ኢሰመኮ የት እንዳሉ አጣርቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጠው ተጠይቋል
ለጥያቄ እንደሚፈለጉ ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ከመሥሪያ ቤታቸው በፌዴራል ፖሊስ የፀጥታ አካላት ከተወሰዱ በኋላ፣ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ‹‹ተለቀዋል›› በሚል ምላሽ ቤተሰብ ሊጠይቃቸውና ሊያገኛቸው እንዳልቻለ፣ ወይም ‹‹የት እንዳሉ አልታወቀም›› የተባሉትን ጋዜጠኞች አካል ነፃ የማውጣት ክስ ማክሰኞ ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ተመሠረተ፡፡
ለጥያቄ መፈለጋቸው ተነግሯቸው ከተወሰዱ 20 ቀናት እንዳለፋቸው የተዘረዘሩት ጋዜጠኞች ከዓውሎ ሚዲያ ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው፣ ፋኑኤል ክንፉ፣ ምሕረት ገብረ ክርስቶስና ሌሎችም የተካተቱ ሲሆን፣ ከኢትዮ ፎረም ደግሞ ጋዜጠኛ አበበ ባዩና ያየሰው ሽመልስን ጨምሮ ከሁለቱም በኩል 14 ጋዜጠኞች መሆናቸውን፣ ክሱን ለፌዴራል የመጀመር ደረጃ ፍርድ ቤት ዘጠነኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ያቀረቡት ጠበቃ ታደለ ገብረ መድኅን በክስ አቤቱታቸው ጠቅሰው አቅርበዋል፡፡
ጋዜጠኞች ከተያዙበት ቀን ጀምሮ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ በሚል ቤተሰቦቻቸውና ጠበቆቻቸው በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት በተደጋጋሚ እየቀረቡ ቢጠባበቁም፣ የያዛቸው አካል ፍርድ ቤት እንዳላቀረባቸው በአቤቱታው ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ እንዲያገናኛቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ፈቃደኛ አለመሆኑንና ‹‹ተለቀዋል›› የሚል ምክንያት በመስጠት ሊያገናኛቸው እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 177 እና ተከታዮቹ ድንጋጌ መሠረት አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ሊያቀርቡ መገደዳቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ጋዜጠኞቹ የት ተወስደው እንደታሰሩ ገለልተኛ አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አጣርቶ እንዲያቀርብ፣ የፌዴራል ፖሊስ ከ48 ሰዓታት በላይ ያለ ፍርድ ቤት ፈቃድ ያሰራቸው በመሆኑ የአካል ነፃነታቸው እንዲከበርላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡
በዕለቱ የፌዴራል ፖሊስ ችሎት ባለመቅረቡ፣ አመልካቾች የፌዴራል ፖሊስ የመሰማት መብት ታልፎ ኃላፊው ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለረቡዕ ሐምሌ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡