በገነት ዓለሙ
የምንነጋገርበት ብዙ ነገር አለ፡፡ ይኼ ሁሉ ብዙ ነገር ግን ዝም ብሎ ብትንትን አይደለም፡፡ ወይም ረቂቅ አይደለም፡፡ ልማት፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲ፣ እኩልነት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የማይታለፉና የማይተኩ መብቶች ስለመሆናቸው ጥርጥርም፣ ፀብም የለውም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ በምትገኝበት ሁኔታ ውስጥ ግን እነዚህን (የመሳሰሉትን) ጥያቄዎች ሁሉ በአንድ ላይ የሚያስገብር ትልቅ የመኖርና ያለ መኖር ጥያቄ አለ፡፡ የሁሉም ማነጣጠሪያ መሆን ያለበት ይህ ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ የትግሎቻችን አስፈላጊነትና ፋይዳም መስተዋልና መመዘን የሚገባው በዚህ በትልቁ አደራ ውስጥ ነው፡፡
ምንድነው ይህ ትልቅ አደራ? ጥያቄዎቻችንንና ችግሮቻችንን ሁሉ በአንድ ላይ የሚያስገብር የመኖርና ያለ መኖር ጥያቄ ምንድነው? ቀደም ሲል፣ ‹‹ልማት፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲ፣ እኩልነት…›› ወዘተረፈ ብለን ዘርዝረናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ለምሳሌ ልማትን ብቻ ነጥለን እንውሰድ፡ መነጠል የምንችል ከሆነ፡፡ ለምሳሌ ልማት ሊሳካልን ቀርቶ ከረሃብ የማምለጥ ጥያቄ ዋና እስከ መሆን የገዘፈበትና ክፉ መለያችንም ሆኖ ኖሯል፡፡ ለምን? ስለምን? የዕድገት ችግራችን ያለው የት ቦታ ላይ ነው? ልማትና ዕድገት ያለ ሰላም፣ ያለ ፖለቲካዊ ሰላም፣ ሰላም ያለ ዴሞክራሲ የሚል ጥያቄ ያስከትላል፡፡
የኢትዮጵያ የነፃነት፣ የእኩልነትና የዴሞክራሲ ትግል ከብዙ፣ ምናልባት ከ1966 ዓ.ም. ወዲህ ባለው 50 ዓመት ያህል ጊዜ ውስጥ በደረሰበት የውጣ ውረድና የዕድገት ደረጃ ላይ፣ በተለይም የ2007 ምርጫ ባቋቋመው መንግሥት ላይ በማግሥቱ የተጫረው የሕዝብ ቁጣ በጉልህና በወሳኝነት እንዳስመዘገበው የቡድኖች መንግሥታዊ ገዥነት፣ ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ የሚመነጭበት አዲስ ምዕራፍ ይከፈት ብሎ አወጀ፣ ጠየቀ፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ላይ የወጣው፣ የሕዝብ ድጋፍም ያገኘው በዚህ ሒሳብ ነው፡፡ መንግሥታዊ ሥልጣንን የመሾም፣ ወይም የመቀባት ጉዳይ የነፃና የትክክለኛ ምርጫ ጉዳይ እንዲሆን ደግሞ ፓርቲዎች ማበብ፣ መፍካት፣ አማራጭ ወይም የምናማርጣቸው ፓርቲዎች ራሳቸው የተወሰነ የዴሞክራሲ አመለካከትና ዴሞክራሲያዊ የድርጅት አኗኗርን መለኪያ ያለፉ መሆን አለባቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተዘረዘሩት መሠረታዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከስም ጌጥ ይልቅ መኗኗሪያ መሆን አለባቸው፡፡ ፓርቲን ከፓርቲ በነፃነት አማርጠን ወደ ሥልጣን በሕዝብ ድምፅ የምናወጣውም መሠረታዊውን የሰውነት፣ የዜግነትና የማኅበረሰብ መብቶችና ነፃነቶችን የሚያስከብርና የማያስከብር ፓርቲ/ቡድን የማማረጥ ጉዳይ ሳይሆን፣ ከእነዚያ ውጪና በላይ የሆኑ ተጨማሪ እሴቶችን የማማረጥና የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑም ፖለቲካችን፣ ግንዛቤያችን፣ ንቃታችንና መኗኗሪያችን ገና አልሆነም፡፡
ይህን ሁኔታ ለመለወጥ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚህ ፖለቲካ፣ የሕዝብ ግንዛቤና ንቃት ላይ የተመሠረተ በሕገ መንግሥቱ በራሱ (በተጻፈ ሕግ) የተረጋገጠውን ‹‹የሕዝብ ሉዓላዊነት›› ዕውንና ሥርዓታዊ ለማድረግ የመንግሥት አውታራት (ምርጫ ቦርድ ብቻ ሳይሆን ተክለ መንግሥቱ በሙሉ) ከፓርቲ ወገናዊነት መፅዳትና ገለልተኛ ሆኖ መቀረፅ አለበት፡፡ ለውጡ ችግርና እንቅፋት፣ ጠላትና ጥቃት ያጋጠመው እዚህ ምዕራፍ ላይ ነው፡፡ ትልቁ የመኖርና ያለ መኖር ጥያቄ የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ የልማት፣ የፍትሕ፣ የእኩልነት፣ የነፃነት፣ የዴሞክራሲ ጥቄዎች የሚገብሩት ለዚህ ለትልቁ ጥያቄ ነው፡፡ ትልቁና ቀዳሚው ጥያቄ ደግሞ ለውጡንና ሽግግሩን ከክሽፈት ማዳን ነው፡፡ የሥርዓት ግንባታ ትግሉ ብቻ ሳይሆን የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የሰላም ትግሉ ለውጡን ከክሽፈት ለማዳን ከመረባረብ መነሳት አለበት፡፡ የለውጥና የሽግግር ጅምሩን ከቅልበሳ ማዳንና ተበታትኖ ከመፋጀት ማምለጥ ሌሎችን የአገር፣ የልማት፣ የሰላም፣ የምርጫ፣ የህዳሴ ግድብ ጥያቄዎች የሚያካትት ማዕቀፍና አደራ ነው፡፡
የለውጡና የሽግግሩ ተቃዋሚዎች የምርጫውን፣ የህዳሴ ግድቡን የግንባታም ሆነ የሙሌት ጉዳይ፣ እንዲሁም የሌሎች ነገሮቻችንን አጀንዳ ‹‹እየመዘዙ›› መሣሪያ አድርገው የሚበጠብጡን ይህንን ዋናውን አደራ ሊያስቱን ነው፡፡ ከአምባገነንነት ወጥቶ ወደ ዴሞክራሲ ለመግባት፣ ሕገ መንግሥታዊ መተማመኛ የተሰጠባቸውን መብቶችና አወቃቀሮች ካሰነካከለ አሠራር እነዚህን ነገሮች መኗኗሪያ ወዳደረገ ሥርዓት ውስጥ ለመግባት፣ መብቶችና ነፃነቶች ከእርጥባን የዘለለና ከጉልበተኛ ጥቃት ነፃ በሆነ ደረጃ ህልውናቸው የሚረጋገጥበት ሕይወት ላይ ለመድረስ፣ የመንግሥት አውታራት የገዥው ፓርቲ/ቡድን አሻንጉሊትም ሆነ የተቃውሞ እልህ መወጫ መሆናቸው ቀርቶ የሁሉም የጋራ አለኝታ እንዲሆኑ ለማድረግ፣ በአስተሳሰብ በማኅበራዊ ግንኙነትና በመንበረ መንግሥቱ ላይ የደረሱ ብልሽቶችን ማደስና ገለልተኛነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ጥቃት የደረሰበትም ይኼ የትግል ምዕራፍ ነው፡፡ ጥቃቱ የተቃጣውና የተቀጣጠለውም መንግሥታዊ ዙፋኑን፣ ቢሮክራሲውን፣ በአጠቃላይ የሠራ የፖለቲካ አካላችንን በፍላጎታቸው ልክ ቀርፀው ይንፈላሰሱ ከነበሩት፣ በልሽቀትና በንቅዘት አብክተው ካበላሹት ጥቅመኞችና ገዥዎች አቅጣጫ ነው፡፡
እና ሌሎች ከዚህ ከዋናው ጥያቄ በታች የሚወድቁና አጣዳፊ ያልሆኑ ከዋናው ጉዳያችን ላይ ትኩረታችንን ከሚያነሱና ከሚከፍሉም ሆነ፣ ከሌሎች ጉዳዮችን ማስተናገድ ያለብን በዚህ አጠቃላይ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነንና ዋናውን የለውጥና የሽግግር ነገር ሳንረሳ ነው፡፡ ከዚያ ማዕቀፍና መቃን ሳንወጣ፣ ዓይናችንንም ከዚያ ሳንነቅል ነው፡፡ ከየትኛውም ፓርቲ ወገናዊነት ነፃ የሆነ የተቋማት ግንባታ ትግላችንን ዋናው የጥበብና የትግል መጀመርያችን አድርገን ነው፡፡ ከሞላ ጎደል እዚህ ማዕቀፍ፣ እዚህ የጋራ ግቢና አደራ ውስጥ ሆነን የምርጫውን ጉዳይ አቃለናል፣ አጠናቀናልም፡፡ የህዳሴ ግድቡን ሁለተኛ ሙሌትም አሳክተናል፣ ወይም በማሳካት ላይ ነን፡፡ ይህንን በተለይም የውኃውን ሁለተኛ ሙሌት ጉዳይ እያወላወልኩ የገለጽኩት፣ ወይም ስፈራ ስቸር ያድበሰበስኩት ሙሌቱ እውነት ነው ውሸት? ‹‹በትክክል›› አልተሞላም፣ ወይም ‹‹ሙሉ›› አልተሞላም፣ የተሞላው በከፊል ነው የሚል ወሬ ረቶኝ፣ እንዲህ ያለ ወሬ ፈቶኝ አይደለም፡፡ ውስንነት ያለብን መሆኑ አይካድም፡፡ በየዘርፉም ገመናችን ብዙ ነው፡፡
እንኳንስ ጠላት ያለበት፣ ልማትሽ ለህልውናዬ የአደጋ ነው የሚል የጎረቤት ‹‹ታሪካዊ›› ባላንጣ ያለበት የዓባይ ግድብ ጉዳይ ይቅርና ተራውና እነሱ (የ‹‹ታሪካዊ›› ጠላቶቻችን አገር ኢንቨስተሮች በቀጥታም፣ በተዘዋዋሪም በሚሳተፉበት መስክም ብዙ ገመና አለብን፡፡ በሌላው ጠላትና ምቀኛ በሌለበት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨትና በማከፋፈል ዘርፉም ውስጥ እኮ ኢትዮጵያ ‹‹ጋዛም እንደዚህ መብራት አይጠፋም›› የሚባልባት አገር ናት፡፡ ወይም ይህን ያህል በገዛ ራሳችን የምንስቅበት አገር ናት፡፡ እኛ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሒደት ሆነ ሙሌት ውስጥ የተለመደውና ተመሳሳይ ሕመማችን በሰው ፊት ቢያጋልጠን ነውርና ነውረኛ የሚሆነው ችግሩን የፖለቲካ ደረጃ ሰጥቶ ላሳጣ ባለው ወገን እንጂ፣ የለውጡንና የሽግግሩን ወገኖች አይደለም፡፡ ለውጡና ሽግግሩማ ያነጣጠረው ይህን የመሰለ ብልሽትን ጭምር ከሥሩና ከመዋቅሩ ለመንቀል ነው፡፡
ብልሽቶቻችን ሥርዓታዊ ናቸው፡፡ ዋናው የለውጡና የሽግግሩ ግብም ሥርዓት መገንባት ነው፡፡ ሥርዓት የመገንባት ትግሉ በሕገ መንግሥት መተማመኛ የተሰጠውን የሕዝብ ሉዓላዊነት ዕውን ለማድረግ ነው፡፡ የመንግሥት አውራትን ፓርቲያዊነት ለማፅዳት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ በየአምስት ዓመት ምርጫ መንግሥትነትን የሚሾም ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ዓምደ መንግሥት ሆኖ የተደራጀበትን ፍጥርጥር ለመቀየር ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለ የትኛውም ገዥ ፓርቲ (በክልልም በማዕከልም) ራሱ የመንግሥት ዓምድ ያልሆነበት፣ በምርጫ ወራጅና ወጪ የሆነበት ሥርዓት ለመገንባት ነው፡፡ ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ የለውጡና የሽግግሩ ግብ ያንኑ ያህል በተፈጥሮ ሀብታችን ላይ የመጠቀም መብታችንንና ነፃነታችንን ሙሉ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ ተራ፣ ወይም ረቂቅ ወይም ሥውር ሚስጥር ያለው አባባል አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ ‹‹ለምለምና ድንግል››ም ነች፡፡ ያንኑ ያህልም አጥንቷና ምልጥልጧ ውጥቶ ደረቅና ረሃብ የሚያዘወትራት አገርም ነች፡፡ የተፈጥሮ ፀጋ በራሱ ለዕድገት ምክንያት አይሆንም፡፡ ወይም ዕድገትን በቀጥታ በውጤትነት አያረጋግጥም፡፡ በተፈጥሮ ፀጋ አለመታደልም፣ ድርቅም በራሱ ላለመልማት ምክንያት አይሆንም፡፡ ድንግል የተፈጥሮ ሀብት በአያሌው ታቅፈው እየተላለቁና እየተራቡ ያሉ አገሮች እንዳሉ ሁሉ፣ የተፈጥሮ ጥፋቶችንና ኮትቻነትን አሸንፈው የበለፀጉ አገሮች አሉ፡፡ ይህ ሕዝቦች እርስ በርሳቸው፣ በሕዝቦችና በመንግሥት፣ በተለይም ሕዝብና መንግሥት በተፈጥሮ ሀብት ላይ ባላቸው የባለቤትነትና የመብት ግንኙነት ጭምር ይወሰናል፡፡ ይህን ግንኙነታችንን፣ ፍጥርጥራችንን ወይም በሌላ የታወቀ የፖለቲካና የሕግ ቋንቋ ‹‹ኮንስቲትዊሽናችንን›› የሚወስነው ሕግ ተግባራዊ ማድረግ የለውጡና የሽግግሩ ዓላማ ነው፡፡
የኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ በተለይም በውኃ ሀብቷ የመጠቀም ጠንቀኛ ችግር ምንጭ ግን የውስጥ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተለይም ሙሌት ጉዳይ በምሳሌነት የሚመጣውም እዚህ ውስጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ብዙ የውኃ ሀብት አላት፡፡ ሀብቷን ግን ማልማትና በሀብቷ መብት መጠቀም አልቻለችም፡፡ ሀብቷን ያላለማች፣ የሰማይ ዝናብ ከመጠበቅ ያልተላቀቀች፣ ውኃ እያላት የሚጠማት አገር ናት፡፡ ረሃብንም ለማሸነፍ በመታገል ላይ ናት፡፡ ረሃብን የማሸነፍ ትግሏ፣ በሌላ አነጋገር የግብርናና የኢንዱስትሪ ልማቷ፣ ዞሮ ዞሮ የውኃ ሀብቷን መሠረት ከማድረግ አይወጣም፡፡ የኢትዮጵያ የውኃ ሀብት ልማት ግን ከምናየውና ከምንሰማው በላይ ውስብሰብ ፈተና፣ ደመኛ ጠላት ያለበት ነው፡፡ ደግሞም የኃያላን ፍርደ ገምድልነት ዓይን አውጥቶ በተንሰራፋበት ዓለም ውስጥ፡፡
ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ ፍትሐዊ ድርሻ ይኑረን ብላ የምትታገል አገር ናት፡፡ በተለይም በዓባይ ወንዝ ላይ ከሱዳንም ይልቅ የዋና፣ ምናልባት የብቻ ያህል የተጠቃሚነቱን ድርሻ የያዘችው ግብፅ እስካሁንም ካላት ጥቅም በላይ ገና ተጨማሪ የምትፈልግ፣ ዓባይን የራሷ ብቻ አድርጋ የምታይ፣ በአገሯ ውስጥ ደግሞ የብቻዬ ነው ብቻ ሳይሆን፣ የእኛ ብቻ ነው ብላ የምታስተምርና ‹‹ታሪክ የፈጠረች›› የምትገርም አገር ነች፡፡ የዓባይ ውኃ ጭቅጭቅ ደግሞ ዋናውን ወንዝ ባለመንካት ብቻ የሚላቀቁት ወይም የሚገላገሉት አይደለም፡፡ የዓባይ ውኃ ጉዳይ ዓባይን የሚመግቡ በርካታ ገባር ወንዞችንም የሚመለከት ጭምር ነው፡፡ እዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ይህ ሁሉ ዓይነ ቁራኛ አለብን፡፡ የየትኞቹም የእነዚህ ወንዞች የውኃ መጠን መብዛትና ማነስ ከትንንሽ የመስኖ ሥራዎች፣ የዝናብ ውኃን ከመሰብሰብ፣ ወደ መሬት ከማስረግና ከመሳሰሉ ተግባራት ጋር ሁሉ ውስብሰብ ግንኙነት ያለው ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ደመኛ ጠላት ‹‹የገዛላት›› እለማለሁ፣ ልማት ይገባኛል በማለቷ ብቻ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ የሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ የሚፈጥረው የዝናብ መዛባት፣ እጥረትና ድርቅ የውኃ ፖለቲካውን አባብሶ ኢትዮጵያን ያለ ኃጢያቷ በዳይ የሚያደርግ ችግር አይመጣምስ ማለት እንዴት ይቻላል? ደግነቱ ኢትዮጵያ ራሷን አረንጓዴ እያለበሰች ነው፡፡
ግብፅ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ያላት የአሜሪካ፣ የእስራኤልና የሌሎች በአጠቃላይ የዓረብ አገሮች ግንኙነት መቆጣጠሪያ የሆነችበት ጂኦ ፖለቲካዊ ሥፍራ ለኢትዮጵያ ‹‹ጥሩ›› አይደለም፡፡ ፍርደ ገምድልነትን (የብድር፣ የዕርዳታ ገንዘብ እንዳናገኝ፣ ጫና እንዲበዛብን፣ ፍትሕ እንዲዛባብን፣ አድልኦ እንዲደርስብን) የደገሰብን ይኼው ጂኦ ፖለቲካዊ ‹‹ዕድላችን›› ነው፡፡ በኃይል የመጠቃት አደጋም አለብን፡፡ የዓይነ ቁራኛ ክትትሉ፣ ስለላውና ዛቻው አብሮን የኖረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ልማትና ሰላም እየጠነከረ መሄድ በራሱ፣ ከሁሉም መከላከያዎችና ዘዴዎች በላይ በውኃ ሀብት መብት መገልገልን የማስከበር አቅም መፍጠር በመሆኑ፣ ተቀናቃኞቿ በዚህ ሥጋት ምክንያት ለውጣችንን፣ ሽግግራችንንና ዴሞክራሲያችንን አይወዱም፡፡ ሌላው ቢቀር ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ያሰናክሉናል፡፡ አሁን ደግሞ የውስጥ ችግራችን ለዚህ ይመቻቸዋል፡፡ የዓለም ሚዲያ በአድልኦ ሰክሮ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ እንዲሁም ‹‹ሰብዓዊነት ቀውስ›› (ሒውማኒቴሪያን ክራይስስ)፣ እንዲሁም የትግራይ ክልል ጦርነት ላይ መዓት ባወራበት፣ ‹‹የዓለም ማኅበር›› እውነት አላይም ብሎ ‹‹የአብዬን እከክ ለእምዬ ልክክ›› መርሁን ያለ ኃፍረት ሙያው ባደረገበት ወቅትና ርብርብ ጊዜ ነው ይህንን የግድቡን ሙሌት ያከናወንነው፡፡ ትችት የተሰነዘረበትና ‹‹የቁንጫ ሌጦ›› የወጣበትም ይኼው ስኬት ነው፡፡
እውነት ነው ይህን በመሰለ የአገር አደራ፣ ግዳጅና የአርበኝነት ሥራ ውስጥ ብዙ የሚያሳቀቁ፣ የሚያሳፍሩና የሚያናድዱ ብዙ ‹‹የወገን ጦር››፣ የ‹‹ገብሮ ባላ›› (Own Goal) ሥራዎች አሉ፡፡ እዚህ መደብ ውስጥ የምፈርጃቸው ተግባሮች ቢያንስ ቢያንስ ያናድዳሉ፣ አቤት ድንቁርናችን ያሰኛሉ፡፡ የህዳሴው ግድብ ሁለተኛው የውኃ ሙሌት የስኬት ሥራ የድል ብሥራት የተነገረበትን ሰበር ዜና ያጀበው (ከዚያም በኋላ የሚሰማው) ‹‹እንጉርጉሮ›› አያናድድም? የለውጡና የሽግግሩ ውጤት የሆኑ በተለይም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ማለፊያ ሥራ፣ እጀ ሰባራ የሚያደርገው ሰው አያያዛችን (በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የማድረግ፣ ወደ መቆያ የመውሰድ፣ ይህንንም ለቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ ግልጽ የማድረግ ሥራችን) ለውጣችንንና ሽግግራችንን ከክሽፈት ያድናል? ሌሎችም ብዙ ገመናዎች አሉብን፡፡ እነዚህ ግን ከንግግር በላይ አይደሉም፡፡ ንግግርን አይጠሉም፡፡ በውይይት፣ በንግግር፣ በጽሑፍ፣ በአንደበት መነገርና መገለጽ ያለባቸው ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን የለውጡና የሽግግሩ ምልክትና ውጤት አድርገን በኩራት የምናነሳውና የምናወሳው እኮ እነዚህንም ስለሚናገር ጭምር ነው፡፡ ሚዲያዎችም ችግሮችን ማንሳት፣ መግለጽ፣ መብትና ነፃነታቸው ነው፡፡ መብትና ነፃነታቸው ላይ ‹‹ገብሮ መብላት›› የሚሆነው እነዚህን ጥፋቶችና የለውጥ ገመናዎች የፖለቲካ ደረጃ ሰጥቶ ማራገብና ለውጡንና ሽግግሩን ማጥቃት ነው፡፡ በተለይም በዚህ የለውጥና የሽግግር ጊዜ የመናገርና ሐሳብን በነፃ የመግለጽ ጉዳይ በአንድ ዋና ቀዳሚ ግብ ላይ ማነጣጠር አለበት፡፡ የሚዲያዎች፣ የንግግርና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና ነፃነት ታጋዮች ተቀዳሚ ተግባር ይህን ነፃነት የሚያጎናፅፋቸው ሰላምና ዴሞክራሲ ሥር እንዲይዝና እንዲፀና መታገል ነው፡፡
ዴሞክራሲና ሰላም በሕግ ባልተከለከሉ መንገዶች ሐሳብን ማፋጨትና የሕዝብን አስተያየት መሳብ እንጂ፣ ብዙና በርካታ የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች የተሳፈሩበትንና የሠፈሩበትን መርከቢቱን ራሷን በጥይት፣ በመጥረቢያ፣ በቆንጨራ፣ በገጀራ መፍለጥና መሸንቆር ማለት አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ጥርት ያለ አቋም መያዝና መተግበር አለበት፡፡ የሕግ አስከባሪዎችም ከዚህ አኳያ የሚወስዱት ዕምርጃ በዚህ ‹‹የገብሮ በላ›› (Own Goal) የሚያስከስስ፣ የሚያሳማ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለውጡና ሽግግሩን የሚያሳጣ መሆን የለበትም፡፡ መሠረታዊውና መንዕሱ መንደርደሪያ ግን ሕግ የማስከበር የመንግሥት የሥልጣን አካላትና የባለሥልጣኖቻቸው ተግባርና ዕርምጃ፣ የራሳቸውንም ሕግ የማክበር የውኃ ልክ በጭራሽ የማያስገምት መሆኑ ነው፡፡
በመጨረሻም ስለዓባይ ውኃ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ኢትዮጵያውያን ስለምናደርገው ተጋድሎ ከዚህ በፊትም ደጋግመን የገለጽናቸውን፣ አሁንም በአስፈላጊነታቸው መጠን ደግመው ተደጋግመው መነገር ያለባቸውን አንዳንድ ጉዳዮች እናንሳ፡፡
በጥቅሉ ስለድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችን (በተለይም ስለዓባይ)፣ የጋራ ፍትሐዊ ጥቅሞቻችን፣ በውስጥና በደጅ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ተወላጆች ጋር ተያይዘው የሚሠሩበት የጥናት/የመረጃ ማደራጃና ማፍለቂያ ማዕከል ተቋቁሞ፣ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች (ቢያንስ ዓረብኛንና እንግሊዝኛን በደንብ በሚያፈሱ አንደበቶችና ብዕሮች) ዕቅጮችን፣ ቅጥፈቶችንና እውነቶችን በረቺ መከራከሪያ እየፈለቀቁ ለመላው ዓለም (ለአፍሪካ፣ ለግብፅና ለመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ፣ ለአውሮፓና ለአሜሪካ፣ እንዲሁም ለዋናዎቹ ዓለም-ገብ መድረኮች) ከጊዜ ጊዜ ማሳወቅ የማንዘናጋበት ግዴታችን መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ በዚህ ረገድ ከብዙ አቅጣጫ ምክረ ሐሳቦች፣ መረጃዎችና የመከራከሪያ ቢጋሮች፣ ወዘተ መፍሰሳቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን የታዩኝን ጥቂት ነጥቦች ልወርውር፡፡
- ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር የምትጋራቸውን ውኃዎች በሰላምና በፍትሐዊነት ለመጠቀም የምታደርገው ትግል ለመግባቢያነት በቅቶ በተግባር እንዲዘልቅ፣ እንቅስቃሴዋና ገጽታዋ በየትኛውም ደረጃ ላይ ቀዳዳ የሌለውና በቀላሉ የማይበገር የጥቃት መከላከያ (ኢንሱሌሽን) ማበጀቱ መሠረታዊ ነው፡፡ ለመጠቃቀስ፣ በአዋሳኝ ጎረቤቶቿ ዘንድ ከአንዳቸውም ጋር ቢሆን በወዳጅነት ረገድ አለመራቆቷ፣ የመከላከያና የመረጃ ኃይሏን ከማዘመንና ሸርን አነፍንፎ ከማምከን ባሻገር ሸርን በሽር አለመመለሷ፣ የራሷን ልማት ስታይ የሌላውን ጥቅም ላለመጉዳት መጠንቀቋ፣ ከዓባይ ውኃና ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ለፍትሐዊ የጋራ ጥቅም ያላትን ራስ ወዳድ ያልሆነ አቋም፣ ከሌሎች ጎረቤቶቿም ጋር የምትተቃቀፍበት መርህ መሆኑን ማሳወቋና በዚሁ መሠረት የማይዋዥቅ ትስስር መፍጠሯ፣ ከሁሉም በላይ የአገር ውስጥ ጠንካራ ሰላም ማበጀቷና ግስጋሴዋ መቀጠሉ አንድ ላይ ውጤታቸው ከፍተኛ ነው፡፡
- የልዕለ ኃያላንና የኃያላን አድሏዊ ጣልቃ ገብነት በዓለማችን ውስጥ በተለያዩ ቀጣናዎች ሰላምንና ፍትሐዊ ጥቅቅምን ሲጎዳ፣ ጠንቅ ሲተክልና ሲያባላ ኖሯል፡፡ በተለይ ከቅኝ ግዛት መስፋፋት አንስቶ፡፡ በዓባይ ተፋሰስ አካባቢም እንዲሁ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያና የሌሎች የናይል/የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ትግል መምጣትና ዛሬ የደረሰበት ደረጃ መድረስ፣ የተተከለ ጠንቅንና አድላዊነትን የማስተካከል ነው፡፡ እናም አሮጌ አድሎኛ ‹‹ባለድርሻነትን›› ታሪካዊ መብት አድርጎ በኃይል፣ በልዕለ ኃያላዊ ጫናና በቀጣፊ መከራከሪያ ለማስቀጠል መሞከር ከንቱ ድካም ነው፡፡ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ያነሱት የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ በምንም መንገድ ወደ ኋላ ሊመለስና ሊታነቅ የማይችል፣ መቀበልን ግድ የሚል ነው ዛሬ፡፡ ምክንያቱም በፍትሐዊነት ተሳስቦና ተባብሮ በሰላም ለማደግ መታገል፣ የምሥራቅ አፍሪካና የመላ አፍሪካ የዘመኑ ጥያቄ ስለሆነ፡፡ ይህ ሁላችንን አቀፍ ጥያቄ ፈክቶ መውጣት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
- የኢትዮጵያን ከድህነት የመውጣት (የመልማት) ጥረት ለማፈን መሞከር፣ የኢትዮጵያን የውስጥ ሰላም መበጥበጥና ጦርነት መክፈት፣ (ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ የመቀነስ አንዳችም ተንኮል ውስጥ ሳትገባ)፣ የግርጌ አገሮችን በዓባይ ውኃ የመጠቀም ዕድል ላይ ክፉኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡ በየትኞቹም የደባና የኃይል ሥልቶች የኢትዮጵያን ድህነት የማስቀጠል ተግባር፣ በራሱ በረሃማነትንና የዓባይ ውኃ መበከልን በማስፋፋት የውኃውን መመናመን ማስከተሉ ያፈጠጠ ሀቅ ነው፡፡ በረሃማነትን ያለ አረንጓዴ ልማት መታገል እንደማይቻል፣ እኛ ለጎረቤቶቻችንም ሆነ ለዓለም አስታዋሽ መሆን አይጠበቅብንም፡፡ የዓባይን ወንዝ መበከል በተመለከተ የዓባይ ተፋሰስ አገሮችም ሆኑ ዓለም ሊያውቁት የሚገባ እውነት አለ፡፡ ዛሬ የዓባይ ውኃ ከጣና ሐይቅ አንስቶ እንቦጭ በሚባል አደገኛ አረም እየተወረረና በመድረቅ አደጋ ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን አረም ለማጥፋትና ጣናንና ዓባይን ከመድረቅ ለማትረፍ ብቻዋን እየተፍጨረጨረች ነው፡፡ ይህ ትግል ኢትዮጵያ ለራሷ ህልውናና ልማት የምታካሂደው ቢሆንም፣ በተዘዋዋሪ አይደለም በቀጥታ የዓባይ ውኃ ለሱዳንና ለግብፅ ያለው አለኝታነት እንዳይቀንስ የመዋደቅም ትግል ነው፡፡ በአጭሩ ኢትዮጵያ የሱዳንንና የግብፅን የጥቅም ቀንበር ብቻዋን ተሸክማለች፡፡ እናም የኢትዮጵያና የተፋሰሱ አገሮች አረንጓዴ ልማት፣ ለሱዳንና ለግብፅ የዓባይ ጥቅም ዋስትና እንጂ ጉዳት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ሰላምና የልማት ተፍጨርጫሪነት በማገዝ ፈንታ ለማሰናከል መሥራት የዓባይን ውኃ ከምንጩ ለማድረቅ ከሚተጋው ከእንቦጭ አረም ጎን መቆም ነው፡፡ በቀላል ቋንቋ ዓባይ እንዲደርቅ የሱዳንና የግብፅ ግድቦች ላንቃቸው ተራቁቶ ሲሰነጣጠቅ ለማየት ከመሥራት አይለይም፡፡ ይህንን ዓብይ ሀቅ የሱዳንና የግብፅ ሕዝቦችና ዓለም ሊያውቁት ይገባል፡፡
- የህዳሴ ግድብ ባመጣው የፊት ለፊት ጥቅም ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ ላይ አንዳችም ቅናሽ ሳታስከትል ውኃው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ውልብልቢቶችን እየመታ እንዲያልፍ በማድረግ የኤሌክትሪክ ኃይል ታገኛለች፡፡ አዲሱ ነገር ውኃው በግድብ ውስጥ በረዥም የጊዜ ሒደት ተጠራቅሞ ኤሌክትሪክ እያመነጨ ማለፉ ነው፡፡ ተደጋግሞ እንደተነገረውም፣ ውኃው በመገደቡ የግብፅንም ሆነ የሱዳንን ፍትሐዊ የውኃ ድርሻ ይጎዳል የሚል ክርክር ፈፅሞ ሐሰት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፊት ያልነበረ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ጥቅም እንዳገኘች ሁሉ፣ እነ ግብፅም በግድቡ ምክንያት በፊት ያልነበረ (አዲስ) ጥቅም ያገኛሉ ሲባል እንደነበረው ከጎርፍ ጥቃት ይጠበቃሉ፡፡ ግድቦቻቸው በደለል ከመሞላትና ከብክለት ይጠበቃሉ (በህዳሴ ግድብ ሲጠራቀም ያየነው ውኃ አፈራማ እንደ መሆኑ፣ ኢትዮጵያ የአፈር መታጠብና የጎርፍ ጭቃ ጣጣን መቆጣጣር ካልቻለች የግርጌ አገሮች ግድቦች በጭቃ እንዳይሞሉ ከማገልገል እጅግም ያለፈ ጥቅም አይኖራትም)፡፡ በሌላ በኩል የህዳሴ ግድብ ከሞላ ጎደል ፈረሰኛ ውኃና ድርቅ የሚፈጥሩትን ዝባት ስለሚያቻችል፣ ሱዳንና ግብፅ ከዓመት ዓመት የተቀራረበ የውኃ መጠን የማግኘት ዕድላቸውን ያሰፋል፡፡ ይህንን ስናስተውል ነው በኢትዮጵያ ድርቅ በተከሰተ ጊዜ ስለውኃ አለቃቀቅ ‹‹ዋስትና ያለው›› ስምምነት ለመፍጠር የሚደረግ ዓይን ያወጣ ጮካነት የሚጋለጠው፡፡ የህዳሴ ግድብ ተቀዳሚ ተልዕኮ የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪነት ከሞላ ጎደል ሙሉ ዓመት (በድርቅ ጊዜም) የሚካሄድ መሆኑ ዕውቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዝናብ እጥረት በደረሰ ጊዜ ግድብ ከመኖሩ በፊት ዓባይ ከኢትዮጵያ ድንበር ይዞት ከሚያልፈው የበለጠ ውኃ ግድቡ የሚያስገኝ መሆኑም አያከራክርም፡፡ ስለዚህ አንድ ከግድቡ በታች ያለ የዓባይ ውኃ ተጠቃሚ፣ ኢትዮጵያ በድርቅ በተመቻች ጊዜ ዓባይ የሚኖረው የውኃ መጠን ሳይነካ ይምጣልኝ እንጂ፣ ከዚያ ያለፈ ውኃ አይምጣልኝ ቢል ጥቅሜ አልገባኝም የማለት አላዋቂነት ይሆንበታል፡፡ በተቃራኒው ድርቅን ምርኩዝ አድርጎ ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የውኃ ድርሻዋን ሳትጠቀም ለእኔ ልትለቅ ቃል ትሰርልኝ ከሆነ ደግሞ፣ አንቺ በድርቅ ተንጨፍረሪ እኔ ግን ልጠቀም ባይነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በድርቅ በተመታች ወቅት፣ ድርቅ በዓባይ ውኃ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ሁሉም የዓባይ ተጋሪ አገሮች የሚጋሩት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የህዳሴ ግድብ መኖር በዓባይ ውኃ ተጋሪዎች ላይ ድርቅ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ የሚያለዝብ ትሩፋት እንዳለው አጉልቶ ማውጣት አስፈላጊ ነው፡፡ እኔ እስከምረዳው ድረስ ኢትዮጵያ በሚኖራት ፍትሐዊ የውኃ ድርሻ መሠረት ኤሌክትሪክ አመንጭቶ ውኃ ከማሳለፍ የዘለለ ግብርና ነክ ልማት ብታካሄድ እንኳ፣ በግብርና ልማት መጠቀምን እንደምትሻ ሁሉ የኑሮና የልማቷ ሞተር የሆነው የኃይል ምንጭ የጎላ ቀውስ በማይደርስበት አኳኋን ውኃ የሚቀንስ ልማቷን የውኃ ስንቅ ከሚሻው የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪነት ጋር ማቻቻል አይቀርላትም፡፡ እናም የህዳሴ ግድብ ለግርጌ ትሩፋት የማስገኘት ባህርይው፣ ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የውኃ ድርሻዋን በምትጠቀምበት ጊዜም ቢሆን ከፋም ለማም ይቀጥላል እንጂ አይመክንም፡፡ ይህም በአግባቡ ሊጤን ይገባል፡፡
- የህዳሴ ግድብን በጋራ ሱዳን፣ ግብፅና ኢትዮጵያ በሦስትዮሽ እናስተዳድር የሚሉ ሐሳብን ኢትዮጵያ የምትቃወመው ድብቅ ዓላማ ስላላት ሳይሆን፣ ሉዓላዊ የውስጥ መብቷን እንደ ማንኛውም ሉዓላዊ አገር ከማስከበር አኳያ መሆኑን አጠንክሮ ለአፍሪካም ለዓለም ከማሳወቅ ባሻገር፣ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ውኃዎችን ተጋሪ የሆኑ አገሮች ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል ስምምነት ፈጥረው በስምምነቱ መሠረት ፍትሐዊ ድርሻቸውን አክብረው መኖራቸውን በጋራ ያስተዳድሩ የሚል ፖሊሲና ድንጋጌ የአፍሪካ ኅብረት ካበጀና ሥራ ላይ ካዋለ፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር የጋራ ጥቅምን ለማስተዳደር የቅን ፍላጎት ችግር እንደማይኖርባት መግለጽም የሚጠቅም ነጥብ ይመስለኛል፡፡
- ከዚህ ቀደም ፍትሐዊ የዓባይ ውኃ ክፍፍል ሲነሳ ግብፆች ይህንን ለማምለጥና የእኛን የመብት ጥያቄ ሰይጣናዊና ግፈኛ አድርጎ ለማቅረብ የሚጠቀሙበት መከራከሪያ፣ ኢትዮጵያ ብዙ ውኃዎች እያሏት ዓባይን ልትገደብ የተነሳችው ያለ አንድ ናይል ሌላ አማራጭ የሌላትን ግብፅ ለማስጠማትና ለማስራብ ነው በሚል አቅጣጫ ማጭበርበር ነበር፡፡ ዛሬም ይኼው ዘዴ ቀጥሏል፡፡ ፍትሐዊ የውኃ ድርሻን የማስከበር ትግል የግብፅን ህልውና ከማሳጣት ጥቃት ጋር ተዛምዶ እንዲታይ የማድረግ ብልጣ ብልጥነትን ለማክሸፍ፣ ግብፆች በዓባይ ውኃ አጠቃቀማቸው የሚታየውን አድፋፊነት፣ ከመጠቀም አልፈው ግዙፍ የከርስ ምድር ውኃ ማጠራቀማቸውን ለሌላም የሚሸጡ መሆናቸውን፣ ወዘተ በደንብ በተጠናቀረ መረጃ መግለጽ (አሁን እንደተያዘው) አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ግን የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ ያመጣው ግብፅን የመሻማት ስስትና የማጥቃት ፍላጎት ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ከድርቅ ጋር በሚያያዝ ችጋር የመጠቃት ረዥም ታሪካችንን ከሰሜን እስከ ምሥራቅ ደቡብ ድረስ ለመቀየር የተነሳሳ ትግል መሆኑን፣ ከኩራዝና ወደ ሰማይ አንጋጦ ውኃ ከመጠበቅ ጋር የተቆራኘ ሰፊ የድህነት ገጽታችንን ከረዥም የድርቅና የረሃብ ታሪካችን ጋር ሰድሮ ማሳየት ያዋጣል፡፡
- እነዚህ የመሳሰሉ ነጥቦች ከምሁራኑና ከሊቃውንቱ ተዋጥተው የአዋጪነታቸው ጥንካሬ ተገምግሞና በመረጃና በትንታኔ ጉልበት አግኝተው በኢትዮጵያ የዓባይ ፍትሐዊ የውኃ ተጠቃሚነት ጥያቄ ላይ የሚነዙ አሉታዊ ሥዕሎችን ለማስተካከል መሥራት አንድ ነገር ነው፡፡ በጉዳዩ የበሰሉ ሐሳብን በማስረዳትና በቋንቋ አቅማቸው የተቡ መልዕክተኞችን ልኮ ለአፍሪካ፣ ለዓረቡና ለምዕራቡ ዓለም ማስረዳት ደግሞ ሌላ ነገር ነው፡፡ አፄ ምኒልክ በዓድዋ ጦርነት ዋዜማ የአውሮፓ አቋም ኢትዮጵያንም የሚያይ አንጀት እንዲኖረው አውሮፓዊውን አልፍሬድ ኢልግ የተባለ መልዕክተኛ ልከው ሠርቶ ነበር፡፡ ከዚህ መማር ይገባናል፡፡ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጉዳቷንና ፍላጎቷን በፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት የተለካ መሆኑን ለዓለም ማስረዳት ከቻለች፣ ተሳስቦ ከመኖርና ከማደግ ፍላጎታችን ጎን የሚቆሙ ለዚህም የሚናገሩ የቅርብና የሩቅ መልዕክተኞች/ወዳጆች ከዓረቡም ከምዕራቡም ዓለም ማፍራታችን ጥርጥር የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ለዚህ ፍሬያማ ውጤት አልማ መሥራት አለባት፡፡ ስኬቷንም ብዙ
‹‹ባዕድ›› ደጋፊ በማግኘት ፍሬ መመዘን ይገባታል፡፡ ይህ ፍሬ ግን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን በውስጥና በውጭ ላለነው ዜጎች በሚያጠጡን ዝተት የፕሮፓጋንዳ ዘይቤ የመገኘቱ ነገር ሱሚ ነው፡፡ - ይህም ሁሉ ተደርጎ በህዳሴ ግድብ ላይ የተያዘው ድርድር ቢጠናቀቅም፣ ከዓባይ ውኃ ጋር የተያያዙ ጣጣዎች ይዘጋሉ ማለት አይደለም፡፡ ዓባይን በተመለከተ የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ግንኙነቶች ጠንቃቃ እንክብካቤ መፈለጋቸው የሚቀጥል ነው፡፡ ይህ ራሱን የቻለ ሥራ ነው፡፡ ይህን ሥራ ለመወጣት የማይዋዥቅ የውስጥ ሰላም በኢትዮጵያ መገንባቱ ወሳኝ ነው፡፡ የውስጥ ሰላምን ይዞ ከተዋሳኝ ጎረቤቶቻችን ጋር ሁሉም የሚሳሳለት የጋራ ልማት ውስጥ መግባት ደግሞ ዋና መተማመኛችን ነው፡፡ የውስጥ ሰላማችን ዋነኛ ቁልፍ ለውጡንና ሽግግሩን ከክሽፈት ማዳን ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡