በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተካሄደው ሁለተኛ ዓመት የውኃ ሙሌት፣ የግድቡን ሁለት ተርባይኖች ወደ ኃይል ማመንጨት ሥራ ለማስገባት በሚያስችል ደረጃ ተሞልቶ መጠናቀቁ ተገለጸ።
ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት ሰኞ ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀትር ላይ ተጠናቆ፣ ወደ ግድብ የሚመጣው ውኃ በግድቡ መካከለኛ ክፍል አናት ላይ መፍሰስ ጀምሯል።
በሐምሌ ወር መጀመርያ ላይ በተጀመረው ሁለተኛው ዙር የግድቡ የውኃ ሙሌት 13.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ለመያዝና በዚህም መሠረት ባለፈው ዓመት የተያዘውን የውኃ መጠን ጨምሮ፣ በአጠቃላይ ከግድቡ ጀርባ የሚተኛውን የውኃ መጠን 18.4 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ማድረስ ታቅዶ ነበር።
ይሁን እንጂ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በዕቅድ የተያዘውን ግብ ሳይመታ ግድቡ በመሙላቱ፣ ውኃው በግድቡ መካከለኛ ክፍል አናት ላይ መፍሰስ ጀምሯል።
በሁለተኛው ዙር የተያዘውን የውኃ መጠን በግድቡ ለመሙላትና ዕቅዱን ለማሳካት የግድቡን መካከለኛ ክፍል ግንባታ ባለፈው ዓመት ከነበረበት 565 ሜትር (ከባህር ጠለል በላይ) ከፍታ ወደ 595 ሜትር ማድረስ ይጠይቅ የነበረ በመሆኑ፣ የግንባታ ክንውኑ ወደሚፈለገው 595 ሜትር ከፍታ ሳይደርስ ከፍተኛ የውኃ መጠን ወደ ግድቡ በመምጣቱና ግንባታው የደረሰበት ከፍታ ድረስ ተሞልቶ በግድቡ መካከለኛ አናት ላይ መፍሰሱ አይቀሬ ሆኗል።
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለግብፅና ለሱዳን የውኃ ሚኒስትሮች በላኩት ደብዳቤ የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት መጀመሩን ማስታወቃቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህ ደብዳቤያቸውም የውኃ ሙሌቱ በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ 6.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንደሚያዝና ቀሪውን 6.6 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ደግሞ በነሐሴ ወር የመጀመርያ ሳምንት ገደማ እንደሚሞላ፣ አጠቃላይ የውኃ ሙሌቱም እስከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ድረስ ሊጠናቀቅ ይችላል የሚል ግምት መኖሩን አስታውቀው ነበር።
‹‹ዛሬ ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. የሁለተኛው ዓመት የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ተገባዶ ውኃው በግድቡ አናት ላይ ፈሷል:: ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችም እንኳን ደስ አላችሁ፤›› በማለት ስለሺ (ዶ/ር) ሁለተኛው ዙር የግድቡ ውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ከሥፍራው ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብስረዋል።
ሚኒስትሩ በዚህ የውኃ ሙሌት የተያዘው የውኃ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ባይገልጹም፣ ‹‹ይህ ስኬት ማለት በግድቡ የተተከሉትን ሁለት የቅድመ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገውን የውኃ መጠን ይዘናል ማለት ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል።
ዘንድሮ እየዘነበ ያለው ውኃ መጠን እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከፈጣሪ የተሰጠን ፀጋ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነና እንዴት እያገዘን እንደሆነ መረዳት እንችላለን። ለዚሁም ምሥጋና ይግባው፤›› ብለዋል።
በቀጣዮቹ ወራት ሁለቱን የቅድመ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ወደ ሥራ በማስገባት ኃይል እንዲያመነጩ ብርቱ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፣ ይህንን ተግባር በፍጥነት በማጠናቀቅ ለውጤት እንደሚደርስና ይህንንም ለሕዝብ እንደሚያበስሩ ገልጸዋል።
በግድቡ የተተከሉት ሁለቱ የቅድመ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች የታችኞቹ ተርባይኖች በመባል የሚታወቁ ሲሆን፣ ይህንን ስያሜ ያገኙትም ተርባይኖቹ በግድቡ የታችኛው አካል ማለትም በ60 ሜትር ከፍታ (ከባህር ጠለል በላይ 560 ሜትር ) ላይ የተገጠሙ በመሆናቸው ነው።
ይህም ማለት ከ560 ሜትር ከፍታ በላይ የተጠራቀመ ውኃ በከፍተኛ ጉልበት ተርባይኖቹን ለመምታት እስከቻለ ድረስ የተርባይኖቹ ኃይል ለማመንጨት ይችላሉ።
በሁለተኛው ዙር ሙሌት የተያዘው የውኃ መጠን ባይገለጽም ወቅታዊ ገጽታን ከሚያሳዩ የግድቡ ሙሌትና የግንባታ ከፍታ ምሥሎች የሚታየው ውኃ ከ560 ሜትር ላቅ ያለ ከፍታ ላይ፣ ነገር ግን ከ595 ሜትር ከፍታ በታች ቢሆንም በቂ የመባል የመወርወሪያ ከፍታ ያገኘ በመሆኑ ሁለቱን ተርባይኖች በማንቀሳቀስ ኃይል ለማመንጨት እንደሚያስችል ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ (ኢንጂነር)፣ ‹‹ማሳካት የምንፈልገው ግብ ኃይል ማመንጨት ነው። በሁለተኛው ዙር የግድቡ የውኃ ሙሌት የተያዘው የውኃ መጠን ይህንን የምንፈልገውን ግብ ለማሳካት ያስቸለናል፤›› ብለዋል።
ክፍሌ (ኢንጂነር) በሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በግድቡ መያዝ የተቻለውን ጨምሮ፣ በአጠቃላይ በግድቡ የታቆረውን የውኃ መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ቀጣዩ ተግባር ሁለቱን የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ወደ ሥራ ማስገባት እንደሆነና ይህም በጥቂት ወራት ዕውን እንደሚሆን ገልጸው፣ ሁለቱ ተርባይኖች እያንዳንቸው 375 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ቢኖራቸውም ወደዚህ ደረጃ የሚደርሱት በሙሉ አቅማቸው መሥራት ሲጀምሩ መሆኑን፣ ይህንንም ለማሳካት ውኃው ተርባይኖቹን ለመምታት የሚወረወርበት ትልቁ ከፍታ ላይ መድረስ እንደሚኖርበት አስረድተዋል።
ይህም ማለት ሁለቱ ተርባይኖች የቅድመ ኃይል ማመንጨት ተግባራቸውን በቅርቡ ሲጀምሩ፣ ሙሉ በሙሉ 750 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫሉ ማለት እንዳልሆነና ወደዚህ አቅም የሚደርሱት በሒደት እንደሚሆን ገልጸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን፣ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው አስተላልፈዋል።
በተመሳሳይ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኰንን፣ ‹‹ተፈጥሮ የሰጠችንን ታላቅ ፀጋ አልምተን ለመጠቀም በገንዘባችሁ፣ በጉልበታችሁ፣ በላባችሁና በዕውቀታችሁ ባደረጋችሁት ብርቱ ርብርብ ለዚህ ታሪካዊ ስኬት በመብቃታችን እንኳን ደስ አለን፤›› ብለዋል።
አክለውም በዚህ የስኬት ግለት ኢትዮጵያን ለውጭ አካላት ተጋላጭ የሚያደርጉ ኃይሎችን በተባበረ ክንድ መመከትና ሴራቸውን ማምከን ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
‹‹የታላቁ ህዳሴ ግድብ ታሪካዊ ፕሮጀክት በዚህ የስኬት ደረጃ ያደረሰ፣ እንዲሁም በብዙ ጫናዎች ሳይበገር ሰላማዊ ምርጫ ያካሄደ ሕዝብ አንድነቱን አጥብቆና ጠብቆ ሲቆም ለውጤት እንደሚበቃ ትልቅ ማሳያ መሆኑን መመልከት ይቻላል። ኢትዮጵያን በየትኛውም አቅጣጫ የሚዳፈሩና የውጭ አካላት ፍላጎት አስፈጻሚ የሆኑ ኃይሎች ዳግም እንዳይመለሱ ሕዝቡ ተባብሮ ኃያልነቱን ማረጋገጥ አለበት፤›› ብለዋል።