Friday, February 23, 2024

ዴሞክራሲያዊ ሽግግር በምርጫ 2013 ዓውድ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በበርካቶች ተስፋ ተጥሎበት የነበረውና በአንዳንዶች ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር የምታደርገው ሕዝበ ውሳኔ ነው ሲባል የነበረው አገራዊ ምርጫ፣ እነሆ ተጠናቅቆ ውጤቱ ይፋ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአገር አቀፍ ደረጃ በ436 የምርጫ ክልሎች የተከናወነውን የምርጫ ውጤት ቅዳሜ ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል በተከናወነ መርሐ ግብር ላይ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በምርጫ ውጤቱ መሠረት ብልፅግና ፓርቲ ከ90 በመቶ በላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ሲያሸንፍ፣ የተቀሩት 15 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በሦስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በአራት የግል ዕጩዎች ተይዘዋል፡፡ በዚህም መሠረት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አምስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ አራት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን፣ እንዲሁም የጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሁለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ያሸነፉ ሲሆን፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር)፣ ካሚል ሸምሱና ገላሳ ዲልቦ በግል ተወዳድረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን አሸንፈዋል፡፡

ቦርዱ የምርጫ ውጤት በቆጠራ ደረጃ ችግሮች ታይቶባቸዋል ባላቸው ሦስት የሕዝብ ተወካዮች የምርጫ ክልሎች ዳግም ቆጠራ እንዲከናወን የወሰነ ሲሆን፣ የምርጫው ሒደት ችግር ገጥሞታል በተባለባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ዘጠኝ የምርጫ ክልሎች ደግሞ ዳግም ድምፅ እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡

የምርጫው ውጤት ይፋ በተደረገበት መድረክ ላይ የምርጫውን ሒደት ሪፖርት ያቀረቡት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ድጋሚ ድምፅ እንዲሰጥባቸው ከተወሰነባቸው ምክንያቶች መካከል፣ ‹‹የታዛቢዎችና የወኪሎች መከልከል፣ ምርጫ ሒደቱ በአካባቢው መስተዳድር መዋቅር ተፅዕኖ ሥር በመውደቁ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መራጭ እንዳይመርጥ ክልከላ መደረጉን ቦርዱ በምርመራው ማመኑ የተወሰኑት ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ምርጫው ከተደረገ ማግሥት ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የምርጫውን ሒደት በማሞካሸት ‹‹ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት›› ምርጫ በመደረጉ እርስ በርስ ሲሞጋገሱ ከርመዋል፡፡ ድምፅ ተሰጥቶ የምርጫ ውጤቱ ይፋ ከተደረገ በኋላም ተመሳሳይ ትርክቶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተሰሙ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ምርጫውም ሆነ የተገኘው ውጤት በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሽግግርን ማምጣት የሚያስችል ሳይሆን፣ አገሪቱ ያለችበትን ቀውስ የሚያባብስ ነው የሚሉ ድምፆች ይደመጣሉ፡፡

በምርጫው እንዳልሳተፍ ተገፍቻለሁ በማለት ለረዥም ጊዜያት ክስ ሲያቀርብ የነበረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ምርጫው በተካሄደ በሁለተኛው ቀን ባወጣው መግለጫ አገሪቱ የገጠማትን የፖለቲካ፣ የደኅንነትና የሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ከግምት በማስገባት በዚህ ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ ተቀባይት ያለው፣ ፍትሐዊና ነፃ ሊሆን አይችልም በማለት ያጣጣለው ሲሆን፣ መንግሥት ለምርጫው የሚያወጣውን ሀብት አገራዊ ውይይትና መግባባት ለመፍጠር እንዲያውለው ጠይቆ ነበር፡፡ ነገር ግን ይኼንን ተደጋጋሚ ጥሪ ግን መንግሥት ችላ በማለት እያደረገ በነበረው የምርጫ ሒደት የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል ሲልም ይከሳል፡፡ መንግሥት ምርጫው እንዲደረግ ያደረገው ግፊት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንዳለ በማቆየት በሥልጣን ላይ ለመሆን እንዲያግዘው ነው ብሎ እንደሚያምንም አስታውቋል፡፡ ስለዚህም ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የተከናወነው ምርጫ በምንም መለኪያ ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምርጫውን በማስመልከት ‹‹ፍትሐዊና አካታች ያልሆነ ምርጫ ዴሞክራሲን ሊያዋልድ አይችልም›› ሲል ሰኔ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹በብሔራዊ መግባባት ያልታጀበ ምርጫ አገሪቱን ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር እንደማያወጣት ደጋግመን አስገንዝበናል፡፡ በተለይም በአንድ ፓርቲ የበላይነት ለተጠመደው ገዥው ፓርቲ የምናቀርበው የውይይት ጥያቄ ሁሉ ወደ ደንቆሮ ውይይት በመቀየሩ፣ የአገራችንን ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ እያሸጋገረ ነው፡፡ የሰሞኑ የፖለቲካ ቴአትርም የዚህ ገታራ አቋሙ ውጤት ነው፤›› ሲል የምርጫውን ሒደት ኮንኖታል፡፡ ስለዚህም፣ ‹‹የአገራችንን ፍላጎቶች የማያሟላ ምርጫ ማለትም ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋትንና ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የማይፈጥር ከሆነ ለሚሊዮኖች የሚሆን ልማትና ብልፅግናንም አያመጣም፤›› ሲል ደምድሟል፡፡

በዚህም ምክንያት ኦፌኮ ሁሉን አካታች የጋራ መንግሥት እንዲቋቋም፣ ሁሉን አካታች ብሔራዊ የመግባባት ድርድር እንዲጀመር፣ ለጋራ መንግሥቱ በጋራ የሚፈጠር ፍኖተ ካርታ እንዲመቻችና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊና ተቀባይነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ በማለት ጥሪ አቅርቧል፡፡ ኦፌኮ ከዚህ አስቀድሞ በሚያዚያ ወር መንግሥት ከብሔራዊ መግባባት እየሸሸ ነው ሲል በመግለጫ ከሶ ነበር፡፡

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ የተሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምክር ቤታቸው አማካይነት ምርጫው ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ነበር ያሉ ቢሆንም፣ በርካቶች የምርጫው ሒደት ውጣ ወረድ የተሞላበት እንደነበር ግን አልሸሸጉም፡፡ ለአብነት ያህል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምርጫውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹አብን በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ተሳትፎ ሲያደርግ ምቹ የምርጫ ምኅዳር አለ በሚል እምነት ሳይሆን፣ ያሉ ችግሮች በሒደት ተፈትተው ቢያንስ የምርጫ ዕለት ሕዝባችን በአንፃራዊነት ድምፁን በነፃነት ይሰጣል በሚል እምነት ነበር፡፡ ሆኖም የምርጫው ሒደት ከተለመደው የገዥው ፓርቲ ጫናና ሕገወጥ ተግባር መላቀቅ አቅቶት፣ ሕዝባችን ተስፋ የጣለበትን የዴሞክራሲ ሒደት የሚያደበዝዝ ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ሲል ሒደቱ ያስገኘዋል የተባለውን ሽግግር እንዳጠለሸው አውስቷል፡፡

ምርጫውን አስመልክቶ ተመሳሳይ ይዘት ያለው መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ ‹‹እንደ አፍሪካ ውስጥ ባሉ በበርካታ ውስብስብ አሠራሮች በተተበተቡ አገሮች ውስጥ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ጥበት፣ ከፍተኛ የሥልጣን ጉጉትና የመሳሰሉት እንቅፋቶች የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን ቀይደው ይይዙታል፡፡ ድህነቱ፣ ኋላ ቀርነቱና የዜጎች የፖለቲካ አረዳድ ወዘተ. ችግሮቹን ይበልጥ ያባብሱታል፤›› ሲል ተንትኖ፣ ኢትዮጵያም ከዚህ የተለየች እንዳልሆነችና በዚህ አጠቃላይ ችግር ላይ የተደመረው የዘውግና የቋንቋ ፖለቲካ በትውልዱ ላይ ቁርሾን ጥሏል በማለት፣ ‹‹ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የተደረገው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሒደቱና ውጤቱ ሙሉ በሙሉ ለሕዝብ የተገለጸ ባይሆንም፣ በብዙ ግልጽ ችግሮች የታጀበ ነበር፤›› ሲል የምርጫውን ተስፋ የሚያደበዝዙ ሁነቶች መኖራቸውን ያስታውሳል፡፡

እነዚህ ሥጋቶችና በምርጫው ሒደት ላይ የቀረቡ ወቀሳዎች ምርጫው የታለመለትን ግብ አልመታም በማለት የሚነሱ ቢሆኑም፣ በተመሳሳይ የታሰበውን ያህል ስብጥር ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፍጠር ባለመቻሉም ጉድለት አሳይቷል ሲል መንግሥትም ጭምር ያመነበት ነው፡፡

ለፓርላማው ድምፅ ከተሰጠባቸው የምርጫ ክልሎች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሆኑት በገዥው ፓርቲ የተያዙ ሲሆን፣ አሥራ አንድ መቀመጫዎች ብቻ በተቃዋሚ ፓርቲዎች የተያዙ ናቸው፡፡ አራት የፓርላማው መቀመጫዎች ደግሞ በግል ዕጩዎች የተያዙ ናቸው፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ያሸነፉ ሦስቱ የግል ተወዳዳሪዎች ከብልፅግና ፓርቲ ዕጩዎች ጋር ተወዳድረው ያሸነፉ ቢሆንም፣ በአዲስ አበባ ካሸነፉት ዕጩ ጋር ግን የብልፅግና ፓርቲ ዕጩ አቅርቦ አልተወዳደረም፡፡ በኦሮሚያ ክልል 11 ዕጩዎች በግል ተወዳድረው ነበር፡፡ በጠቅላላው በምርጫው የተሳተፉ የግል ዕጩዎች 148 ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ የተወዳደሩት የግል ዕጩዎች ሁለት ብቻ ነበሩ፡፡

ካሁን ቀደም በነበሩ አምስት ምርጫዎች ከ2007 ዓ.ም. ምርጫ ከተመሠረተው መንግሥት በስተቀር በሁሉም ምክር ቤቶች ተቃዋሚዎች መቀመጫ ያሸነፉ ሲሆን፣ በምርጫ 1987 ዓ.ም. አራት ተቃዋሚዎችና ስምንት የግል ዕጩዎች፣ በ1992 ዓ.ም. ምርጫ 10 ተቃዋሚዎችና 13 የግል ዕጩዎች፣ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ 236 ተቃዋሚዎችና አንድ የግል ዕጩ፣ እንዲሁም በ2002 ዓ.ም. ምርጫ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪልና አንድ የግል ዕጩ በፓርላማው መቀመጫ አግኝተው ነበር፡፡ ይሁንና ምርጫው በተከናወነና መንግሥት በተመሠረተ ማግሥት ወደ አመፅና ብጥብጥ ያመራው የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ምንም ተቃዋሚ ወደ ፓርላማ ያላስገባ ሲሆን፣ በዚህም ምርጫ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መቶ በመቶ ማሸነፉን ያወጀበት ነበር፡፡

በሰኔ 14ቱ ስድስተኛ ምርጫም ኢሕአዴግን የተካው ብልፅግና ፓርቲ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ በተደረገባቸው የምርጫ ክልሎች ከ90 በመቶ በላይ ድምፅ ያጋበሰ ሲሆን፣ ይኼም በምርጫው አነሰም በዛ ድጋፍ የነበራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕሳቤዎች ውክልና እንዳይኖራቸው ማድረጉ አይቀርም የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሌ የማይባሉ ናቸው፡፡

የምርጫውን ሒደት አስመልክቶ ከሪፖርተር ጋር ከሳምንት በፊት ቆይታ ያደረጉትና ይኼው ጥያቄ የቀረበላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ራሔል ባፌ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አንድ ፓርቲ አብላጫ ድምፅ ካገኘ መንግሥት እንዲመሠርት የሚፈቅድ እንደሆነ በማስታወስ፣ ‹‹አንድ መንግሥት 50+1 ድምፅ ሲያገኝ እንግዲህ ብቻዬን ልምራ ላይል ይችላል፡፡ ደግሞ አነሰም በዛም ሁሉም ተከታይ ሕዝብ ከኋላው አለና መሳተፍ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ አንዱ 5,050 ድምፅ አግኝቶ ቢያሸንፍና ሌላው 5,045 ድምፅ አግኝቶ ሳያሸንፍ ቢቀር፣ እኩል ገደማ ተከታይ ያለው ይቀራል ማለት ነው፡፡ እነዚህም ነገሮች ከግንዛቤ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ነገሮች ለውጥና ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ሊኖሩ ስለሚችሉ ይኼንን በተመለከተ አጥጋቢ ምላሽ ሊኖር የሚችለው ከምጫርው ውጤት በኋላ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

የዚህ አንደኛው የመፍትሔ አማራጭ የምርጫ ሥርዓቱን በድጋሚ መመልከት እንደሚሆንም ራሔል (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡

ይኼንን አመለካከት የምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር አባል ብዙወርቅ ከተተ የምርጫ ውጤት ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ሲደረግ በመጋራት ያንፀባረቁት ሲሆን፣ አብላጫ ድምፅ ያገኘ ፓርቲ ብቻ መንግሥት ይመሥርት (First Past the Post) የሚለው የምርጫ ሥርዓት መቀየር እንዳለበት በዚህ የምርጫ ሒደት እንደተረዱ ጠቁመዋል፡፡

ካሁን ቀደም በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በወቅቱ ገዥ ፓርቲ በነበረው ኢሕአዴግ መካከል ለረዥም ጊዜያት በተደረጉ ውይይቶች የምርጫ ሥርዓቱን ለመቀየር ከስምምነት ተደርሶ የነበረ ሲሆን፣ 80 በመቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በአብላጫ ድምፅ፣ እንዲሁም 20 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በተመጣጣኝ ውክልና ፓርቲዎች ባገኙት ድምፅ ልክ ተመጣጣኝ መቀመጫ እንዲያገኙ ያስችላቸው ነበር፡፡ ይሁንና ይኼ በሒደት ላይ ሆኖ ሳይጠናቀቅ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ወር  በመጣው አገራዊ ለውጥ ሳቢያ ይኼ ውሳኔ ከግብ ሳይደርስ ቀርቷል፡፡ ይኼ የምርጫ ሥርዓት የፓርላማውን መቀመጫ ቁጥርም ከፍ ያደርገው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ዝግጅት ማድረግ በጀመረበት በ2011 ዓ.ም. ደግሞ ከምርጫው አስቀድሞ የፓርላማ መቀመጫ ቁጥርና የክልሎች ውክልና፣ እንዲሁም የምርጫ ሥርዓት ለውጥ ይቅደም የሚሉ ውይይቶች መደመጣቸውን ምክንያት በማድረግ ባወጣው ማብራሪያ፣ የምርጫ ሥርዓቱን በምርጫ ዝግጅት ወቅት መቀየር የሕገ መንግሥት ማሻሻያን የሚጠይቅና ከፍተኛ ወጪ ያለው፣ የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎች የሚያስፈልጉት፣ የክልሎች የፓርላማ መቀመጫ ቁጥርን መቀየርና የምርጫ ክልሎችን ዳግም ማካለል የሚፈልግ፣ ብሎም የቦርዱን ውስጣዊ አደረጃጀት መለወጥ የሚፈልግ በመሆኑ አስቸጋሪ ነው ብሎ ነበር፡፡

የምርጫውን ውጤት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት መራጩንና በምርጫው የተሳተፉ ፓርቲዎችን፣ እንዲሁም የምርጫ ቦርድን ያመሠገኑ ሲሆን፣ በምርጫው መሳተፍና ማሸነፍ ከሚሰጠው ደስታ በዘለለ ድምፅ አግኝተው ፓርላማ ያልገቡ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተለያዩ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ለማሳተፍ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፣ ‹‹በታሪካዊው ምርጫ ተሳታፊ መሆን በራሱ የሚፈጥረው ደስታ እንዳለ ሆኖ፣ ፓርቲያችን በሕዝብ ይሁንታ አግኝቶ አገር ለማስተዳደር መመረጡ አስደስቶናል። በውጤቱም ከአሸናፊነት ይልቅ ኃላፊነት፣ ከድል አድራጊነት ይልቅ ታላቅ የሆነ አገራዊ አደራ እንዲያድርብን አድርጎናል።

‹‹መንግሥት የሚመሠረተው በሕዝብ በተመረጡ ፓርቲዎች ቢሆንም፣ አገርን መምራትና ማስተዳደር ግን ለተመረጡ ፓርቲዎችና መሪዎች ብቻ የሚተው አይደለም። ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸውም እስከ የሚቀጥለው ምርጫ በመንግሥት አስተዳደርና ሕዝብን በማገልገል ሒደት ውስጥ ሚናቸው ሰፊ ሊሆን እንደሚገባ ለማስታወስ እወዳለሁ።

‹‹በቀጣይ ወራት ብልፅግና በሚመሠርተው መንግሥት ውስጥ በአስፈጻሚው አካልም ሆነ በፍርድ ቤቶች፣ በሌሎችም የፌደራልና የክልል ተቋማት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው፣ በዘንድሮው ምርጫ በኃላፊነትና በብቃት የተወዳደሩ የሕዝብ አለኝቶችን ከዚህ በፊት ካደረግነው በእጅጉ ከፍ ባለና አዎንታዊ ለውጥ በሚፈጥር መልኩ እንደምናካትታቸው ለመግለጽ እወዳለሁ፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያን ምርጫ አስመልክተው በለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት ድረ ገጽ ላይ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ምርጫ ድምፅ ሳይሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያነገሠ ነው›› (Ethiopia’s Election is a Coronation of Abiy Ahmed Before the Polls) በሚል ርዕስ መብራቱ ከለቻ (ዶ/ር) የተባሉ የሲቪክ ትምህርትና ፖለቲካ ትምህርት ምሁር ባስነበበት ጽሑፍ፣ ምርጫው ጠቅላይ ሚኒስትሩን በታሪክ ሊያስዘክራቸው ይችል የነበረ ቢሆንም ቅሉ በእጅጉ የወደቁበት ነው ብለዋል፡፡

‹‹ምርጫው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣን ለማጠናከር የተደረገ ነው፡፡ ከዓብይ ብልፅግና ፓርቲ ጋር የተፎካከሩ ብቁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሉም፤›› ሲሉም ምርጫው አለበት ስላሉት ጉድለት አውስተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኦሮሚያ የአገሪቱ ትልቁ ክልል ሆኖ ሳለና ፓርላማው ካለው 547 መቀመጫዎች መካከል 178 መቀመጫዎችን የሚወክል ቢሆን፣ የኦሮሚያ ክልል ዋና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኦፌኮና ኦነግ ፍትሐዊ ባልሆነ ሁኔታና በጫና ከምርጫው ተገፍተው ወጥተዋል ሲሊም ተችተዋል፡፡

በበርካቶች ምልከታ ምርጫ ብቻውን የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚያመጣ ባይሆንም፣ ምርጫ ማድረግ ግን ለዴሞክራሲ ሽግግር አንዱ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ ይሁንና ምርጫ ሕዝቡ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ አስተሳሰቦች የሚወከሉበትና ወደ ዴሞክራሲ ሊያሻግር የሚችል ስብጥር ያለው ልምምድ እንዲሆን በተሳትፎና በውክልና ረገድ ብቁ ሊሆን ይገባልም ይላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ስድስተኛው ምርጫ በበርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች አይ እና አዎ ‹‹አያዎ›› መልክ የተሰጠው ቢሆንም፣ በውክልና ደረጃ ያስገኘው ውጤት ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተሳሰቦች በመንግሥት ፖሊሲና ሕጎች ውስጥ ሊወከሉ የማይችሉ ድምፆች እንዳሉ ያሳያል ሲሉ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ መንግሥትም አሳትፋለሁ ባለው መሠረት በተለያዩ የአስፈጻሚው አካላት ውስጥ ሹመት ቢሰጣቸውም፣ እነዚህ ሹመኞች የሚያስፈጽሙት መንግሥት የመሠረተውን ፓርቲ ፖሊሲዎች ነው? ወይስ በጋራ ፖሊሲዎቹ የሚቀረፁበትና ቅርፅ የሚይዙበት መንገድ ይመቻች ይሆን? ሲሉ የሚጠይቁ አልጠፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -