ኢትዮጵያና ኤርትራ የእግር ኳስ ጨዋታ ካደረጉ ሩብ ምዕት ዓመት ያህል አስቆጥረዋል፡፡ በ1990 ዓ.ም. ሁለቱ አገሮች ወደ ጦርነት ከመግባታቸው ቀደም ብሎ፣ ኤርትራ ከመገንጠሏ በፊት የኤርትራ ክለቦች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ሻምፒዮና ላይ ይሳተፉ ነበር፡፡
በ2010 ዓ.ም. ሁለቱ አገሮች ዕርቅ ማውረዳቸውን ተከትሎ የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይከናወን ቆይቷል፡፡ ከ20 ዓመት በላይ የዘለቀው የሁለቱ አገሮች በስፖርቱ ዓለም አለመገናኘት፣ ዘንድሮ ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ እግር ኳስ ውድድር መታደስ ችሏል፡፡
በኢትዮጵያ አዘጋጅነት እየተከናወነ ባለው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን በባህር ዳር ከትሟል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ብሔራዊ ቡድንም በአንድ ቋት ሥር ተመድበዋል፡፡ ተጋባዧዋን ዴሞክራቲክ ኮንጎ ጨምሮ ዘጠኝ የምሥራቅና የመካከለኛው የአፍሪካ አገሮች ተሳታፊ ናቸው፡፡ ዑጋንዳ፣ ታንዛኒያ እንዲሁም ተጋባዧ ዴሞክራቲክ ኮንጎ በምድብ ሀ፤ ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲና ኤርትራ ምድብ ለ እንዲሁም ጂቡቲ፣ ደቡብ ሱዳንና ኬንያ በምድብ ሦስት ላይ ተቀምጠዋል፡፡
በብስክሌት፣ በእግር ኳስና በአትሌቲክስ የጎላ ተሳትፎ ያላት ኤርትራ፣ የመጀመርያ የሴካፋ ተሳትፎዋ እ.ኤ.አ. በ1999 አድርጋለች፡፡ ከዓመት የሴካፋ ተሳትፎ በኋላ በካፍና ፊፋ በአባልነት ተመዝግባለች፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ በሴካፋ ውድድር ታሪኩ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ መቻሉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ የኤርትራ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን በሚሳተፍባቸው ውድድሮች ላይ ተጫዋቾች ከቡድን ውስጥ ተለይተው ሲጠፉም አብሮ ይነሳል፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራ ዕርቅ ማውረዳቸውን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ ቡና ኤርትራዊውን ተከላካይ ሮቤል ተክለ ሚካኤልን ማስፈረሙ ይታወሳል፡፡ በባህር ዳሩ ውድድር በርካታ የኤርትራ ተጫዋቾች በኢትዮጵያ ክለቦች መልማዮች ዕድል ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በውድድሩ የበላይነት ያላት ዑጋንዳ አሁንም ከፍተኛ ግምት ቢሰጣትም በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ትልቅ ግምት አግኝቷል፡፡
በውድድሩ 17 ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን፣ የየምድባቸው አንደኛ የሚሆኑ ቡድኖች በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያልፋሉ፡፡ ጨዋታዎቹ የቴሌቪዥን ሥርጭት ያገኛሉ ተብሏል፡፡
ጨዋታውን ለመዳኘት ሁለት ኢትዮጵያውያን ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘውና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት ተመርጠዋል፡፡