አቢሲኒያ ባንክ ለአራት የግል ማይክሮፋይናንስ ተቋማት የፋይናንስ አቅም ማጎልበት የሚያግዝ የ600 ሚሊዮን ብር ብድር ለማቅረብ ስምምነት ተፋራረመ፡፡ ባንኩ ብድር ለማቅረብ ስምምነት ያደረገው ከዳይናሚክ፣ ከሐርቡ፣ ከመተማመንና ከንስር ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ጋር ነው፡፡
በአቢሲኒያ ባንክና በአራቱ የፋይናንስ ተቋማት መካከል ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ተቋማቱ ተንቀሳቃሽ የብድር ዋስትና የሚያገኙበትን ዕድል እየፈጠረ አነቃቂ የብድር ሥርዓት አማራጮች እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ነው፡፡
ስምምነቱ የ600 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ያንግ አፍሪካ ወርክስ (Young Africa Works) ስትራቴጂ መሠረት በተደራጀው ብሪጅ ፕሮግራም የሚሰናዳ ነው፡፡ ከፈርስ ኮንሰልት ጋር በአጋርነት የሚተገበር እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የፋይናንስ እጥረት የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ትልቁ እንቅፋት ሲሆን፣ ይህም በገንዘብ ተቋማት ለጥቃቅንና አነስተኛ ማዕከላት የተመቸ የብድር ዋስትና ዕድል ባለመኖሩ ነው፡፡
ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት አበዳሪ አካላት ለብድር ማስያዣ ዋስትና የሚጠይቁትን ቋሚ ንብረት እንደ መሬት ወይም ሕንፃ አለማግኘታቸው የገንዘብ አቅማቸውን እንዳያጠናክሩ አግዷቸው እንደነበርና በተደረገው ስምምነቱ ችግራቸውን በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍ እንደሚያስችል ተነግሯል፡፡
የአዲስ ምዕራፍ መጀመርያ የሆነው ስምምነት አዲሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ተንቀሳቃሽ የብድር ዋስትና ምዝገባ መመርያን ለመተግበር ጭምር ያስችላል ተብሏል፡፡
ይህንኑ ጉዳይ በሚመለከተው የብሔራዊ ባንክ መመርያ፣ ባንኮች የሚያስቀምጡትን ሁለት መሥፈርቶች የሚይዝ ነው፡፡ ይህም በግብርናው መስክ ለተሰማሩ ግለሰቦች፣ ለኅብረት ሥራ ማኅበራትና ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ብድሮችን ተደራሽ ማድረግ፣ ብድሩ የተለዩት ተጠቃሚ አካላት እንዲደርስ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት እንዲሁም በጅምላ ብድሮች የሚሰጥበት የብድር ተቋም ማደራጀት ናቸው፡፡
ከአቢሲኒያ ባንክ ጋር የተደረሰው ስምምነት ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ከዚህ በፊት ጥብቅ የሆነባቸውን የዋስትና መሥፈርቶችን በማቅለል ከገንዘብ ምንጮች የሚደረግ ድጋፍን የሚያጠናክር የጅምላ ብድር መድረክ መፍጠር ይሆናል ተብሏል፡፡
ብሪጅስ ፕሮግራም ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የገንዘብ ማፈላለግ ሒደቱን ሲሠራበት የቆየ ሲሆን፣ የፋይናንስ እጥረት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታትና መፍትሔዎችን ለባንኮች እንዲሁም ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እየሠራ እንደሚገኝም ስምምነቱን በተመለከተ በማቅረብ ያወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡
በዚህ ስምምነት ዙሪያ የዳይናሚክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በዕውቀቱ አላምረው እንደገለጹት፣ ‹‹ዳይናሚክ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በብሪጅስ ፕሮግራም አማካይነት የቴክኒክ ዕገዛ እንዲሁም የገንዘብ ሽፋን በማሰናዳት ወጣቶች ብዙ ርቀት እንዳይሄዱ የሚያደርግ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡
‹‹ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ባለፉት ዓመታት ያጋጠሟቸውን የተለመዱ የብድር ፈንድ ተግዳሮቶች ለማስወገድ ጊዜው አሁን ነው፤›› ያሉት የንስር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳዊት ዋቅጋሪ፣ ስምምነት ባንኮች ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ ምንጮችን እንዲፈጥሩ ብቻ ሳይሆን ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የትስስር ማዕቀፍ ለማቋቋም የሚያገለግል ይሆናል ብለዋል፡፡ አያይዘውም የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለጥቃቅንና አነስተኛ ማዕከላት የፋይናንስ ተደራሽነትን እንዲያሳድጉ እንቅፋት የሆነውን የገንዘብ እጥረት ችግር የሚፈታ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የአቢሲኒያ ባንክ አመራሮች በሰጡት መግለጫ፣ ለብሪጅስ ፕሮግራምና ለማስተር ካርድ ፋውንዴሸን በባንኩና በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት መካከል ያለውን ትስስር በማመቻቸታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ስምምነቱን ለወጣቶች ፋይናንስ ተደራሽ በማድረግ የጥሬ ዋስትና ጥያቄዎችን ለማቃለል እንደ ትልቅ አማራጭ እንደሆነ ጠቁመወዋል፡፡
‹‹ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ለወጣቶች ዕድሎችን ለማመቻቸት ወሳኝ ሚና ቢኖራቸውም አሁንም አዳጋች ተግዳሮትና ዕድል ነው፡፡ ይህ አዲስ አጋርነት ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የሥራ ዕድል ፈጠራን አቅም ለመጨመር በሚጫወተው ሚና ደስተኞች ነን›› ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ ዓለማሁ ክንዴ ናቸው፡፡
አቢሲኒያ ባንክ ከ25 ዓመታት በላይ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ከስምምነቱ አትራፊ የግል ባንኮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ባንኩ የ2013 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በተመለከተ ይፋ ባደረገው መረጃ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 2.87 ቢሊዮን ብር አትርፏል፡፡ ከ560 በላይ ቅርንጫፎችም አሉት፡፡