Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በቢሊዮን የሚቆጠር ትርፍ እያጋበሱ በሕዝብ እንባ መሳለቅ ተገቢ አይደለም!!

ኢትዮጵያ እያለፈችበት ያለው ወቅት እጅግ በጣም ፈታኝና የተወሳሰበ ነው፡፡ በተለይ ሕዝቡ በኑሮ ውድነት፣ በዋጋ ግሽበት እየከፈለ ያለው ዋጋ አሁን ላይ ከአቅም በላይ ሆኗል፡፡ ሰው በቀን አንድ ጊዜ ለመብላት መከራ ላይ መሆኑን በየዕለቱ የሬዲዮ፣ የቴሌቪዥንና የጋዜጣ ዋና አርዕስት መሆኑ ይታወቃል፡፡

መንግሥትም ለዚህ ችግር መፍትሔ እሰጣለሁ እያለ በእነዚሁ ሚዲያዎች እየወጣ ይምላል ይገዛታል፡፡ በነጋዴውና ደላላ በሚላቸው ላይ የችግሩ መንስዔ ናቸው በማለት የማስፈራሪያና ዛቻ እንጉርጉሮ አድርጎ ተመልሶ ወደ ጎሬው ይገባል፡፡

ግን ዛቻውም ይሁን ማስፈራሪያው ችግሩን ከማባባስ ውጪ ያመጣው አንዳችም መፍትሔ የለም፡፡ ለምን ሲባል ‹‹ችግሩ ያለው ቦሌ፣ ዛቻና ማስፈራሪያው ጉለሌ›› ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ በእውነት በዚህ ዘመን ያለ ነጋዴ ከባንክ ብድር ሳይበደር የሚሠራ ያለ አይመስለኝም፡፡ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ ለፍጆታም ይሁን ለኢንቨስትመንት የሚቀርቡ ግብዓቶች ከ60 በመቶ እስከ 70 በመቶ ከውጭ የሚመጡና የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ ናቸው፡፡

ታዲያ እውነት መንግሥት ዓይኑን ከፍቶ ቢመለከት ኖሮ በዚህ ሥራ ላይ ዋና ተዋናይ የሆነውን የባንኩን ዘርፍ መመልከት ነበረበት፡፡

ባንኮች ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በወለድና በአገልግሎት ዋጋቸው ላይ የጨመሩትን ጭማሪ በአትኩሮት ቢመለከት ለችግሩ ማለቴ ለዋጋ ንረቱ መንስዔ የሆነውን ከ30 በመቶ እስከ 40 በመቶ መነሻ ሊረዳ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ባለፉት አምስት ዓመታት ባንኮች ለአስቀማጩ የጨመሩት የወለድ መጠን ቢታይ ከአንድ በመቶ ያለፈ አይደለም አሁን የሚከፈለው ወለድ ሰባት በመቶ ነው፡፡ ይኼም ባንኮች ለተበዳሪ ወለድ የሚያሰሉት በየቀኑ ሲሆን አስቀማጭ ግን ወሩን ሙሉ ለተቀመጠ ወለድ አያገኝም፡፡

እንዲህ በሰባት በመቶ የገዙትን ያውም ለ30 ቀን ካልተቀመጠ የማይከፍሉበትን ገንዘብ የሚያበድሩበት ወለድ ከእጥፍ በላይ ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ባንኮች የወለድ መጠናቸውን ከአሥር እስከ 13 በመቶ የነበረውን ወደ ከ17 በመቶ እስከ 20 በመቶ አሳድገውታል፡፡ በአማካይ የባንኮች ወለድ 15 በመቶ ሆኗል፡፡ እንግዲህ ይኼ በዋጋ ግሽበት ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ እንኳን ኢኮኖሚስቶቹ እኛም ተጠቂዎቹ በቀላሉ እንረዳዋለን፡፡

ይኼም አልበቃ ብሏቸው በእያንዳንዱ የአገልግሎት ታሪፋቸው ላይ ያደረጉት ጭማሪ ከአራትና አምስት እጥፍ በላይ ነው፡፡ በተለይ ምንም የአገልግሎት ክፍያ ሳይከፍሉ ያገኙትን በሐዋላም ይሁን በኤክስፖርት የተቀበሉትን የውጭ ምንዛሪ የሚሸጡበትን ዋጋና የሚሰበስቡትን ኮሚሽን በእጥፍ ጨምረዋል፡፡ ከ3.5 በመቶ እስከ አራት በመቶ የነበረው የኤልሲ ኮሚሽን አሁን ከሰባት በመቶ እስከ አሥር ደርሷል፡፡ ከዚህ ጋር ተጓዳኝ የነበሩ በመቶዎች ይከፈል የነበረው የአገልግሎት ዋጋ አሁን በሺዎች ሆኗል፡፡

ከዚህ በፊት አንድ ተበዳሪ ብድሩን በወቅቱ ባይከፍል ጉዳዩ ወደ ሕግ እስካልሄደ ድረስ የቅጣት የወለድ ጭማሪ በፍጹም አይደረግበትም ነበር፡፡ አሁን የባንኮች ስግብግብነት ልኩን አልፎ በአገሪቱ ላይ ያለውን የገንዘብ እጥረት፣ የዋጋ ንረት፣ በፖለቲካ ያለውን ችግር፣ የበጀት መዛባት እያወቁና እየተረዱ አንድ ተበዳሪ በእነዚህ ምክንያቶች ብድሩን ባይከፍል ወዲያው የመቀጫ ወለድ በማለት የሦስት በመቶ የወለድ ጭማሪ ያደርጋሉ፡፡

እያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ በየጊዜው ከሚጨምረው የዕቃ ዋጋ በላይ ባንኩ ከልክ በላይ የሚያስከፍለው የወለድ ተመንና ያም አልበቃ ብሎ የመቀጫ ወለድ ጭማሪ በሕዝቡ ላይ እየነደደ ላለው የኑሮ እሳት ነዳጅ መጨመር ነው፡፡ ከዚያም በዓመቱ መጨረሻ ‹‹በቢሊዮን አተረፍን፣ እጥፍ አደግን›› እያሉ በሕዝብ ችግር ላይ መመጻደቅና መዝፈን አግባብ አይደለም፡፡

ባለፈው በተወካዮች ምክር ቤት ጠቀላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በግልጽ እንዳስቀመጡት፣ እነዚህ የባንኩ ባለቤት ነን የሚሉ ባለሀብቶች ድርሻቸው ከስምንት በመቶ በላይ አይደለም፡፡ ስምንት አዋጥቶ በ92 በመቶ ባለድርሻ በሆነው ሕዝብ ላይ እንዲህ ዓይነት አግባብ የሌለው ትርፍ መዛቅ ግፍ አይደለም? ጭብጦአቸውን ይዘው ተጠግተው አጥንቱን መጋጥ አግባብ ነው? ይኼንን ሁሉ የኑሮ ጫና መፍጠር ተገቢ ነው? ባለፈው ለህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዙ ሲባል ያ ሁሉ ጩኸት የነበረው በእውነት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ መሻሻል ወይም ለግል ኪሱ ማደለቢያ ነው?

እንዲያው ማን ይሙት ይኼ ሁሉ የኮሮና ጫና ባለበት፣ አገራችን ከግራ ከቀኝ በተወጠረችበት፣ የጤፍ፣ የዘይት፣ የዳቦ ዋጋ ንሮ ሕዝብ እያለቀሰ ባለበትና ብዙ ፋብሪካዎች ሥራ ለማቆም በሚውተረተሩበት በዚህ ችግርና ፈተና በበዛበት ዓመት የባንኩ ዘርፍ ለብቻው ተለይቶ በየዓመቱ ከ30 በመቶ እስከ 100 በመቶ ዕድገት የሚያሳይበት በቢሊዮኖች ትርፍ የሚዝቅበት ምክንያት ጤናማ ነው? ሕዝብ ደም እንባ እያለቀሰ ሌላው በቢሊዮኖች ትርፍ የሚደንስበት አካሄድ ጤነኛ አይመስለኝም፡፡

ባንኮች በወለድ ላይ፣ በአገልግሎት ዋጋ ላይና በኤልሲ ኮሚሽኖች ላይ ያደረጉት እስከ 100 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ ከዚህ ጋር ተደምሮ የሚመጣው ታክስና በነጋዴው የሚጨመረው ትርፍ በሙሉ ወርዶ የሚወድቀው ኑሮ ወገቡን ባጎበጠው መከረኛ ሕዝብ ላይ ነው፡፡

ይኼ የችግር ጊዜ እስኪያልፍ እንኳን ምናለ ገንዘቡን ሰጥቶ ተጠቀሙ ላለው ሕዝብ አዘኔታ ቢኖር? ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ባንኮቹ በዓመቱ መጨረሻ ብቅ እያሉ ይኼንን ያህል ቢሊዮን አተረፍን ካለፈው ዓመት በዚህ ያህል ፐርሰንት አደግን እያሉ በሚዲያ መዝፈናቸው ይኼ ጤነኛ አስተሳሰብና አካሄድ አይመስልም፡፡ በነዋይ መታወር ወደ ጥፋት ያመራል፡፡ እያጎረሳችሁ ያለውን ሕዝብ እጅ አትንከሱ፡፡ አሥር በመቶና 20 በመቶ ካተረፋችሁ ይበቃል፡፡

በመጨረሻም መንግሥት በእውነቱ ግሽበቱን መቆጣጠር ከፈለገ ለባንኮች የብድር ወለድ፣ የአገልግሎትና ኮሚሽን ጣራ ያብጅላቸው፡፡ አላግባብ እየተነሱ በሕዝብ ላይ የሚጨምሩትን ዋጋ ሕዝቡ ሊሸከምበት የሚችለው ትከሻ የለውም፡፡ ወገቡ ጎብጦ ሊሰበር አፋፍ ላይ ያለ ሕዝብ ነው፡፡ በልቶ ማደር ሕዝቡ አቅቶት፣ ፋብሪካዎች ሠራተኛ ካልቀነስን እያሉ እየተንገዳገዱ፣ ድርጅቶች ገበያ ውስጥ ለመቆየት መከራ እያዩ፣ ይኼ የባንክ ዘርፍ ብቻ በቢሊዮን የሚቆጠር ትርፍ እያጋበሰ በሕዝብ እንባ መሳለቅ ተገቢ አይደለም፡፡

አሠራሩ ይፈተሽ በሕዝብ ገንዘብ የግለሰብ ኪስ ማደለብ ይብቃ፡፡ የሕዝብ ገንዘብ ለሕዝቡ በፍትሐዊነት ይዳረስ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት