በመንግሥት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚሠሩ ሠራተኞች፣ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችሉ ጥናቶች መጠናቀቃቸው ተገለጸ፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተዋል፡፡ ፓርኮቹም 86 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ ቀጥተኛ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት ወጣት ሴቶች እንደሆኑ የገለጹት አቶ ሽፈራው፣ ጤንነቱና ደኅንነቱ በተጠበቀ መኖሪያ ቤት እንዲኖሩ ማስቻል በምርታማነት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ፈታኝ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የቤት አቅርቦት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
እስካሁን የተሳካ ሥራ ተሠራ የሚባለው በቦሌ ለሚ የኢንዱስትሪ ፓርክ አንድ ኩባንያ ከሁለት ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የቤት ግንባታ አከናውኖ ሠራተኞችን ማኖር መጀመሩ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ኩባንያው አሁንም እስከ ስድስት ሺሕ ሠራተኞችን ለማኖር የሚያስችሉ ቤቶችን ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ተብሏል፡፡
በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁ ለስድስት ሺሕ ሠራተኞች የሚሆኑ ዓለም አቀፍ የዲዛይን ይዘት ያላቸው ቤቶችን ለመገንባት አንቴክስ የተባለው ኩባንያ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሽፈራው፣ በሐዋሳም በተለያዩ ዲዛይነሮች የቤቶች ግንባታ ተግባራዊ ይደርጋል ብለዋል፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚገኝ ብድርን ታሳቢ በማድረግ፣ ሕጋዊ ይዞታ ያላቸው በኢንዱስትሪ ፓርኩ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ብድር እየወሰዱና ቤት እየሠሩ ለሠራተኞች ተደራሽ የሚሆንበትን ዘዴ በመፍጠር፣ በሌላ በኩል ባለሀብቶች በሌሎች ፓርኮች እንደሚያደርጉት የራሳቸውን ግንባታ እንዲያከናውኑ የሚደረግበት ሁኔታ በማመቻቸት፣ እንዲሁም የሪል ስቴት አልሚዎች እንዲሳተፉ በማድረግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ለሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጤታማነት ወሳኝ እንደሆነ ያስታወቁት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮ በሚቀጥለው የበጀት ዓመት ከቤቶች ግንባታ ጋር በተያያዘ እንዴት መሥራት ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ጥናቶች እንደተከናወኑ አስታውቀዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በዚህ ሥራ ውስጥ በጀት ይዞ የማይገባ ቢሆንም፣ ሌሎች ቁልፍ አካላት የሚባሉት አየተሳተፉ የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለማቅረብ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ቤቶቹ የሚገነቡት በበቂ ሁኔታ በክልሎች ተከልለው በተሰጡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ቤቶቹ ወደ ሠራተኞች የሚተላለፉት በሚገነቡዋቸው ድርጅቶች በነፃ እንደሆነ፣ ሆኖም ኮርፖሬሽኑ በሒደቱ ላይ ክትትል የማድረግ ሚና እንዳለው ተጠቁሟል፡፡
በሪል ስቴት ደረጃ የሚገነቡ ቤቶችን በተመለከተ በኮርፖሬሽኑ ውል ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ኢንቨስተሩ ወይም ኩባንያውና የሪል ስቴት አልሚው እንደሚዋዋሉ ተገልጾ፣ ይህም ኩባንያዎቹ ለሠራተኞቻቸው የሚያወጡትን የትራንስፖርት ወጪ ለመቀነስና የምርታማነትን ጊዜ ለመጨመር በሚል የሚደረግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ለ6,500 የፋብሪካ ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ለማቅረብ ኮርነር ስቶን ሀውሲንግ ደቨሎፕመንት ግሩፕ ከተባለ ኩባንያ ጋር ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስምምነት እንዳካሄደ ያስታወሱት አቶ ሽፈራው፣ ይህ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 13 ሕንፃዎችን ያካተተ ነው፡፡ ገንብቶ ለማጠናቀቅ 18 ወራት እንደሚያስፈልግ፣ ፕሮጀክት ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለውን የቤት አቅርቦት ችግር ያቃልላል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚገኙ ሠራተኞች የሚደረገው የቤት ልማት እንቅስቃሴ፣ በሌሎች ፓርኮችም እንደሚቀጥል አቶ ሽፈራው ጨምረው ገልጸዋል፡፡