Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

​​​​​​​‹‹የአገር ውስጥ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ማስወገድ ችለናል›› አቶ አቤ ሳኖ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአገሪቱ ትልቁ ባንክ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የመንግሥት ባንክ በሚል ስያሜ እ.ኤ.አ. በ1935 ዓ.ም. ነው የተቋቋመው፡፡ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ባለቤትነት ከሚተዳደሩ ሁለት ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የዛሬ 80 ዓመታት አካባቢ ሲቋቋም ከአርባ የማይበልጡ ሠራተኞችና ሁለት ቅርንጫፎችን ይዞ ነው፡፡ ባንኩ ይዞ የተነሳውም የካፒታል መጠኑ እዚህ ግባ የማይባል ነበር፡፡ አሁን ባንኩ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያለው ሲሆን፣ ከ1,700 በላይ ቅርንጫፎችን በተለያየ የአገሪቱ ክልሎች ከፍቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ትልቁ ባንክ ስለመሆኑ ሌላው ማሳያ ደግሞ አጠቃላይ የባንኩ ሀብት መጠን በዚህ ወር ከአንድ ትሪሊዮን በላይ መሻገሩ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የቁጠባ ሒሳብ ካላቸው ዜጎች ግማሽ ያህል ወይም ከ34 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳብ ያላቸው ናቸው፡፡ በአገሪቱ ኢንዱስትሪ ውስጥ በየዓመቱ ለብድር ከሚውለው ገንዘብ ውስጥ እስከ 60 በመቶ የሚሆነው በንግድ ባንክ የሚሸፈን ነው፡፡ ባንኩ መንግሥታዊ እንደ መሆኑ እንደ ፖሊሲ ባንክ በማገልገልም ላይ ነው፡፡ የ80 ዓመታት ዕድሜ ያለው ንግድ ባንክ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖለት እዚህ አልደረሰም፡፡ ብዙ ተግዳሮቶች ገጥሞታል፡፡ ከብድር አሰጣጥና አመላለስ ጋር ብዙ ችግሮች እንደነበሩበት የሚጠቀስ ሲሆን፣ በተለይ ባንኩ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሰጠውን ብድር መልሶ መሰብሰብ አለመቻሉ የባንኩን ህልውና አደጋ ውስጥ እስከ መክተት አድርሶም ነበር፡፡ ወደ 800 ቢሊዮን ብር የብድር ክምችት ያለው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 80 በመቶ አካባቢ የሚሆነው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የወሰዱት ነው፡፡ ባንኩ የነበሩበትን ተደራራቢ ችግሮች ለመፍታትና መፍትሔ ለመስጠት ሥር ነቀል ለውጥ ውስጥ ለመግባት ያስችለኛል ያላቸውን ሥራዎች እያከናወነ ነው፡፡ በተለይ ባንኩን ለሁለተኛ ጊዜ በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ዕድል ያገኙት አቶ አቤ ሳኖ ትልቁ ፈተናም ከዚሁ አልመለስ ካለው ብድር ጋር የተያያዘና ሌሎች የማኔጅመንት ችግሮች ናቸው፡፡ ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት በታሪኩ የመጀመርያ የተባለውን ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፉም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደረገ ያለው የለውጥ ሒደት ውጤት ነው ተብሎ ይጠቀሳል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በፋይናንስ ዘርፉም ሆነ በአጠቃላይ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሚና ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለይ ከብድር አመላለስ ጋር በተያያዘ እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም በወቅታዊ የባንኩ በተያያዥ ጉዳዮች ላይ የባንኩን ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖን ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡ አቶ አቤ ሳኖ በቀድሞ የአርሲ ጠቅላይ ግዛት፣ በሲሬ ወረዳ በ1966 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሲሬ፣ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዳማ ከተማ ተከታትለዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሒሳብ አያያዝ ትምህርት ቢኤ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ አቶ አቤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተቀጠሩት በሐምሌ 1989 ዓ.ም. በኢምፕሎይ ሊደርሺፕ ፕሮግራም አማካይነት ሲሆን፣ ሥራ የጀመሩት በመሀል ከተማ ቅርንጫፍ ነበር፡፡ በባንኩ የአጭር ጊዜ ብድሮች ኦፊሰርነት፣ የብድር ጥናትና ትንተና (በከፍተኛ የብድር ተንታኝነት)፣ በአነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች ብድር በቡድን መሪነት፣ በመጨረሻም በኮርፖሬት ክሬዲት መምርያ (በተጠባባቂ ሥራ አስኪጅነት) ለስምንት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ አቶ አቤ በመጨረሻም የባንኩ ፕሬዚዳንት በመሆን ከጥር 23 ቀን 1998 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2001 ዓ.ም. ድረስ አገልግለዋል፡፡ ያኔ ወጣት የባንኩ ፕሬዚዳንት በመሆን የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡ በባንኩ ፕሬዚዳንትነት ወቅት ቀደም ሲል ተሰጥተው ሳይሰበሰቡ የቆዩ ብድሮችን በማሰባሰብና የሚሰጡ ብድሮችን ተመላሽ የሚሆኑበት አሠራር በመዘርጋት የሚታወቁ ሲሆን፣ ከባንኩ ከለቀቁ በኋላ ተመልሰው የባንኩ ፕሬዚዳንት ለመሆን የተመረጡበት ዋነኛ ምክንያት ያለበትን የብድር አመላለስ ችግር ለማስተካል ጭምር ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትነታቸው ባሻገር የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት በመሆኑም እያገለገሉ ናቸው፡፡ ከአቶ አቤ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ እንዲህ ተዘጋጅቷል፡፡    

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን ትልቁን ባንክ በሁለት የታሪክ አጋጣሚ በተለያዩ ወቅቶች በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ዕድል አግኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለሦስት ዓመት ከመሩ በኋላ ወደ ሌላ የግል ባንክ ሄደው፣ እንደገና ተመልሰው በፕሬዚዳንትነት መምራት ጀምረዋል፡፡ ሲሄዱ የነበረውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲመለሱ እንዴት አገኙት?

አቶ አቤ፡- እንዲህ ያለው አጋጣሚ ብዙ ጊዜ የሚፈጠር አይደለም፡፡ በዓለም ላይ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ወደ ቀድሞ ክለባቸው ተመለሱ ሲባል አልፎ አልፎ ይሰማል፣ እንደዚያ ነው የሆነው፡፡ ስሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ስመለስ ያገኘሁት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጣም ከፍተኛ ልዩነት ነው ያለው፡፡ ነገሮች ተመሳሳይነትም አላቸው፡፡ እኔ ጥዬ የሄድኩት ቀለል ያሉ ብዙ ነገሮች ፀድተውና መስመር ይዘው ለሩጫ የተዘጋጀ ባንክ ነበር፡፡ አሁን ብዙ ሮጦ ሮጦ ሸክም አብዝቶ በሸክሞቹ ብዛት የተለያዩ ፈተናዎች መያዝ ሲጀምር ነው ወይም በተወሰነ ደረጃ ገድገድ ማለት ሲጀምር ነው ተመልሼ የመጣሁት፡፡ ያ ለእኔ መሠረታዊ ልዩነት የለውም፡፡ እርግጥ አሁን መጠኑ በዝቷል፡፡ ነገሮች በቀላሉ ለመታረም አይችሉም፡፡ ከመጠኑ የተነሳ ይከብዳሉ፡፡ ኃላፊነት በዝቶበታል፡፡ ብድሮቹም ተቀያይረዋል፡፡ ብዙ ነገር አለ፡፡ መጀመርያ ፕሬዚዳንት ስሆን ከዕድሜዬ በፊት ነው የሆንኩት፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ፕሬዚዳንት ስሆን ለራሴ ያሳሰብኩት ብዙ ጊዜ እዚያ ቦታ ላይ መቀጠል የለብኝም የሚል ነበር፡፡ ምክንያቴ ደግሞ አልጠነከርኩም፣ ጉዳት ይደርስብኛል ብዬ ሥጋት ነበረብኝና ከአምስት ዓመት የበለጠ አልሠራም ብዬ ነበር፡፡ ኃላፊነት የተቀበልኩበት ምክንያት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋም ውስጥ አገልግሎ በሰላም የወጣ ከእኔ በፊት አልነበረም፡፡ ምናልባት የአቶ ለይኩንን ስም ብቻ ልናነሳ እንችላለን እንጂ፣ በተረፈ ሌሎቹ ግማሹ ይባረራል፣ ይታሰራል፣ ይሞታል፣ የነበረው ሁኔታ መልካም አልነበረም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ያኔ የነበረው አስተሳሰብ ንግድ ባንክ እጅግ ግዙፍ የሆነ፣ ችግሮቹ በጣም የከበዱና ሊፈቱ የማይችሉ የተወሳሰቡ ናቸው የሚል ነው፡፡ አይኤምኤፍ ሲል አራት ቦታ ይከፋፈል ይልም ነበር፡፡ እኔ አንዳንድ ነገሮች አነብ ነበር፡፡ ባንኩንም በሪፎም ፕሮግራም ላይ ያኔ ቢፒአር ተብሎ የሚሠራ ነገር ስለነበር ከዚያ አንፃር ሳየው ባንኩ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ምኑ እንደገዘፈባቸው አይገባኝም ነበር፡፡ ለእኔ በጣም ቀላል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አሁንስ?

አቶ አቤ፡- አሁን ሳየው ግን በጣም ግዙፍ ነው፡፡ የተሻለ ልምድ አግኝቼ የተሻለ ነገር ይዤ ነው የመጣሁት፡፡ ግን ባንኩ በጣም ገዝፎ ነው የጠበቀኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሲገቡ የተሻለ ክፍያ ነበረዎት፡፡ እዚህ ካለው ጋር ላይጣጣም ይችላል፡፡ እዚያ ቆይተው ድጋሚ የኢትዮጵየ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ይሁኑ ሲባሉ ኃላፊነቱን እንዴ ተቀበሉት? ኃላፊነቱን የተቀበሉት የአገር ጉዳይ ሆኖብዎትም ነው ይባላል፡፡ የተሻለ አግኝተው አይደለም?

አቶ አቤ፡- ያኔ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት በነበርኩበት ወቅት ዕቅዴ አምስት ዓመት ለማገልገል ነበር፡፡ በዚህ ኃላፊነት ከአምስት ዓመት በላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ላይ መሥራት ጫናው ከባድ ነው፡፡ እንደ አገር ችግር አለ፡፡ እዚህ ላይ ደግሞ አንዳንድ የፖለቲካ ችግር ሲቀላቀልበት በጣም የከበደ ነው የሚሆነው፡፡ ጭንቀት ነው የሚወልደው፣ ለዚያ ነው ያልፈለግኩት፡፡ በሆነ አጋጣሚ ተጣልቼ ደግሞ ችግር እንዲደርስብኝ አልፈለግሁም፡፡ ከዩኒቨርሲቲ በወጣሁ በሰባተኛ ዓመቴ ነው ፕሬዚዳንት የሆንኩት፡፡ አምስት ዓመት ብዬ በሦስት ዓመቴ ስወጣ ያልሠራኋቸው የቀሩ ነገሮች አሉና ስሜቱ ነበረኝ፡፡ የበለጠ ደግሞ የሠራተኛውን ስሜት ያየሁት ወደ መውጫዬ አካባቢ ነው፡፡ ከሠራተኛው ጋር የነበረኝ ግንኙነት በጣም እየጠነከረ ሄዶ ነበር፡፡ ባንኩን በጣም ነው የምወደው፡፡ ሠራተኛው ደግሞ ባንኩን የበለጠ እንድወደው አደረገኝ፡፡ ባንኩን የለቀቅሁትም ገንዘብ ፍለጋ አይደለም፡፡ ሁሌም የዚህን ባንክ ስኬት ነው የምፈልገው፡፡ ችግር ሲገጥመውና በአንዳንድ ነገር ሲወቀስ በጣም ነበር የማዝነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጥተው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እያሉ ማለት ነው?

አቶ አቤ፡- አዎ እዚያ ሆኜ የውጭ ኮረስፖንደንት ባንኮች ይመጣሉ፡፡ እኔ ፕሬዚዳንት የሆንኩበትን ባንክ ትንሽ ነው ብለው ሳይንቁ እኔን ስለሚያውቁ ይመጡ ነበር፡፡ ሲመጡ ስለንግድ ባንክ ምሬት ያቀርባሉ፡፡ ተቸግረናል እንዴት እናድርግ ይሉኝ ነበር፡፡ ይህንን ስሰማ ያመኝ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማለት ኢትዮጵያ እንድትታመን ቁልፍ ሚና የሚጫወት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ክፍያ ላይ ተቸግሯል ሲባል አዝን ነበር፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ እንደ ዜጋ ቅር ይለኝ ነበር፡፡ ባንኩ የተሻለ ሁኔታ እንዲገጥመው ምኞቴ ነበረ፡፡ ግን በምንም ተዓምር ተመልሼ ባንኩን እመራለሁ ብዬ ሐሳብ አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን ብዙዎች የእኔን ስሜት ያውቁ ነበርና ባንኩ የነበረበትን አደጋ የገለጹበት መንገድ ልቋቋመው የምችለው አልነበረም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ከሆነ ትንሽ ጊዜ አገልግዬ ባንኩን ከተቻለ ማሻሻል በሚል ነው የተመለስኩት፡፡ እርግጥ የሚወደኝና የሚያውቀኝ የባንኩ ሠራተኛ መንምኗል፣ የለም፡፡ አዲስ ኃይልና ትውልድ ነው ያለው፡፡ የሚጠብቀኝ ተግዳሮት እንዳለና ብዙ ነገሮች ተወሳስበው ሊጠብቁኝ እንደሚችሉ ግምት ነበረኝ፡፡ ግን መጥቼ ያየሁትን ያህል ይሆናል ብዬ አልገመትኩም፡፡

ሪፖርተር፡- እስኪ ችግሩን ንገሩኝ፣ እንደዚያ ውስብስብ ያለው ነገር ምንድነው? ምክንያቱ ከውጭ የተበላሻሸ የብድር አሰጣጥና ማኔጅመንት ጉዳይ ይሰማ ስለነበር የእርስዎንም ምልከታ ይንገሩኝ፡፡

አቶ አቤ፡- ብዙው ችግር የትልቅነት ችግር ነው፡፡ አንዳንዴ ትልቅነት በራሱ ችግር ነው፡፡ አንዳንዱን በሚዲያ ለማውጣት ሊከብድ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ሀብት ያለው እዚህ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፣ ሌላ የለም፡፡ እዚህ አገር ልማትም፣ ችግርም ሲመጣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ነው፡፡ ፕሮጀክቶች በሥርዓት አይመሩም፡፡ ገንዘቡ ሁሉ የሚወጣው ከኢትዮጵያ ንግድ ላይ ባንክ ነው፡፡ አንዳንዱ ፕሮጀክት ገንዘብ የሚለቀቅለት በወጉ ተጠንቶ አይደለም፡፡ ማነሳሳቱ በመንግሥት ይጀመራል፡፡ ጥናት የለም፣ በቂ ክትትል የለም፡፡ ከተጀመረም ወደ ግለሰቦች ፍላጎትና ፕሮግራም ሊሄድ ይችላል፡፡ ፕሮጀክቶች በጊዜ አልቀው ብድራቸውን መመለስ ካልቻሉ በጣም ትልቅ አደጋ ያመጣሉ፡፡ መንግሥት መጨረሻ ላይ ያለበትን ዕውነታ ሲረዳ ባንኩን ማዳን ያስፈልጋል አለ፡፡ እኔ እንደመጣሁ ያለውን ሁኔታ በሚገባቸው ቋንቋ ማስረዳት ችያለሁ፡፡ ይህ ባንኩን ለማዳን ትልቅ ሰክሰስ ነበር፡፡ ብድር ሰጥተህ ብድር የማይከፈል ከሆነ፣ ብድር ስለሰጠህ ደግሞ ወለድ ሒሳብ ትሠራና ትርፍ ተገኘ ተብሎ ግብር ይከፈላል፡፡ ላልተከፈለ ብድር ግብር ትከፍላለህ፡፡ ችግሩ ይህንን ሁሉ የሚያደርግ ነበርና የባንኩን ሊኪውዲቲ በጣም የሚያስደነግጥ ሁኔታ ላይ አድርሶታል፡፡ ምን እንዲህ እንዳደረገው አያውቁም ነበር፡፡ ሒሳብ ሲሠራ ላልተከፈለ ዕዳ ወለድ አግኝቻለሁ ተብሎ ትርፍ ተሠርቶ፣ ተከፍሎ፣ ግን ሳይሰበሰብ ግብር ሲከፈል ነበር፡፡ ግብር የምትከፍለው ደግሞ በካሽ ነው፡፡ ይህ መዝገብ ላይ ሲታይ ሀብት አለው፣ ግን ገንዘብ የለም፡፡ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች የተፈጠሩበትና የበዙበት ነበር፡፡ አቀናጅቶ ባንኩን ወደ አንድ አቅጣጫ ለማስጓዝ ተግዳሮት ነበሩበት፡፡ የማኔጅመንትም ችግር ነበር፡፡ ለውጡ በጣም የተጠና አልነበረምና መንገራገጭ አምጥቷል፡፡   

ሪፖርተር፡- ይህ በመሆኑ ባንኩ ላይ ያደረሰው ነገር ምንድነው?

አቶ አቤ፡- ብዙ ችግር አምጥቷል፡፡ ቁልፍ ሰዎች እንዲለቁ አድርጓል፡፡ ሲስተሙን የማያውቁ ሰዎች በአንድ ጊዜ ቢሮውን ሲረከቡ ችግር ነበረው፡፡ ይህ ባንክ ነው፡፡ የፖለቲካ ተቋም አይደለም፡፡ ሥራውን ስትሠራ ሲስተሞች አሉ፡፡ በተለይ አይቲ አካባቢ ብዙ ነገር አለ፡፡ ይህንኑ የሚመራው ሰው ፋይናንስ መምራት፣ አይቲ መምራት፣ ብድር መምራትና ባንክ አካባቢ ያለውን ነገር መምራት ልምድ ይጠይቃል፡፡ የባንኩን ባህልና የሥራ ሒደቶች ማወቅ ይጠይቃል፡፡ ባንክ ነው የሚሠራው በሚል ድንገት ሌላ ግሩፕ ስታመጣ ልትተካው የምትችል ነገር አይደለም፡፡ እና እዚህ አካባቢ የተሄደበት መንገድ ጥበብ የጎደለው ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ስንገባ ፈተና ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አንዱ ፈተና በተለይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ያልተከፈለ 600 እና 700 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ብድር ሊከፈል አለመቻሉ አንዱ ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ብቻ ባንኩ ይወድቅ እንደነበር በጣም ግልጽ ነበር፡፡ ይህንን ሸክም እንዴት ተወጥተነዋል ይላሉ? ይህንን ያህል የመንግሥት ብድርስ እንዴት እየተመለሰ ነው?

አቶ አቤ፡- እርግጥ የመንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ በግሉም ቢሆን ትልልቅ ብድሮች ነበሩ፡፡ የግል ተበዳሪዎች ብዙ ስላልነበሩ ብዙ ትኩረት አላገኘም፡፡ እንዲሁ ተለቅ ተለቅ ያሉ ከመንግሥት ጋር የሚገናኙ የግል ብድሮች ፈተና ነበረባቸው፡፡ እንግዲህ ከዚህ መውጫ መንገድ ብድር መሰብሰብ ነው፡፡ ሌላ መንገድ የለም፡፡ ከዚህ አንፃር የነበረው ችግር አንዱ የማትችለውን ነገር ማበደር ነው፡፡ ቅድሚያ ማግኘት ያለበት አስቀማጩ ነው፡፡ በሄደበት ቦታ ብሩን ማግኘት አለበት፡፡ ይህ ብር ጠፍቶ ችግር ነበር፡፡ ብር ለማግኘት ሠልፍ ነበር፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመትና ሁለት ዓመት ተኩል አካባቢ በቂ ሊኪውዲቲ አልነበረም፡፡ ይህ የተፈጠረው የሊኪውዲቱ ማኔጅመንቱ ላይ ችግር ተፈጥሮ ነው፡፡ ምክንያም የሰጠኸውን ብድር መሰብሰብ ካልቻልክ ማበደርህንም ታቆማህ ማለት ነው፡፡ ያለችዋ ተቀማጭ ትወጣ ነበር፡፡ አሁንም ለውጥ የመጣው መጀመርያ የመንግሥት ብድር እንዲቆም በማድረጋችን ነው፡፡ ትልቅ ገንዘብ የሚያስወጡ ፕሮጀክቶች እንዲቀንሱ፣ መንግሥት ቁልፍና ይጠቅሙኛል የሚላቸውን ብቻ በእነሱ ላይ አተኩሮ እንዲሠራና ሌሎቹ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙና እንዲቀንሱ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንዳይጀመሩ ነው የተደረገው፡፡ የግል ብድርም መጠኑ እንዲቀንስ ተደርጓል፡፡ የረዥም ጊዜ ትልልቅ ብድሮች እንዳይሰጡ አደረግን፡፡ ምክንያቱም የባንኩ አብዛኛው ብድር የረዥም ጊዜ ነው፡፡ ይህ ጤነኛ አይደለም፡፡ የብድር ሚዛን ተጠብቆ ነው መሄድ ያለበት፡፡ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ተብሎ ሚዛኑ ተጠብቆ መሄድ ነበረበት፡፡ እንዲህ ሲሆን ተሰብሳቢ ይኖርሃል፡፡ ግን አንድ ግሩፕ ላይ ካደረግክ ያ ግሩፕ ችግር ከገጠመው አብረህ ትወድቃለህ፡፡ ስለዚህ እሱን ለማስተካከል ነው እየሠራን ያለነው፡፡ ትልልቅ ብድሮችን በማቆማችን ገንዘብ የማግኘት ዕድል አገኘኝ፡፡ የበለጠ ደግሞ ተቀማጭ ማሰባሰብ ላይ ሠራን፡፡ ተቀማጩ መጣ ብለን ደግሞ ወዲያው ወደ ማበደር አልሄድንም፡፡ መጀመርያ የሠራነው ማረሙ ላይ ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- የመንግሥት ብድር ጉዳይን እንዴት አደረጋችሁት? ምክንያቱም ይህንን ከፍተኛ ዕዳ መንግሥት እንዲረከበው ይደረጋል ተብሏልና አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው?

አቶ አቤ፡- የመንግሥት ብድር መንግሥት እንዲረከበው አድርገናል፡፡ ይህ በጣም ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በአዋጅ መንግሥት ዕዳውን እንዲረከብ ተደርጓል፡፡ አሁን እየተፈራረምን ነው ያለነው፡፡ መንግሥት ተበድሮም ለምኖም መክፈል ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ብድሮቹ ሲሰጡ ገንዘብ ሚኒስቴር ዋስ ሆኖ ነው፡፡ ከዚያ ገንዘብ ውስጥ የጠፋ አለ፡፡ ለህዳሴ ግድብ ብዙ ገንዘብ ነው የወጣው፡፡ ያ ሁሉ ገንዘብ ግን ሥራ ላይ የዋለ አይደለም፡፡ ተጥሎ እንደ ገና የተገነባ ሁሉ አለ፡፡ ያላግባብ የተሠራ ሥራ ሁሉ አለ፡፡ ሌሎቹም በተመሳሳይ የሚታዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ስኳር ፕሮጀክቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የማበደሪያ ፕሮጀክቱም እንዲሁ ተጀምሮ በጣም ችግር እየሆነ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ወደ ገደል የተወረወረ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ወጥቶባቸው ሜዳ ላይ የተጣሉ ናቸው፡፡ ግን በመንግሥት ዋስትና ተጀምረው የነበሩ የግብር ከፋዮች ገንዘብ ነው፡፡ ምክንያም በመንግሥት ዋስትና የተሰጣቸው በመሆናቸው መከፈል አለባቸው፡፡ ንግድ ባንክ ለጊዜው ነው እንጂ ሊኪውዲቲ የተቸገረው ገንዘብ ይከፈላል፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶች ሲቀርቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲያጠና ዕድል አልተሰጠውም፡፡ ይህ ዕድል ቢኖረው የተወሰነው ችግር መቀነስ በቻለ ነበር፡፡ ቢያንስ የገንዘብ አወጣጡን ማየት ይችላል፡፡ የሚከፈልበትን መጨረሻ እያየ ለፕሮጀክቱ ጠቃሚ ነው አይደለም እያለ ትንሽ ይረዳ ነበር፡፡ ግን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያንን ዕድል አልሰጡትም፡፡ ስናዝህ ክፈል ነበር የሚባለው፡፡ ከገንዘብ ሚኒስቴር ደብዳቤ ሲጻፍ ቼክ ተበጥሶ ነው ይላክ የነበረው፡፡ በዚህ መንገድ የተሰጠ ብድር ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይህ ለመንግሥት ትልቅ ዕዳ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- መንግሥት ይህንን ዕዳ እየከፈለ ነው? እስካሁን ምን ያህል ተከፈላችሁ?

አቶ አቤ፡- አሁን መመለስ ጀምሯል፡፡ የመጀመርያው የቴሌኮም ፈቃድ ሽያጭ 850 ሚሊዮን ዶላር ተመጣጣኝ ባለፈው ሳምንት ገብቷል፡፡ በሚቀጥለውም ፈቃድ ሲሸጥ ለእኛ ለዕዳው ክፍያ ይውላል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ እንዲሁም በማድረግ ድርጅቶችን ወደ ግል በሚዛወር የሚከፈል ይሆናል፡፡ ‹‹ሊያቢሊቲ ሄድ አሴት ማኔጅመንት›› በሚል የተቋቋመው ተቋምም ከዚሁ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሚሠራ ነው፡፡ በዓለም ላይ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር እንዲህ ዓይነት ድርጅት ይቋቋማል፡፡ ይህንን ሲያደርግ አገሮች ያግዛሉ፡፡ ከዚያ በሚገኘው ዕዳውን ይከፍላል፡፡ ዕዳው በኢኮኖሚ ላይ ችግር እንዳያመጣ የሚደረግበት አሠራር ስለሆነ ዕቅድ አውጥቶ ፈንድ ለመፈለግ ነው፡፡ በራስ አቅም ፕራይቬታዝ በማድረግ ክፍያውን ለመፈጸም ነው ዕቅድ ያለው፡፡ እናም እኛ የመጀመርው ክፍያ ተከፍሏል፡፡ ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በቀጣይም በመስከረም ተመሳሳይ ክፍያ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

ሪፖርተር፡- እንዲህ እየተከፈለ ከመጣ ባንኩ ላይ ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ እንዴት ይገለጻል? ሊለውጠው የሚችለው ነገር አለ?

አቶ አቤ፡- ገንዘቡ ሲመጣ ለሚፈለገው ዓላማ ይውላል፡፡ ያው የተጀመሩ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ለመጠናቀቅ ፈተና ሆነው ነበር፡፡ እና አሁን ምርታማ ሊሆኑ ያሉትን መጨረስ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ መምጣቱ የህዳሴ ግድብን ለመጨረስ ቁልፍ ነገር ነው፡፡ መልሰን ለማበደር ዕድል ይሰጠናል፡፡ ለግል ተበዳሪዎች እናበድራለን፡፡ ገንዘባችን ሲመለስ ለደንበኞቻችን በቂ የማበደር አቅም አገኘን ማለት ነው፡፡ አጠቃላይ ገንዘቡ ግን ከአሥር እስከ 12 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ይከፈላል፡፡ በአንዴ ቢመጣም ምንም አናደርገውም፡፡ ግን በየዓመቱ እንደዚህ ከተመለሰልን እኛም በየዓመቱ ደንበኛ እየፈጠርን በዋናነት ወደ ግል ዘርፍ እንዲዞር ነው የታቀደው፡፡    

ሪፖርተር፡- ባንኩ አደጋ ውስጥ ነበር፡፡ በተለይ የሰጠውን ብድር ከማስመለስ አኳያ የነበረበት ችግር ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት የተበላሸ የብድር ምጣኔው (NPL) የበዛ ነበር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ይህንን መቀነስ እየቻላችሁ ነው? በምን ያህል መጠን?

አቶ አቤ፡- የተበላሸ የብድር መጠኑን ብዙም አልቀነስንም፡፡ ገና ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል፡፡ እኔ እዚህ ስመጣ ያለው ችግር  እንደተጠበቀ ሆኖ ኮቪድም ነበር፡፡ እንደዚያ ሲሆን የተበላሸ የብድር መጠን እንዳይበዛ ነው እየተከላከልን ያለነው፡፡ ትልቁና የሚያሠጋ የነበረው የመንግሥት የልማት ድርጀቶች ብድር መቀነሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይህ ብድር የመንግሥት ዋስትና ስላለው ጊዜው ቢያልፍበትም የተበላሸ ብድር አይቆጠርም፡፡ ነገር ግን የገንዘብ ሊኪውዲቲ ባለማምጣቱ ፈተና ነበረው፡፡ ይህ መቀረፉ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ከግሎቹም ለመሰብሰብ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ አሁን ወደ ጨረታም ገብተናል፡፡ በፊት ጨረታውን ያዘገየነው ኮቪድ በኢኮኖሚውም፣ በኅብረተሰቡም ላይ ብዙ ድንጋጤ በማምጣቱ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ለኮንዶሚኒየም ቤቶች የሦስት ወር ጊዜ የዕፎይታ ጊዜ ሰጥተናል፡፡ የሌሎችንም ነጋዴዎች እንዲሁ በማስታመም ጊዜ በማራዘም ነበር የቆየነው፡፡ ምክንያቱም ቀጥታ ውጤቱ ባይታይባቸውም የሥነ ልቦና ጫናው ነበርና በኋላ ግን ባልተጠበቀ መንገድ ሁሉም እየተፈታ ነው ያለው፡፡ የፀጥታ ችግሩም ፈተና ፈጥሮ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ያንን ማውራት የለብንም፡፡ ወደ መደበኛ ሥራ መመለስ አለብን ብለን ወደ ሐራጅ ገብተናል፡፡ አሁን ሕጋዊ ዕርምጃ እየወሰድን ነው፡፡ ብድር ለመሰብሰብ ወደ ሕጋዊ ዕርምጃ ገብተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ተሰብሳቢ ብድር ተብሎ የሚታሰበው ምን ያህል ነው?

አቶ አቤ፡- ተሰብሳቢውማ ብዙ ነው፡፡ ሁሉም ያበደርነው ብድር ተሰብሳቢ ነው የሚባለው፡፡ የባንኩ የሰጠው ብድር በአጠቃላይ ወደ 800 ቢሊዮን ብር ገደማ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ 90 ቢሊዮን ብር የግሉ ዘርፍ ነው፡፡ አብዛኛው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ነው፡፡ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የልማት ድርጅቶች ነው፡፡ ባንኩም ትኩረት አድርጎ ሲሠራ የነበረው የመንግሥት ፕሮግራሞች ላይ ነው፡፡ የግሎቹ ደግሞ በግል ዘርፎች ላይ ሲያተኩሩ ነበር፡፡ ንግድ ባንክ ደግሞ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ አተኩሮ ይሠራ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ለግል ዘርፍ የሰጠው ብድር የግል ባንኮች ከሰጡትም ይበልጣል፡፡ ነገር ግን ሊሆን የሚገባውን ያህል ነው ብለን አናምንም፡፡ ቢያንስ 50፣ 50 አካባቢ እንኳን ቢደርስ እያልን ነው፡፡ በዚህ አቅጣጫ እንዲሄድ እየሠራ ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን ጤናማ ይሆናል፡፡ ብድር አሰጣጡ ጤናማ ይሆናል፡፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተዘፍቆበት ከነበረው ችግር ወጥቷል ማለት ይቻላል?

አቶ አቤ፡- ፈተና እንጂ ችግር የሚባል ነገር አይደለም፡፡ አንዱ ሲያልፍ ሌላ ፈተና ይመጣል፣ እየተወጣን እንሄዳለን፡፡ ቁልፍ ችግር የነበረው የሊኪውዲቱ ችግር ነው፡፡ የሊኪውዲቲ ችግሩ የውጭ ምንዛሪም ነው፡፡ በተለይ የአገር ውስጥ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ማስወገድ ችለናል፡፡ በብሔራዊ ባንክ የሊኪውዲቲ መለኪያ የባንኩ ሊኪውዲቲ ምጣኔ 11 በመቶ ላይ ነበር፡፡ ዝቅተኛው 15 በመቶ ነበር፡፡ አሁን ግን 21.5 በመቶ ነው፡፡ በሰኔ የዘጋነው ይህ ባለፉት አሥር ዓመታት ሆኖ አያውቅም፡፡ ሊኪውዲቲው በጣም ችግር ላይ የቆየ ነው፡፡ አሁን ግን ትልቅ ግስጋሴ አሳይቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ከ15 በመቶ በታች የሚወርድበት ሁኔታ የለም፡፡ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግዴታዎች ብዙ ነበሩበት፡፡ አሁን ግን እሱን አቅልለናል፡፡ በዚህም ምክንያት የውጭ ምንዛሪ ሳንሰጥ አቋርጠን ቆይተናል፡፡ ምክንያቱም ቀደም ብሎ በአገር ውስጥ የሊኪውዲቲ ችግር ነበር፡፡ እሱን ለማስተካከል ሲሠራ በነበረው ሥራ የአገር ውስጥ ሊኪውዲቲን በውጭ ምንዛሪው ሊኪውዲቲ እንዲሸጋገር አድርጎት ነበር፡፡ አሁን ግን ያለውን የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ መልሰን ወደ ጤንነቱ መልሰነዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ቢዝነስ ነው፡፡ ውድድሩም ከባድ እየሆነ ነው፡፡ ቴክኖሎጂውን ማዘመን ነው፡፡    

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...