ተጨማሪ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሊቋቋም ነው
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር አገልግሎት ሰጪ ቢሮዎች ተበታትነው ስለሚገኙና በየዓመቱ ለሕንፃ ኪራይ የሚወጣውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ለማስቀረት፣ አስተዳደሩ የአገልግሎት ሰጪ ቢሮዎችን በአንድ ቦታ ሊገነባ እንደሆነ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት የ2013 የሥራ ዘመን ማጠቃላይ ጉባዔውን ቅዳሜ ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በፌደሬሽን ምክር ቤት አዳራሽ ባከናወነበት ወቅት እንዳስታወቁት፣ ከአዲስ አበባ ቢሮዎች መበታተንና ኪራይ ጋር ተያይዞ ያለው ጉዳይ መቀረፍ ያለበት ችግር ነው፡፡
አስተዳደሩ ለቢሮ ኪራይ በሚያወጣው ወጪ ከፍተኛ ገንዘብ እያባከነ እንደሆነ ያስታወቁት ምክትል ከንቲባዋ፣ በየዓመቱም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ለኪራይ እንደሚወጣና ይህም ከተማዋን የማይመጥን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
አስተዳደሩ መሬት ለተለያዩ አካላት የሚያቀርብ ሆኖ ሳለ ለኪራይ በሚል ይኼን ያህል መጠን ያለው ወጪ ማውጣቱ ተገቢ አይደለም የሚለውን በፍጥነት ለመመለስ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ያስታወቁት ወ/ሮ አዳነች፣ የአዲስ አበባ አገልግሎት ሰጪ ቢሮዎች አንድ ላይ የሚገነቡበት ፕሮጀክት የቦታ ልየታና ዲዛይን ሥራ እንደተጠናቀቀ አስታውቀዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም. የከተማ አስተዳደሩ ከሚያስጀምራቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች አንዱ የአዲስ አበባ አስፈጻሚ ቢሮዎች ሰብሰብ ብለው በአንድ ቦታ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ ማድረግ እንደሆነ ያስታወቁት ምክትል ከንቲባዋ፣ እስከ ዲዛይን ያለው ሥራ በመጠናቀቁ በቀጣይ ግንባታ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡
አስፈጻሚ ቢሮዎች በተበታተነ ሁኔታ በመገኘታቸው ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር ሰፊ ክፍተት መፈጠሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ነዋሪዎች ከመሬትና ከግንባታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለመፈጸም አንዴ መሬት ባንክ፣ በሌላ ጊዜ ግንባታ ፈቃድ ጽሕፈት ቤት፣ በሒደቱ የተፈጠረ ሁኔታም ካጋጠመ ቅሬታ ለማቅረብ ደግሞ ሌላ ክፍለ ከተማ አቋርጦ ቅሬታ ለማሰማት የሚደረጉ መጉላላቶች እንደነበሩና የሚደርሰውም የጊዜ ብክነት ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ወ/ሮ አዳነች አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም አስተዳደሩ ከቴክኖሎጂ ጋር በተገናኘ የሚያከናውናቸው ቋሚ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ስለሆኑ፣ እነዚህን በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ ቢሮዎች ሳይሆን ከተማ አስተዳደሩ በሚያስገነባቸው ቢሮዎች ሊከናወኑ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
የወረዳዎች ጉዳይም እንደዚሁ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ያስታወቁት ምክትል ከንቲባዋ፣ ሁሉም በአንድ ጊዜ የሚዳረስ ባይሆንም የሴክተር ተቋማት ጉዳዮች እየተሸጋሸገ ሲሄድ፣ እንዲሁም ከዚህ ቀደም የከተማ አስተዳደሩ ባደረገው ማጣራት የተገኙ ባለቤት አልባ ሕንፃዎችንም በመመልከት የሚመለስ እንደሆነ ወ/ሮ አዳነች ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ዕድሳት በመጀመሩ ምክንያት የከተማ አስተዳደሩ ለከተማው ምክር ቤት የሚሆን ቢሮ ከማመቻቸት ጋር በተያያዘ መጉላላቶች እንደነበሩ በምክር ቤቱ የማጠቃለያ ጉባዔ ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ ለጊዜው በተለምዶ ማዘጋጃ ቤት የሚባለው ሕንፃ ተጠናቆ ምክር ቤቱ እንደሚዘዋወርና ሆኖም የአዲስ አበባ ምክር ቤት ቋሚ የሆነ ጽሕፈት ቤትና የመሰብሰቢያ አዳራሽ ያስፈልገዋል የሚለውን ከግምት ውስጥ በመክተት፣ ፒያሳ አካባቢ እየተገነባ በሚገኘው የዓድዋ ቤተ መዘክር ራሱን የቻለ አዳራሽና ጽሕፈት ቤት እየተገነባለት እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ችግር የከተማ አስተዳደሩ የሚረዳው እንደሆነ የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ፣ ከተማዋ የአፍሪካ ኅብረትና የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ እንደ መሆኗ መጠን አዲስ አበባን የሚመጥን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለአዲስ አበባ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ያስረዱት ወ/ሮ አዳነች፣ በቅርብ ቀን ሌላ ተጨማሪ ጣቢያ ለማቋቋም ከውጭ ኩባንያ ጋር ስምምነት መፈጸሙንና ለመሬት አቅርቦት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡