አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በሐረሪ ከተማ የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ክፍያ ሥርዓትን ለማዘመን የአንበሳ ሄሎካሽ ባንኪግ አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለውን የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ባንኩ ይህንን የሦስትዮሽ ስምምነት ያደረገው ከሐረሪ ክልል ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣንና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ‹‹ደራሽ የተቀናጀ የአገልግሎት ክፍያ ሥርዓት፤›› ጋር ነው፡፡
ዓርብ ሐምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው የስምምነት ፊርማ ላይ እንደተገለጸው፣ የተቀናጀ የክፍያ ሥርዓቱ በሐረሪ ክልል የሚገኙ የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያቸውን ‹‹አንበሳ ሄሎካሽ›› በተሰኘ የሞባይል ወኪል ባንክ አገልግሎት በኩል ለመፈጸም የሚያስችል ነው፡፡
ይኼኸኼሔኼሔሄው የሞባይል ወኪል ባንክ አገልግሎት የባለሥልጣኑ ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያቸውን እንደ ከዚህ ቀደም በአካል ቀርበው መክፈል ሳይጠበቅባቸው ካሉበት ሥፍራ ሆነው በእጅ ስልካቸው አማካይነት ክፍያ ለመፈጸም የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡
የክፍያ ሥርዓቱ በሐረር ከተማ የሚገኙ የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ደንበኞች ክፍያ ለመፈጸም ያጋጥማቸው የነበረውን ውጣ ውረድ ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር ከመሆኑም በላይ፣ ጊዜ ቆጣቢ መሆኑን የባንኩና የሐረሪ ውኃና ፍሳሽ ኃላፊዎች ስለ አገልግሎቱ በሰጡት ማብራሪያ አመልክተዋል፡፡
የተቀናጀ የአገልግሎት ክፍያ ሥርዓቱ በአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ የሄሎካሽ አገልግሎት፣ በኢንፎርሜን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ደራሽ የተቀናጀ የአገልግሎት ክፍያ ሥርዓት አቅራቢነት እንዲሁም በሐረሪ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ትብብር የሚሠራ ነው፡፡ አጠቃቀሙም ቀላል፣ ፈጣንና አስተማማኝ የክፍያ ሥርዓት እንደሆነም በዕለቱ ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ይህንን አገልግሎት በተመለከተ የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ተከስተ እንደገለጹት፣ ደንበኞች የክፍያ አገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን መጀመርያ በአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ የአንበሳ ሄሎካሽ ሒሳብ መክፈት የሚጠበቅባችው ሲሆን፣ ከሐረሪ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የሚሰጣቸውን የደንበኛ ኮድ በማስገባት ከሞባይል ሒሳባቸው ክፍያውን በቀጥታ መፈጸም ይችላሉ፡፡
ደንበኞች ከሐምሌ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የውኃ አገልግሎት ክፍያቸውን በአንበሳ ሄሎካሽ በኩል መፈጸም የሚችሉ ሲሆን፣ ክፍያውን እንደፈጸሙ ደንበኞች የክፍያ ማረጋገጫ አጭር የጽሑፍ መልዕክት (SMS) በስልካቸው ይደርሳቸዋል፡፡
አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በሄሎካሽ የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የአውቶቡስ የጉዞ ትኬት መቁረጥና አውታር ኦንላይን የሙዚቃ ግብይት አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆን፣ የአንበሳ ሄሎካሽ አገልግሎት ደንበኞችን የሞባይል የአየር ሰዓት መግዛት፣ ገንዘብ መላክ፣ መቀበልና ወጪ ማድረግ እንዲሁም ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክ ክፍያዎችን መፈጸም እንደሚያስላቸውም ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ደንበኞች በሞባይላቸው ከሚያደርጉት ክፍያ በተጨማሪ በአቅራቢያቸው በሚገኙ የአንበሳ ባንክ ቅርንጫፍ እንዲሁም የባንክ ወኪሎች ጋር በመሄድ የውኃ አገልግሎት ክፍያ መፈጸም የሚችሉበት የአሠራር ሥርዓት የተዘረጋ መሆኑም ታውቋል፡፡
አንበሳ ሄሎካሽ ከ6,000 በላይ ደንበኞች አሉት፡፡ በመላ አገሪቱ ባሉ ከ3,000 በላይ ወኪሎች አማካይነት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ባንክ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የሐረር ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን አገልግሎት 22,000 ደንበኞች እንዳሉት የገለጹት የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጁ አቶ አህመድ ሰይድ፣ የሐረር ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት እስካሁን 16,000 ደንበኞቹን በሞባይል ስልክ በማገናኘት ክፍያቸውን በጊዜያዊነት በሞባይላቸው ክፍያ እንዲፈጸሙ ይደረግ ነበር ተብሏል፡፡ ከዚያም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ክፍያው በዚያ እንዲፈጸም በማድረግ ሲሠራ እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ከአንበሳ ባንክ ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት ተገልጋዮች አማራጭ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል፡፡