Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት​​​​​​​መፍትሔ የታጣለት የኦሊምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እሰጣ ገባ

​​​​​​​መፍትሔ የታጣለት የኦሊምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እሰጣ ገባ

ቀን:

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የአትሌቶችና ኦፊሻሎች የጉዞና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ሐምሌ 19 ቀን 2013 ዓ.ም.  ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ጋዜጣዊ መግለጫውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገዛኸኝ አበራ እና የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በጋራ ሰጥተዋል፡፡ 

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የቶኪዮ 2020 (2021) ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ቡድን አጠቃላይ ሁኔታ ‹‹መንግሥታችንና ሕዝባችን ይወቅልን›› ያሉትን ጉዳይ አብራርተዋል፡፡

እንደ ጋዜጣዊ መግለጫው ከሆነ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሥሩ ባደራጃቸው የቴክኒክና የሕክምና ኮሚቴ ተግባራትን ተቆጣጥረው እንዲሠሩና በየጊዜው ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ በማቅረብ ከኅዳር ወር 2013 .. ጀምሮ፣ ተገቢውን ክትትልና ውሳኔ በመወሰን የአትሌቲክስ ቡድኑን ለጉዞ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የመጀመርያው ልዑክ ሐምሌ 13 ቀን ወደ ጃፓን ሲያመራ፣ ሁለተኛው ዙር ተጓዦች ሐምሌ 17 ወደ ሥፍራው አቅንተዋል፡፡ ከጉዞ ሒደትና ከአትሌቶች ምርጫ ጋር በተያያዘም እየተነሱ ያሉትን ችግሮች ግልጽ ሊሆኑ ይገባቸዋል ያላቸውን ጉዳዮች ፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡ የአትሌቶች ምልመላና ምርጫን በተመለከትም አትሌቶች የተመለመሉበትና ወደ ሆቴል እንዲገቡ የተደረገው በዓለም ላይ ባገኙት የተሻለ የሩጫ ሰዓት መሆኑን ገልጾ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ክፍተት የታየበትን የሦስት ሺሕ ሜትር መሰናክል ወንዶችና 5,000 ሜትር ወንዶችን አመራረጥ ላይ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

በተለይ በሦስት ሺሕ መሰናክል ከለሜቻ ግርማ ጋር በተያያዘ ምርጫ ውስጥ መካተት አለመቻሉን ተከትሎ፣ ከፍተኛ ቅሬታ ሲነሳ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

እንደ መግለጫው ከሆነ፣ አትሌቱ በኳታር ዶኃ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባመጣው የተሻለ ውጤት ስምንት ወራት በፌዴሬሽኑ ፍላጎት የቡድኑ አባል ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ በደረሰበት የእግር ጉዳት የማጣሪያ ውድድሮችን ሊሳተፍ አልቻለም፡፡

በዚህ ምክንያት ጥር 8 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው የመጀመርያ ማጣሪያ50ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድርም እንዲሁም የአትሌቲክስ ቡድኑ የመጨረሻ ማጣሪያ በሆነው የሄንግሎ ትሪያል መሳተፍ ያልቻለ መሆኑን ተገልጿል፡፡

በፌዴሬሽኑ ውሳኔ ከቡድኑ ጋር እንዲቆይ በማድረግ እስከ መጨረሻው የምዝገባ ሰኔ 28 ቀን ድረስ ውጤታማ ሆኖ ባለመገኘቱ ከተወዳዳሪነት መሰረዙ ተገልጿል፡፡ በአንፃሩ በኦሊምፒክ ኮሚቴው ዝርዝር (Short List) ላይ ተመዝግቦ እንደሚታይና ሦስተኛ ደረጃ ያገኘው ይለ ማርያም አማረ የተሰረዘ መሆኑ፣ በመጨረሻው የጉዞ ቀን ፌዴሬሽኑ ማወቁን ገልጾ፣ ይኼም አሠራር በፌዴሬሽኑ በኩል ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል ተደምጧል፡፡

በሌላ በኩል ከአትሌቶች ምርጫ ጋር በተያያዘ ክርክር ሲያስነሳ የነበረው አምስት ሺሕ ሜትር ወንድ ተወዳዳሪዎችን በሚመለከት ነበር፡፡

ከመጀመርያው የዝግጅት ጊዜ ጀምሮ በረጅም ርቀት ማለትም አምስት ሺሕ አሥር ሺሕ ሜትር ልምምድ ሲያደርጉ ከነበሩት አትሌቶች መካከል እንደየፍላጎታቸውና ልምዳቸው መሠረት በሄንግሎ ትሪያል የተወዳደሩና ውጤታማ የሆኑ አትሌቶችን በመለየት በወቅቱ ፌዴሬሽኑ ለኦሊምፒክ ኮሚቴው መግለጹን አስታውቋል፡፡

ሆኖም ከፌዴሬሽኑ ዕውቅና ውጭ አሥር ሺሕ ሜትር በመወዳደር አራተኛ ደረጃ በማገኘት ተጠባባቂ የነበረው ሃጎስ ብረሕይወት፣ ለፌዴሬሽኑ ሳያሳውቅ ከሆቴል ወጥቶ የሄደና አምስት ሺሕ ሜትር ዝርዝር ውስጥ እንደተካተትና  በተጨማሪም የአምስት ሺሕ ሜትር ተወዳዳሪው ሙክታር እድሪስ በማጣሪያ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ከቡድኑ የተቀነሰ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዓት በኦሊምፒክ ቡድኑ ውስጥ ተካቶ ለመጓዝ ዝግጅቱን ማጠናቀቁና የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረጉን ፌዴሬሽኑ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ በዝግጅትና በውድድር ውጤታቸውን ማረጋገጥ የቻሉ  አትሌቶችን መብት የሚጋፋ ከመሆኑም በላይ፣ ‹‹በሕዝባችን ውስጥ መወናበድና ማሳሳት እየተፈጠረ በመሆኑ›› በአግባቡ ማሳወቅ እንደሚገባ እንዲሁም፣ ተገቢ የሆኑ አትሌቶችም መብታቸው እንዲከበር ማድረግ ይገባል ሲል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ይሞግታል፡፡

የጉዞ ሒደትንና መረጃ አሰጣጥን በሚመለከት የአንድ አገር የስፖርት ልዑክ አገሩን ወክሎ የሚገኝ አምባሳደር ተደርጎ አንደሚቆጠር የጠቀሰው ፌዴሬሽኑ፣  ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለጉዞ የሚያስፈልገው ፓስፖርት፣ አክሬዲቴሽን፣ የአውሮፕላን ትኬትና ሌሎች መረጃዎች ቀድሞ ለአትሌቶች ማሳወቅ ሲኖርበት፣ አትሌቱ በጥሩ ሥነ ልቦናና ዝግጅት ጉዞውን እንዳይፈጽም አድርጎታል፡፡

በጉዞ ዕለት በአየር መንገድ ውስጥ የተገኙት የሦስት ሺሕ መሰናከል አትሌቱ ኃይለ ማርያምና የሕክምና ባለሙያው አያሌው ጥላሁን (ዶ/ር)፣ በሕግ እንደሚፈለግ  ግለሰብ ከአየር ማረፊያው እንዲመለሱ መደረጋቸው አግባብ አለመሆኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ተጠቅሷል፡፡

በተለይ የሕክምና ባለሙያው ለስምንት ወራት አትሌቶቹን በሕክምና ሙያ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩና ሰባት ጊዜ በኦሊምፒክ በመሳተፍ ልምድ ያላቸው ባለሙያ ከአየር መንገድ መመለሳቸው፣ አጠቃላይ የአትሌቱንና የኦፊሻሉን ሥነ ልቦና በመጉዳት ውጤት እንዲበላሽ የሚያደርግ አሠራር በመሆኑ፣ ሁሉም ተጓዦች የጉዞ መረጃዎች ግልጽ እንዲሆን ጠይቆ ጉዳዩን ደግሞ ‹‹መንግሥትና ሕዝብ እንዲያውቅልኝ›› ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተመርጠው የአትሌቲክስ ቡድኑ መሪ የሆኑት በዛብህ ወልዴ (ዶ/ር) እና የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በኦሊምፒክ መንደር ውስጥ ገብተው ተገቢውን የአትሌቶች ክትትልና ድጋፍ እንዳያደርጉ ከውድድሩ ቦታ 38 ኪሎ ሜትር ርቀት ባለው ሆቴል እንዲቀመጡና ምንም ዓይነት መረጃ እንዳያገኙ እንደተደረጉ ፌዴሬሽኑ በጋዜጣዊ መግለጫው አንስቷል፡፡

 ‹‹በውድድር ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ልምድና ክህሎት ያላቸው የአስተዳደር፣ የቴክኒክና የሕክምና ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ አሁን የምንመለከተው ግን ቡድኑን አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ በውድድር ወቅት የቴክኒክና የዶፒንግን ሁኔታዎችን የሚከታተሉ በተለይም በማራቶን ውድድር ወቅት በየጣቢያው በመገኘት ለአትሌቶቻችን ውኃና ተጨማሪ ምግብ የሚያቀርቡ በቂ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የቴክኒክ ቡድን መሪም ባለመመደቡ በውጤቱ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያደርስ ስለሆነ ከወዲሁ ማስተካከያ እንዲደረግበት፣ ይህንንም መንግሥታችንና ሕዝባችንን እንዲያውቀውና እንዲከታተለው እንጠይቃለን፤›› ሲል ፌዴሬሽኑ በጋዜጣዊ መግለጫው አሳስቧል፡፡

ከአንድ ዓመት መራዘም በኋላ መከናወን የጀመረው የቶኪዮ ኦሊምፒክ፣  ጨዋታው እየተከናወነ ባለበት በአሁኑ ወቅት በጃፓን ከፍተኛ የሆነ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ ሥጋቱ ሁሉም ዘንድ አለ፡፡ አሁንም ቢሆን መሰረዝ ወይም መቋረጥ አለበት የሚሉ አስተያየቶችም አልታጡም፡፡

ሆኖም በኮቪድ-19 ምክንያት ለሚከሰተው ችግር መወዳደር የማይችሉ አትሌቶች ቢኖሩ ተጠባባቂ አትሌቶች መሄድ ሲገባቸው፣ ተወዳዳሪ አትሌቶችና ኦፊሻሎች እየተቀነሱ የማይመለከታቸው 30 በላይ የሚሆኑ ሌሎች ግለሰቦች የተሰጠውን ኮታ መሙላታቸው መንግሥትና ሕዝብ ይወቅልን ሲል አብራርቷል፡፡

ሹክቻ የማይለየው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጉዳይ ገና ዝግጅት ሲጀማምር ውዝግብ ውስጥ መግባቱ ይታወሳል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ በአትሌቲክስና ኦሊምፒክ ኮሚቴ መካከል የተከሰተው አለመግባባት ይፈታል ተብሎ ቢጠበቅም ጭራሽ እየባሰበት መጥቷል፡፡ ስፖርት ኮሚሽንም ሆነ ባህልና ቱሪዝም ችግሩን ይፈታሉ ተብሎ ቢጠበቅም ምንም ዓይነት መፍትሔ ሲያመጡ አልታዩም፡፡

የዘንድሮ ኦሊምፒክ በርካታ ችግሮችን እያስተናገደ ሲሆን፣ በተለይ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ወቅት ኢትዮጵያ በተሟላ መልኩ አለመቅረቧ በርካቶችን አስቆጥቶ ነበር፡፡

ይኼም ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ የነበራትን በጎ ገጽታ ከማጠልሸትም ባሻገር፣ ከዚህ ቀደም ጀግኖች አትሌቶች ያኖሩትን ታሪክ ክብር መንሳት እንደሆነ በርካቶች አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ከነገ ሐሙስ ሌሊት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የማጣሪያ ውድድር የሚያደርጉ ሲሆን፣ ከወዲሁ ወደ ሥፍራው ማምራት ጀምረዋል፡፡ ሆኖም ከዚህ ቀደም ስም ዝርዝራቸው በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይፋ የሆኑ አትሌቶች ቢኖሩም አሁንም ከኤርፖርት ይመለሱ አይመለሱ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...