Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያው በበጀት ዓመቱ ያገበያየው የምርት መጠን ቀነሰ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2013 በጀት ዓመት 614,586 ሜትሪክ ቶን ምርት በ39.6 ቢሊዮን ብር በማገበያየት ከዕቅዱ በምርት በመጠን 96 በመቶ፣ በዋጋ በ102 በመቶ ማሳካት መቻሉን ሐሙስ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡ ምርት ገበያው ዓመታዊውን አፈጻጸም ባወጣው መግለጫው በበጀት ዓመቱ ከተገበያየው ምርት መጠን ውስጥ ቡና 35.5 በመቶ፣ ሰሊጥ 31 በመቶ ድርሻ ነበራቸው፡፡ ሌሎች ጥራጥሬዎች 33.4 በመቶ ድርሻ እንደነበራቸው አመልክቷል፡፡ ነገር ግን ከቀደሙት ዓመታት ሲነፃፀር ቀንሷል፡፡

የምርት ገበያው የ2013 በጀት ዓመት አፈጻጸም ከ2012 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር፣ በምርትም ሆነ በግብይት ዋጋው ያነሰ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ምርት ገበያው በ2012 በጀት ዓመት አገበያይቶ የነበረው የምርት መጠን 761,904 ቶን መሆኑን የወቅቱ ሪፖርት ሲያሳይ፣ በ2013 በጀት ዓመት ያገበያየው ደግሞ 614,586 ቶን ነው፡፡ ይህም ዘንድሮ በምርት ገበያው የተገበያየው የምርት መጠን በ147,586 ቶን መቀነሱን የሚያሳይ ነው፡፡ በተመሳሳይ በ2012 በጀት ዓመት በምርት ገበያው የቀረበው ምርት የተገበያየበት ዋጋ 40 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ከዘንድሮ አንፃር ሲታይ የግብይት ዋጋው ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ መቀነሱን ያሳያል፡፡   

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የዘንድሮ ሪፖርት በምርት ገበያው በኩል የተካሄደው የግብይት መጠን የግብይት ዋጋ ዘንድሮ ለምን እንደቀነሰ አልጠቀሰም፡፡ ሆኖም ዘንድሮ በምርት ገበያው የተገበያየው የምርት መጠን ካለፉት አምስት ዓመት ወዲህም ዝቅተኛው የሚባል መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

የምርት ገበያው ያለፉት አምስት ዓመታት የግብይት መጠንን በሚያሳዩ መረጃዎች መሠረት፣ በ2009 በጀት ዓመት 621,508 ቶን፣ በ2010 በጀት ዓመት 652,000 ቶን፣ በ2011 በጀት ዓመት 681,805 ቶን እና በ2012 በጀት ዓመት ደግሞ 761,904 ቶን ምርቶችን አገበያይቷል፡፡ ይህ የግብይት መጠን በየዓመቱ ዕድገት እያሳየ የመጣ ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን የተገበያየው የምርት መጠን ወደ 614,586 ቶን ዝቅ ከማለቱም በላይ ከ2009 ወዲህ ዝቅተኛ ምርት የቀረበበት ዓመት መሆኑንም ያሳያል፡፡

ዘንድሮ በምርት ገበያው የተገበያየው የምርት መጠንና የግብይት ዋጋ በዚህን ያህል ደረጃ የቀነሰ ቢሆንም፣ ምርት ገበያው በሌሎች ክንውኖቹ የተሻለ አፈጻጸም ያሳየበት ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ ዘንድሮ ለግብይት የቀረቡ ምርቶችን ጥራት በሁሉም ቅርንጫፎች በመመርመር 68,391 የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት የተሰጠ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ 

የ2013 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምን በማስመልከት ከወጣው መረጃ ለመገንዘብ እንደተቻለው፣ በክፍያና ርክክብ ሥርዓትም በቅርቡ የተካተቱትን እናት ባንክና ዘመን ባንክን ጨምሮ በ17 ባንኮች በመረጃ መረብ በተገናኙ ከአሥር ሺሕ በላይ የገዥዎችና የአቅራቢዎች የባንክ አካውንቶች ያለ ምንም እንከን መከናወኑን ጠቅሷል፡፡

ከምርት ሻጮች ሁለት በመቶ ዊዝ ሆልዲንግ ታክስ 756 ሚሊዮን ብር፣ ከአገር ውስጥ ቡና ተገበያዮች ቫት 847 ሚሊዮን ብር፣ ምርት ገበያው ከሚሰበስበው የአገልግሎት ክፍያና ከመሳሰሉ ቫት 60 ሚሊዮን ብር፣ በድምሩ 1.7 ቢሊዮን ብር ግብር በመሰብሰብ ለመንግሥት ገቢ ማድረጉንም አሳውቋል፡፡

ለግብርና ምርት አቀነባባሪ ኢንዱስትሪዎች በቂ ግብይት እንዲያገኙ ለማስቻል በጥቅምት 2013 ዓ.ም. በከፈተው ልዩ የግብይት መስኮት አማይነት እስካሁን 463,680 ኩንታል አኩሪ አተር በ990 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ ለአቀነባባሪ ኢንዱስትሪዎች ያገበያየው የአኩሪ አተር መጠን ከጠቅላላ የምርቱ ግብይት 50 በመቶ እንደሚሸፍንም የምርት ገበያው መግለጫ ያመለክታል፡፡

በየዓመቱ እየተካሄደ በሚገኘው የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ውድድር ላይ በ2013 በብሔራዊ ደረጃ አሸናፊ የሆኑ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸውን ቡናዎች በማይክሮ ሎት ግብይት ሥርዓት እንደተከናወነም ተገልጿል፡፡

የምርት መቀበያ ቅርንጫፎችንና የግብይት ማዕከላትን ተደራሽነት ለማሳደግ በቴፒና ሚዛን አማን አዳዲስ ቅርንጫፎች መክፈቱ የምርት ገበያውን የቅርንጫፎች ቁጥር 25 አድርሷል፡፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ሦስት ቅርንጫፎችን ለመክፈት የአዋጭነት ጥናት ተሠርቷል፡፡

የጎንደር የግብይት ማዕከል ተመርቆ ሥራ መጀመሩና የአዳማና ጅማ የግብይት ማዕከላት ግንባታቸው በመጠናቀቁ ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉም ተጠቅሷል፡፡ ክልላዊ የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላት ብዛት ወደ ስድስት ከፍ ብሏል በቡሌ ሆራና በመቱ የተገነቡ የተሟላ አገልግሎት የሚጡ ሁለት መጋዘኖች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ሥራ ጀምረዋል፡፡ በጎንደርና በሁመራ እየተገነቡ የሚገኙ መጋዘኖች ግንባታቸው በወጣላቸው ዕቅድ መሠረት እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ምርት ገበያውን ለማዘመን ዘርፈ ብዙ የማሻሻያ ሥራዎች በመሥራት ላይ መሆኑን የገለጸው ምርት ገበያው፣ በዚህም የቡና ናሙና ማሳያ በሁሉም የቡና መቀበያ ቅርንጫፎች ተዘጋጅተው ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርቡ የቡና ምርቶችን ናሙና ገዥዎች አይተው እንዲገዙ መደረጉ በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡

ከደረጃ በታች የሚመጡ ምርቶች ሲኖሩ አቅራቢዎች የማበጠርና የጭነት አገልግሎት የሚያገኙበት አሠራርም ተዘርግቷል፡፡  እንዲሁም ለጥራጥሬና ቅባት እህል አቅራቢዎችና ገዥዎች ለግብይት ከመምጣታቸው በፊት በመረጃ መረብ የቅድመ ግብይት መረጃ የሚያገኙበት አሠራር መዘርጋቱን በመግለጽ፣ በበጀት ዓመቱ የተሠሩ ሥራዎችን አመልክቷል፡፡

በተጨማሪም የFuture/Forward የግብይት ሥርዓትን ለመጀመር የሚያስችል የመጀመርያ ደረጃ የአዋጪነት ጥናት በውስጥ አቅም ተሠርቶ ተጠናቋል፡፡ የአፈጻጸም ዕቅድ ለማዘጋጀት ከአይኤሲ ጋር በመተባበርና በዘርፉ ልምድ ያለው የውጭ ኮንሰልታንት እንዲሳተፍበት በማድረግ የመጨረሻ ደረጃ ጥናቱ በመከናወን ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡  

የምርት ገበያው በፋይናንስ አፈጻጸም ረገድ እንዳመለከተው፣ በ2013 በጀት ዓመት ምርት ገበያው ከኦፕሬሽንና ኦፕሬሽናል ካልሆኑ ምንጮች ያገኘው አጠቃላይ ገቢ 775 ሚሊዮን ብር መሆኑን ገልጾ፣ ይህ አፈጻጸሙ ከታቀደው በላይ 106 በመቶ ያሳካሁት ነው ብሏል፡፡

የዘንድሮ ገቢው ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይም 20 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ የበጀት ዓመቱ ጠቅላላ ወጪ ደግሞ 517 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከ2012 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ የ14 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየም ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዘንድሮ ዓመታዊ ሪፖርቱ ያገኘውን ትርፍም አሳውቋል፡፡ በዚሁ መሠረት በ2013 በሒሳብ ዓመት ከ258 ሚሊዮን ብር በላይ ከታክስ በፊት ትርፍ አግኝቷል፡፡ ይህ የትርፍ መጠንም በበጀት ዓመቱ ይመዘገባል ተብሎ ከታሰበው በ15 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡ ከአጠቃላይ የሥራ አፈጻጸሙ ጋር በተያያዘ እንደተግዳሮት የጠቀሰው ጉዳይ ከኮንትሮባንድ ግብይት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ የኮንትሮባንድ ንግድ ከዚህ ቀደም ለግብይት ሥርዓቱ ማነቆ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ ዘንደሮም ምርት ገበያው ትልቁ ችግሬ ነው ብሎ አመልክቷል፡፡

 ግብይታቸው በምርት ገበያው በኩል የተከናወነው ለአገር ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት የሚችሉ ምርቶች አሁንም ወደ ጎረቤት አገሮች በኮንትሮባንድ እየወጡ በመሆኑና ይህንንም መግታት አለመቻሉን ጠቅሷል፡፡ በመሆኑም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሕገወጥ ንግድን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ ስለመሆኑ አመልክቷል፡፡

ምርት ገበያው የማዕድን ምርቶችን ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለማስገባት ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ጋር በተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ መሠረት በ2014 በጀት ዓመት ኦፖል፣ ሳፋሪና ኢመራልድ ማዕድናትን ማገበያየት እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

የማዕድናት ግብይት ለመጀመር ባለፉት ወራት ከሁሉቱም መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች ያሉበት የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የዝግጅት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑንና እስካሁን የኮንትራት ዝግጅትና የግብይት ሞዳሊቲ ተዘጋጅተዋል ብሏል፡፡

በቅርቡ በማዕድን ምርትና ግብይት ላይ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ጋር የኢንዱስትሪ ምክክር በማድረግ በቀጥታ ወደ ሥራ መግባት የሚችል ስለመሆኑ ታውቋል፡፡

ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ አሥር የተለዩ ምርቶችን በምርት ገበያው በኩል ለማገበያየት ውጥን መያዙን የገለጸው ምርት ገበያው በምርት ገበያው በኩል ግብይታቸው እንዲፈጸም ከተለዩት ምርቶች አብዛኛዎቹ የቅመማ ቅመም ምርቶች ናቸው፡፡ የእነዚህ ምርቶች የአዋጪነት ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም አሳውቋል፡፡  

በአዲሱ በጀት ዓመትና በቀጣዮቹ ዓመታት ወደ ግብይት ሥርዓቱ ሊገቡ የሚችሉ 10 ምርቶች ተብለው የተጠቀሱት ሙጫ፣ አብሽ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ እርድ፣ ኮረሪማ፣ ጓያ፣ ኦቾሎኒ፣ ሩዝና የዱባ ፍሬ ናቸው፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የርግብ አተር፣ ዥንጉርጉር ቦሎቄና ፒንቶ ቢን ወደ ግብይት ሥርዓቱ መካተታቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች