በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ እንዳለው ይጠቀሳል፡፡ ሆኖም ዘርፉ የዕድሜውን ያህል አላደገም፡፡ በአሁኑ ወቅት ባንኮች እያሳዩ ካለው ዕድገት አንፃር የኢንሹራንስ ዘርፍ ሲታይ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ዘርፉን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታዎች ቢኖሩም በአግባቡ ስላልተሠራባቸው ኢንዱስትሪው ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጽኦ እንዳላበረከተ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ችግሩ እንዳለ ሆኖ አሁንም ዘርፉን ሊያሳድግ ይችላል የተባለ ሌላ ዕድል ብቅ ብሏል፡፡ እስካሁን እየተሠራበት ካለው የኢንሹራንስ አገልግሎት በተጨማሪ እንደ አማራጭ የቀረበው ደግሞ ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ ወይም ታካፉል የሚል መጠሪያ ያለው የኢንሹራንስ አገልግሎት ነው፡፡ ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዕድገት ጋር ተጣጥሞ መጓዝ እንዳለበትም የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ካለወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎት ሊራመድ ስለማይችል በዚህ ረገድ ብዙ መሠራት እንዳለበትም ይጠቅሳሉ፡፡ ይህንን ሐሳብ ከሚስማሙበትና በዘርፉ እየሠሩ ካሉት መካከል የአልፋ ሰርተፊኬሽን ኮንሰልት ሰርቪስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢብሳ መሐመድ አብደላ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ኢብሳ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎቶች መጀመር በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና በአጭር ጊዜ የታየውም ውጤት ይህንኑ እንደሚያመለክት ይገልጻሉ፡፡ ኩባንያቸው ይህንን ዘርፍ ለማሳደግም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር እየሠራ ነው፡፡ አቶ ኢብሳ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ዘርፍ አግኝተዋል፡፡ ማስተርስ ዲግሪያቸውን ደግሞ በቢዝነስ አድሚንሰትሬሽን ያገኙ ሲሆን በባንኪንግና ኢንሹራንስ ዘርፍ ኤክስኪዩቲቭ ዲፕሎማ አላቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በእስላሚክ ባንኪንግ ዶክትሬታቸውን እየተማሩ ነው፡፡ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት በተለይም በታካፉል ኢንሹራንስ ዙሪያ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከወለድ ነፃ ባንክና የኢንሹራንስ አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው እንቅስቃሴ እንዴት ይታያል? በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ዘርፍ ጅማሮስ ምን ይመስላል?
አቶ ኢብሳ፡- ከወለድ ነፃ ባንክና የኢንሹራንስ አገልግሎት በዓለም ላይ እየሰፋ ነው፡፡ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎትን በምናይበት ጊዜ ሰዎች ከሃይማኖት ጋር ያያይዙትና ትልቁ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት የሚሠራበት አገር ሳዑዲ ዓረቢያ ነው ይላሉ፡፡ ግን በዚህ ዘርፍ ሳዑዲ ወደ አምስተኛ ደረጃ ላይ ነው ያለችው፡፡ ከወለድ ነፃና የፋይናንስ ዘርፍ እየተስፋፋ፣ ትልልቅ ባንኮች እየሠሩበትና ሥልጠናውም በለንደን እየተሰጠ ነው፡፡ ምክንያቱም አማራጭ የፋይናንስ አገልግሎት በመሆኑ ነው፡፡ ይኼ ንፁህ ቢዝነስ ነው፡፡በተመሳሳይ መልኩ ከወለድ ነፃ ባንክ ሲጠቀም ከወለድ ነፃ ኢንሹራንስ የሚጠቀም ይሆናል፡፡ እንዲያውም ባንኮቹ ሥራ እንደመጀመራቸው ኢንሹራንሶቹ ዘግይተዋል፡፡ ምክንያቱም ወለድ አልባ ባንክ የሚጠቀሙ ሁሉ መደበኛውን ኢንሹራንስ እየተጠቀሙ የሚገኙ በመሆናቸው ወደ ሸሪዓ በምንመጣ ጊዜ ይህ በቀጥታ የሚፋረስ ነውና በሌላኛው መልኩ ወለድ የነካው ኢንሹራንስ በግዳጅ ተጠቃሚ ሆነው ስለሚገኙ በአገር አቀፍ ደረጃ በእነዚህ አማራጮች መጠቀም የተፈቀደ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥም ባንኮች በመስኮት ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ አገልግሎቱ ከተጀመረ አጭር ጊዜ ቢሆንም ለፋይናንስ ኢንዱስትሪ ጥንካሬ እየፈጠረ ነው፡፡ ከመስኮቶች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት እየተጀመረ ነው፡፡ አሁን አዳዲስ የተቀላቀሉ ያሉት እንደነ ዘምዘም፣ ሒጅራና ሌሎች መጪዎችም በሒደት ላይ ያሉ ባንኮችም አሉ፡፡ አሁን እየወጡ ያሉ ጆርናሎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ቀጥሎ በከፍተኛ ደረጃ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እያደገች መሆኑን ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በወለድ አልባ ፋይናንስ ኢንዲስትሪው መሪ ሆው የሚገኙት እንደ ማሌዥያ፣ ባህሬይንና ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ፣ እንዲሁም ከአፍሪካ ናይጄሪያ መሪ ስትሆን ቀጥሎ ደግሞ ኢትዮጵያ ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ የሚገኙ አገሮች ኢራቅ፣ ናይጄሪያና ኢትዮጵያ መሆናቸውን የቅርብ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ በዚህ በወለድ አልባ ፋይናንስ ዘርፍ እጅግ በከፍተኛ ደረጃ እያደገች የምትገኝ አገር ናት፡፡ በወለድ አልባ ፋይናንስ ውስጥ ሰዎች የመጠቀም ዕድላቸው ሰፍቷል፡፡ ዘመናዊነትን ከመከተል የሚገድብ ሰበብ አይኖራቸውም፡፡ የሰዎች ዘመናዊነት ከሚረጋገጥባቸው መስኮች አንዱ ባንክንና ኢንሹራንስን መጠቀም ነው፡፡ ገንዘባቸውን ከሥጋት ማራቅ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም ገንዘባቸውን በመጠቀም ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትን ማስመዝገብ ነው፡፡ ይህ ውጤት የተገኘው እስካሁን ባለው በመስኮት ደረጃ በሚጠው ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ነው፡፡ ባንኮች አካባቢ ስትሄድ ውጤት እያገኙበት ነው፡፡ አሁን እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች ባንኮች በመስኮት ደረጃ እየሰጡ ባሉት ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘንድሮ መጨረሻ ላይ ከወለድ ነፃ ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ከ52 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጀመረ እጅግ በጣም ትንሽ ዕድሜ ያለው ቢሆንም፣ በጣም ጥሩ ውጤት አሳይቷል፡፡ በዚህ ዘርፍ ብቻ የሚሠሩ ባንኮች ሲገቡ ደግሞ የበለጠ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ይህ ትልቅ አማራጭ የባንክ አገልግሎት የበለጠ ውጤት እንዲያመጣ አሁንም መሠራት አለበት፡፡ ነገር ግን ይህ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሙሉ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ሙሉ አይደለም የሚሉት ለምንድነው?
አቶ ኢብሳ፡- አገልግሎታቸው በተመሳሳይ ከሚታየው ከወለድ ነፃ ኢንሹራንስ አገልግሎት ጋር ባለመተሳሰሩ ነው፡፡ ይኼም አንድ ሰው ወለድን ሳይጠቀም ከወለድ አልባ ባንክ በሚጠቀምበት ጊዜ ከወለድ ነፃ ኢንሹራንስን ነው መጠቀም ያለበት፡፡ በዚህ በኩል ወለድን ሸሽተህ በኢንሹራንሱ በኩል በወለድ ኢንሹራንስ በምትጠቀምበት ጊዜ የሚጣረስ ነገር አለው፣ ይደበላለቃል፡፡ ስለዚህ ትክክል አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም ከወለድ ነፃ ኢንሹራንስ አገልግሎት ስላልነበረ አማራጭ ስለሌለ፣ ግዳጅ ትጠቀምበታለህ፡፡ አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎት ወይም ታካፉል ኢንሹራንስ በሱፐርቫይዘሪ ደረጃ ተፈቅዶ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በመስኮት ደረጃ ጀምረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከወለድ ነፃ ወይም ታካፉል የሚባለው የኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲጀመር ተፈቅዶ በመስኮት ደረጃ እየተሰጠ ነው፡፡ የታካፉል ይዘትና ጠቀሜታ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ኢብሳ፡- ታካፉል ማለት ከዓረብኛው ካፋላ ከሚለው ቃል የተወሰደ ነው፡፡ ሥጋትን መጋራት መካፈል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎት መስጠት በመፈቀዱ ብዙ ኢንሹራንስ ካምፓኒዎች ይህንን አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል፡፡ አንዳንዶቹም በመስኮት ደረጃ ሥራውን ጀምረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ግሎባል ኢንሹራንስ የመጀመርያው ሆኗል፡፡ ሌሎች ኩባንያዎችም ወደዚህ መግባታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ የኢንሹራንስ አገልግሎት መጀመር ለኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ለማኅበረሰቡ ሊኖረው የሚችለው ጠቀሜታ እንዴት ይታያል፡፡ አጠቃላይ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውንስ እንዴት ያዩታል?
አቶ ኢብሳ፡- በአገራችን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የባንክ ኢንዱስትሪን ያህል አስተዋጽኦው የጎላ አይደለም፡፡ የኢንሹራንሱ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ችግሩ ከካምፓኒዎቹ ሳይሆን እኛ አገር ላይ ስለ ኢንሹራንስ ያለው ዕውቀት እጅግ አነስተኛ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ካልተገደደ በስተቀር ወደ ኢንሹራንስ አይመጣም፡፡ የዚህችን አገር ውጥንቅጥ፣ ችግሮች የሚፈታው ከባንክ ይልቅ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ በሌላው አገርም ላይ ይህ በደንብ ጎልቶ ይታያል፡፡ በሕይወት እያለህ የምትገባው ኢንሹራንስ አደጋ ቢደርስብህ የምትጠበቅበትን ትልቅ ዕድል የሚፈጥርልህ ነው፡፡ በተለያዩ ዘርፎች የምትገባው ኢንሹራንስ አንተንም በዙሪያህ ያሉትንም የቀደመ ሕይወት ችግር ከገጠመህ በኋላም ሊያስቀጥል መቻሉ ነው፡፡ ለልጆች ትምህርታቸው አይቋረጥም፣ ቤተሰብ አይበተንም፡፡ ምክንያቱም ኢንሹራንሶች ያንን አደጋ ሥጋቱን ወስደው አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ካሳ ይከፍላሉና፡፡ ይህ ካሳ ቤተሰብን ይታደጋል፡፡ እኛ አገር ላይ ግን ተቃራኒ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሕይወት ኢንሹራንስ ከጠቅላላው የኢንሹራንስ ሽፋን አንፃር ሲታይ አሥር በመቶ አይሞላም፡፡ በሌላው ዓለም የሕይወት ኢንሹራንስ ድርሻ 80 በመቶ እና 90 በመቶ ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህ የእኛ አገር የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ካለው ከ90 በመቶ በላይ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ሽፋን ውስጥ ደግሞ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የሞተር ኢንሹራንስ ነው፡፡ ሞተር ኢንሹራንስ ደግሞ በተፈጥሮው ለሥጋት የቀረበ ነው፡፡ ለአደጋ ቅርብ ነው፡፡ ቤተሰብን፣ ገንዘብን የሚያሳጣ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ታካፉል አዲስ የኢንሹራንስ አገልግሎት የአገሪቱን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ሊቀይረው ይችላል?
አቶ ኢብሳ፡- በጣም ይለውጠዋል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው የእኛ ማኅበረሰብ ሃይማኖተኛም ነው፡፡ በተጨማሪም ወለድ የማይጠቀም ሰፊ ማኅበረሰብ አለ፡፡ አሁን አገልግሎት ላይ ያለውን የኢንሹራንስ ሽፋን በእምነቱ ምክንያት የማይጠቀም ማኅበረሰብ አለ፡፡ የባንኮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በፍጥነት እያደገ በመሆኑ ታካፉል ኢንሹራንስም በዚያው ልክ የማደግና አጠቃላይ ኢንዱስትሪውን የመቀየር አቅሙ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ይኼም የሚያሳየው ሰፊው ማኅበረሰብ በወለድ ምክንያት ከባንክ የራቀና ገንዘቡንም ተገቢ ባልሆነ ቦታ በማስቀመጥ እያባከነ የነበረ መሆኑን ነው፡፡ ኢንሹራንሱም ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያለው ነው፡፡ ማኅበረሰቡም ከዚህ ጋር ነው የሚጠቀመው፡፡ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት እየተጠቀመ የወለድ አልባ ባንክ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ይበደራል፣ ሕንፃ ይሠራል፡፡ ማንኛውም ገንዘቡ መሥራት ያለበትን የንግድ ሥራ ሁሉ ይሠራል፡፡ እነዚህ ኢንሹራንሶች ታካፉልን ሲጀምሩ የመጀመርያ ሥራቸው ሆኖ ደንበኛ ፍለጋ አይሄዱም፡፡ በተመቻቸ መልኩ ከባንኮች ጋር ይሠራሉ፡፡ ደንበኛ ባንኩ ጋር አላቸው፡፡ እነዚህን ነው ወደ ሥራ የሚቀይሩት፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ከሚገኝበት ሽልብታ ያነቃዋል፡፡ በተለይም ሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስን ብቻ ይጠቀም የነበረው ማኅበረሰብ ከወለድ አልባ ኢንሹራንስ መጠቀም ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ኢንሹራንስ ሥራውም አስተማማኝ እንዲሆን ይረዳል፡፡ የኢንሹራንስ ሐሳብ አንድ ሰው አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ካሳ እንዲያገኝ ማስቻል ነው፡፡ ከወለድ አልባ ኢንሹራንስ አንፃርም በእምነቱ ሳቢያ የተገለለው ማኅበረተሰብ ዕድሉን ተጠቅሞ ካሳ የሚያገኝበት መንገድ ከፍ ይላል፡፡ ሌላው ደግሞ የተለያዩ የኢንሹራንስ ዓይነቶችና አገልግሎቶች ይፈጠራሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በመደበኛው የኢንሹራንስና ከወለድ ነፃ (ታካፉል) ኢንሹራንስ መካከል ያለው አንድነትና ልዩነት እንዴት ሊገለጽ ይችላል?
አቶ ኢብሳ፡- በመጀመርያ ደረጃ አንድነታቸው ሁለቱም ኢንሹራንሶች መሆናቸው ነው፡፡ ኢንሹራንስ ማለት ለሚደርሱብህ ችግሮች ነገ ካሳ መክፈል ማለት ነው፡፡ መደበኛው ላይ ግን ኢንሹራንስን የሚገዛው ሰው ለኢንሹራንስ ድርጅቱ ነው አደጋውን አሳልፎ የሚሰጠው፡፡ ለኢንሹራንስ ኩባንያው ዓረቦን ከከፈለ ያለው ኃላፊነት የኢንሹራንስ ድርጅቱ ይሆናል፡፡ መሠረታዊ ልዩነታቸውም ያለው እዚህ ጋር ነው፡፡ ወደ ታካፉል ስንመጣ ኢንሹራንስ ዓረቦን ገዝቶ የኢንሹራንስ ሽፋን የተሰጠው ሰው አደጋውንም ይካፈላል፡፡ አደጋው ባልደረሰ ጊዜም ትርፉን ይካፈላል፡፡
ሪፖርተር፡- እዚህ ጋር ግልጽ እንዲሆን በታካፉል ኢንሹራንስ ሲገባ አደጋንም የመካፈል ኃላፊነት አለበት፣ ትርፍም ተካፋይ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንድ ኢንሹራንስ ኩባንያ ሲቋቋም ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡ ከዚያም በኋላ ደንበኞች ይመጣሉ፡፡ ደንበኞችና ባለአክሲዮኖች ወይም ካፒታል ያሰባሰቡ ሰዎች ትርፉና ኪሳራቸውን እንዴት ነው ሊካፈሉ የሚችሉት?
አቶ ኢብሳ፡- ባለአክሲዮኖች እንደ መደበኛው ኢንሹራንስ ናቸው፡፡ ደንበኛውም እንደዚያው ደንበኛ ነው፡፡ ዓረቦን በሚከፍሉበት ጊዜ የጋራ የሆነ ፈንድ አላቸው፡፡ ኢንሹራንስ ሲገባ ዓረቦን ይከፍላል፡፡ ይህ ዓረቦን ፈንድ ላይ ይቀመጣል፡፡ ለካሳ የሚቀነስ፣ ለሕግና ለመሳሰሉት የሚቀነስ መቶኛ ይቀመጣሉ፡፡ ይህ በመቶኛ ተሠልቶ ከተቀመጠ በኋላ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ለምሣሌ የአሥር ብር አደጋ ቢደርስ አሥር ብሩን ኢንሹራንሱም ደንበኛውም ይካፈላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ሕጉ ወጥቷል እንዴት ነው እየተሠራበት ያለው?
አቶ ኢብሳ፡- አሁን ትልቁ ችግርና በጣም ትልቅ ማነቆ የሚሆነው የሰው ኃይል እጥረት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በቂ የሠለጠነ የሰው ኃይል የለም፡፡ ይህ ትልቅ ፈተና በመሆኑ እዚሁ ላይ ቀን ከሌሊት ሊሠራበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም መደበኛው ኢንሹራንስ ዘርፍ ሥራ ላይም ይህ ችግር ጎልቶ ያለ እንደመሆኑ እዚህኛው ላይ ሰዎችን ማሠልጠን፣ ሰዎችን ማብቃት ያስፈልጋል፡፡ አሁን በመስኮት ደረጃ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ለመንቀሳቀስ ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል፡፡ ስለዚህ መሠራት ያለበት ጉዳይ ሰዎችን በከፍተኛ ደረጃ ማብቃትና በይበልጥ የሰው ኃይል ሥልጠና ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ከሆነ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ በባንኩም ሆነ በኢንሹራንሱ ዘርፍ አማካይነት ምጣኔ ሀብታዊና የገንዘብ ዕድገት ይኖራል፡፡ ሆኖም ትልቁ ራስ ምታት የሰው ኃይል እጥረት ነውና ይህ ጉዳይ በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡- እንደጠቀሱት በአጠቃላይ የፋይናንስ ኢንዱስሪው ውስጥ ትልቅ ችግር ሆኖ የሚታየው የሰው ኃይል እጥረት ነው፡፡ ይህንን እንዴት ነው መወጣት የሚቻለው? ባለው የሰው ኃይል እጥረት ሳቢያ ኩባንያዎች ሰዎች እየተነጣጠቁ ነው፡፡ የኢንሹራንስና ባንክ ዘርፍ የሚያሠለጥኑ ተቋሞች አለመኖራቸው ተግዳሮት ነው፡፡ መፍትሔ የሚያገኝበት መንገድ ምንድነው ብለው ያስባሉ?
አቶ ኢብሳ፡- አሁን ለምሳሌ የእኛ ድርጅት አልፋ ሰርተፊኬሽን ኮንሰልታንሲ ዕውቀት ላይ ነው የሚሠራው፡፡ የዕውቀት ሽግግር ነው ለውጥ የሚያመጣው፡፡ በዚህ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ኢንሹራንሱም ሆነ ባንኩ በመደበኛው መስክ ራሱ የሰው ኃይል እጥረት እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ የሰው ኃይሉ የበዛ ቢመስልም፣ አንድን ሥራ አስኪያጅ አሥር ቦታ ታገኘዋለህ፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ቦታ ላይ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላ ቦታ ላይ፡፡ እርግጥ ነው የሰው እጥረት አለ፡፡ ማብቃት ላይ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ድክመት አለብን፡፡ መሠራትም ያለበት እዚህ ላይ ነው፡፡ በዋናነትም ወደ ዕውቀት የሚያሸጋግሩ ተቋሞች መብዛት አለባቸው፡፡ በመሠረታዊነትም ሊገለጹ የሚችሉ የዕውቀት ደረጃዎች አሉ፡፡ እነዚህን ወደ ከፍተኛው የዕውቀት ደረጃ ማድረስና ማብቃት እንችላለን የሚለው ጉዳይ በቀጥታ ሊሠራበት የሚገባ ነው፡፡ በአልፋ ሰርተፊኬሽንና ኮንሰልታንሲም እየሠራን የምንገኘው እዚህ ላይ ነው፡፡ በተለይም ከወለድ አልባው ኢንሹራንስና ባንክ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ይኼ ብቻውን ግን በቂ አይደለም፡፡ እንደ አልፋ ዓይነት ከሃያ በላይ ተቋሞች ያስፈልጋሉ፡፡ በቂ ሀብት አለ፣ ሰዎች ለማሠልጠን ዝግጁ ናቸው፣ የሰው ኃይሉም ዝግጁ ነው፡፡ የሚያሠለጥኑና ጥራት ያለው የሰው ኃይል ማብቃት የሚችሉ በተለይም አገር በቀል ተቋሞች በዚህ ደረጃ የሉም፡፡ እነዚህ አገር በቀል ድርጅቶች ግን በተጠናከረ መልኩ ሊስፋፉ ይገባቸዋል፡፡ በዘርፉ ዕውቀት ያላቸው በርካታ ታላላቅ ሰዎችም በጡረታ ላይ ወይም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ ናቸው፡፡ እነርሱ ወደዚህ ዘርፍ ቢመለሱና ዕውቀታቸውን ቢያሸጋግሩ የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ችግሩ ያለው አሁን ራሳቸው ባንኮች ወይም ኢንሹራንሶች ላይ ብቻ አይደለም፡፡ መደበኛው ባንክ ላይ ለምሳሌ ብሔራዊ ባንክ በጊዜ ሒደት የራሱ የሆነ ብቃት አዳብሯል፡፡ እስላሚክ ባንክና ታካፉል ላይ ግን ብሔራዊ ባንክ ያወጣቸውን መመርያዎች በሼሪዓ ሕግ አግባብ መሠራቱን ለማረጋገጥ ተቆጣጣሪው መሥሪያ ቤትም ለዚህ የሚሆኑ የራሱ ባለሙያዎች ያስፈልጉታል፡፡ እዚህ አካባቢ ችግር አይኖርም?
አቶ ኢብሳ፡- ትልቁ ክፍተት እንዲሁም እዚያ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም ሕጉን አውጥቶታል፡፡ ለምሣሌ እንደ አማራጭ ሐሳብ ወይም እንደ መፍትሔ የሸሪዓ አማካሪ ቦርድ በባንኩም ሆነ በኢንሹራንሱ አሉ፡፡ በዘርፉ ዕውቀት ግን በደንብ በሥልጠና መደገፍ አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡- እስካሁን ምን ሠርታችኋል?
አቶ ኢብሳ፡- ይህ ድርጅት በዋናነት የሚሠራውም አቅም ግንባታና ቴክኖሎጂ ላይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በተካፉል መስክ የመሠማራት ፕሮጀክቶችን ለተወሰኑ ኢንሹራንስ ተቋሞች ሠርተንላቸው፣ ሥልጠና ሰጥተን በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገቡ ናቸው፡፡ በዕውቀት ደረጃ ሥልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ ሠራተኛ እናሠለጥናለን፣ ፕሮጀክቶቻቸውና ፖሊሲዎቻቸውን እንቀርፃለን ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ከዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት አንፃር ሊያመጣ የሚችለው እንዴት ይመዘናል? እንዲያውም በሁለትና በሦስት ዓመት ውስጥ የባንክና ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚከፈት ይሆናልና በዚህ መልክስ የባንክና ኢንሹራንስ ተቋማት ሊያበረክቱ የሚችሉት ድርሻ ምንድን ነው?
አቶ ኢብሳ፡- አሁንም እኮ ወደዚያው እየመጣን ነው፡፡ ካፒታላችንን እናሳድግ ዕድገታችንን እናስቀጥል ማለት ከዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪው ጋር ተወዳዳሪ የሆኑ ባንኮችንና ኢንሹራንሶችን መፍጠር ነው፡፡ ይኼንን ለማምጣት ግን አሁን ያሉት ተቋማት ተበታትነው ከሚሠሩ ይልቅ ሰብሰብ ብለው አቅማቸውን አደርጅተው በጋራ ጠንከር ያለ ከዓለም ጋር መወዳደር የሚችል ሐሳብና አቅም እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የውጭ ኩባንያዎች መግባታቸው አይቀርምና ለዚያ መዘጋጀት የግድ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከገለጻዎ መረዳት እንደቻልኩት ከባድ ችግር ተደርጎ ሊታይ የሚገባው የሰው ኃይል ማነስ ነው፡፡ ምንድን ነው መደረግ ያለበት? ሰውን ማብቃት እንዴት ነው የሚቻለው? እንዲያውም በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ተቋማቱ ከዓመታዊ ትርፋቸው የተወሰነ መጠን ለዚሁ ጉዳይ እንዲያውሉ ያዛል፡፡ ይህስ በአግባቡ ተግባራዊ ሆኗል ወይ? መሆን ያለበትስ ምንድን ነው?
አቶ ኢብሳ፡- እነዚህ የፋይናንስ ድርጅቶች እንደ ሌላ ድርጅቶች አይደሉም፡፡ የሰው ኃይላቸውን ለማብቃት የትርፋቸውን ሁለት በመቶ ለሥልጠና እንዲያውሉ ይገደዳሉ፡፡ እዚህ ላይ ነው ችግር ያለው፡፡ ተቋማቱም በተፈቀደላቸው መጠን መጠቀማቸውን በሚመለከት ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል፡፡ ለአገር ፋይዳ ያለው ሥራ እየተሠራ ነው ወይ? ሌላው ዘርፍ ምናልባት ለሥልጠና በቂ የሆነ ሀብት የለኝም ማለት ይችላል፡፡ ፋይናንሶች ግን አላቸውም፣ ሕግም ያስገድዳቸዋል፡፡ አጠቃቀማቸው አግባብ መሆኑንና ማብቃት ላይ ያለባቸውን ክፍተት የፋይናንስ ተቋማት ቀውስ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢንዱስትሪውን በጠቅላላ ለመቀየር ምን መደረግ አለበት? በመንግሥት ሆነ በግል ባንኮች ምን ሊደረግ ይገባል? ከአክሲዮን ባለሀብቶች ጀምሮ ምን ይጠበቃል? በአገራችን የባንኩ ዘርፍ አትራፊ ነው ስለሚባል ባለአክሲዮኖች ትርፍ ማግኘት አለባቸው ተብሎ ነው ትኩረት የሚደረገውና ስለዚህም ሁሉንም ባለድርሻ አካል ትኩረት ባደረገ መልኩ መደረግ የሚገባው ምንድን ነው?
አቶ ኢብሳ፡- የዚህ ሁሉ ባለቤት መሆን ያለበት ሕዝብ ነው፡፡ መንግሥት መመርያ ያወጣል፣ በአግባቡ ተግባራዊ መደረጉን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፡፡ የአገሪቱን የትርፋማነት አቅጣጫ ያሳያል፡፡ ባለአክሲዮኖች ትርፋማ እንዲሆኑ፣ ሠራተኞቹ እንዲያድጉና ድርጅቱም ዕድገቱ የተጠበቀ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ሕዝብ እንደ ሕዝብ አስፈላጊነቱን መረዳት አለበት፡፡ ስለዚህም አንዱ ከአንዱ ተነጣጥሎ የሚታይበት ሳይሆን ሕዝብ፣ መንግሥት፣ ባንክ፣ ኢንሹራንስና ሠራተኞችም ሆኑ ባለአክሲዮኖች የዘርፉ አጋር ናቸው፡፡ ተነጣጥለው የሚሠሩ አይደሉም፡፡ መሆን ያለበትም ግንዛቤን ማሳደግ፣ ማስተማር በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማስቻል ተገቢ ነው፡፡ የባንኮች፣ የኢንሹራንስ ማኅበሮችና ባለአክሲዮኖች አሉ፣ መንግሥት አለ፡፡ እነዚህ እየተናበቡ መሠራት አለባቸው፡፡ በእነዚህ በአራቱ መካከል ያለው ክፍተት የምንፈልገው ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎናል፡፡ ሆኖም በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ በዘመቻ መልክም ቢሆን ጥቅሙን ማሳየት አለበት፡፡ ባለአክሲዮኖችን ለማስረዳት ብቻ ተብሎ ደግሞ ወደማይሆን ውድድር ውስጥ አለመግባት ያስፈልጋል፡፡ በኢንሹራንስ ዘርፍ ትልቁ ውድቀት የዓረቦን ዋጋ ነው፡፡ ዝቅተኛውን መጠን ማኅበሩ ማስቀመጥ አልቻለም፡፡ ይህ እስካልመጣ ድረስ ኪሳራ ነው፡፡ ማኅበሩ ዝቅተኛ የዓረቦን ዋጋ የሚባለውን እንዲያፀድቅ ካላደረገ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያ በጠቅላላ ፈተና ውስጥ ይገባል፡፡ ስለዚህ ማኅበሩ ጠንከር ማለት አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ብዙ ጥቅም ይሰጣል የሚባለውና ሌሎች ዓለማት በስፋት የሚጠቀሙበት የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የቀዘቀዘበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ኢብሳ፡- ማኅበረሰቡ ላይ አልተሠራም፡፡ በዕውቀት ላይ አልተሠራም፡፡ ሌላው ትልቁ ነገር የትምህርት ማዕቀፉ ውስጥ የለም፡፡ ስለገንዘብ አጠቃቀም፣ የኢንሹራንስ ጠቀሜታ የሚገኘው ከትምህርት ነው፡፡ ሰዎች ኢንሹራንስ እንደሚያስፈልጋቸው የሚገልጽ ትምህርት የለንም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ መሠረታዊ ጉዳዮች የትምህርት ሥርዓት ውስጥ እስካልገቡ ድረስ አይሆንም፡፡ አገር የምትለወጠው በትምህርት ነው፡፡ ከታች ጀምሮ መሠራት አለበት፡፡ እዚህ አገር እኮ ግድ ካልሆነበት ሰው ኢንሹራንስ አይገባም፡፡ በአጠቃላይ የሕይወት ሆነ የሕይወት ነክ ኢንሹራንስ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ለመገኘት አንዱና መሠረታዊው ችግር በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ያለመሆኑና የፋይናንስ ዘርፉን የሚመለከት ትምህርት በትምህርት ሥርዓት ውስጥ አለመሰጠቱ ነው፡፡ አሁን በሚዲያ የልጆች ቁጠባ ተብሎ ማስታወቂያ ይነገራል፡፡ ግን ስለመቆጠብ ጥቅም ልጆች እኮ አልተማሩም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ነገሮች መታሰብ አለባቸው፡፡ ሌላው ጉዳይ በኢንዱስትሪ ውስጥ የዋጋ ሰበራ እንዲቀር የኢንሹራንስ ማኅበር መሥራት አለበት፡፡ ሕጉ እንዲወጣ በማድረጉ ረገድ ሊሠራ ይገባል፡፡ ኅብረተሰቡ ስለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ያለው ግንዛቤ እንዲጨምር መሠራት አለበት፡፡