በፍልፍሉ በላይነህ ገበየሁ
የኢሕአዴግ መንግሥት አገሪቱን ከተቆጣጠረ ከአራት ዓመታት በኋላ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሥርዓት ገበያ መር እንዲሆን አውጆ፣ በኢትዮጵያ የግል ባንኮች መቋቋማቸው የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህ ባንኮች ይብዛም ይነስም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ አሻራቸውን እያሳረፉ ይገኛሉ፡፡ ባንኮቹ በወቅቱ በተፈቀደ ካፒታል 25 ሚሊዮን ብር የተቋቋሙ መሆናቸውም የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የመጀመርያዎቹ ባንኮች ገበያውን ሲቀላቀሉ የነበረው መነሻ ካፒታል ነው፡፡
ይህም የካፒታል መጠን እስከ 1993 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ሲያገለግል ቆይቶ ኅብረትና ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ገበያውን ከተቀላቀሉ በኋላ፣ የባንክ ሥራን ለመጀመር የተፈቀደ ካፒታል መጠኑ ወደ 75 ሚሊዮን ብር፣ ቀጥሎም የተፈቀደ ካፒታል ወደ 125 ሚሊዮን ብር ከፍ ያለ ሲሆን፣ ይህም እስከ 2007 ዓ.ም. ከዚያም እስከ 500 ሚሊዮን ብር አድጎ አሁን ደግሞ ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ተወስኗል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ከላይ የተጠቀሰው የተፈቀደ ካፒታል መሆኑ ነው፡፡ በወቅቱ ሥራ ሲጀምሩ ግን የተከፈለው ከዚያ በታች እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡
ከዚህ ከመጀመርያ የግል ባንክ አዋሽ አንስቶ በቅርቡ ሥራ እስከ ጀመረው ዘምዘም ባንክ ድረስ 17 የግል ባንኮች ገበያው ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ባንኮች አሁን ባለው ሁኔታ ተደራሽነታቸው ከአገሪቱ ሕዝብ ከ30 በመቶ እምብዛም ያልዘለለ መሆኑን የባንኮቹ መረጃዎች ይጠቁማል፡፡ ከጥቅማቸው አኳያ ካየነው እጅግ ዘርፈ ብዙ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከእነዚህም መካከል የአገሪቱን ኢንቨስትመንት ማሳደግ፣ የባንክ ተደራሽነትና የገንዘብ አቅርቦት፣ የሥራ አጥ ቁጥርን ከመቀነሱ አኳያ ጉልህ ድርሻን ከመወጣታቸውም በተጨማሪ፣ ለመዲናችን ውበትን ያላበሱ ሕንፃዎችን መገንባታቸው ከአገር ገጽታ ግንባታ አኳያ ያስመሠግናቸዋል፡፡ በዚያው መጠን እነዚህ ባንኮች እየሰጡ ከሚገኙት አገልግሎት አኳያ ዓመታዊ የትርፍ መጠናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጅጉ እየጨመረ በመሆኑና በመስኩ ሰፊ ገበያ ያለ መሆኑን በመረዳት፣ ተጨማሪ ከ20 የሚበልጡ ባንኮች ገበያውን ለመቀላቀል አስፈላጊውን መሥፈርት በማሟላት ላይ ይገኛሉ፡፡
እነዚህ ባንኮች ገበያው ውስጥ መቆየታቸው እንዲሁም ሌሎች አዳዲስ ባንኮች ገበያውን ለመቀላቀል የሚያደርጉትን ጥረት ከሚደግፉ ግለሰቦች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ነገር ግን ዛሬ ባንኮች እያተረፉ የሚገኙትን የትርፍ መጠን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮና ከባለ አክሲዮኖቻቸው ከተሰበሰበ ካፒታል ጋር በማወዳደር ለማቅረብ ልሞክርና ወደ ሌሎች ጉዳዮች እንመለሳለን፡፡
አንባቢያን እንዲረዱ የተወሰኑ ባንኮችን የተከፈለ ካፒታል እስከ መጋቢት 2013 ዓ.ም. እና የትርፍ መጠናቸውን ሰኔ 2013 ዓ.ም. እንደ ምሳሌ ለማቅረብ ልሞክር፡፡ የባንኮቹ የተከፈለ ካፒታል የሰኔ 2013 ዓ.ም. ያልተወሰደበት ምክንያት ሰኔ ወር ላይ የተከፈለው ካፒታል የዓመት ትርፍ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ግምት ውስጥ ስለማይገባ ነው፡፡ ለአንባቢያን በሰንጠረዡ ላይ የምትመለከቱት ቁጥር በቢሊዮን የተቀመጠ መሆኑን እንድትረዱልኝ እጠይቃለሁ፡፡
የባንኩ ስም |
የተከፈለ ካፒታል መጋቢት 2013 ዓ.ም. |
ዓመታዊ ትርፍ ሰኔ 2013 ዓ.ም. |
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ |
በሪፖርቱ አልተገለጸም |
20.00 |
አዋሽ ባንክ |
8.08 |
5.7 |
ዳሽን ባንክ |
3.9 |
2.5 |
ኦሮሚያ ኅብረት ባንክ |
3.4 |
2.2 |
ዓባይ ባንክ |
2.7 |
1.1 |
ኅብረት ባንክ |
3.8 |
1.8 |
ዘመን ባንክ |
2.0 |
1.4 |
ከላይ በሰንጠረዥ ያሉት እንደ ምሳሌ ቀረቡ እንጂ ሌሎቹም አብዛኞቹ ባንኮች ካላቸው ካፒታልና በየዓመቱ የሚያስመዘግቡት የትርፍ መጠን ከሚያንቀሳቅሱት ካፒታል ጋር ሲነፃፀር ከ60 በመቶ በላይ ነው፡፡ እነዚህ ባንኮች እንግዲህ ይህንን ትርፍ ያገኙት ከ70 እስከ 80 በመቶ በላይ ከሰጡት ብድር ላይ በወለድ መልክ የሚሰበስቡት ሲሆን፣ ከ20 እስከ 30 በመቶ ከወጪ ንግድ የሚገኝ ትርፍ መሆኑን የባንኮቹ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ መመልከት ይቻላል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገላለጽ እንግዲህ የእነዚህ የግል ባንኮች በአጠቃላይ ከሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ ውስጥ የራሳቸውን ካፒታል ብቻ ከተመለከትን፣ እ.ኤ.አ. መጋቢት 2021 ዓ.ም. 50 ቢሊዮን ማለትም ከሚያንቀሳቅሱት የገንዘብ መጠን ከስምንት በመቶ አይዘልም፡፡ ነገር ግን ከሕዝብ የሰበሰቡት የገንዘብ መጠን ከ590 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ባንኮች ለአስቀማጭ (ለቆጣቢ) ደንበኞቻቸው በዓመት በአማካይ ከ4.5 እስከ 5.75 በመቶ ድረስ ወለድ ይከፍላሉ፡፡ ይህንን ስል ባንኮቹ ሌሎች የተወሰኑ ወጪዎች እንዳሉባቸውም አልዘነጋሁትም፡፡
እንግዲህ የገቢያቸውን ምንጭ ከ70 በመቶ እስከ 80 በመቶ በላይ ከወለድ የሚገኝ ገቢ ነው ካልን፣ ሁሉም በሚባል ደረጃ የግል ባንኮች ላበደሩት ብድር የሚያስከፍሉት የወለድ መጠን ለአጭር ጊዜ ብድር በዓመት ከ14 እስከ ከአምስት እስከ 18 በመቶ የሚደርስ ሲሆን፣ ለረጅም ጊዜ ደግሞ በዓመት ከ16 እስከ 20 በመቶ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በአብዛኛው አምራች ፋብሪካዎች፣ አስመጪዎች፣ አከፋፋዮች፣ ቸርቻሪዎች የንግድ ሥራቸውን ለማሳለጥ ከእነዚህ ባንኮች የሚበደሩ ናቸው፡፡ እነሱም እንደዚሁ የባንክ ዕዳቸውን ከወለዱ ጋር መክፈል ስለሚጠበቅባቸው፣ ይህንን የባንክ ወለድ ጨምረው ትርፍ ማግኘት ስላለባቸው ያለ የሌለ ነገር ተጠቅመው ሸማቹ ማኅበረሰብ ላይ ከሚገባው በላይ ዋጋ ይጭናሉ፡፡
አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር በየትኛውም አገር የሚኖር ማኅበረሰብ ለመሠረታዊ ፍላጎት የሚሆኑትን ሸቀጦች ሁሉ ማምረት ስለማይችል አንዱን ሸጦ ሌላውን የሚሸምት ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ስለባንኮቹ ትርፍ አንብቤ እየተገረምኩ ሳሰላስል ኢትዮ ቴሌኮም ከ56 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን በፋና ዜና ዕወጃ ላይ አድምጬ ደነገጥኩኝ፡፡ ኧረ ለመሆኑ ኢትዮ ቴሌኮም አውሮፓና አሜሪካ ነግዶ ነው? ከእዚህ ሕዝብ ቀምቶ ነው ከበሮ የሚያስደልቀው? ለማንኛውም ከአፍሪካ አገሮችም የቴሌኮም ታሪፍ ውድ ከሆነባቸው አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ በዚህ ርዕስ ላይ ሌላ ጊዜ እመለሳለሁ፡፡ ለዛሬ በጀመርኩበት ርዕስ ላይ ባተኩር ይመረጣል፡፡
እንደ መነሻ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዋሽ፣ አቢሲኒያ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በቅርቡ የትርፍ መጠናቸውን በመገናኛ ብዙኃን ሲገልጹ ሰምተን ደንግጠናል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 20 ቢሊዮን ብር አዋሽ 5.8 ቢሊዮን ብር፣ አቢሲኒያ 2.8 ቢሊዮን ብር፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ 2.2 ቢሊዮን ብር፣ ሌሎች ተጨማሪ ወደ ዘጠኝ የሚጠጉ ባንኮች እንደዚሁ ትርፋቸው ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረሳቸው ከተለያዩ ምንጮች እየሰማን እንገኛለን፡፡ ለመሆኑ ይህንን ትርፍ በመገናኛ ብዙኃን ለሕዝቡ ሲገልጹ ለምን እንደማይከብዳቸው አይገባኝም፡፡ በየትኛውም ዓለም አንድ ድርጅት በአንድ አጋጣሚ ማለትም ተዓምር የተፈጠረ ዕድል ከሌለ በስተቀር ነግዶ ከ70 በመቶ በላይ ትርፍ ሊያገኝ አይችልም፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች (በነገራችን ላይ ይህ የመንግሥት ባንክንም ይጨምራል) ወደኋላ ተመልሰን የአምስት ተከታታይ ዓመታት ትርፋቸውን እንኳን ብንመለከት፣ የካፒታላቸውን ከ60 በመቶ በላይ ትርፍ እያገኙ ነው ያሉ፡፡ ይህ ማለት አስቀማጩ ሕዝብ ያስቀመጠውን ገንዘብ መልሰው ለሕዝብ አገልግሎት በብድር መልክ ለገበያ ሲያቀርቡት በተጋነነ የወለድ መጠን ማኅበረሰብን እያስከፈሉት መሆኑ፣ በራሱ ገበያው ውስጥ እንዲቆዩ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን የራሳቸውን የገንዘብ አስቀማጭ ደንበኞች (ሕዝብ) እየጎዱት እንደሆነ አልተረዱትም፡፡ ምክንያቱም የእነሱ ደንበኛ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከእነሱ አስመጪዎች፣ አምራቾች፣ አከፋፋዮች ወይም ቸርቻሪዎች ላይ ምርትን ስለሚገዙ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በራሳቸው ደንበኞች፣ እንዲሁም በሕዝቡ ላይ የኑሮ ጫና እየፈጠሩ መሆኑን ሊረዱት ይገባል፡፡
ሌላኛው ትርፍ የሚሰበስቡበት መንገድ ደግሞ በውጭ ምንዛሪ ግኝታቸው ነው፡፡ ይህ ዘርፍ ቢዳሰስ ብዙ ሊወራበት የሚችል ነው፡፡ እንዲሁም በሕዝቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠረ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ባንኮቻችን የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ተከትለው ምን እያደረጉ እንዳሉ ሁሉም የሚያውቀውና ገሃድ የወጣ ሀቅ በመሆኑ መናገር አያስፈልግም፡፡ ከተፈለገም ተቆጣጣሪው አካል ይመርምረው፡፡ ለዚያውም አንዳንዴ ለማስቲካና ለከረሜላ ማስመጫ የሚፈቀድ የውጭ ምንዛሪ እያለ ስለእጥረት እናወራለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን ከፍተኛ እጥረት ያለበት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ ባንኮቻችን ትንሽ እንኳን ገበሬው ጋር ወርደው በፋይናንስ ለመደገፍ ሲሞክሩ አይታዩም፡፡ ይህ የባንኮቻችን ችግር ብቻ ሳይሆን፣ የመንግሥታችንም ችግር ነው፡፡ በኋላ እመለስበታለሁ፡፡
በተለይም ደግሞ ግርም የሚለኝ የእነዚህን ባንኮች ተልዕኮ፣ እሴትና የተመሠረቱበትን ዓላማ ላነበበ ሰው አንድ ደስ የሚል ዓረፍተ ነገር ተጽፎ ይገኛል፡፡ “Corporate Social Responsibility” ተቋማዊ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ይገልጻሉ፡፡ ይህንንም ባየሁት ቁጥር እገረማለሁ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ሰብስበው መልሰው የሚያበድሩ ባንኮች፣ ይህንን ሕዝብ ከድህነት ለማላቀቅ ምን ሠርተዋል? ከ80 በመቶ በላይ ገበሬ በሆነበት አገር ገበሬውን ከሞፈርና ቀንበር (ጥንታዊ ማረሻው) መቼ አላቀቁት? ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሥራ ፈተው አገር የሚረብሹ (አንዳንዶች ለእኩይ ተግባራቸው የሚጠቀሙባቸው) ወጣቶችን አደራጅተው ሥራ ለመፍጠር መቼ ሙከራ አድርገው ያውቃሉ? ከተሞች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የቤት እጥረት እንዳለ እየታወቀና ሠራተኛው በቤት ኪራይና በኑሮ ውድነት እየተማረረ፣ እንዲሁም እጮኛሞች ለመጋባት የቤት ኪራይ ውድነትን እያሰቡ ዕድሜያቸው እያለፈ ሲሄድ የአገራችን ባንኮች ግን ይህንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮና የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ፣ ኅብረተሰቡ ቤት ሠርቶ እንዲኖር መቼ ብድር በዝቅተኛ የወለድ መጠን ማቅረብ ቻሉ? ይህንን ጥያቄ ባንኮቻችን ብቻ ሳይሆኑ፣ መንግሥትም መጠየቅ ይኖርበታል፡፡
እንግዲህ ሕዝቡ ላይ የኑሮ ጫና ፈጥረው ካላቸው ሀብት ከ70 በመቶ በላይ ትርፍ የሚሰበስቡና የሕዝቡ ድህነት ምንም ሳያሳስባቸው በቢሊዮን የሚቆጠር ትርፋቸውን በመገናኛ ብዙኃን የሚያስነግሩና እየጨፈሩ የሚገኙት ባንኮቻችን ቆም ብለው ቢያስቡ፣ ለዚህ ምስኪን ሕዝብ የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍና ለመቀነስና ከድህነት ለማውጣት ትንሽ ነገር ብቻ እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ፡፡
በመጀመርያ ደረጃ አራጣ የመሰለ የብድር ወለድ ክፍያችሁን ብትቀንሱ ምናልባት ነጋዴውም በተወሰነ ደረጃ የዋጋ ማሻሻያ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ በየመጽሔቶቻችሁ፣ ማስታወቂያና አጀንዳዎቻችሁ ላይ እንደ ጻፋችሁት በትንሹም ቢሆን ተቋማዊ ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን ብትወጡ፡፡ ይህንን ስል እንደ ምሳሌ የምገልጸው ይህች አገር ከ115 እስከ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ናት፡፡ ለዚያውም ከ20 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በምግብ እጥረት ውስጥ በሚኖርበት አገር፣ ከዚያም አልፎ ከ60 በመቶ በላይ ሕዝቡ መሠረታዊ ፍላጎትን ሟሟላት ባልቻለበት አገር የእናንተ ሚና ቀላል የሚባል አይሆንም፡፡ አንድ ሊደረግ የሚችል የመፍትሔ ሐሳብ ልጠቁም፡፡ በአገራችን ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ በግብርና የሚተዳደር ነው፡፡
እንደሚታወቀው ይህ ገበሬ ያለችውን ትንሽ መሬት አርሶ ለራሱና ለቤተሰቡ እንኳን ቀለብ ማምረት አልቻለም፡፡ ስለዚህ በአንድ አካባቢ የሚኖረውን ገበሬ በማደራጀት ኩታ ገጠም የሆነ መሬቱን አሰባስቦ በማኅበር ተደራጅቶና ብድር አግኝቶ በዘመናዊ መንገድ እርሻውን እንዲከውን፣ ብሎም ባለሙያ ተቀጥሮለት (በባንኮቹ ወይም በመንግሥትም ሊሆን ይችላል) እንዲያርስ ባንኮች በዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ ብድር ቢያቀርቡለት ገበሬውንም ከድህነት ማላቀቅ ይቻላል፡፡
ለባንኮችም የአገር ኢኮኖሚ በአደገና የገበሬው ሕይወት በተቀየረ ቁጥር የእነሱን ዕድገት ያፋጥነዋል፡፡ ከዚሁ ሳልወጣ ዛሬ ለአገራችን፣ ለባንኮቻችን፣ ለአስመጪዎቻችንና ለኢንዱስትሪዎቻችን ችግር የሆነውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን የሚያቀርቡ ገበሬዎች፣ እንዲሁም አርብቶ አደሮችን በማደራጀት ምርትን በስፋትና በብዛት እንዲያመርቱ በዝቅተኛ ወለድ ብድር ከማቅረብም በተጨማሪ፣ በሙያው የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ቀጥረው የራሳቸውን (የባንክ) ባለሙያዎችንም አሠልጥነው ገበሬው ጋር ቢሠሩ ለአገርም ለወገንም ይጠቅማሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በተወሰነ ደረጃ ያሻሽላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ወደ ውጭ የምንልካቸው ምርቶች በአብዛኛው ገበሬው ማሳው ላይ ይበላሻሉ ወይም የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ ጠብቀው አይመረቱም፡፡
ለባንኮቻችን ይህንን ሳስገነዝብ በመንግሥት በኩልም ባንኮችን ሊያሠራ የሚችል መሬትን ጨምሮ የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግና የማኅበረሰብ ንቃተ ህሊና ላይ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም ገበሬው ተደራጅቶና መሬቱን በዋስትና አስይዞ እንዳይበደር መሬት የመንግሥት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በከተሞች ያለውን የኑሮ ውድነትና የቤት ችግር ለመቅረፍ ሠራተኛውን በማደራጀት፣ መንግሥትም መሬትን በማቅረብ፣ ባንኮች ደግሞ በዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ ብድር ቢያቀርቡ የከተማውን ሕዝብ የኑሮ ደረጃ በተወሰነም ቢሆን ይቀየራል ብዬ አምናለሁ፡፡
በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እነዚህ በመንግሥትና በግል ድርጅት ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች፣ አሠሪዎቻቸው ገበሬውና የገበሬው ልጆች ካልሆነም የእነሱ ቤተሰቦች የእናንተ የባንኮች ደንበኞችና የመንግሥት ግብር ከፋዮች ናቸው፡፡ ይህንን ሐሳብ መንግሥት፣ የከተማ መስተዳድሮች፣ እንዲሁም ባንኮች በጥምረት ወደ ተግባር ሊቀይሩት ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ በመጨረሻም አተረፍን የምትሉት ገንዘብ ከዚሁ ሕዝብ ጉሮሮ የተነጠቀ መሆኑን አውቃችሁ፣ ይህንኑ ሕዝብ ከድህነት ብታወጡት ትርፋችሁም ይበልጥ ያድጋል እንጂ አይቀንስም፡፡ እናንተም አድጋችሁ አገርንም መንግሥትንም ታሳድጋላችሁ፣ ታግዛላችሁ፡፡
የሕዝቡ ኑሮ ሲሻሻል እናንተም ትሻሻላላችሁ፣ ይበልጥም ታተርፋላችሁ፡፡ ምክንያቱም የሕዝቡ የኢኮኖሚ መሻሻልና ማደግ የእናንተ መሻሻልና ማደግ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የባንኮቻችንን አደረጃጀት ብንፈትሽ ገሚሱ በብሔር፣ ገሚሱ በሃይማኖት የተደራጁ መሆናቸው በራሱ የኢንዱስትሪው ራስ ምታት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ከሕዝቡ የሰበሰቡትን ገንዘብ ለተወሰነ ቡድን የሚያበድሩበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ገበያውን ለመቀላቀል ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት ላይ የሚገኙ ባንኮችም አደረጃጀታቸው ተመሳሳይ መሆኑ ሁሉም የሚያውቀው ሀቅ በመሆኑና ይህም አደረጃጀት በፖለቲካው መስክ አገርን ዋጋ እያስከፈለ ስለሆነ፣ የንግድ ተቋማት ከዚህ ዓይነት አደረጃጀት እንዲላቀቁ መንግሥትና ተቆጣጣሪው መሥሪያ ቤት የተቋማቱን አደረጃጀት የማስተካከልና እያተረፉ ካሉት ትርፍ አኳያ “ለሕዝቡ ምን መደረግ አለበት?” የሚለውን ሊያስቡበት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥቼ እጠይቃለሁ፡፡ በመጨረሻም በዚህ ሐሳብ ዙሪያ አስተያየት ያላችሁን በዚሁ ጋዜጣ ለመሞገት ዝግጁ መሆኔን በአክብሮት እገልጻለሁ፡፡
በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እስክንገናኝ ቸር እንሰንብት!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ሲኒየር የባንክ ባለሙያና አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡