Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የታሰሩ ጋዜጠኞች የእስር ትዕዛዝ ካልቀረበባቸው ባፋጣኝ ሊለቀቁ ይገባል አለ

ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የታሰሩ ጋዜጠኞች የእስር ትዕዛዝ ካልቀረበባቸው ባፋጣኝ ሊለቀቁ ይገባል አለ

ቀን:

መንግሥት ሆቴሎችን ጨምሮ ከ80 በላይ ጭፈራ ቤቶች መዝጋቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በእስር ላይ የሚገኙ የኢትዮ ፎረምና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሠራተኞች አያያዝ ሕግን የተከተለ ሊሆን እንደሚገባ በመጥቀስ፣ የፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ ካልቀረበባቸው በአፋጣኝ ሊለቀቁ ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡

በፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ከሁለት ሳምንት በፊት በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ የሚገኙትን በቃሉ አላምረው፣ ያየሰው ሽመልስ፣ ፋኑኤል ክንፉ፣ አበበ ባዩ፣ መልካም ፍሬ ይማም፣ ፍቅርተ የኑስ፣ ዊንታና በርሄና ምሕረት ገብረ ክርስቶስን ጨምሮ 21 የኢትዮ ፎረምና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሠራተኞች አያያዝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በቅርበት ሲከታተል መቆየቱን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከእነዚህ ታሳሪዎች መካከል ሦስቱንና አንድ ሌላ ታሳሪን ጨምሮ አራት እስረኞች ማክሰኞ ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ መለቀቃቸውን፣ ቀሪዎቹ ታሳሪዎች በወንጀል ስለተጠረጠሩ ለምርመራ ሥራ በእስር እንዲቆዩ በፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ትዕዛዝ መሰጠቱን ፖሊስ እንዳስታወቀው ጠቁሟል፡፡

ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ እስከ ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ድረስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አለማየቱን፣ ታሳሪዎቹን ለመጎብኘት አለመቻሉን፣ እንዲሁም ታሳሪዎቹ ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከጠበቆቻቸው ጋር ሳይገናኙ ከአንድ ሳምንት በላይ መቆየታቸው እጅግ የሚያሳስበው እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ስለሆነም የፌዴራል ፖሊስና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት አሁንም በእስር ያሉ የአውሎ ሚዲያና የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞችና ሠራተኞች በሙሉ በአፋጣኝ ከቤተሰቦቻቸውና ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲገናኙ እንዲያደርጉ፣ የታሳሪዎቹን የእስር ሁኔታ ሕጋዊነት እንዲያስረዱና ከፍርድ ቤት የተሰጠ የእስር ትዕዛዝ ካልቀረበ በስተቀር ታሳሪዎቹ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ ኢሰመኮ አሳስቧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በመሀል አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ የአገርን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ዘፈኖችን በመክፈት፣ የኅብረተሰቡን ሰላም በመንሳትና የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን የበለጠ እንዲተላለፍ ምክንያት ሆነዋል ያላቸውን ሀርመኒና ካሌብ ሆቴሎችን ጨምሮ ከ80 በላይ ሆቴሎችና የጭፈራ ቤቶች መዝጋቱን የቦሌ ክፍለ ከተማ አስታወቀ፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ለሪፖርተር እንደገለጸው ሆቴሎችና ጭፈራ ቤቶቹ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተዘጉት የንግድ ፈቃዳቸው ከሚፈቀድላቸው ስምሪት ውጪ በራቁት ጭፈራ ቤትነት፣ ከፍተኛ በሆነ የድምፅ መጠን ዘፈኖችን በመልቀቅ፣ የአገርን ክብር ዝቅ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን ጭፈራ ቤቶች ውስጥ በመረጋገጥ፣ እንዲሁም የአገር መከላከያ ሠራዊትን ክብር የሚነኩ ዘፈኖች በማሰማታቸው ነው፡፡

ካሌብ ሆቴል፣ ሀርመኒ ሆቴል፣ “XO” ጭፈራ ቤትና ጄይን ክለብ የመሳሰሉትን በዋነኝነት የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ሲያካሂደው የነበረውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ለጥሞና ጊዜ በማለት የተኩስ አቁም ማድረጉን ተከትሎ፣ ‹‹ትግራይ አሸነፈች›› በማለት የአገርን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ዘፈኖች በከፍተኛ የድምፅ መጠን በመክፈት ሲያስጨፍሩ እንደነበር የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ፊልሞን ጋሻው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ይህንን ድርጊት የፈጸሙ ሆቴሎችና ጭፈራ ቤቶች እንዲታሸጉ መንግሥት ኃላፊነት ስላለበት፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይጠብቅ ወይም ከክፍለ ከተማው ትዕዛዝ ሳይመጣለት፣ ከንግድ ሕጉ ውጪ በተገኙት ላይ ዕርምጃ መውሰዱን አቶ ፊልሞን ገልጸዋል፡፡

‹‹ለዚህች አገር መከታ የሆነውን የአገር መከላከያ ሠራዊት ክብር የሚነኩ ዘፈኖች በመክፈትና የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ በመርገጥ፣ እንዲሁም የአንድ ክልል ባንዲራ በማውለብለብ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ስግብግብ ነጋዴን ከሌላው ለይተን አናየውም፤›› ሲሉ አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡

የታሸጉት ቤቶች መንግሥት የአገር መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ እንዲወጣ ማድረጉን ተከትሎ፣ ‹‹የትግራይ እናት አልቅሰሽ አትቀሪም›› የሚሉና መሰል ዘፈኖችን በጭፈራ ቤቱ በማስከፈትና በራቁት በማስጨፈር፣ ብር በመበተን በከፍተኛ ሁኔታ የነዋሪውን ሰላም ሲያውኩ እንደነበር አክለው ገልጸዋል፡፡

አንዳንዶቹ የጭፈራ ቤቶች ሕወሓትን በገንዘብ ይረዱ የነበሩ እንደሆኑ የገለጹት አስተዳደሪው፣ ‹‹በዚህም ይህን ኃይል የሚደግፍን አካል የገንዘብ ምንጭ እናደርቃለን፤›› ብለዋል፡፡

የተዘጉ ቤቶችን በተቋቋመው ግብረ ኃይል መሠረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ውሳኔ የሚተላለፍ እንደሆነ አቶ ፊልሞን  ተናግረዋል፡፡

በወረዳው አስተዳዳር አማካይነት የጭፈራ ቤቶቹ ከተዘጉ በኋላ፣ በአካባቢው ይታዩ የነበሩ የዝርፊያና የስርቆት እንቅስቃሴዎች መቆማቸውን አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ሥፍራዎች በርካታ የመጠጥና የጭፈራ ቤቶች ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጸምባቸው ነበር ተብለው፣ በሚገኙባቸው ክፍላተ ከተሞች ወረዳዎች አማካይነት ተመሳሳይ ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

በተመሳሳይ ቀን በፒያሳ፣ በካዛንችስና ሌሎችም አካባቢዎች የሚገኙ መዝናኛ ቤቶች መታሸጋቸውንና ዘርን መሠረት ባደረገ መልኩ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች መታሰራቸውን፣ የታሰሩትም ከአዲስ አበባ ውጪ መሆኑንና ፍርድ ቤት ካለመቅረባቸው በተጨማሪ የሕግ አማካሪዎቻቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን እያገኙ እንዳልሆነ ሰሞኑን በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በመሠራጨት ላይ ነው፡፡ ይህንን በሚመለከት ሪፖርተር የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...