Monday, June 24, 2024

​​​​​​​ከሰላም የተሻለ አማራጭም ሆነ አቋራጭ የለም!

ከአገርና ከሕዝብ ህልውና በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ማንነት፣ ወሰን፣ መሬትም ሆነ ማንኛውም ጉዳይ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆን የሚችሉት አገር ሰላም ስትሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት የውጭ ወራሪ ኃይሎችን ስትመክት የኖረች አገር ናት፡፡ በዚህ ምክንያት አሁንም ታሪካዊ ጠላቶች አሉዋት፡፡ ጥቅማቸውን አስቀድመው የሚነሱ የውጭ ኃይሎች ደግሞ ሁሌም አኩራፊ እንዲኖር ይፈልጋሉ፡፡ የሰላምን በር ዘግቶ የግጭት በርን መበርገድ የሚጠቅመው ለኢትዮጵያዊያን ሳይሆን፣ የራሳቸውን ዘላቂ ጥቅም ብቻ አስልተው የሚንቀሳቀሱ የውጭ ጣልቃ ገብ ኃይሎችንና የኢትዮጵያን መዳከም የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከናወኑ ግጭቶች በሙሉ የጎዱት ንፁኃንን ነው፡፡ በግጭቶቹ ሳቢያ በርካቶች ለሕልፈት ተዳርገዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል፡፡ በሰላም እንጂ በግጭት ማንም አሸናፊ መሆን አይችልም፡፡ ሁሉም ወገኖች አሸናፊ የሚሆኑት ለንግግር፣ ለድርድርናስምምነት ዝግጁ መሆን ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ እርግጥ ነው በአንድ ወገን ሰላም ፈላጊነት ብቻ ጦርነትን ማስቀረት አይቻልም፡፡ ሌላው ወገን ለሰላም ጀርባውን ሰጥቶ ትንኮሳ እየፈጸመ ችግር ሲፈጥር፣ በአስገዳጅ ሁኔታ ምክንያት የማይፈለግ ጦርነት ውስጥ ይገባል፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ከጦርነት ውጪ አማራጭ የለም የሚል ኃይል ሲገጥም፣ ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከ ዳር በጋራ ተነስተው በቃ ማለት አለባቸው፡፡ ማንም አሸናፊ ከማይሆንበት ጦርነት ይልቅ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገው ሰላም ይበልጣል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ሚሊዮኖች በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው፣ ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ የተጋለጡባት ምስኪን አገር ናት፡፡ በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቶች በርካቶችን እያፈናቀሉ አርሶ አደሮች ሳይቀሩ ለተረጂነት እየተዳረጉ ያሉባት አሳዛኝ አገር ናት፡፡ የኑሮ ውድነቱ ብዙዎችን ናላቸውን እያዞረው መፈጠራቸውን እየጠሉ የሚኖሩባት የምንዱባን አገር ናት፡፡ ለመግለጽ የሚቸግር ፅኑ ድህነት አሁንም ብዙዎችን ያሰቃያል፡፡ ኢኮኖሚው በአገር ውስጥና በውጭ ብድር ዕዳ፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በግጭት፣ በኮሮና ወረርሽኝና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ተቀዛቅዟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት ተጨምሮበት፣ ለመተንበይ አስቸጋሪ ሊሆን የሚችል ሥጋት እየተደቀነ ነው፡፡ ሥራ አጥነት አሁንም የአገር ራስ ምታት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በአቅርቦትና በፍላጎት መሀል ያለው ልዩነት ሊጠብ ባለመቻሉ የዋጋ ግሽበት ከመቼውም ጊዜ በላይ እያሻቀበ ነው፡፡ በአገር ውስጥ መመረት የሚገባቸው የምግብ ዓይነቶችና ጥሬ ዕቃዎች ከውጭ ስለሚሸመቱ፣ በመከራ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ እየተሻሙ ችግሩ እየከበደ ነው፡፡ አገር የምታድገውና ለዜጎች ምቹ የምትሆነው በጦርነት ሳይሆን በልማት ብቻ ቢሆንም፣ የሰላም መንገድ ተዘግቶ አሁንም ጦርነት እያንዣበበ ነው፡፡ ጦርነት ደግሞ የአገር አንጡራ ሀብትን እምሽክ አድርጎ ነው የሚበላው፡፡ ለሰላም ዕድል ካልተሰጠ መጪው ጊዜ አሳሳቢ ነው፡፡

ሁሌም እንደምንለው ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ ሕዝቧም የተከበረ፣ አስተዋይና አርቆ አሳቢ ነው፡፡ ይኼ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ በአራቱም ማዕዘናት በተለያዩ መልክዓ ምድሮች ውስጥ ቢኖርም፣ የሚጋራቸው አኩሪ የሆኑ የጋራ እሴቶች አሉት፡፡ የተለያዩ ማንነቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ እምነቶች፣ ወዘተ ቢኖሩም ለአገሩ ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ በሰላምና በመከባበር ዘመናትን አሳልፏል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ልዩነቶች ሳይገድቡት ተጋብቶና ተዋልዶ አንድነቱን ጠብቆ ኖሯል፡፡ አልፎ አልፎ ችግሮች ቢያጋጥሙም አስደማሚ በሆነው የሽምግልና ሥርዓቱ የተበደለን እያስካሰ፣ የበደለን ደግሞ እየገሰፀ መኖር ይችልበታል፡፡ እንዲህ ዓይነት በሥርዓት መኖር የሚችል አስተዋይ ሕዝብ ሰላሙ የተቃወሰው፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ስለበዙ ነው፡፡ በተለይ ቂም፣ ጥላቻ፣ ክፋትና ሴራ ውስጥ በመዘፈቅ ከአገር በላይ ለግላዊና ለቡድናዊ ጥቅሞች እየተዋደቁ፣ በሕዝብ ላይ የሚቆምሩ አልጠግብ ባዮች ገለል ለማለት ስላልፈቀዱ ነው፡፡ ዘመኑን የማይዋጅ የጽንፈኝነት ዓላማ በማቀንቀን በሕዝብ ስም መነገድ ስለበዛ ነው፡፡ ለዚህ የሠለጠነ ዘመን የማይመጥን አጉል ድርጊት እንዲያበቃ መደረግ አለበት፡፡ ለሰላም መከፈል ያለበት ሁሉ ተከፍሎ ከጦርነት አዙሪት ውስጥ መውጣት የግድ ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ከገባንበት ቀውስ ውስጥ ለመውጣት ከእኛ በላይ ማንም እንደሌለ ማመን ይገባናል፡፡ ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ለማንም ጥገኛ ሆነው አያውቁም፡፡ የጥገኝነት አስተሳሰብና ሥነ ልቦና የሌለው ሕዝባችን በታሪክ ያጋጠሙትን ፈተናዎች ያለፈው፣ በጠንካራ አንድነቱና ኅብረቱ ነው፡፡ በዚህ ዘመንም ይህ ጥሩ ልምድ ሊያገለግል ሲገባ፣ ባዕዳን ሥር በሚርመጠመጡ ተላላኪዎች አገር እየተበደለች ነው፡፡ እኛ ውስጣችንን በድፍረት መፈተሽና የጎደሉንን ነገሮች ያለ ምንም መደባበቅ መነጋገር ስንጀምር፣ እንኳን ወደ ባዕዳን ልናንጋጥጥ ከእነ መፈጠራቸውም አናስታውሳቸውም፡፡ ከምንም ነገር በላይ ማመን ያለብን ሰላማችን እጃችን ውስጥ መሆኑን ነው፡፡ ምክንያታዊ በመሆን በሠለጠነ መንገድ መነጋገር ከተቻለ፣ መጀመርያ መግባባት የሚያስፈልገው የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ነው፡፡ ሰላማዊና ሥልጡን ዴሞክራሲያዊ ፉክክር የሚፈልገው በሕግ የበላይነት ማመን ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር ሐሳብን በነፃነት መግለጽና መደራጀት፣ የሚፈልጉትን መደገፍና የማይፈልጉትን መቃወም ይቻላል፡፡ ለዚህም ሕግና ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ለአገር ህልውና ከልባቸው የሚያስቡ ይህንን ጉዳይ በጥሞና ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ከአገር ሰላም በፊት የሚቀድም የለምና፡፡

ከአገር በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ከሕዝብ በላይ ምንም የሚቀድም የለም፡፡፡ ሕዝብ የሚደሰተው አገሩ ሰላም ስትሆንለትና በዕድገት ወደፊት ስትራመድለት ነው፡፡ ዴሞክራሲዊና ሰብዓዊ መብቶቹ ተከብረው በአገሩ ጉዳይ ዋነኛ ተሳታፊ ሲሆን ነው፡፡ ሰላሙ እየተናጋ፣ ደኅንነቱ አደጋ ውስጥ እየገባ፣ በስንት ትግል የሚያኖረው ሕይወቱ እየተመሰቃቀለና የአገሩ ህልውና ከድጡ ወደ ማጡ ሲሆንበት ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ችግሮች ጊዜያዊና ኃላፊ እንዲሆኑ ሕዝቡ ውስጥ ያሉ ዘመን ተሸጋሪ እሴቶች ሊከበሩ ይገባል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት፣ በቀቢፀ ተስፋ ወጣቶችን ለጥፋት ማሰማራት፣ ከመቀራረብ ይልቅ እልህ ውስጥ የሚከቱ አጉል ድርጊቶችን መፈጸምና አገርን የባሰ ቀውስ ውስጥ የሚዘፍቁ እኩይ ድርጊቶችን በፍጥነት ማቆም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ለዓመታት ተሞክረው ያልተሳኩ ፍጥጫዎችንና ግጭቶችን በማበረታታት የተጠመዱ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች፣ በዚህ መንገድ የሚፈልጉትን ዓላማ እናሳካለን ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል፡፡ ሞኝ ይመስል ከስህተት አለመማር የሚያስገኘው ለውጥ የለም፡፡ ንፁኃንን እያስፈጁ የረከሰ ዓላማ ሒሳብ ማወራረጃ ማድረግ ወንጀል ነው፡፡ አገር የሚያስፈልጋት ሰላም ነው፡፡

ለመሠረታዊ ለውጥ የሚያግዙ አቅም ያላቸው ዜጎች በአገር ውስጥም በውጭም እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ይህ አቅም ጥበብን ከብልኃት ጋር አዛምደው ሲጠቀሙበት ውጤቱ ከሚጠበቀው በላይ ነው፡፡ በመጀመርያ አገር ለምትባለው የጋራ ቤት ማሰብ፣ አርዓያነት ያለው ሥነ ምግባር መላበስ፣ ለዴሞክራሲ መሠረታዊ እሴቶች ዋጋ መስጠት፣ ከአድልኦ አስተሳሰብ በመላቀቅ ሰብዓዊ ፍጡራንን እኩል ማስተናገድ፣ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል እውነተኛውና ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ማግኛ ብቸኛ መንገድ መሆኑን ማመን፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ከልብ መሥራት፣ ከአመፃና ከውድመት ድርጊቶች መታቀብ፣ ሕዝብን ማክበርና ለፈቃዱ መታዘዝ ከተቻለ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡ ይህ ምኞት የሚሳካው ግን በዋዛ አይደለም፡፡ በበርካታ አደናቃፊ ችግሮች የተከበበ ነው፡፡ ሆኖም ለአገር ማሰብ ከተቻለ ከፀሐይ በታች የማይቻል ነገር የለም፡፡ መሰሪነትና ሴረኝነት በተፀናወተው ፖለቲካችን ለቅንነት አንድ ስንዝር ቢገኝለት ይኼ ከባድ ወቅት በጥበብ ይታለፋል፡፡፡ ቅንነት በስፋትና በጥልቀት ሲናኝ ደግሞ ኢትዮጵያ አገራችን አንገቷን ካስደፋት ቀውስ ውስጥ በፍጥነት ትወጣለች፡፡ በአራቱም ማዕዘናት ያለው ሕዝባችን ደስ ብሎት በነፃነት እንዲኖር፣ ቅንነት የግድ የሚልበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ፈተናው ከባድ ቢሆንም ማለፍ ይቻላል፡፡ ለዚህ በጎ ምኞት መሳካት ግን ሰላም ለማስፈን መረባረብ ተገቢ ነው፡፡ ከሰላም የተሻለ አማራጭም ሆነ አቋራጭ የለም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል...

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...