Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

በክረምቱ ምክንያት ሥራ ከመቆሙ በፊት ልደታ የሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሄጄ በመመለስ ላይ ነኝ፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት የምሟገትበት ጉዳይ አላልቅ ብሎኝ በወር አንዴም ቢሆን በቀጠሮ እቀርባለሁ፡፡ የእኔና የተከራካሪዬ ጉዳይ በሽምግልና ማለቅ ሲገባው በእሱ ግትር አቋም ምክንያት ስንከራከር ሁለት ድፍን ዓመታት አልቀው ሦስተኛውን ይዘናል፡፡ በቀደም እንኳ እዚያ የሄድኩት የቀጠሮውን ቀን የያዘው ማስታወሻዬ ስለጠፋብኝና ጠበቃዬም ውጭ አገር ስለሄደ በመዝገብ ቤት በኩል ላጣራ ነበር፡፡ መስከረም ሲብት ክርክራችን ስለሚቀጥል ቀኑን ማወቅ ነበረብኝ፡፡ የቀጠሮውን ቀን አውቄ ወደ መኪናዬ ሳመራ ድንገት አንዲት ሴት መጥታ ድቅን አለችብኝ፡፡ ከዚህ በፊት አይቻት ስለማላውቅ ግራ ገብቶኝ አያት ጀመር፡፡ እሷ ግን ፈገግ ብላ ታየኛለች፡፡

ዕድሜዋ በግምት አርባው አጋማሽ ላይ የምትሆንና በምቾት ላይ ያለች የምትመስል ሴት አሁንም መንገዱን ዘግታብኝ ሳቅ እያለች ታየኛለች፡፡ ‹‹ይቅርታ እንተዋወቃለን?›› በማለት ፈራ ተባ እያልኩ ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ይህች ሴት መልስ ሳትሰጠኝ ከትከት ብላ ሳቀች፡፡ ይኼኔ ነው መፍራት፡፡ እሷ ስትስቅ እስቲ በልጅነት ወይም በወጣትነት የማውቃት ትሆን ብዬ አተኩሬ ሳያት አንዳችም ምልክት አጣሁ፡፡ ‹‹የእኔ እህት እባክሽን ማን እንደሆንሽ ንገሪኝ?›› የሚል የተማፅኖ ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ የማላውቃት ሴት እንደሚያውቀኝ ሆና አጠገቤ ቆማ ስትስቅ ለሚያየኝም ደግ አይደለም፡፡ ባለትዳርና የልጆች አባት ስለሆንኩ እሳቀቃለሁ፡፡

ሴትየዋ ‹‹ወይ ጉድ? አላውቅሺም ልትለኝ ነው? ሌላው ቀርቶ ያ አንከራታች የፍቅር ጊዜያችን ይረሳኻል?›› ስትለኝ በድንጋጤ ጀርባዬ ላይ ላብ ሲንቆረቆር ተሰማኝ፡፡ አናቴን በዱላ የተመታሁ ይመስል ደነዘዝኩ፡፡ ድንዛዜ ውስጥ ሆኜ የተናገረቻቸው ቃላት ጭንቅላቴ ውስጥ ሲያስተጋቡ የሴትየዋ ሳቅ ታክሎበት ጭልምልም አለብኝ፡፡ በግምት ለአንድ ደቂቃ ያህል ዓይኖቼን ጨፍኜ ከቆየሁ በኋላ ስከፍታቸው ሴትየዋ ፊለ ፊቴ ተገትራ ትስቃለች፡፡ መንገድ ላይ የሚተላለፉ ሰዎች የእኔን ሁኔታና የእሷን አሳሳቅ እያዩ በመገረም ያልፋሉ፡፡ እኔ በሥራዬ ምክንያት ብዙ ሰዎችን ስለማወቅ የምገባበት ጠፍቶኛል፡፡ ‹‹ይቅርታ የእኔ እህት አንተዋወቅም፤›› ብያት ገፋ አድርጌያት ላልፍ ስል እጄን ግጥም አድርጋ ያዘችኝ፡፡ ጉድ ፈላ፡፡

- Advertisement -

አሁን በዚህ ድንጋጤና መሸበር ውስጥ ሆኜ ከሴትየዋ ጋር መታገል ተገቢ ስላልመሰለኝ ዝም ብያት ቆምኩ፡፡ ‹‹ከፈለግህ መኪናህ ውስጥ ገብተን የት እንደምንተዋወቅ ልንገርህ፤›› ስትለኝ፣ ‹‹ኧረ እኔ መኪና የለኝም፤›› አልኳት፡፡ እጄ ላይ የሚታየውን የመኪና ቁልፍ እየነካካች፣ ‹‹ይኼው መኪና አለህ፤›› ብላኝ ሳቀችብኝ፡፡ ‹‹እባክሽ መኪናዬ ጋራዥ ስለሆነች ነው እንጂ መኖሩንማ አለኝ፡፡ አሁን የተገናኘነው ራይድ ጠርቼ ልሄድ ስል ነው፤›› በማለት በፍፁም መኪናዬ ውስጥ እንዳትገባ መከላከያ አቀረብኩ፡፡ ኋላ ገብታ ሌላ ጣጣ ብታመጣብኝስ? ‹ተደፈርኩ፣ ተቀማሁ፣ ተመታሁ፣› ወዘተ ብላ ውርደት ውስጥ ብገባስ? በዚህ መሀል ወደ መንገዱ ማዶ እያሳየችኝ ‹‹ካፌ ገብተን እናውራ፤›› ብላኝ ፈቃደኝነቴን ሳትጠይቀኝ ጎተተችኝ፡፡ ምንም ማድረግ ስላልቻልኩ ተከተልኳት፡፡ ቢያንስ ይኼኛው ይሻላል፡፡

ካፌው ውስጥ ገብተን እኔ ውኃ እሷ ማኪያቶ ካዘዝን በኋላ የተረጋጋሁ መስዬ፣ ‹‹እቱ የት ነው የምንተዋወቀው?›› ስላት፣ ‹‹አይ የድሮው ግርማቸው አሁን አላውቅሽም ነው የምትለኝ?›› ብላ አፍጥጣ ስታየኝ ደነገጥኩ፡፡ ለካ ስሜንም ታውቃለች፡፡ ‹‹ማ. ነ. ሽ. አ.  ን. ቺ…?›› በማለት ቃላቱን ስጎትት ከት ብላ ሳቀችብኝ፡፡ እንዴ ይህች ሴት ማን ናት? በመሀል ስልኳ ሲጮህ ከእጅ ቦርሳዋ አውጥታ አየት አደረገችውና መልሳ ዘጋችው፡፡ ትንሽ ቆይቶ ሲጮህ ‹‹አንሺው እንጂ›› አልኳት፡፡ ‹‹ከአንድ ሰዓት በኋላ እመጣለሁ፣ ቼኩን ስለፈረምኩልህ ትወስዳለህ ጠብቀኝ!›› ብላው ዘጋችበት፡፡ ማን ትሆን ይህቺ ሴት?

‹‹ለመሆኑ እኔና አንቺ የት ነው የምንተዋወቀው?›› በማለት አዲስ ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ‹‹ካምፓስ ስድስት ኪሎ…›› ብላ መለሰች፡፡ ‹‹የትኛው ዲፓርትመንት?›› በቤቴ ልይዛት ነው፡፡ ‹‹ኢኮኖሚክስ?›› አለች፡፡ ‹‹ከመቼ እስከ መቼ?›› ስላት፣ ‹‹ከ1979 ዓ.ም. እስከ 1982 ዓ.ም.›› ስትል ልክ ናት፡፡ ‹‹መቼ ነበር በፍቅር የምንተዋወቀው?›› ስላት፣ ‹‹ዓይን ለዓይን እየተያየን ያሳለፍናቸው አራት ዓመታት ይረሱሃል?›› አለችኝ፡፡ እኔ እንኳን ከእሷ ጋር የዓይን ፍቅር ሊይዘኝ ቀርቶ አይቻትም አላውቅም፡፡ ይህች ሴት ልታውቀኝ ትችላለች ነገር ግን እኔ በጭራሽ ስለማላውቃት፣ ‹‹እንግዲህ እኔ ትዝ አላለኝም፡፡ አንቺ ግን ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ እንዴት አስታወሽኝ?›› በማለት በመገረም ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው የገጠመኝ፡፡

‹‹ለካ አራት ዓመት ሙሉ በዓይኖቼ ስዳስስህ አንተ አታየኝም ነበር? እኔ እኮ የዘመኑ ዓይን አፋርነት ጋርዶህ በይሉኝታ ተሸብበህ የምትኖር መስሎኝ ነው እንጂ፣ ልበ ድንጋይ መሆንህን ባውቅ ኖሮ መቼ አናግርህ ነበር?›› ብላኝ በጥፊ አጩላኝ ሄደች፡፡ እሷ በንዴት ወንበሩንና ጠረጴዛውን ገፋፍታ ስትወጣ ካፌው ውስጥ ያሉ ሰዎች ዓይኖች እኔ ላይ ቀሩ፡፡ በድንጋጤ ውስጥ ሆኜ ተፈናጥሬ ስወጣ አስተናጋጁ ተንደርድሮ መንገድ ላይ ይዞኝ ሒሳብ ሲያስከፍለኝ ዕብድ እመስል ነበር፡፡ ይኼንን የማይታመንና የሚያስገርም ነገር ለጓደኛዬ ብነግረው፣ ‹‹ለጊዜው እግዜር አውጥቶሃል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ትዝታና ድብርት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አደጋ ሊያደርሱ ስለሚችሉ ጠንቀቅ በል…›› ካለኝ ወዲህ በሐሳብ እየባነንኩ ነው ያለሁት፡፡ አሁንማ ያቺን ሴት እያሰብኩ መገለማመጥ ሆኗል ሥራዬ፡፡

(ግርማቸው አ. ከሪቼ) 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...