከተላችን፣ ጠንሳሹም ሕወሓት/ኢሕአዴግ መራሹ የፖለቲካ ኃይል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አሁን ያለው የአክራሪ ብሔርተኛውና የኅብረ ብሔራዊ አንድነት ኃይሉ ፍጥጫ ሲታይም የአባባሉ እውነትነት ጎልቶ ይታያል፡፡

እሱ ብቻ ሳይሆን ግን 1960ዎቹ ፖለቲካ አብዛኛው ተዋናይ በማንነትና በዘር ላይ የተመሠረተን የፖለቲካ ትግል እንደ ጠቃሚ አማራጭ ወስዶ እንደነበር ተደጋግሞ የተባለ ሀቅ ነው፡፡ በተለይ የፊውዳሉን አገዛዝ ለመገንደስ፣ በአንድ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋና መሰል ሁነቶች ላይ ያነጣጠረ የሚመስል አገዛዝና ሕዝብን ያልነጠለ ትግል ተካሄዷል፡፡ የሥርዓቱ ባህልና እምነት ተደርገው የተቆጠሩ ዕሴቶች ላይም ዛሬም ድረስ በተሳሳተ መንገድ የበቀል ሾተል ተቀስሮ ይታያል፡፡ ይህ አዝማሚያ ግን ለምንምና ለማንም የማይበጅ አብሮ የማያኖር ችግራችን ነው፡፡

ባለፉት 30 ዓመታት በተጨባጭ እንደታየውም የሕዝቦችን መብትና ታሪክ ለማክበር በሚል ሰበብ፣ ከአገራዊ አንድነት ይልቅ የብሔርና የማንነት መብትና ጥቅምን ለማስከበር ከሚዛኑ ያለፈ ትኩረት መስጠትም ነበር፡፡ ከሁሉ በላይ ይህን አስተሳሰብ በአዲሱ ትወልድ ላይ ለማስረፅሐሰተኛና የተጋነነ ትርክትን በተራ የፖለቲካ ቀለም እየቀቡ ጥላቻን መዝራት ዛሬ ለደረስንበት አብሮነት መዳከምና የቂም በቀል ፖለቲካ ዳርጎን ይገኛል፡፡ ፍጥጫውም ከትናንት እስከ ነገ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች ከአዙሪቱ መውጣት እየፈለጉ አይደለም፡፡ ይህም መታረምን፣ የተስተካከለና ከሞላ ጎደል የምንግባባት ትርክት ሊመሠረት ግድ ነው፡፡

እንግዲህ ይህ ለምንና እንዴት ሆነ ከማለት ይልቅ፣ ከጥላቻና ዘረኛ አስተሳሰብ የጎሳና የዘር ፖለቲካ ቅኝት እየወጣን ወደ አገራዊ አንድነትና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ የሕዝብ ኅብረት ልንመለስ እንችላለን ብሎ ማብሰልሰል ተገቢና አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በተለይ ነገሮችን በሆደ ሰፊነት ከፈተሽናቸው የተለያዩ ፋሽስታዊ ባህሪ የነበራቸውና በዘረኝነት ብቻ ለከፋ ግጭትና መለያየት የተዳረጉ የዓለም አገሮች አካሄድም ትምህርት ሊሆነን ይችላል፡፡

ለአብነት ለመጠቃቀስ ያህል ጀርመንን በቀዳሚነት ማንሳት ይቻላል፡፡ የናዚ ፓርቲ አምባገነን መሪ አዶልፍ ሂትለር ጀርመኖችን ከዓለም የነጠለ ፋሽስት ብቻ ሳይሆን፣ የውስጥ አንድነታቸውንም የሚሸረሽር ዘረኛና ከፋፋይ አዘቅት ውስጥ ከቷቸው ነበር፡፡ የዚያ አስተሳሰብ ጥንስስ የአገርን ዓለም አቀፍ ገጽታ ከማጠልሸት ባሻገር፣ በርዕዮተ ዓለምና በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ተገፍቶ በርሊንን ከሁለት የከፈለ ግንብ እስከ መገንባት ያደረሰ ነበር፡፡ ጀርመናዊያንም ምሥራቅና ምዕራብ በሚል ተከፋፍለው ለዓመታት ቆይተዋል፡፡

በኋላ ግን የጀርመን ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ በአብዛኛው ምሁርና የፖለቲካ ኃይል ግልጽ ምክክርና ኅብረት ፈጥረው፣ ሕዝቡንም በማንቃት ዘመን ተሻጋሪ ጠንካራ አገራዊ አንድነት አረጋግጠዋል፡፡ ዛሬ በቆዳ ስፋቷ ከእኛዋ ኦሮሚያ ክልል ያነሰችው ጀርመን፣ በሥልጣኔም ሆነ በዓለም አቀፍ ተፅዕኖዋ ግንባር ቀደም የምድራችን ተጠቃሽ አገር የሆነችውም፣ ከአገራዊ አንድነት በሚመነጭ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዞዋ ነው፡፡ የጠባብነትን አስተሳሰብ በማሽቀንጠር ለሥልጣኔና ዕድገት በሰጡት ትኩረት መነሻም ነው፡፡ የመከላከያና የደኅንነት ኃይሏንም እንደ ሕዝቦች ዋስትና ከመቁጠር አፈንግጣ አታውቅም፡፡

ለዚህ ጽሑፍ ማጠናከሪያ በሁለተኛነት ሩሲያን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገችና በሶሻሊዝም ርዕዮት ቀዳሚ መሞከሪያነት የምትታወቅ ምድር፣ በታሪኳ  በተመሳሳይ በጠባብነትና በዘረኝነት ከፍተኛ ፈተና አስተናግዳለች፡፡ ከሩሲያ አብዮት በኋላ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሥርዓት ግራ ዘመም (Center Left) በመሆኑና በኒዮሊብራሊዝም ኃይሉ የቀዝቃዛው ጦርነት ተፅዕኖ የተባበሩት ሩሲያ ወደ 15 ብጥስጥስ አገሮች ልትበተን ችላለች፡፡ ዛሬም ድረስ የእነ ስታሊን ብሔር ተኮር የፖለቲካ ፈለግ የኪሳራ ምልክት ሆኖ ከመጠቀሱ ባሻገር፣ ከእኛው የኢሕአዴግ መራሹ ሕገ መንግሥት ውጪ አንድም የተከተለው አገር እንደሌለ ይታወቃል፡፡

ይሁንና አሁንም የተባበሩት ሩሲያ ፓርቲ ሀልዮትን በማግኘቱ (በተለይ ከቭላድሚር ፑቲን መምጣት በኋላ) በአንድ በኩል በዕድገትና ሥልጣኔ ቀዳሚ የምትባል አገር፣ በሌላ በኩል ያለውን ሕዝብ የሚያስተሳስር፣ የተበተነውንም የሚመልስ የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ምድር ለመሆን አልተቸገሩም ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን የዓለም የኃይል ሚዛን አንዱ ክንፍ የሚገኘው ሞስኮ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እዚህም ላይ ታዲያ በብዝኃነት  ላይ የተመሠረተ አገራዊ አንድነት ማቆጥቆጡ ለተገኘው ዕድገት ድርሻው ከፍተኛ ሆኖ እንደሚገኝ መዘንጋት አይገባም፡፡

የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉት አዳጊ አገሮች አንዷ የሆነችው ቻይናንም ብንመለከት፣ በሕዝቧ አንድነትና አብሮነት ረገድ የማይናወጥ ሐውልት በመገንባት ከትውልድ ትውልድ የምትሸጋገር ምድር ነች፡፡ ይህም በተባበረና በሚደማመጥ የሕዝብ አቅም ዓለምን ጉድ ያሰኘ ዕድገትና ሥልጣኔ እንድታረጋግጥ  ከማስቻሉም ባሻገር፣ የዓለምን አንድ አምስተኛ ሕዝብ ይዛ በከፍተኛ ብሔራዊ መግባባትና የማይናወጥ አብሮነት የምትጠቀስ መሆኗ ሊያከራክር አይችልም፡፡

በመሠረቱ ፌዴራላዊ አስተዳደርን ባትከተልም 1.5 ቢሊዮን ገደማ ከሚደርሰው የቻይናዝብ 93 በመቶ የሚሆነው ሀንበሚባለው ብሔር የሚታቀፍ ነው፡፡ ቀሪው ስድስት በመቶ የሚሆነወ ሕዝብም 56 አናሳ ብሔሮች አባል እንደሆነ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ግን በኮሙዩኒስት ፓርቲውም ሆነ በአገረ መንግሥቱ እንደ መጠናቸው የሚወከሉበት አግባብ ስላለ፣ እንዲሁም በቻይና በእኩልነት መንፈስ የሚጠቀሙበት ዕርምጃም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ስለመጣ፣ ምንም ቢሆን እንደ ሕዝብ በአንድነታቸውና በቻይና ሉዓላዊነት ሊደራደሩ አይችሉም፡፡ መነጣጠልና የቂም በቀል ፖለቲካ ለማቀንቀን የሚጋብዝ የኋላ ትርክት በዞረበትም አይታዩም፡፡ በዚህም በአሁኑ ጊዜ የዓለማችን ቁጥር አንድ የኢኮኖሚ መሪና ፈርጣማ የመከላከያ ኃይል ባለቤት መሆን ችለዋል፡፡

ከላይ ከጠቃቀስናቸው አገሮች ሌላ በተለይ ፌዴራላዊ ሥርዓትን የሚያራምዱ እንደ ህንድ፣ ካናዳ፣ አሜሪካና መሰል አገሮችንም ስንመለከት፣ በቀለም (አልፎ አልፎ የሚታይ ችግር ቢኖርም) በዘርና በጎሳ ተሰባስቦ ከመታገልም ሆነ አንዱ ሌላውን ከማሳደድ ልክፍት ከተላቀቁ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ አረረም መረርም በአገራቸው አንድነትና በሉዓላዊ ሰንደቃቸው ላይ መደናገርና መወዛገብ ውስጥ ሊገቡ አይችሉም፡፡ ዛሬ በእነዚህ አገሮች የሚኖሩት የእኛዎቹ አንዳንድ ምሁራን ተብዬዎችና ፖለቲከኞች ግን፣ አገራችንን ወደ ፍርስራሽነት በሚቀይሩ አደገኛ ቅስቀሳዎች ላይ ተጠምደው ማየት እጅግ የሚያሳዝን እውነታ ነው፡፡

ብዙዎቹ አገሮች በታሪካቸው ብዙ ውጣ ውረዶችን፣ አስከፊ ጦርነቶችና አገዛዞችን ማሠለፋቸው ቢታወቅም የዛሬው ትውልድ በሥልጣኔና በዕድገት የራሱን ታሪክ እንዲጽፍ ከማንቃት ባሻገር፣ በማይበጀው ትርክትና ጥላቻ እንዲጠመድ አይፈልጉም፡፡ የዜግነት ፖለቲካ ሥር በሰደደበት መስተጋብር ውስጥ ፌዴራላዊ ሥርዓትን ለእኩልነትና ለአንድነት በመጠቀምም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በጠባብነት የተለከፍን ኢትዮጵያዊያን ከእንዲህ ያሉ በጎ እሴቶች ትምህርት መውሰድ ስለምን ተሳነን ነው መባል ያለበት፡፡

እነዚህና ሌሎች በርካታ አገሮችን አብነቶች ስንፈትሽ የአገራችንስ ነባራዊ ሁኔታ እንዴት ሊሆን ይገባዋል የሚል ተጠየቅ ማንሳትም ተገቢ ነው፡፡ ገዥውን ፓርቲ፣ መንግሥትንም ሆነ መላውን የፖለቲካ ልሂቃን እባካችሁ ከዘር፣ ከጎሳና ከጥላቻ ፖለቲካ ወጥተን በአንድ አገር በእኩልነትና በመተሳሰብ እንደሚኖር ሕዝብ ተደማምጠን፣ በሠለጠነ መንገድ እንጓዝ ለማለት እሻለሁ፡፡ እኔ ካልበላሁት ልድፋው የሚልና እኔ ያልመራኋት አገር ትበተን የሚለው የአንዳንድ ፖለቲከኞች ስካር አደብ ሊገዛ እንደሚገባውም ሳልጠቁም ማለፍ አልሻም፡፡

በመሠረቱ ከላይ እንደ ተጠቆመው የአገራችን አንዱ ትውልድ በጎሳ ፌዴራሊዝምና አክራሪ ብሔርተኝነት ሲነጉድ በመቆየቱ፣ ሁላችንንም ጎሰኛና መንደርተኛ እያደረገን መጥቷል፡፡ ነገር ግን በዚህ አካሄድ ከቀጠልን የጋራ ቤትና በታሪከ ‹‹የእኛ›› ስንላት የኖርናትን አገር ለልጆቻችን ስለማስተላለፋችን ዋስትና ሊኖረን አይችልም፡፡ ልማት፣ ሰላምና ዕድገት ማሰብ ከንቱ ምኞት ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና የሕዝባችን በነፃነት የመወሰን መብት ለማረጋገጥ መነሳት ሲገባ፣ ዓለም በናቀው ከፋፋይ አስተሳሰብ አገርን ለመበተን መንቀሳቀስም ከወንጀሎች ሁሉ የከፋ ወንጀል ነው፡፡

እርግጥ አገራችን ባለፉት ሦስት አሠርት የኢሕአዴግ/ብልፅግና አመራር ዓመታት የቆየችው ከመደብ ይልቅ፣ በብሔር የመብት ጥያቄ ላይ የሚነታረክ ትውልድ እንደ ያዘች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ሁነትም በልዩነት መዘውርና በነጣጣይ ፖለቲካ ተረግዞ የወለደልን አክራሪ ብሔርተኝነትን፣ የፖለቲካ ጥላቻንና መጠፋፋትን ነው፡፡ እንደ አገር የምንከተለው በማንነት ላይ የሚያተኩረው ፌዴራሊዝምም ቢሆን በልማት፣ በብሔረሰቦች መብትና ታሪክ በማስተዋወቅ ረገድ ያመጣው ለውጥ ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው የሕዝቡንና የአገርን አብሮነትና መስተጋብር በተቃርኖ ፖለቲካ በማናጋት የአገረ መንግሥቱን አንድነት ክፉኛ ከማዳከም ባሻገር፣ በክልሎች አወሳሰንና በማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ የደነቀረብን ፍጥጫም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

እንዲያው ራሳችንን ከላይ ካነሳናቸው አገሮች የኅብረ ብሔራዊ አንድነትና የአገረ መንግሥት ጥንካሬ ጋር ማነፃፀሩን ትተን፣ የብሔር ፌዴራሊዝም አዋጭና ዘላቂ የሕዝባችን አንድነት የሚያስከብር ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ በዚህ ደረጃ በፖለቲከኞች ገፋፊነት የምንባላ ሆነን መገኘት ነበረብን? እንደ አገር ‹‹ተለወጥን!›› እያልንስ ይህን ያህል ትርምስ (ተዟዙሮ የመሥራት፣ በየአካባቢው ተረጋግቶ የመኖር፣ የማልማትና የመጠቀም ሥጋት ተባብሶ) ይታይ ነበር? የዚህን እውነታ ሥር መሠረት ሳይመረምሩ በጥላቻ የዞረ ድምረ መላጋቱ ብቻ ለየትኛውም ፖለቲከኛ የሚበጅ አይደለም፡፡

እስኪ ነገሩን በጥሞና እናጢነው፡፡ ችግሩ የተዘራው 27 ዓመታቱ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት አገዛዝ ዘመን ቢሆንም፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ምን ያህል ግጭት፣ ሥርዓት አልበኝነትና መፈናቀል እንደተከሰተ፣ እንዲሁም የንፁኃን ዕልቂትና የሕዝብ አለመተማመን፣ እንዲሁም የአገር ገጽታ እንዳሽቆለቆለ መመዘን የሚከብድ አይሆንም፡፡ በተለይ በማንነት ላይተመሠረቱት አብዛኛዎቹ ክልሎች ከፌዴራሉ መንግሥት ያፈነገጠ አካሄድ ለመከተል በመሞከርና የአገሪቱን ጉዳይም ‹‹አያገባኝም›› ወደ የሚል ጠርዝ በመግፋት ፀያፍ ተግባር ሲያሳዩ ተመልክተናል፡፡ ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ጠበቅ ያለ የሕግ የበላይነት የማስከበር ዕርምጃ እየወሰደ ቢሆንም፣ መቀመጫቸውን በውጭ ያደረጉ የጥላቻ ሰባኪዎች፣ በአገር ውስጥ በለውጥ ተገዳዳሪዎችና በመንግሥት በኩል አሁንም ያልተቋጨ ፍጥጫ መኖሩ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው በሌላው ዓለም እምብዛም ያልተስፋፋ፣ የሥርዓቱ አካሄድ ከአብሮነት ይልቅ ልዩነትና የፈጠራ ተረክ የሞላበት ሆኖ ነበር የቆየው፡፡ ይህ ጉዞ የዘር ፖለቲካን በመውለድ በሁሉም አካባቢ መካረርና የመስገብገብ ፍላጎት እንዲባባስ ከማድረጉ ባሻገር፣ ኢትዮጵያን የጥቂት የገዥ መደብነት ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች መጠቀሚያ ሆኖ መጋለጧም አይዘነጋም፡፡ በመሠረቱ በጎሳ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ትግል በየትኛውም ዓለም ቢሆን በዚህ ዘመን የሌለ ሲሆን፣ በነበረበት የቀደሙት ጊዜያትም አገሮቹን በኪሳራ ያዋረደ እንደነበር ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ፌዴራላዊ ሥርዓት መተግበሩ በራሱ ችግር ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ፈተና እየሆነ ያለው ግን ክልሎች በዋናነት በብሔር ንፍቀ ክበብ በመካለላቸው፣ ከአቃፊነት ይልቅ የገፊነት ፖለቲካ ጥርስ እያወጣ በመምጣቱ፣ በዘር የተደራጁ ሚዲያ፣ ፖሊስና ልዩ ኃይል የመሳሰሉትን በአቅማቸው ልክ ብቻ ሳይሆን፣ እንዳሻቸው በመገንባታቸውና በማዘዛቸው አጉል ፉክክር መፍጠሩ ነው፡፡ በፌዴራል መንግሥቱና በአንዳንድ ክልሎች (በተለይ ትግራይ) መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሄዶ ወደ ጦርነት መቀየሩ ይታወሳል፡፡ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ጦርነት ለኩሶ እንዳይሆኑ ከሆነ በኋላ ሰሞኑን የማንሰራራት ምልክት ቢያሳይም፣ ለሌላ ዙር ውድመት እየተዘጋጀ በመሆኑ ተጨማሪ ጥፋት ሊደርስ ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡  

እንግዲህ  ዛሬ እንደ አገር ለውጥ ለማስቀጠልም ሆነ፣ የሕዝባችንን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ጠብቆ ለመሄድ ፍልሚያው በተጠናከረበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነው የምንገኘው፡፡ በዚያው ልክ አገርን ወደ ኋላ የሚመልሱና የተጠረቃቀሙ ተግዳሮቶችም አላላውስ እንዳሉን በግልጽ መረዳት ተገቢ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ  ጭምር በመጥቀስ፣ እንደ ዜጋ የመፍትሔ ሐሳብ መስጠት የሚያስፈልገውም የችግሮቹ ሁሉ ሰንኮፍ ከዘርና ከቂም በቀል ፖለቲካ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው፡፡ ግን ለአገር ፋይዳ ከሌላቸው ፖለቲከኞች አስተሳሰብ ተላቀን በአንድ አገራዊነት መንፈስ መቆም ከቻልን ከውድቀት መዳን የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ይህን ለማድረግ ደግሞ መንግሥትም ቢሆን የሕዝቡን ትክክለኛ ፍላጎት በግልጽ የሚያረጋግጥ መፍትሔ ያለ ይሉኝታ ማመላከት ይኖርበታል፡፡ በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በኩልም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግልን ማጠናከር ግድ የሚል ብቻ ሳይሆን፣ ጽንፈኞችና አገር አፍራሽ አስተሳሰቦችን ከጨዋታው ሜዳ እያስወጡ፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት እንዲያጡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም ለሁሉም ሕዝቦች በፍትሐዊነት የምትጠቅም አገር መገንባት ይኖርብናል፣ ይቻላልም፡፡ ዓለም ከናቀውና አገር ከሚያመሳቅል የፖለቲካ አስተሳሰብ እንላቀቅ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...