የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በኦንላይን የውክልና ሰነድ ማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ሌሎች ባንኮችም በቀጥታ የኤጀንሲውን ዳታ ቤዝ በመጠቀም ሰነድ ማረጋገጥ የሚችሉበት ስምምነት ይደረጋል፡፡
በሁለቱ ወገኖች የተደረገውን ስምምነት አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሕጋዊ ውክልና ሰነዶችን የማረጋገጥ ሥርዓትን ቀልጣፋ ለማድረግ ከኤጀንሲው ጋር በጋራ ለመሥራት ይችላል፡፡ ሰነዶችን በኦንላይን የማረጋገጡ ሥራ የደንበኞችን ዕርካታ ለመጨመርና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለው እንደሆነም ባንኩ አስታውቋል፡፡
በዚህ ስምምነት ዙሪያ የፌዴራል የሰነዶች ማረጋጫና ምዝገባ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች ወደ ባንኩ ይዘው የቀረቡት የውክልና ሰነድ ትክክለኛ ስለመሆኑ የኤጀንሲውን የመረጃ ቋት በቀጥታ በመጠቀም ለባንኩ የቀረቡ ሰነዶች ትክክለኛ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችለው ነው፡፡
እንዲህ ያለው አገልግሎት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ1,700 ቅርንጫፎቹ የሚሰጥ መሆኑንም በዚሁ ስምምነት ላይ ተገልጿል፡፡ ባንኩ ከኤጀንሲው ጋር የደረሰው ስምምነት ሐሰተኛ ውክልና ሰነድ ይዞ በመቅረብ የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ ከባንኩ ለማውጣት የሚደረግ ወንጀልን በመከላከሉ ረገድ የሚሰጠው ጠቀሜ ከፍተኛ ነው፡፡
እንደ ኤጀንሲው መረጃም ከሆነ በኦንላይን ውክልና የመስጠትና የመቀበል ሒደት መጀመሩ ከዚህ በፊት ከአንድ እስከ ሁለት ሳምንት ይፈጅ የነበረው አገልግሎት አሁን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የማረጋገጥ ሥራው እንዲፈጸም መደረጉ አገልግሎቱን በደቂቃዎች ውስጥ ለመስጠት የሚያስችል ነው፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤጀንሲው ከመስከረም 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ዳታ ቤዝ ያከማቻቸውን በሥርዓት የተደገፉ፣ የተረጋገጡና የተመዘገቡ ሰነዶች መጠቀም የሚያስችለው ይሆናል፡፡
ከመስከረም 2012 ዓ.ም. በፊት ለተመዘገቡ ሰነዶች ግን የተለመደውን የማኑዋል አገልግሎት ከኤጀንሲው በማግኘት የሚሠራ መሆኑንም ባንኩ አስታውቋል፡፡
የሰነዶች ማረጋጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት ከሚሰጣቸው ከ50 በላይ የተለያዩ አገልግሎቶች ውስጥ ሃያ አምስቱን በቴክኖሎጂ አስደግፎ እየሰጠ ነው፡፡
ኤጀንሲው ከከፍተኛ ተገልጋዮች ውስጥ በዋናነት የሚቀመጠው የውክልና ውል መሆኑም ተገልጿል፡፡ ሰነዶችን በቀጥታ የኤጀንሲውን ዳታ ቤዝ በመጠቀም ለማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደተሰጠው ዓይነት ዕድል ሌሎች ባንኮችም እንዲያገኙ ለማስቻል ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ በቅርቡ ተመሳሳይ ስምምነት ከግል ባንኮች ጋር እንደሚደረግ ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡
ነሐሴ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በኤጀንሲው መካከል የተደረሰውን ስምምነት በባንኩ በኩል የባንኩ ማዕከላዊ ሪጅን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኪዳኔ መንገሻ፣ በኤጀንሲው በኩል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሙሉቀን አማረ ፈርመዋል፡፡