በህዳሴ ግድቡ ላይ ያለውን ውዝግብ ሊፈታ የሚችለው ውይይት ብቻ እንደሆነ ሱዳን ገለጸች
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታ ምክር ቤት አባላት በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ውዝግብ፣ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በውይይት እንዲፈታ ቢሉም፣ የግብፅ መንግሥት ግን አሁንም ኢትዮጵያ የግብፅን የውኃ ድርሻ እስካልነካች ድረስ ብቻ ግድቡን ለልማት ማዋል እንደምትችል እየገለጸ ነው።
የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ ኤል ሲሲ ባለፈው ሐሙስ ሐምሌ 8 ቀን ባደረጉት ንግግር ‹‹ኢትዮጵያውያን የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለልማታቸው እንዲያውሉት እንሻለን፡፡ የኢትዮያውያንን የኑሮ ሁኔታ እንዲሁ እንዲሻሻል እንሻለን፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
መንግሥታቸውና አገራቸው ግብፅ ከኢትዮጵያና ሱዳን ባለፈ የመላው አፍሪካ ሕይወት እንዲሻሻል ከመሻት ባለፈ ድጋፍም እንደሚያደርጉና ይህንንም ለሁለቱም አገሮች ጭምር እንዳሳወቁ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለልማታቸው እንዲያውሉት እንሻለን። ይህ የሚሆነው ግን በአንድ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ይህም የግብፅ የውኃ ድርሻ የማይነካ ከሆነ ብቻ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህን የተናገሩት በሃያ ከሪማ ብሔራዊ ኮንፈረንስ ላይ ባደረጉት ንግግር ሲሆን፣ የግብፅን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር የማይታለፍ ቀይ መስመር እንደሆነም ገልጸዋል።
ግብፅ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ብዙ አማራጭ አላት ያሉት ፕሬዚዳንቱ አማራጮቹን እንደ ሁኔታዎች አስፈላጊት መጠቀም ይገባልም ብለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ እየገነባች ባለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላችሁ ሥጋት ተገቢ ነው። ነገር ግን መጨነቅ አያስፈልግም›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ስለዚህ ግድብ በዝርዝርና በተረጋጋ መንፈስ መነጋገር ይሻላል። እኛ በጉዳዩ ላይ ያለንን ሥጋት በምክንያትና በተጠና ዕቅድ ነው የምናየው፤›› ብለዋል።
የግብፅ ብሔራዊ ጥቅምን መንካት እንደማይቻል የተናገሩት አል ሲሲ፣ አገራቸው ትልቅ የኢኮኖሚና ወታደራዊ አቅም ያላት በመሆኑ ፍላጎቷንና ጥቅሟን ለማስከበር በተጠና መንገድ እንደምትጠቀምበት ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና የሱዳን የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሐን ከአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ሐምሌ 7 ቀን በተወያዩበት ወቅት፣ የህዳሴ ግድቡ ውዝግብ ብቸኛ መፍትሔ ውይይት ብቻ መሆኑን አመልክተዋል።
ሱዳን የህዳሴ ግድቡ ውዝግብ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ እንደምትሻና በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ እንደምትሠራም ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ከሱዳን በመቀጠል በኢትዮጵያ ጉብኝት የማድረግ ፕርግራም ይዘው እንደነበር፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ወደ አገራቸው መመለሳቸው ታውቋል።
ግብፅና ሱዳን የህዳሴ ግድቡ ሁለተኛ ዓመት ሙሌትን ኢትዮጵያ ስምምነት ሳይደረስ ዘንድሮ እንዳታካሂድ ከፍተኛ ጫና እያደረጉ ቢሆንም፣ የውኃ ሙሌቱ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንኑ አስመልክቶ ለሱዳንና ግብፅ በደብዳቤ ያሳወቀ ሲሆን፣ ዘንድሮ በግድቡ የሚያዘው አጠቃላይ 13.4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ በነሐሴ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ እንደሚጠናቀቅ ገልጻለች።
በተያዘው ዕቅድ መሠረት እስከ ሐምሌ ወር 25 ቀን ድረስ በግድቡ 6.9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ የሚሞላ መሆኑም ታውቋል።