- Advertisement -

ከተፋሰሱ አገሮች ስምምነት ዝንፍ ያላለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሙሌት አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው

አገራችን ምንም እንኳን የሕዝብና የመንግሥትን ቀልብ ሰቅሶ በያዘ ግጭትና ሕግ የማስከበር ዕርምጃ ላይ ብትሆንም፣ ክረምቱን የያዙ የልማት መርሐ ግብሮች ተጠናክረው መቀጠላቸው አልቀረም፡፡ አንዱ በአገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤቶቻችንም የተረፈ የአረንጓዴ ልማትና የችግኝ ተከላ ሥራ በተጠናከረ መንገድ መከናወኑን መንግሥት አረጋግጧል፡፡ ሌላው ትልቁ ስኬታማ ተግባር የኢትዮጵያ የዚህ ዘመን ትውልድ ሥጋት ላለባቸው ጎረቤቶቻችንም መራጋትን የፈጠረው ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ሁለተኛ ዙር ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ነው፡፡ በዚህም በመጪዎቹ ወራት ቢያንስ ከሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት እንደሚጀመር ተነግሯል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ከዋነኛ ፕሮጀክቶቻችን የመጀመርያዎቹን እሸቶች ስንቀምስ ግን ጎረቤቶቻችን በተለይ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችም ተቋዳሽ እንጂ ተጎጂ እንደማይሆኑ፣ በሙሌቱ ወቅት የታየው ተፅዕኖ አልባው የውኃ ፍሰት አንድ ማሳያ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡ ይህ ደግሞ በዓባይ ተፋሰስ አገሮች ቀድሞ የተያዘውን የጋራ አቋም ያጠበቀና በጋራ የመጠቀም የትብብር መንፈስን ያጠናከረ ዕርምጃ ተደርጎ በመወሰድ ላይ ነው፡፡

በመሠረቱ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚካሄዱ ማናቸውም ፕሮጀክቶች የዚህ ዘመን ትውልድ አሻራ ውጤቶች ናቸው፡፡ ምሥራቅ አፍሪካዊያኑ “ናይል” በሚሉት፣ በአብዛኛው የእኛ የተፈጥሮ ሀብት በሆነው ዓባይ ላይ በተፋሰሱ አገሮች መካከል ጠንካራ የትብብር ማዕቀፍ ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ የነበረው፣ ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ወዲህ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በተሟላ መንገድ ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች የስምምነት ማዕቀፉን በየምክር ቤቶቻቸው ባያፀድቁትም፣ የጋራ አቋም የተንፀባረቀበት ጉዳይ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በእርግጥ ለአሥር ዓመታት (እ.ኤ.አ. ከ1999 እስከ 2010 ገደማ) የዘለቀው የናይል ተፋሰስ አገሮች ስምምነት ብዙ የተደከመበት ነበር። በአንፃራዊነት የላይኛው ተፋሰስ አገሮች መግባባትና ተፅዕኖ ማሳደር የጀመሩበት በዕውቀትና በሙያዊ ብስለት ለመምከር ጥረት የተደረገበት ወቅት መሆኑም ይታመናል፡፡ በዚህ ረገድ አገራችን የነበራት የመሪነት ሚና በታሪክ ተከትቦ የሚኖር ብቻ ሳይሆን ኬንያ፣ ኡጋንዳና ሩዋንዳን የመሳሰሉ አገሮች አሁንም ለስምምነቱም ሆነ ለግድባችን ያላቸው አጋርነት በዘላቂነት የቀጠለ ነው፡፡

በቀደሙት ዘመናት በታችኛው ተፋሰስ አገርች በተለይም በግብፅና በአጋሮቿ በነበረው ጫና፣ በተለያዩ ጊዜያት በቀጣናው በተለይም በኢትዮጵያ በነበሩ መንግሥታት የአቅም ማነስ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ መዳከም ምክንያት ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ሕዝቦች ከውኃው ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸው የሚያስቆጭ ነበር። ያ ሁኔታ እዲቀጥል የሚፈቅድ ትውልድ ሊኖር እንደማይችል ግን በገቢር እየታየ ነው፡፡ የስምምነት ማዕቀፉ ግን ቢያንስ ውኃው ሌሎች ባለቤቶችም አሉት፣ ግማሽ ቢሊዮን የሚሆኑ ሕዝቦች የበይ ተመልካች ሆነው መቅረታቸውም ማብቃት አለበት የሚል መነሳሳትን ፈጥሯል፡፡ በእርግጥ በርካታ ግብፃዊያን ዓባይ ከየት እንደሚነሳ መገንዘብ የጀመሩት ከተፋሰሱ አገሮች ምክክር መጠናከርና ከኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመር ወዲህ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ፈርኦናዊያኑ ገዥዎች ሕዝባቸውን ለዘመናት ሲያወናብዱት በመኖራቸው ብዥታው ከፍተኛ ሆኖ ነው የቆየው፡፡

 “አፍሪካን ሶሳይቲ” በመባል የሚታወቀው የግብፅ ተቋም ዳይሬክተር በአንድ ወቅት (እ.ኤ.አ. በየካቲት 2019) ግብፅን ለጎበኘው የአፍሪካ ጋዜጠኞች ቡድን ይህንኑ ሐሳብ መናገራቸውን ተጽፎ አንብቤያለሁ፡፡ ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ዓረብ ነን ብሎ ያምን ነበር፣ 40 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከዚህ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት አቋም አልነበረውም። ይህም ከአፍሪካዊ ማንነትን ያፈነገጠ ብዥታ ማርበቡን የሚያሳይ ነው፡፡ “ዓባይ ሥሩ ኢትዮጵያ ፍሬው ግብፅ ነው” የሚለው ዓለም አቀፍ ትንታኔ የቆየ ጭብጥ ቢሆንም፣ ግብፅ አጠቃላይ ሕይወቷ የተመሠረተው በአፍሪካ ላይ መሆኑን እስከ መርሳት ደርሳ የነበረው ለዘመናት ነው፡፡ ከዚህ ሰመመን ነቅታ በዚያው በተለመደው የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ እያቅማማችም ቢሆን፣ በተለይ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ለመደራደር የሞከረችው ከዚያ በኋላ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ከዚህ ቀደም  ደጋግመው፣ ‹‹ግብፅ ከአፍሪካ ተነጥላ የኖረችባቸው ዓመታት አግባብነት አልነበራቸውም፣ ሥር መሠረቷን አስቷታል፣ ለዚህም ቀላል የማይባል ዋጋ ከፍላለች፤›› የማለታቸው መነሻም ይኸው ከሰመመን የመላቀቅ ጉዳይ ነበር የሚሉ ተንታኞች ትንሽ አልነበሩም።

- Advertisement -

በነባሩ ታሪክ ግን የግብፅ መሪዎችም ሆኑ ፖለቲከኞች በወሬ እንጂ በገቢር ለዚህ ዕሳቤ ሲገዙ አለመታየታቸው ለናይል ተፋሰስ አገሮች ስምምነት ዕውን መሆን የነበራቸውን ሸውራራ ዕይታ ያመለክታል፡፡ በእሱ ብቻ ሳይሆን በቅርቦቹ የሦስትዮሽ (ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ) የድርድር መድረኮች ላይ ሁሉ በሚያነሱት መንቻካና አደናቃፊ አቋም ደጋግመው ማሳየታቸው አልቀረም፡፡ ቢያንስ ግን አሁን ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሁለተኛው ሙሌት እንኳን ምንም ዓይነት ጫና ባለመፍጠሩ ወደ ቀልባቸው ሊመለሱ ይገባቸዋል፡፡

በዚህ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ብቻ ሳይሆኑ የመላው ዓለም የውኃ ሀብት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሞጋቾች የተስማሙበት እውነት መተግበሩን በስክነት መረዳት አለባቸው፡፡ የዓባይንም ሆነ የሌሎች አገሮች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የውኃ  አጠቃቀም ከግለኝነት ይልቅ በጋራና በሰጥቶ መቀበል መርህ ከመጠቀም ውጪ አማራጭ እንደሌለም መታመን አለበት፡፡

ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ውስጥ ረጅም ግዛት አቋርጦ ለም አፈሯን እየጠራረገ የሚከንፈው የዓባይ ወንዝ በግብፅ ተረጋግቶና የተለያዩ ጠቀሜታዎችን እየሰጠ መፍሰሱ ባይቀርም፣ በኢትዮጵም ትልቅ ጥቅም (ለጎረቤቶችም የሚተርፍ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ) መደረጉ ቅቡልነት ያለው ጥበበኛ ውሳኔ መሆኑን መቀበል ግድ ይላል፡፡ በተግባርም የታየው ይኸው እውነታ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም ሆነ ነገ በታላቁ የህዳሴ ግድባችን ብቻ ሳይሆን በሁሉም የውኃ ፕሮጀክቶቻችን ከመላው የናይል ተፋሰስ አገሮች ስምምነት ዝንፍ እንደማንል በተግባር መታየቱ የሚያኮራ ብቻ ሳይሆን፣ በመጭው የታሪክ ጉዞም አገርን እያረጋጉ ለተመሳሳይ ልማት መነሳት እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው፡፡

በመሠረቱ ገና ከመነሻው “የናይል ተፋሰስ አገሮች የጋራ ስምምነት ማዕቀፍ’’ ላይ በመመሥረት ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ተልዕኮው፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ነው፡፡ ይህም የሱዳንንም ሆነ የግብፅን መሠረታዊ ጥቅም እንደማይጎዳ፣ እንዲያውም ለሁለቱም የሚጠቅም መሆኑንና ጉልህ ተፅዕኖ እንደሌለው አገራችን ደጋግማ ስታስረዳ ነበር የቆየችው፡፡ እነሆ ገና በግድቡ ሙሌቶች የተረጋገጠው ሀቅም ይኸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የግብፅን የኖረ ሥጋት ለመቀነስ ከዓመታት በፊት በዓለም አቀፍና ከሦስቱ አገሮች በተውጣጡ የዘርፉ ሊቃውንት ፕሮጀክቱን እስከ ማስመርመር ደርሳለች፡፡ ምክረ ሐሳቡንም ከሞላ ጎደል በቅንነት  ተቀብላለች፡፡ የግድቡ ዲዛይን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን በዓለም አቀፍ የሙያተኞች ቡድን አረጋግጣለች፡፡ እነዚህ ሁሉ እውነታዎች ታዲያ ለጋራ ተጠቃሚነት ሲባል የተከፈሉ የሰጥቶ መቀበል ዕሳቤዎች እንጂ፣ በማንም ተፅዕኖ በመንበርከክ የተካሄዱ ሽንፈቶች አልነበሩም፡፡

እስካሁን በተካሄዱ ሙያዊ ግምገማዎች በተለይ ዋናው የኃይል ማመንጫ ግድብ በጠንካራ አለት ላይ ያረፈ መሆኑን፣ የመሬት መንቀጥቀጥ የማያሠጋው እንደሆነና በብዙ ሺሕ ዓመታት አንድ ጊዜ ጎርፍ ቢከሰት እንኳን ማሳለፍ እንደሚችል በጥናት  መረጋገጡ ለግብፅም ሆነ ለሱዳን ዕፎይታ የሚሰጥ መሆን ነበረበት፡፡ የጎርፍ ሥጋታቸውን የሚቀንስ ፕሮጀክት ለመሆኑም አሁን እንኳን በሺዎች የሚቆጠር ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እየታያዘ የሱዳን አንዳንድ ቦታዎች በጎርፍ እየተመቱ በመሆናቸው ነው፡፡ ሌላው ይቅር ከዓመታት በፊት የሙያተኞቹ ቡድን ባቀረበው ምክረ ሐሳብ (ሪኮሜንዴሽን) መሠረት ቀጣዩ ሥራ ምክረ ሐሳብን ተግባራዊ ለማድረግ የሦስቱን አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ግብፅ) ማዕቀፍ ማደራጀት ሆኖ ሲያበቃ፣ ቸል የተባለው በራሳቸው ሥጋት መነሻ ነው፡፡ ሦስቱ አገሮች ተገናኝተው ከዓመታት በፊት ገና መነጋገር ሲጀምሩ፣ ግብፅ በማዕቀፉ አባላት ላይ ተቃውሞ ማሰማቷም ቢሆን ገና ከጅምሩ ድርድሩን የፈለገችው ጊዜ ለመግዛትና ለማደናቀፍ ብቻ እንደነበር አሳይቶ አልፏል፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያና ሱዳን ከሦስቱም አገሮች የተውጣጡ ሙያተኞች ሥራውን መከታተል ይችላሉ ሲሉ ግብፅ ግን፣ ‹‹አይሆንም የዓለም አቀፍ ሙያተኞችም ካልገቡበት አሻፈረኝ›› ነበር ያላቸው፡፡ የአተገባበሩን የማዕቀፍ ኮሚቴ ለማቋቋም ሌላ ዓለም አቀፍ ኮሚቴ አያስፈልግም ብትባልም “አይሆንም” ብላም ነበር፡፡ እርግጥ ይህንንም “እሺ” ቢሏት ሌላ ተቃውሞ ማምጣቷ አይቀርም ነበር፡፡ ደግሞም አምጥታለች፡፡ በመሠረቱ በግንባታው ሒደት ላይ ስለአተገባበር ማዕቀፍ ምሥረታ አጀንዳ ተይዞ እያለ፣ ከአጀንዳው ውጪ የሆነና በሌሎቹ አገሮች ተቀባይነት የሌለውን የመተማመኛ ማጠናከሪያ ሲስተም የሚል ባለሰባት ነጥብ ዶሴ ተሸክማ የመጣችው ግብፅ ነበረች፡፡ የአንድ ትውልድ ዕድሜ በጠየቀ ውጣ ውረድና ድርድር የተረቀቀውን ስምምነት አገራችን ስትፈርምና ስታፀድቅ፣ ግብፅ የአገሯን አለመረጋጋት ሰበብ እያደረገች “ቋሚ መንግሥት ካልመሠረትኩ አልፈርምም” እያለች ስታንጓትት እንደነበርም የሚረሳ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ አባባሏን በትዕግሥት ያሠለፈችው ግን ይህ ጊዜ እንደሚመጣ ተዘንግቶ አልነበረም፡፡

ከዓመታት በፊት ካርቱም ውስጥ በተካሄደ ‹‹የምሥራቅ ናይል አገሮች የምክክር መድረክ›› ላይ አዘጋጆቹ ኢትዮጵያና ሱዳን፣ በህዳሴው ግድብ የግንባታ ሒደት ዙሪያ ያላቸውን ተመሳሳይ አቋም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ የባለሙያዎች ማብራሪያ አስደግፈው አቅርበው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የምክረ ሐሳብ ሒደቱን ለመታዘብ በሥፍራው ከታደሙ የበርካታ አገሮች አምባሳደሮች ዲፕሎማሲያዊ ከበሬታን አግኝተው እንደነበርም አይዘነጋም። ያን ዕሳቤ ዛሬ ዕውን መሆን በጀመረው ፕሮጀክታችን ሀቅነቱን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ቀደም ሲል የዚሁ “የምሥራቅ ናይል አገሮች የምክክር መድረክ’’ የተሰኘው ተከታታይ ውይይት አባል የነበረችው ግብፅ በአንፃሩ፣ መድረኩን ጥላ እንደ ወጣችና ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን የህዳሴ ግድብ ለማስቆም ያለመ ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ ለማሰባሰብ ፊቷን ወደ ምዕራባውያኑ ኃያላን መንግሥታት እንዳዞረች አይዘነጋም። በዚህም የአሜሪካ፣ የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት፣ በኋላም የዓረብ ሊግን በር እስከ ማንኳኳት ደርሳ ነበር፡፡ አገራችን ግን ነገም የምትኮራበትና በስክነት የተቀበለችው የአፍሪካ ኅብረትን አደራዳሪነት ብቻ በመሆኑ ወደ ውጤቱ ተቃርባለች፡፡

እስካሁንም ግን የዓባይ ውኃን የፍትሐዊና የምክንያታዊ አጠቃቀም ዲፕሎማሲ መቋጫ አልባ ያደረገው የካይሮ ተለዋዋጭ ሐሳብና የቅኝ ግዛት አቋም ብቻ ሳይሆን፣ የጋራ ስምምነቱን የመግፋት አካሄዷ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የኢትዮጵያን ጉዞ የሚያስቆም ባይሆንም፣ ለጊዜው እውነቱ እስኪታወቅ ድረስ የካይሮ ፖለቲከኞች የግብፅን ሕዝብ አፍ እያዘጉበት ነው፡፡ አሁንም ታዲያ መፍትሔው ውኃ መሙላት ብቻ ሳይሆን፣ ግድባችንን አጠናቅቆ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ፍሬ መልቀም ብቻ ነው፡፡ እርግጥ ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከወደ ካይሮ የሚሰማው ነገር የአገራችንን እውነትና የፍትሕን አሸናፊነት አመላካች ነው፡፡ ለአብነት ያህል ከሳምንታት በፊት የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ ሁለተኛው የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በአገራቸው ላይ የሚያመጣው ጉዳት እንደሌለ መናገራቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በአንድ በኩል የዘንድሮው ክረምት ከፍተኛ ጎርፍ እንደሚኖር፣ በሌላ በኩል በአስዋን ግድብ በቂ ውኃ መያዛቸውን በመጥቀስ ነበር ሥጋት እንደሌለባቸው ያስረዱት፡፡ ይህን የተናገሩትም ለአገሪቱ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሜቴ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ከቀናት በፊት ደግሞ ፕሬዚዳንት አልሲሲም ለመላው ሕዝብ ግድቡም ሆነ የውኃ ሙሊቱ የግብፅ ሥጋት እንደማይሆን፣ ነገር ግን ለጋራ ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚበጅ ስምምነት መፈራረም እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ሰምተናል፡፡ ታዲያ የካይሮ ሰዎች ያ ሁሉ ማደናገር፣ ሱዳንን ጭምር ጥቅሟን በሚበድል ደረጃ ወዲያና ወዲህ ማላጋትና ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ምክንያቱ ምን ይሆን ብሎ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በአገራችን የውስጥ ጉዳይ ገብቶ በሴራ እስከ ማባላትና ማዳከም ድረስ የሚጠነሰሰው ሸፍጥስ ምን ለማግኘት ነው ያስብላል፡፡ ነገር ግን አገራችንም ሆነች መላው የተፋሰሱ አገሮች የያዙትን የፀና አቋም ወደኋላ የሚመልስ ምንም ነገር የለውም፡፡

ግብፃዊያኑ ግን የተፋሰሱን የውኃ አጠቃቀም የበላይነታቸውን ለማስጠበቅና ኢትዮጵያ የዓባይን ትሩፋት መቅመስ ከጀመረች፣ ነገም በማይቆም የመልማት ፍላጎት ታመልጠናለች ከሚል ሥጋት የሚመነጭ ነው፡፡ ይህ ከሚሆንም አገሪቱ ትዳከም፣ ትንኮታኮት ከሚል እቡይነት ይነሳል፡፡ ይህ ሴራ ለማንም ሆነ ለማን የሚበጅ አይደለም፡፡ ብዙ ርቀትም የሚያሻግር አይደለም፡፡ በመሠረቱ ስምምነቱም እንዳለ ሆኖ አገራችን፣ “ዓባይን ገድቤ የግብፅን ጉሮሮ እዘጋለሁ” የሚል አቋም ጥንትም አልነበራትም፣ ዛሬም የላትም፡፡ ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሚሆን ኃይል እየሰጠ የሚያልፍ ግድብ ለመገንባት ነው የተነሳችው፡፡ ለግብፅ የሚሄደው የውኃ መጠን ትርጉም ባለው ሁኔታ ሳይቀንስ ኃይል አመንጭቶ የሚሄድና ጥቅሟን የማይነካ፣ ግብፆችን ጉልህ ሥጋት ውስጥ የማይጥል ፕሮጀክት ነው እየገነባች ያለችው፡፡ ዕውን እየሆነ ያለውም ይኸውና ይኸው ብቻ ነው፡፡

ሲጠቃለል በየትኛውም አጋጣሚ እንደ ሕዝብም ሆነ መንግሥት የተፋሰሱ አገሮችንም ሆነ ዓለም አቀፍ ኃይሎችን ከጎናችን ለማሠለፍ እንትጋ፡፡ የመልካም ግንኙነት ሥራችንንም እንቀጥልበት፣ በዓባይ ውኃ የመጠቀም የተፈጥሮ መብታችንም የማይሸራረፍ መሆኑን እንንገራቸው፡፡ ሚዲያዎቻችንም ለልዩነትና ለከንቱ መባላት ከሚሰጡት ትኩረት ላይ ቀንሰው፣ ከአየር ሰዓታቸውም ሆነ ከገጾቻቸው ላይ ቆርሰው ለዚህ ብሔራዊ ጉዳይ ቦታ እንደሚሰጡት ይታመናል፣ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም ነገሩ የመላይቱ ኢትዮጵያና የሕዝቧ ደኅንነትና የዕድገት ዋስትና መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ በሐሳብ መለያየት ውበት ቢሆንም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ግን መለያየት የለብንም፡፡ ወይም ልዩነቶቻችንን የቻልነውን ያህል አጥብበን ለአንድ ዓላማ ልንሠለፍለት የሚገባው ሥራ ነው፡፡ ዓባይ ያስተሳሰረን ኢትዮጵያዊያን ከእውነትና ከፍትሕ ዝንፍ ያለ አቋም ላይ አይደለንምና፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

- Advertisement -

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን

ከ ተመሳሳይ አምዶች

የግለሰቦች ለመብታቸው ኃላፊነት አለመውሰድ ለአገር ያለው አደጋ

በያሬድ ኃይለመስቀል አንድ የማከብረው ኢኮኖሚስት አንድ መጽሐፍ እንዳነብ መራኝና ማንበብ ጀመርኩኝ። ይህንን መጽሐፍ ሳነበው ከዋናው ሐሳብ ወጣ ብሎ ስለ “የነፃ ተጓዦች ሀተታ” (The Free Rider...

የሰላም ዕጦት የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አንድምታ

በጌታሁን አስማማው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment – an Introduction to the History of America People›› በሚለው አነስ ያለ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ...

የኢትዮጵያን ትንሳዔ ለማብሰርና ለመከወን ነባራዊውን ዓለም እንዴት እንገንዘብ?

በጌታነህ አማረ እንግዲህ የኢትዮጵያን ትንሳዔ የማብሰርና የመከወን ጉዳይ አይቀሬ በመሆኑ፣ ለዚህ ይረዳን ዘንድ አንዳንድ ነባራዊ ሁኔታዎችን መገንዘብ ግድ ይለናል፡፡ ዓለም በአሁኑ ጊዜ በኢኮኖሚ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ...

‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል››

በአሰፋ አደፍርስ እነኛ የጥንቶቹ አያት፣ ቅድመ አያትና ቅም አያቶቻችን እንደ እኛ ምሕንድስናን፣ የምጣኔ ሀብትንና የሕግ ትምህርትን በቃል የሸመደዱ አልነበሩም፡፡ በተፈጥሮ ዕውቀታቸው የዓለምን ሁኔታ የተገነዘቡና ያገናዘቡ፣...

የኢትዮጵያን ትንሳዔ ለማብሰርና ለመከወን ምን ዓይነት ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል?

በጌታነህ አማረ እንግዲህ ሁሉም ሰው እንደሚያውቀውና ከታሪክ እንደሚሰማው ከሆነ፣ በቀድሞው ጊዜ ኢትዮጵያ ታላቅ አገር እንደነበረችና አሁንም ተመልሳ ታላቅ እንደምትሆን ነው፡፡ ይህ በአብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የታመነበት...

ለፕሮፌሰር ዓለም አንተ ገብረ ሥላሴ ግልጽ ማስታወሻ

በአንዳርጋቸው አሰግድ ‹‹ትውስታዎቼ ስለመሬት ይዞታና የተለያዩ ፖለቲካዊና አገራዊ ጉዳዮች›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ የኃይሌ ፊዳንና የእኔን ስሞች ያወሱባቸውን ገጾች ጓደኞቼ ልከውልኝ ደረሱኝ። ከዚያም ‹‹ናሁ››...

አዳዲስ ጽሁፎች

መንግሥት ገቢ ከመሰብሰብ ባሻገር ለሕዝብ ኑሮ ትኩረት ይስጥ!

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማደግ ያለበት በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ ከሚሰበሰብ ታክስ ብቻ ሳይሆን ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከማዕድን፣ ከአገልግሎትና ከሌሎች ሀብት አመንጪ ዘርፎች ጭምር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው...

የኢትዮጵያን ትንሳዔ ለማብሰርና ለመከወን ምን እናድርግ?

በጌታነህ አማረ ኢትዮጵያ ማለት ታላቅ አገር ቀደምት የሰው ዘር መገኛና የሥልጣኔ ባለቤት የሆነች አገር እንደነበረች ታሪክ ሲያወሳን ይኖራል። በዚያውም ልክ ይህች ታላቅ ነበረች የምትባል አገር...

የምድራችን (የሰው ልጆች) ተማፅኖ — አረንጓዴ ፖለቲካ!

(ወጥመዶችና ማምለጫችን) በታደሰ ሻንቆ የወጥመዶች ዓለም በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ዘንድ ያሉ ውዝግቦችና ግጭቶች ምንም ተቀባቡ ምን፣ መሬትን ውኃን አፈርን ማዕድናትን ንግድንና መሰል ጥቅሞችን የተመለከቱ ናቸው፡፡ በእነዚህ...

‹‹መንግሥት ከሁሉም ነገር በላይ ቅድሚያ ሰጥቶ የኢኮኖሚ ጫናውን ለመቀነስ የነዳጅ ድጎማውን መቀጠል ይኖርበታል›› ሰርካለም ገብረ ክርስቶስ (ዶ/ር)፣  የነዳጅ ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ

የነዳጅ ግብይት ሥርዓትን ለመዘርጋትና ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለ አዲስ አዋጅ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡ በኢትዮጵያ በነዳጅ ሥርጭት ግብይትና በአጠቃላይ በዘርፉ ያሉትን ማነቆዎች...

ስለካፒታል ገበያ ምንነትና ፋይዳ ያልተቋረጠና የተብራራ መረጃ ማድረስ ያሻል!

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ በይፋ ሥራ ጀምሯል፡፡ አገራዊ ኢኮኖሚውን ከመደገፍና ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች የሚውል ካፒታል ለማሰባሰብ እንደ አንድ አማራጭ የሚወሰድና ለኢትዮጵያ እንደ አዲስ ምዕራፍ የሚታይ ዕርምጃ...

ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተያዘለት የሥነ ተዋልዶ ጤና ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

በኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተከሰቱ ጦርነቶችና ግጭቶች ምክንያት እየተስተጓጎለ የመጣውን የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት መልሶ ለማጠናከር ያስችላል የተባለ የ1.28 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ...
[the_ad id="124766"]

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን