Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምቱኒዚያ ዳግም በአመፅ

ቱኒዚያ ዳግም በአመፅ

ቀን:

R2217 Briefs

Keywords:-

Seble

ቱኒዚያ ዳግም በአመፅ

ከአሥር ዓመታት በፊት የዓረብ አገሮችን ያናወጠው አብዮት መነሻ ነች፡፡ ዓረብ ስፕሪንግ (የዓረብ አብዮት) መወለጃ የሆነችው ቱኒዚያ እንደ ሶሪያ፣ የመንና ሊቢያ እስካሁን ለዘለቀው የርስ በርስ ጦርነት አልተዳረችም፡፡ የዓረብ አብዮት ግቡን ከመታባቸው አገሮችም ቀዳሚ ናት፡፡

እ.ኤ.አ. በ2011 በቱኒዚያ ከተካሄደው የዓረብ አብዮት በኋላ በአገሪቱ በርካታ ዴሞክራሲያዊ መዋቅራዊ ለውጦች ተካሂደዋል፡፡ ምንም እንኳን ቶሎ ቶሎ ሹመኞችን ማንሳትና የሥልጣን መቀያየር ቢኖርም፣ ከቀደመው የተሻለ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲካሄድም መሠረት ጥሏል፡፡

አብዮቱ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በቅጡ ለመፍታት ባያስችልም፣ እንደሌሎቹ የዓረብ አገሮች ብጥብጥ፣ ጦርነትና የርስ በርስ ግጭት ውስጥ አለመክተቱ በአገሪቱ የተካሄደውን አብዮት በተወሰነ መልኩ ውጤታማ አድርጎታል፡፡

ከአልጄሪያ በምዕራብ ከሊቢያ በደቡብ የምትዋሰነውና ከ11.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ቱኒዚያ፣ ዜጎቿ በአገሪቱ ለውጥ ያመጣውን አመፅ ካካሄዱ በኋላ ዳግም በስፋት ወደጎዳና የወጡት ሰሞኑን ነው፡፡

ከአሥር ዓመታት በፊት የቱኒዚያ አብዮት እንዲቀሰቀስ የመጀመርያው ምክንያት አትክልት በመሸጥ ይተዳደር የነበረው መሐመድ ቦዚዝ የመሸጫ ጋሪው በፖሊስ ከተወሰደበት በኋላ ራሱን በእሳት አቃጥሎ መግደሉ ነበር፡፡

ለስርአተ ቀብር የወጡ በርካቶች ወጣት ሥራ አጥነት፣ የመንግሥት ብድር ጫና፣ ሙስና በቱኒዚያ ተንሰራፍቷልና መንግሥት ሥልጣን ይልቀቅልን ያሉበትም ነበር፡፡ ይህ ከሆነ ዛሬ አሥር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ሆኖም እነዚህ ችግሮች ዛሬም በቅጡ ያልተቀረፉ መሆናቸውን የሚገልጹ ወጣቶች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የፈጠረውን ኢኮኖሚያዊ ጫናም ጨምረው መንግሥታቸውን ጥያቄ አለን ብለዋል፡፡

ይህ ጥያቄያቸው የመጣው ደግሞ መንግሥት ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ በቂ ምላሽ አልሰጠም በሚል ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ካኢስ ሳኤድ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሂቺም ሚቺቺና ፓርላማውን አግደዋል፡፡

ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ቱኒዚያውያንን ለዳግም ተቃውሞ እንደዳረጋቸው የዘገበው አልጀዚራ፣ አገሪቱ ከ2011ዱ ዓረብ ስፕሪንግ በኋላ ከፍተኛ የተባለው የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብታለች ብሏል፡፡

እሑድ ሐምሌ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሂቺም ሚቺቺ ከሥልጣን ያገዱት ፕሬዚዳንት ሳኤድ፣ ፓርላማውን ማገድ ብቻ ሳይሆን የአባላቱን ያለመከሰስ መብትም ገፈዋል፡፡

አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሾሙና ካቢኔ እንደሚያዋቅሩ መግለጻቸውን ተከትሎም በተቀናቃኞቻቸው በኩል ዴሞክራሲ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ተብለዋል፡፡ በደጋፊዎቻቸው የድጋፍ ሠልፍ የተቸራቸው ፕሬዚዳንቱ፣ በፓርላማው አፈጉባዔ ግን ተወቅሰዋል፡፡

አፈ ጉባዔው የፕሬዚዳንቱን ድርጊት ‹‹በአብዮቱና በሕገመንሥቱ ላይ የተቃጣ መፈንቅለ መንግሥት›› ሲሉ ኮንነውታል፡፡

የሕዝቡን አመፅ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሥልጣን አንስተው ፓርላማውን ለ30 ቀናት ያገዱት ፕሬዚዳንቱ፣ የፓርላማው የዕግድ ጊዜ እንደ አስፈላጊነቱ ሊራዘም እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በአግባቡ አልተከላከላችሁም ይህም ለኢኮኖሚ ቀውስ ዳርጓል ያሉት ተቃዋሚዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን እንዲለቁ ጠይቀው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንቱ የኢኮኖሚ ውድቀቱን እንደሚያረጋጉ፣ በየመሥሪያ ቤቱ ከሚኒስትሮች ቀጥሎ ያሉ ሠራተኞች ኃላፊነት ወስደው እንዲሠሩ ማዘዛቸውንና አዲስ ካቢኔ እንደሚያዋቅሩ አሳውቀዋል፡፡

ቱኒዚያ ዳግም በአመፅ

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ይበልጡኑ የተጎዳው የቱኒዚያ ኢኮኖሚ የአገሪቱን ዜጎች ፈትኗቸዋል፡፡ ባለፈው ወር መግለጫ የሰጡት ጤና ሚኒስትሩም የአገሪቱ የጤና ሥርዓት መሽመድመዱን ተናግረው ነበር፡፡ ከ11.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት ቱኒዚያ ከ17 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሞተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱና የፓርላማ አባሎቹ የተመረጡት በተለያየ ጊዜ በተደረገው ምርጫ በ2019 ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ አምና ነው የተሾሙት፡፡ ከእሳቸው ቀዳሚ የነበሩት ኤልያስ ፋካፋኪ በሙስና ወንጀል በመጠርጠራቸው ነበር ከአጭር የሥልጣን ጊዜ በኋላ የተነሱት፡፡ እሳቸውን የተኩት ሚቺቺ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችል አቅምና አሠራር ባለመፍጠራቸውና አስቸኳይ ሪፎርም ባለማድረጋቸው ይወቀሳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ