በፀጋ ቁምላቸው
በአገራችን ከነበረውና ካለው ተሞክሮ አኳያ በርካታ የአገራችን ምሁራንና ተቆርቋሪ ግለሰቦች በዚህና መሰል የአገራችን ጋዜጦች ላይ የሚያሳስቧቸውን፣ የሚያስጨንቋቸውንና ዕረፍት የሚነሷቸውን የአገር አንገብጋቢ ችግሮች ሲጽፉ፣ መፍትሔ እንዲፈለግላቸው ሲያሳስቡ፣ የመጨረሻ ውጤታቸውም አገርንና ወገንን እንደሚጎዳ ሲያስጠነቅቁ፣ ለሰላማችንና ለዕድገታችንም መሰናክል ሆነው እንደሚኖሩ፣ አገሪቱንም ከዘመኑ የዓለም ሒደት ጋር እያጣረሱ ዘወትር ‹‹ባለህበት ሂድ›› ዓይነት ጉዞ ላይ ይዘዋት እንደሚዘልቁ ደግመው ደጋግመው ሲያሳስቡ፣ በአንፃሩ ገንቢና መልካም ነገሮችንና ሒደቶችንም እያነሱ ሲያወድሱና ሲያበረታቱ ኖረዋል፡፡ ከጥቂት ጊዜ ወዲህም ጥቂቶቹ ለእርስዎ ‹‹ይድረስ›› እያሉ ሲጽፉ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ እኔም ለዓመታት በውስጤ ሲብሰለሰል ለቆየው አገራዊ ምልከታና ለጠነከረ ግላዊ ጭንቀቴ ምንም መፍትሔ ስላጣሁ፣ እነሆ ዛሬ ይድረስ ለእርስዎ ለማለት ወሰንኩ፡፡
ይህች እናት አገራችን ወትሮም ሆነ አሁን ምርጥና እጅግ ላቅ ያለ ሰብዕና የነበራቸውንና ያላቸውን ልጆቿን ስታፈራ ኖራለች፡፡ እነዚያ የአገርና የወገን ልዩ ፍቅር ተዋህዷቸው የተፈጠሩ ግለሰቦች በሕይወት ዘመናቸው ለአገርና ለወገን እጅግ ላቅ ያለ አገልግሎት አበርክተውና እጅግ የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያልፋሉ፡፡ እንዳለፉት እንደ እነዚያ በርካታ ጀግኖቻችን አይሁን እንጂ ጥቂቶች አሁንም አሉን፡፡
ታዲያ እነዚያ አኩሪ ጀግኖቻችንም ሆኑ አሁን ያሉን ልሂቃን በሕይወት ዘመናቸው ማንነታቸው በሚገባ ሳይታወቅ፣ ወገናቸው ሳይረዳቸው ይቆዩና ስለእነሱ ማንነትና እንዴትነት የሚወሳው በሕልፈተ ሕይወታቸው ጊዜ ብቻ ይሆናል፡፡ ያውም ለአንድ ሳምንት ብቻ፡፡ እናም ያ የሳምንት ርብርቦሽም ቀስ እያለ ወዲያውኑ ሲከስም ይታያል፡፡ ይህ ለዘመናት ያየሁት ሒደት ነው፡፡ ከጥቂት ጊዜ ወዲህ ግን በአርቲስቶቻችን አካባቢ የሚታየው የተሻለ ድርጊት በመጠኑም ቢሆን የሚያፅናና ሆኗል፡፡ ከቀብር ሳምንት የሚሻገር የሟች ማስታወሻዎችን ሲሞካክሩ ይታያልና፡፡
በበኩሌ የሰው ልጅ ላቅና ለየት ያለ ባለ ክህሎት፣ ጀግንነትም ሆነ ምጡቅ በሆነ ሰብዕና ለእናት አገሩና ለወገኑ እጅግ ለየት ያለ አበርክቶ ከታየበት፣ ያ ሰው በሕይወት ዘመኑ ሊመሠገንና ሊወደስ፣ ማንነቱንም ወገኑ በሚገባ እንዲገነዘበው ሊደረግ ይገባል እላለሁ፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ሌሎች አገሮች እንደሚያደርጉት ሁሉ ተከታታይ ትውልዶች ስለዚያ ሰው ማንነትና ምንነት አውቀው እንዲኖሩ፣ ከሕልፈተ ሕይወቱ በኋላም መታሰቢያ ሐውልቶችንና (ቤተሰብ ከሚያስቀምጠው አነስተኛ የቀብር ሐውልት ውጪ ማለቴ ነው) መሰል መታሰቢያዎችና ማስታወሻዎች ሊቆሙለት ይገባል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
ዛሬ ይህን ጽሑፍ ይድረስ ለእርስዎ ብዬ ለማለት የወሰንኩትም፣ ለዓመታት በዚህ ዓብይ ጉዳይ ላይ ሲቆረቁረኝ የቆየ ጉዳይ ስላለ ነው፡፡
የጽሑፉ አቅራቢ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹የስፖርት ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ›› በመሆን ለበርካታ ዓመታት ሳገለግል ቆይቻለሁ፡፡ በዚህ የአገልግሎት ዘመኔም የአገራችንን የስፖርት አጀማመር፣ ሒደትና የነበረበትንም ሆነ አሁን የደረሰበትን ደረጃ በሚገባ የማውቅ ይመስለኛል፡፡ በዚሁ መንገድም የአገሪቱን ስፖርት መሥሪያ ቤቱንና የአመራር ባለሥልጣናቱንም የማወቅ ዕድሉ ከሞላ ጎደል አጋጥሞኛል፡፡
ከዚህ አኳያም ለአገራቸው ቀርቶ ለአኅጉራቸው አፍሪካና ለመላው ዓለም ስፖርት ክንውን የላቀ አስተዋጽኦ አበርክተው ያለፉትን የምንጊዜም መኩሪያችንን ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማን፣ በቅርበትና በሚገባ ጠንቅቄ ለማወቅ ዕድሉን ያገኘሁ ነበርኩ፡፡ ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ቀደም ሲል (በወጣትነት ዘመናቸው) ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከዚያም ለብሔራዊ ቡድን ሲጫወቱ የቆዩ ሲሆን፣ ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡም በትምህርት ሚኒስቴርና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አገልግለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በእነዚህ ጥቂት ዓመታት በፅኑ የስፖርት ፍቅር የተነደፈው የይድነቃቸው ተሰማ ልቦና ዕረፍት አላገኘም ነበር፡፡ በመሆኑም በወቅቱ ወደነበሩት በርካታ ባለሥልጣናት እየቀረቡ ያቀዱትን አጀንዳ በተግባር በመተርጎም የሌት ተቀን ጥረታቸውን ቀጠሉ፡፡ ከልብ ጥረት ከተደረገ ደግሞ በተግባር የማይተረጎም ህልም የለምና እሳቸውም የደከሙበትን ጥረት አሳክተው፣ በ1936 ዓ.ም. በስምንት ብር በተከራዩዋት እጅግ አነስተኛ ክፍል የመጀመርያውን የአገሪቱን የስፖርት ጽሕፈት ቤት አንድ ረዳት ብቻ ይዘው ይጀምራሉ፡፡
እነሆ በዚያ ሁኔታ የተጀመረው የአገሪቱ የስፖርት መሥሪያ ቤትም በዘመናት ሒደት አሁን ካለበት ደረጃ የደረሰ ሲሆን፣ በየጊዜው የተቋቋሙት ፌዴሬሽኖቻችንም እንደ ዕድገቶቻቸው በአኅጉርና በዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች መሳተፋቸውን ጀምረው ግንባር ቀደም በሆነው የአትሌቲክስ ውጤታችን፣ የእናት አገራችንን ስም የዓለም ኅብረተሰብ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲሰማውና እንዲያውቀው ለማድረግ ተቻለ፡፡
ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ከ40 ዓመታት በላይ በቆየው አገልግሎታቸው የአገራችንን ስፖርት በዋና ዳይሬክተርነት፣ በረዳት ሚኒስትርነት፣ በምክትል ሚኒስትርነትና በመጨረሻም በኮሚሽነርነት ሲያገለግሉ የኖሩ ነበሩ፡፡ ከአገራቸው ባሻገርም በየጊዜው ለአፍሪካና ለዓለም ስፖርቶች መሪነት በመመረጥ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት፣ የአፍሪካ ስፖርት ኮንፌዴሬሽኖች ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር የክብር ሊቀመንበር፣ የአፍሪካ ስፖርት የበላይ ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባል፣ የኢንተርናሽናል ኦሎምፒክ ኮሚቴ (IOC) አባልና የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽን (FIFA) አባል በመሆን፣ በተለይም በሁለቱ አንጋፋ የዓለም ስፖርት ማኅበራት ውስጥ የተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎችን ሲመሩ የነበሩና እጅግ የላቀ ሰብዕና የተላበሱ መኩሪያችን ነበሩ፡፡
ስለሆነም በሕልፈተ ሕይወታቸው ወቅት ከመላው ዓለም የጎረፈውን የሐዘን መግለጫ የማንነታቸው ምስክርነት ሊሆን የቻለ ነበር፡፡ በተለይም ታዋቂው የኮትዲቯሩ የሥነ ጽሑፍ ሰው የላኩት እንጉርጉሮ ብዙዎቻችንን ለወራት ሲያስለቅሰን ቆይቷል፡፡
‹‹እናልቅስ አፍሪካውያን ወንድሞች፣
አዲስ መከራ አኅጉራችንን መትቷታል፣
አባችን ተሰማ አብቅቷል፣
አሳዛኝ እውነት፣
ጥሩው የአፍሪካ ስፖርት ደቀ መዝሙር በ66 ዓመቱ አልፏል››፣
ወዘተ.
የሚገርመው ደግሞ በሕይወት ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ሞሮኮ ካዛብላንካ ውስጥ ለእኚያ ታላቅ ሰው ከፍተኛው ስታዲየም በስማቸው ተሰይሞ የኖረ ሲሆን፣ እንዲህ ሲያኮሩን ለቆዩት ሰው በአገራቸው ግን ‹‹ለእነ አቶ አብነት ገብረ መስቀል ምሥጋና ይድረሳቸውና በቢሾፍቱ የሚገኘውን የወጣቶች ስፖርት አካዴሚ በአቶ ይድነቃቸው ስም ከመሰየማቸው በስተቀር››፣ በመንግሥት በኩል ታስቦበት ለእሳቸው መታሰቢያ በስማቸው የተሰየመ ነገር አለመኖሩ የብዙዎቻችንን ልቦና ሰብሮት ይኖራል፡፡ የስፖርት ቤተሰቡም ሕመም ሆኖ ቆይቷል፡፡
በዚህ በኩል የአገሪቱን ስፖርት የበላይነት የሚመራው የስፖርት ኮሚሽናችንን በየጊዜው በኃላፊነት ሲመሩ የቆዩት ባለሥልጣናት ላይም ሁኔታው ጣት ሲያስጠቁም ቆይቷል፡፡
የሚገርመው ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ከፊል ክልሎች በርከት ያሉ (ኢንተርናሽናል) ውድድሮችን ሊያስተናግዱ የሚችሉ ስታዲየሞች ተሠርተው እያሉ፣ አንዱም እንኳ በእሳቸው ስም እንዲሰየም አለመወሰኑ የስፖርት ቤተሰቡን ቅስም ሰብሮት ቆይቷል፡፡ ዛሬ እኔ ይህንን ደብዳቤዬን ይድረስ ብዬ ለክቡርነትዎ ልጽፍ የወደድኩትም የግሌን ፅኑ ምኞት ብቻ በመያዝ ሳይሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠረውን የአገራችንን ስፖርት አፍቃሪ የዓመታት ቅሬታ አንግቤ ይህንን የብዙዎችን ፅኑ ምኞትንም በማካተት ለክቡርነትዎ አቤት ለማለት ነው፡፡
የአቶ ይድነቃቸው ተሰማን ማንነትና እንዴትነት በሚገባ ጠንቅቀው እንደሚያውቁት አልጠራጠርም፡፡ ክብር ፕሬዚዳንትነት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ደግሞ በቅርበት የሚያውቁት ሀቅ እንደሆነ በእርግጠኝነት እናገራለሁ፡፡
በመሆኑም ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ይሠራል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውና ሥራው ከተጀመረ በኋላም ለተወሰነ ጊዜ ግንባታው ተቋርጦ የቆየው በአዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ ስታዲየም አሁን ወደ ፍፃሜው እየተቃረበ ስለሆነ፣ ‹‹አደይ አበባ ስታዲየም›› የሚለው ስያሜ ተለውጦ ብርቅዬና ድንቅ የኢትዮጵያ ልጅ በነበሩት ሰው ስም ‹‹ይድነቃቸው ተሰማ ስታዲየም›› ተብሎ ቢሰየም፣ እውነቴን ነው የምልዎ የሚሊዮኖች የረዥም ጊዜ ምኞት ተሳካ ማለት ይሆናል፡፡ ይህም ሁኔታ አንዱን የአገራችንን አጉል ልማድ አርሞና አስተካክሎ የወደፊቱን ጉዞም በእጅጉ ሊለውጠው ይችላል፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው እናት አገራችን በአደይ አበባ የተሞላችና በአበቦች አብባ የምትኖር ናት፡፡ በተለይ ደግሞ በየዓመቱ መስከረም፣ ጥቅምትና ኅዳር ወራት በመጡ ቁጥር መላው የአገራችን አካባቢ በአደይ አበባ አምሮና ተውቦ የብዙዎቻችንም ልቦና በዚያ ውብ ምልክታ ረክቶና ፈክቶ እነዚያን ወራት ያሳልፋል፡፡ እናም ተፈጥሮ ያደለችንን ፀጋ በየዓመቱ እየረካንበት የምንኖር እስከሆነ ድረስ፣ ይህ ስታዲየም ግን በሁሉም መልኩ በእኚያ ምንጊዜም በማንረሳቸው በታላቁ ሰው ስም ቢሰየም ከእኛ በዘለለ የዓለምን ትኩረት ይስባል፡፡ በሚመረቅበት ጊዜም ይህንን ስያሜ ቢቀዳጅ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የዘለዓለም ኩራት ይሆናልና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከልብ አስበውት እዚያ ውሳኔ ላይ እንዲደረስ ቢደረግ እያልኩ ልባዊ የአክብሮት ማሳሰቢያዬን አቀርባለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የስፖርት ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡