Thursday, February 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የደኅንነት ሥጋት እንዳለባቸው ተናገሩ

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የደኅንነት ሥጋት እንዳለባቸው ተናገሩ

ቀን:

በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ መታሰር ምክንያት በደጋፊዎቻቸው የተነሳው አመፅ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ሥፍራዎች ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የደኅንነት ሥጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ የፍርድ ቤት ሠራተኛ የሆነው አቶ ኮስሞስ ገብረ ሚካኤል ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በተቀሰቀሰው ሁከት ምክንያት ነዳጅ ማደያዎችና ሱፐር ማርኬቶች የተዘጉ በመሆናቸው፣ ሰዎች የዕለት ጉርሳቸውን ሲያጡ በድጋሚ ቤት ለቤት ዘረፋ እንዳይደረግ ሥጋት ተፈጥሯል፡፡

በደርባን ከተማ በግምት ከ60,000 እስከ 100,000  የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ የገለጹት አቶ ኮስሞስ፣ በአብዛኛው በንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በከተማዋ ከ45,000 በላይ መደብሮች መዘረፋቸውን፣ በኢኮኖሚስቶች ግምት 80 ቢሊዮን ብር (16 ቢሊዮን ራንድ) የሚሆን ንብረት መውደሙን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ኮስሞስ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ሁከት በላይ፣ ኳዋዙሉ ናታል በሚባለው ክልል 80 በመቶ የሚሆኑ መደብሮች መዘረፋቸውን መስማታቸውን አስረድተዋል፡፡

በደርባን ከተማና አካባቢዋ የነዳጅ ማደያዎችና በተለያዩ ሱፐር ማርኬቶች የዕለት ጉርስ ለመሸመት ረዣዥም ሠልፎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አኗኗርና የንግድ እንቅስቃሴ ሦስት ዓይነት መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ኮስሞስ፣ የመጀመርያው በብዛት በችርቻሮ ንግድ በመንደር (ሎኬሽን) የተሰማሩ፣ ሁለተኛው በጅምላ አከፋፋይነት የሚሠሩ፣ እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ በተነሳው አመፅ የተጎዱት በይበልጥ ሞሎች ላይ የሚነግዱ የትልልቅ መደብሮች ባለቤት መሆናቸውንና ከ20 ዓመታት በላይ በንግድ ላይ የቆዩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አንድ መደብር የማይዛቸው ዕቃዎች ከስምንት እስከ አሥር ሚሊዮን ብር እንደሚገመቱ ገልጸው፣ ከኢትዮጵያውያን መደብሮች ንብረታቸው እንደተዘረፈ ተናግረዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ከ15 ዓመታት በላይ የኖሩት አቶ ኮስሞስ፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዜጎቹን ለመጠበቅ ያደረገው እንቅስቃሴ እምብዛም መሆኑን፣ ተንቀሳቅሷል ከተባለም በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ጥንቃቄ አድርጉ የሚል ማሳሰቢያ መስጠቱ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

የናይጄሪያና የሌሎች አገሮች ኤምባሲዎች የዜጎቻቸውን ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጥሩ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግን ለደረሰው ውድመት እንኳን የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ኃላፊነት እንዲወስድ ግፊት አላደረገም ብለዋል፡፡

በደርባን አካባቢ በአነስተኛ ከተማ መኖር ከጀመረ 20 ዓመታት እንዳስቆጠረ የሚናገረው አቶ ፋሲል ሽመልስ፣ በአካባቢው በተነሳው ሁከት ሁለት መደብሮቹ መዘረፋቸውንና አሥር ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማጣቱን ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

አቶ ፋሲል በጠቅላላ ሎኬሽን (መንደር) በሚባለው  ቦታ የኢትዮጵያዊያን መደብሮች መውደማቸውን ገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሱፐር ማርኬቶችና ለዕለት የምግብ ፍጆታ የሚውሉ መገበያያዎች ስለተዘጉ የቤት ለቤት ዝርፊያዎች እንዳይቀጥሉ ሥጋት እንደገባቸው ተናግሯል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ፍሪናኬን ከተማ ነዋሪ የሆነው አቶ በላይ አዳነ (አክቲቪስት) እንደተናገረው፣ በተለይ ሎኬሽን (መንደር) የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ንብረት አሽሽተው ወደ ዋና ከተማዎች መሄዳቸውንና ዘመድ ዘንድ መጠለላቸውን ተናግረዋል፡፡ በግምት 80 በመቶ ያህሉ ንብረት የወደመባቸው የነጮች ትልልቅ ሞሎች መሆናቸውን፣ እንዲሁም ሞሎችን ተከራይተው የሚነግዱ ኢትዮጵያዊያንም እንደ ወደመባቸው ጠቁሟል፡፡

በአጠቃላይ በደቡብ አፍሪካ 250,000 ኢትዮጵያውያን እንዳሉ የሚናገረው አቶ በላይ፣ በአሁኑ ጊዜ እርስ በርስ እየተጋገዙ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

በኳዋዙሉ ናታል፣ በሃውቴን፣ በደርባን፣ በጆሃንስበርግ፣ እንዲሁም በዙሪያቸው በሚገኙ ከተሞችና ሎኬሽኖች (መንደሮች) ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ኤምባሲው፣ ‹‹ከማኅበረሰባችን የሚዲያ ተቋማት፣ ከየአካባቢያችሁ የማኅበረሰብ አደረጃጀት መሪዎች፣ እንዲሁም ከአገሪቱ የመንግሥት አካላትና ከሚዲያ ተቋማት በየጊዜው የሚሰጡ መረጃዎችንና መመርያዎችን በንቃት እንድትከታተሉ፤›› ብሏል፡፡

በየአካባቢው ከሚገኙ የሌሎች አገሮች ዜጎች፣ የታክሲ ማኅበራት፣ የፀጥታ አካላትና አመፁን ለመከላከል ከሚጥሩ ሌሎች አደረጃጀቶችና አካላት ጋር በመቀናጀትና በመተባበር ራሳቸውን ከጉዳቱ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ብሏል፡፡

በጉዳቱ ሰለባ የሆኑትን ዜጎችን ለማስጠለል፣ የማፅናናትና መልሶ ለመርዳት እየተደረገ ላለው ጥረት ኤምባሲው አመሥግኖ፣ የእርስ በርስ የመደጋገፍና የመረዳዳት ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡

የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ መታሰራቸው ከተሰማ በኋላ በዋናነነት በትልልቅ የንግድና የኢኮኖሚ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ዝርፊያና ቃጠሎ መፈጸሙ፣ ይህም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ውድመት እንዳስከተለ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በስፋት ዘግበዋል፡፡ ከሁከቱ ጋር በተገናኘ ከ100 በላይ ሰዎች እንደ ሞቱና 1,700 የሚደርሱ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰምቷል፡፡

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አመፁን ለማስቆምና ዋነኛ ጠንሳሾችን ሕግ ፊት ለማቅረብ፣ 25,000 የሚጠጋ ሠራዊት ማሰማራቱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...