Sunday, December 3, 2023

የወንጀል ሪከርድ አለበት የተባለው የሃጫሉ ገዳይ በሞት እንዲቀጣ ተጠየቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት 3፡30 አካባቢ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ገድሏል የተባለው ግለሰብ፣ ቀድሞም ሁለት የወንጀል ሪከርድ እንዳለበት በመጠቆም በሞት እንዲቀጣ ተጠየቀ፡፡

ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎች፣ ግለሰቡ በሞት እንዲቀጣ ጥያቄውን ያቀረበው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡

በባጃጅና የባቡር ሐዲድ ስርቆት የከረመ የወንጀል ሪከርድ እንደነበረበትና በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ምክንያት ክሱ እንደተቋረጠለት የተገለጸውና ድምፃዊ ሃጫሉን መግደሉ በሰነድና በሰዎች ምስክርት ተረጋግጦበታል በማለት ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ያለው ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ የሚባል መሆኑ ይታወሳል፡፡

በወንጀል ድርጊቱ ተጠርጥረው ከጥላሁን ያሚ ጋር ክስ የተመሠረተባቸውና ተጠቅሶባቸው የነበረው የተከሰሱበት የፀረ ሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ድንጋጌ ወደ መደበኛ የወንጀል ሕግ ተቀይሮ ጥፋተኛ የተባሉት ተከሳሶች ከበደ ገመቹና አብዲ ዓለማየሁ መሆናቸውም ይታወሳል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃና ተከሳሾች የቅጣት ማቅለያ እንዲያቀርቡ ለሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው ቀጠሮ መሠረት፣ ዓቃቤ ሕግ በዋና ገዳይነት ጥፋተኛ በተባለው ጥላሁን ያሚ ላይ ሁለት የወንጀል ሪከርድ እንዳለበት በመጥቀስና በድምፃዊው ላይ የፈጸመውን ግድያ በማንሳት በሞት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

በሁለቱ ተከሳሾች ላይ ማለትም በከበደ ገመቹ ላይ ፍርድ ቤቱ በራሱ ቅጣት ውሳኔ እንዲሰጥና አብዲ ዓለማየሁ የቅጣት ማቅለያ ካለው እንደማይቃወም በመግለጽ የቅጣት ማክበጃ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የሦስቱም ተከሳሾች ተከላካይ ጠበቃ፣ ተከሳሾቹ ከዚህ ቀደም የነበራቸው ባህሪ መልካም እንደነበር፣ በወንጀል ሕጉ 82 እና 83 ድንጋጌ መሠረት ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን እንዲያቀልላቸው ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን አስተያየቶች ከሰማ በኋላ፣ ተከሳሾቹ ተጨማሪ የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ ካላቸው እስከ ቅጣት መወሰኛ ቀን ድረስ በጽሕፈት ቤት በኩል ማቅረብ እንደሚችሉ በመጠቆም፣ ቅጣት ለመወሰን ለሐምሌ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -