በገነት ዓለሙ
አንድ ‹‹ዕዳ አለቀ››፡፡ የምርጫው ዕዳ አልቋል፡፡ በዚህ ረገድ በዚህ ወሳኝ የምርጫ ማካሄድ ረዥም ጊዜ የወሰደ ውዝግብ ውስጥ፣ ‹‹ዕዳው አያልቅም›› የምንለው፣ እንደዚያ እያልን የምናንጎራጉርለት የምርጫ ጉዳይ የለም፡፡ ይህንን መነሻዬንና መንደርደሪያዬን ግን በደንብ አድርጌ ላጥራ፣ ላብራራ፡፡
የምርጫው ዕዳ አልቋል፣ ስለዚህም አንድ ዕዳ አለቀ ስል ከዚህ በኋላ ምርጫ የለም፣ ምርጫ ቦርድ የሚሠራውም ሆነ የሚያስበው ሥራ የለውም ማለትም ሆነ የሚያሳስብ፣ የሚያንገበግብ የምርጫ ጉዳይ የለንም ማለት አይደለም፡፡ ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ሐምሌ የመጀመሪያ ሳምንት ድረስ የነበረው የምጥ ጊዜ ቢረሳ፣ ሌላው ቢቀር ለጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ የያዝንለት በሶማሌ ክልል፣ በሐረሪ ክልል (ሙሉ በሙሉ)፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በከፊል፣ እንዲሁም የውሳኔ ሕዝብን አስመልክቶ የሚካሄደው ምርጫ ገና የቤት ሥራችን ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምፅ በተሰጠባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥም ቢሆን፣ በሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የውጤት መግለጫ መሠረት ገና ‹‹ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንባቸው›› የምርጫ ክልሎች እንዳሉና ብዛታቸውም አሥር ለተወካዮች ምክር ቤት፣ ለክልል ምክር ቤት ደግሞ ሰባት መሆኑ ተነግሯል፡፡ ይህን የመሳሰሉ ገና ያላለቁ፣ የማጠናቀቅና የማጥራት ሥራ የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉብን፡፡
አሁንም ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ምርጫ 2013 ውስጥ የገባነው የመጀመሪያውን የድኅረ ለውጥና የሽግግር ውስጥ ምርጫ ያደረግነው፣ በዚህ ምርጫ አማካይነት የአገሪቱን ሕዝቦች ሉዓላዊነት መወከል የሠመረለትም ሆነ ከናካቴውም የሚችል ሪፐብሊክ ማደራጀት ይዋጣልናል ብለን አይደለም፡፡ የምርጫው ዓላማና ግብ ከዚያ በፊት ዴሞክራሲንና የዴሞክራሲን ንጣፍ ማደላደል ነው፡፡ ለየትኛውም ቡድን ሳይወግን የሚያገለግል አውታረ መንግሥት የማነፅ ሥራ ውስጥ መግባትን ማለማመድ፣ እዚህ ዓይነት ዘርፈ ብዙ የማሻሻያ ሒደት ጋር መተዋወቅን ማፍለቅለቅ ነው፡፡ መንግሥትን በምርጫና በአማራጭ ፓርቲ/ፓርቲዎች መቀየር፣ በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ምክር ቤቶችን በምርጫ ማደራጀት የሚቻለው የሕዝቦች መራጭነት፣ ሿሚነትና ተቆጣጣሪነት እውነት የሚሆነው፣ ‹‹በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው›› የሚለው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌም ሆነ የአፍሪካ ኅብረት መርህ ትርጉም ያለው፣ የሚገዙትና የሚጠብቁት ሕግ የሚሆነው መንግሥታዊ አውታራት ከሁሉም በላይ ደግሞ የፀጥታና የደኅንነት አውታራት ከፖለቲካ ቡድን መዳፍ ነፃ ሲሆኑ ነው፡፡
በዚህ የለውጥና የሽግግር ምዕራፍ ውስጥ፣ ለየትኛውም ቡድን ሳይወግን የሚያገለግል አውታረ መንግሥት የማነፅ ሥራ ውስጥ መግባትን ከሌሎች መካከል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሞካሪነት፣ ተሞካሪነት፣ እንዲሁም የማይናቅ መከራ አማካይነት ተዋውቀናል፡፡ ቀላል ሙከራ፣ ቀላል መከራም አልነበረም፡፡ ምርጫ ቦርድ ራሱ ብዙ ሙከራና መከራ ውስጥ ገብቷል፡፡ ራሳቸው ከፖለቲካ ቡድን ተፅዕኖ/መዳፍ ነፃ መውጣት፣ ትግልና እነፃ ውስጥ መግባት ካለባቸው ሌሎች አውታረ መንግሥታትና የዴሞክራሲ ተቋማት ጋር ተላግቷል፡፡ በሐሳብ ተለያይቷል፡፡ ምርጫውን በማስፈጸም ሒደት ውስጥ ላጋጠሙ እንቅፋቶች፣ ተቃውሞዎችና አደጋዎች ተጋልጧል፡፡ የዚህ ምርጫ ዓላማና ግብ ተደጋግሞ እንደተገለጸው የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አሁኑና በአንዴ አምጦ መውለድ ሳይሆን፣ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የሚዲያ ተቋማትንም አካቶ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ለዘመናት የጎደለውን ማሟላት ነው፡፡ ለየትኛውም ቡድን ሳይወግን የሚያገለግል አውታረ መንግሥት ማቋቋምና ማነፅ፣ ሥራ ውስጥ ገብተናል፡፡ ምርጫውም ገለልተኛ የመንግሥት አውታራትን የማነፅ ሥራ ውስጥ መግባት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጃችንን ይዞ አስጎብኝቶናል፡፡
የምርጫው ውጤት በተገለጸበት ዕለት ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በነበረው ሥነ ሥርዓት ላይ የሰማናቸው ንግግሮች ይህንን የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ያሉትን ሰምተናል፡፡ ምርጫ ቦርድ መደበኛና የዕለት ተዕለት ሥራውን ሲሠራ፣ ሥራውን ሲሠራ ብቻ ገንዘብ ያለውን፣ የአገር ገንዘብና ሀብት የሚያገኝን፣ ባለመሣሪያን፣ ባለጠመንጃን እንደሚያስቀይም ነግረውናል፡፡ ሚዲያው በተለይም የመንግሥት ሚዲያው፣ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ክሳድ ወይም አንገትጌ ላይ ሌት ተቀን ከማይለየው ማይክራፎን ጋር ያሳያቸውን መከራ በግልጽ ተናግረዋል፡፡ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት (ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ) በምርጫው ውጤት ይፋ ማድረጊያ ቀን የክብር እንግዳ ሆነው እንዲገኙ የተደረገላቸውን ግብዣ ተቀብለው የመጡት ሳያወላውሉ፣ ሳያመነቱ እንዳልሆነ የነገሩን በገደምዳሜ አይደለም፡፡ በግልጽና በዝርዝር ነው፡፡ ለየትኛውም ቡድን ሳይወግን፣ ተለጣፊ ሳይሆን፣ ሁሉንም በገለልተኛነት የሚያገለግል አውታረ መንግሥት የማነፅ ሥራ ውስጥ የገባንበትን ይህንን ተልዕኮ የእሳቸው በእንግድነት መገኘት አያበላሸውም ወይ ብለው ጠይቀው፣ በዚህ ጥያቄ አማካይነት ራሳቸውን ሞግተው ነው፡፡ እነዚህ ከላይ የጠቃቀስናቸው ምሳሌዎች የትልልቅ ነገሮች ጅምር ዕርምጃዎች፣ የተመሳሳይ ትልልቅ መጪ ነገሮች ማሳያዎች ናቸው፡፡ ከማጡ፣ ከአረንቋው ገና አላወጣንም፡፡ እንደዚያ ያለ አረንቋና ጭቃ ውስጥ ግን የምንኖርና ከዚያም መውጣት ያለብን መሆኑን ግን በቁርጠኝነት ያሳያሉ፡፡
ከዚህ ጋር የሚካሄደውና ይህንን የመሳሰለው በብዙ ከበባ፣ በብዙ ጠንቅ፣ በብዙ ጠላት የተወጠረው ሽግግር ውስጥ የሚከናወነው የለውጥ ሥራችን ገና ይቀጥላል፡፡ ያለቀለትም፣ ተከፍሎ ያበቃለትም ዕዳ አይደለም፡፡ ምርጫ ቦርድን ራሱን፣ ከምርጫ ቦርድ ጋር አብረው የሚሠሩትን መንግሥታዊ የሥልጣን አካላትና ባለሥልጣናት ጭምር እንደ ሕገ መንግሥዊ ፍጥርጥራቸው ገለልተኛ አድርጎ እንደገና የመገንባትና ከሕግ በላይ ለመሆን በማያስችልና በማያመች ለውጥ ውስጥ እንዲገቡ የማድረጉ ሥራ ግን ገና ጅምር ላይ ነው፡፡ ገና ጨቅላ ነው፡፡ አዛላቂ ትግልና ርብርብ የሚጠይቅ የአንድ ምርጫ፣ ለዚያውም የአንድ የድኅረ ለውጥ የመጀመርያ ምርጫ ብቻ ተልዕኮ አይደለም፡፡
በመግቢያዬ ላይ እንደ ጠቀስኩት ግን ይህ ምርጫ የብዙዎቹ የለውጡ ውስጥ ተቀናቃኞች የፈሪ ዱላና መቃወሚያ ሆኖ ያገለገለውንና ያደናገረውን አንድ የመከራከሪያ አጀንዳ ዘግቷል፣ ወይም ቀይሯል፡፡ ይህ ለውጥ እንዴት እንደ መጣና ለውጡንም ኢትዮጵያና ሕዝቧ እንዴት እንደተቀበሉት እንኳን እኛ አውሮፓም፣ አሜሪካም፣ ዓለም አቀፋዊ ኅብረተሰብም ያውቃል፡፡ ዓብይ አህመድ በለውጡ መሪነታቸው የኖቤል የሰላም ሽልማት ያገኙት መፈናቀልም፣ መገለልም፣ በመብት መንጓለልም፣ መገደልም በነበረበት በለውጡ ውስጥ ነው፡፡ የለውጡም ዓላማ አሁኑና ወዲያውኑ ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ሕዝባዊ መንግሥት በአዋጅ ለማቋቋም የተሻለ ሕገ መንግሥት ለኢትዮጵያ ‹‹ለመስጠት›› ወዘተ አይደለም፡፡ የለውጡ ዋና ዓላማና ግብ ባለው ሕገ መንግሥትና የእሱም ውላጅ በሆኑ ሕጎች ውስጥ መኗኗርን ማለማመድ፣ የመንግሥት የሥልጣን አጠቃቀምን ባለው ሕግ ውስጥ መቃኛ የተበጀለት ማድረግ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የመንግሥት የሥልጣን አያያዝንና በሥልጣን ላይ መቆየትን ሥርዓታዊ ማድረግ ነው፡፡ ለውጡ ሲመጣ ሕገ መንግሥቱን የሚደግፉም፣ የሚቃወሙም ነበሩ፣ አሉም፡፡
ለውጡ ግን ሕገ መንግሥቱን የሚደግፉትም፣ የሚቃወሙትም፣ እንዲለወጥ የሚፈልጉትም መጀመርያ መነሻቸውና ማኮብኮቢያቸው ይኼው ሕገ መንግሥት እንዲሆን ለውጡ ጠየቀ፡፡ በዚህ ውስጥ ብዙ መፈነካከር ቢኖርም፣ በለውጥ ኃይሎች መካከል ዋነኛውን ጎላ ያለውን መለያየት ያመጣው በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተደነገገው የየአምስት ዓመት ምርጫ ነው፡፡ ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ›› (አንቀጽ 54/1) እና ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፣ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሄዶ ይጠናቀቃል›› (58/3) የሚሉት የሕገ መንግሥት አንቀጾች እንዴትና በምን ዓይነት ሁኔታ (ውጥረት፣ ውዝግብ፣ ክፍፍል ውስጥ) ለትርጉም እንደቀረቡ የቅርብ ጊዜ፣ የሚያዝያ ወር 2012 ዓ.ም. ትዝታችን ነው፡፡ ከመስከረም 20ዎች በኋላ፣ ወይም ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ በኋላ (ምርጫ ተካሄዶ መንግሥት ካልተመሠረተ) ሕጋዊ መንግሥት የለም ማለት የመጣው፣ በዚህ ምንያትም የተለያየ ዓይነት የመንግሥት አደረጃጀት መላና ‹‹የመፍትሔ ሐሳብ›› ከየአቅጣጫው የተሰነዘረው፣ የመታገያ ምክንያት/አጀንዳ ሆኖ ያገለገለው ከዚህ በኋላ ነው፡፡
እንደገና መልሼ ያነሳሁት ያኔ ዋናውና እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ያናከሰውና ሥልጡን ባለጉዳይና ሥልጡን መድረክ ያላጋጠመው የክርክር ጭብጥ ዛሬም፣ ነገም፣ ትናንትም ጭምር ምርጫ የሚካሄደው አምስት ዓመት እየተቆጠረ ነው? ወይስ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታዎች ስላሟላን ነው የሚለው ነው፡፡ ነበርም፡፡ ለትርጉም የቀረቡትና የተተረጎሙት የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች አሁን ዛሬ የገባንበት ጣጣ ውስጥ ተገፍቶ መግባትን ያህል የሚያላጋ አለመግባባት የሚፈጥሩ አልነበሩም፡፡ ያደግንበትና ብዙ ‹‹የሠለጠንበት›› ሥልጣንና ትክክኛነት፣ እውነተኛት የእኔ ብቻ ማለትና መሠሪ መንገድን የትግል መሣሪያ ማድረግ ለዚህ አብቅቶናል፡፡ አንቀጽ 54/1 ራሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት… በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ›› ብቻ አይልም፡፡ በዚህ ተጎርዶ በቀረበው አንቀጽ ውስጥ በራሱ የሕዝብ ተወካዮች በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ ማለት፣ ሕዝብ እንደራሴያዊ ውክልና መስጠት ይችል ዘንድ ይህን በዋስትናነት የሚያረጋግጥ ሥርዓታዊ መተማመኛ የሚሰጥ የተጨበጠ ነገር ይፈልጋል፡፡ ይህንን መከራከሪያ የሚያጠናክረው በተጠቀሰው ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ ውስጥ ተጎምዶ የቀረው የምርጫ ትርጉም ነው፡፡ አንቀጽ 54/1ን እንዳለ ልጥቀሰው፡፡ ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሁሉ አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ›› ይላል፡፡
እንዲህ ያለ ለውጥና ሽግግር ውስጥ ከተገባ በኋላ ምን ዓይነት መሰናዶ አድርጌ ምርጫ ውስጥ ልግባ? ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ በሚደረግ ሽግግር ውስጥ የመጀመርያው ምርጫ የቀጠሮ ጊዜ ከምን ዓይነት ቅድመ ዝግጅቶች በኋላ ይምጣ ይባላል እንጂ፣ ከዕለታት አንድ ቀን ለይምሰልና ለይስሙላ በተደረገ የአገር ማፈሪያ በሆነ ምርጫ ላይ ተመሥርቶ ‹‹ቀን ቆጥሮ›› ምርጫ ላድርግ ማለት መጀመርያውኑም ትክክል አልነበረም፡፡ አሁንም ምርጫውን 2013 ላይ ስላደረግን ትክክል አይሆንም (ያለፈውን ምርጫ የአገር ማፈሪያ ያልኩት ሱዛን ራይስ የተባሉ ዛሬ የኢትዮጵያ ደመኛ ጠላት የሆኑ ሴትዮ ያኔ 2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከኦባማ ጋር በመጡ ጊዜ በምርጫው መቶ በመቶ ዴሞክራሲያዊነት ላይ ስለሳቁ ሳይሆን፣ ለውጡን ያመጣው በ2007 ምርጫ በ2008 ዓ.ም. መስከረም የተቋቋመው መንግሥት ላይ ኅዳር ወር የተነሳው ተቃውሞ ተስፋፍቶ በመቀጣጠሉ ነው)፡፡
ምርጫውን በብዙ ውጣ ውረዶች ብቻ ሳይሆን፣ አገር ታይቶ በማይታወቅ ውጥረትና ቀውስ ውስጥ በገባችበት ወቅትም ቢሆን መንግሥታዊ አውታራትን ከፖለቲካ ቡድን መዳፍ ውስጥ ነፃ የማውጣት ሥራ እየሠራች ጭምር፣ የማይናቅ ማለፊያ ውጤት ያስመዘገበ ምርጫ አድርጋ አስመዝግባለች፡፡ ምርጫውን ማለፊያ የምለው ብልፅግና የተባለው ፓርቲ ስላሸነፈ አይደለም፡፡ ለውጡንና አገሪቱን የሚመራው ፓርቲ ማሸነፉ ግን አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ የግድ አስፈላጊ ነበር፡፡ የዚህ ምክንያት የብልፅግና ፓርቲን ርዕዮተ ዓለም ወይም ፕሮግራም ወይም የምርጫ ማኒፌስቶ የመውደድ፣ እሱን ከሌሎች በላይ አድርጎ የማምለክ ጉዳይ አይደለም፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ጉድለት ፓርቲዎችን በፕሮግራማቸው አወዳድሮ የእኔ የማለትም ሆነ የመውደድ ፍጥርጥር የሌለው፣ ሥርዓቱ ባለብዙ ፓርቲ ቢባልም (ባለአንድ ፓርቲ የሕግ ድንጋጌን ቢያስቀርም) በተግባር ግን ፓርቲዎች የማይፈኩበት፣ አማራጮች የማይፈልቁበት፣ ወዘተ መሆኑ ነው፡፡ የቡድኖች መንግሥታዊ ገዥነት ከአዲስ፣ ታይቶ ከማይታወቅ፣ ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ የሚመበጭበት አዲስ ምዕራፍ ኢትዮጵያ ውስጥ መከፈትና እሱም መስፋፋትና መፋፋት አለበት ከተባለ፣ በአሁኑ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ለውጡንና ሽግግሩን ከክሽፈትና ከመጨናገፍ ማዳን ዴሞክራሲን ብቻ ሳይሆን አገርን ጭምር የማዳን ሥራ ነው፡፡ የለውጡንና ለውጡን የሚመራው የመንግሥቱን መሪዎች የመምረጥም ጉዳይ አስፈላጊነት ይኼውና ይኼው ብቻ ነው፡፡ በማኒፌስቷቸው የመለከፍ፣ በመሪዎቹ ማንነትና ሰብዕና ፍቅር የመውደቅ ጉዳይ አይደለም፡፡
በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ መራጭ ዝም ብሎና በደመ ነፍሱ ሳይሆን፣ አገር አሁን የምትገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ ገብቶትና አሳስቦት ሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ መርጧል፡፡ ከሁሉም በላይ ምርጫው፣ በተለይም የድምፅ መስጫው ቀን ያላንዳች የፀጥታ ችግር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የግርግር መደገሻ ሳይሆን፣ የለውጡ ተጠናዋቾች የግርታና የጋጋታ አመፅ መነሻ ሆኖ ሳያገለግል እንዲጠናቀቅ አድርጓል፡፡
መራጩ ሕዝብ በዚህ ረገድ ያደረገው የጥንቃቄ ብዛትም በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የሚኖረውን የተቃዋሚ ፓርቲዎች/ግለሰቦች ቁጥርና ስብጥር ላይ ሲበዛ ንፉግ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ሕዝብ በጣም እርግጠኛ ለመሆንና በዳኝነቱና በምርጫው ብልህነት ረገድ ቢሰስትም ገዥውን ፓርቲ ሙጥኝ በማለቱ በኩል መሳሳቱን መርጦ፣ ከገዥው ፓርቲ ከብልፅግና ውጪ ላሉት ፓርቲዎች የሰጠው የመቀመጫ ብዛት ከዚህ በፊት ከነበረው ጋር እንኳን የሚወዳደር አይደለም፡፡ የዚህን የጀርባ ምክንያት ፓርቲዎች፣ በተለይም በምርጫው ውስጥ የተሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ለተለያየ ዓላማ ሊያጠኑት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
ለማነፃፃሪያ ያህል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዚህ በፊት በነበሩት በአምስቱም የምክር ቤት ዘመናት የነበሩትን ጥንቅር የሚሳይ መረጃ ከዚህ ጋር አያይዣለሁ፡፡
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፓርቲዎችና የግል ተመራጭ መቀመጫዎች በአምስቱም የምክር ቤት ዘመናት
ተ.ቁ |
የፓርላማው ዘመናት |
የኢሕአዴግ |
አጋር ፓርቲ |
ተቃዋሚ ፓርቲ |
የግል |
ድምር |
1 |
ከ1988 – 1992 |
490 |
45 |
4 |
8 |
547 |
2 |
ከ1993 – 1997 |
479 |
45 |
10 |
13 |
547 |
3 |
ከ1998 – 2002 |
365 |
45 |
236 |
1 |
547 |
4 |
ከ2003 – 2007 |
500 |
45 |
1 |
1 |
547 |
5 |
ከ2008 – 2012 |
502 |
45 |
– |
– |
547 |
ምርጫው ገና ለጳጉሜን 1 ቀን የተቀጠው ሥራ ቢቀረውም፣ የሰኔ 14 ሥራ ከነበሩት መካከል ወደ ሌላ የምርጫ ቀን ወደ ጳጉሜን 1 ቀን በቀጠሮ ያደረ ቢኖርም፣ በ2014 ዓ.ም. መስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ (መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም.) ላይ መንግሥት የሚያቋቁመው ፓርቲ ከአሁኑ ታውቋል፡፡ በዚህ ምክንያት ከሁሉም በላይ ደግሞ ምርጫው ውስጥ ብቸኛ መልዕክት ሆኖ ጎልቶ የወጣው የመራጩ ሕዝብ ውሳኔ ሕዝብ (ሪፈረንደም) የተለያዩ የእስከ ዛሬ መከራከሪያና መቃወሚያ አጀንዳዎችን አስቀይሯል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ምርጫው ‹‹በጊዜው›› ማለትም ከ2007 ምርጫ ጀምሮ በሚቆጠር የአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ባለመካሄዱ፣ እንደሚደግፋቸው ወገኖች ይህ አሁን ያለው መንግሥት ከመስከረም 2013 ጀምሮ ቅቡልነት (ሌጅትመሲ) የለውም ብሎ በይፋ አቋም ይዞ ባያውቅም፣ በተለይም አንቶኒ ብሊንከንና ይኼው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራው የአገሪቱ የስቴት ዲፓርትመንት አንድ ላይ (ከሌሎችም ጋር አብረውና ተባብረው) በኢትዮጵያና በምሥራቅ አፍሪካ፣ በዚያውም በመላው አፍሪካ አንገት ላይ ጉልበታቸውን የጫኑ ግዙፍና ሌላ ዴሪክ ሾቪን (Derek Chauvin) ሆነው አርፈዋል፡፡ እነ ብሊንከን የሰኔ 14 ሪፈረንደም የተሰጠበትን ሁኔታ ወኔና ቆራጥነት እንዳላየ ማለፍ ባይችሉም፣ በይፋና በአደባባይ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመምረጥ መብት የመገልገል ነፃነት ቢያደንቁም፣ አሁንም ከምርጫው በኋላ ምርጫው የተካሄደበትን/ተካሄደበት የሚሉትን ዳራ ማሳበቢያ አድርገው፣ እውነቱን ለመናገር አርቲ ቡርቲውን ከመቀበጣጠር አልተመለሱም፡፡
ምርጫው ከፍተኛ አለመረጋጋት ባለበት ሁኔታ ነው የተካሄደው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ ተሰሚ (ቮካል) የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ታስረዋል የሚባሉ መከራከሪያዎቻቸውን አርቲ ቡርቲ ያልኳቸው፣ የባጡን የቆጡን ከመቀበጣጠር ለይቼ ያላየኋቸው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች የታሰሩት የምርጫው ቀን ከመቆረጡ ከዓመት በፊት በሰኔ 2012 ዓ.ም. ውስጥ ከሃጫሉ መገደል በኋላና በዚያ ምክንያት የትም ቦታ የትኛውም መንግሥት የማይታገሰው ግድያ/መግደል የትግል መሣሪያ የሆነበት ዘመቻ በመከፈቱ ነው፡፡ ከዚያ ቀደም ባለው የትግል ወቅት ዝም ተብሎ የኖረው ጥቃትና ውድመት ከግድያ ጋር አሁንም የትግል መሣሪያ እሆናለሁ በማለቱ ነው፡፡ ያኔ ይህን ተቃውሞ ትንፍሽ ያለ፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ብሎ የጻፈ ማንም አልበረም፡፡ ከምርጫ ራሳቸውን አገለሉ የተባሉ ፓርቲዎችም ጉዳይ የሚካተተው እዚሁ ትርኪ ምርኪ ሰበብና ምክንያት ውስጥ ነው፡፡ የምርጫው ዕዳ ይህን ያህል ቢያልቅም የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ቀውስ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለዋወጠና ‹‹የቸገረ ነገር›› እየሆነ መጥቷል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡