ቴሌ ብር እና ሄሎ ጤና የጤና መረጃ አገልግሎትን በቀላሉ ማድረስ የሚያስችልና ለተለያዩ የሕክምና ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ የጥሪ ማዕከል ይፋ አድርገዋል፡፡
የጤናውን ዘርፍ ለማገዝ የሕክምና አገልግሎት ከምክር ጋር ማግኘት ከሚያስችለው 8455 የጥሪ ማዕከል ለሚገኘው አገልግሎት ከቴሌ ብር ዋሌት መክፈል እንዲቻልም ተደርጓል፡፡
የሕክምና ባለሙያዎች ምላሽ የሚሰጡበትን የጥሪ ማዕከሉን አገልግሎት ለማግኘት በቴሌ ብር በኩል የአገልግሎት ክፍያ መፈጸም እንደሚያስፈልግ የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል መኒ የሥራ ክፍል ኃላፊ አቶ ብሩክ አድሃና ተናግረዋል፡፡
ሄሎ ጤና አገልግሎት ኅብረተሰቡ በማንኛውም ቦታና ሰዓት የምክር አገልግሎትና የሕክምና ቀጠሮ ማመቻቸት የሚያስችል መሆኑን የሄሎ ጤና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሜሎን በቀለ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የጥሪ ማዕከሉ 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ ተላላፊ በሆኑና ባልሆኑ በሽታዎች እንዲሁም ኮቪድ-19ን ለተመለከቱ ጥያቄዎች በሕክምና ባለሙያዎች ምላሽም ይሰጣል፡፡
አገልግሎቱ የሕክምና ማዕከላትን መጨናነቅ ለመቀነስ፣ ታካሚዎች ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በውጭ አገሮችም ቀጠሮ ለማስያዝ ያስችላል፡፡ የእንስሳትና የዕፅዋት ሕክምና የማማከር አገልግሎትም ይሰጣል፡፡