Saturday, June 15, 2024

​​​​​​​ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገቦች መፈንጫ እንዳትሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የታላላቅ ታሪኮች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የገጠሟትን ፈተናዎች የተሻገረችው በልጆቿ ነው፡፡ የወራሪዎችንና የተስፋፊዎችን ምኞት ከማክሰም ጀምሮ፣ በውስጥ ለሥልጣን የተደረጉ ሽኩቻዎችንና ጦርነቶችን ጭምር ያካሄደችው በልጆቿ ነው፡፡ አንዱ ሥልጣን ላይ ሲወጣ ሌላው ሲወርድ ሥርዓቶች እየተቀያየሩ እዚህ ዘመን የተደረሰው፣ ባዕዳን በቀጥታ ጣልቃ ሳይገቡ በልጆቿ መካከል በተከናወኑ ፍትጊያዎች ነው፡፡ ጨቋኝነትም ሆነ ተጨቋኝነት የነበረው በኢትዮጵያዊያን የእርስ በርስ መስተጋብር ነው፡፡ ምንም እንኳ በዚህ መስተጋብር ውስጥ ከፍተኛ ቅራኔዎች እንደነበሩ ግልጽ ቢሆንም፣ ተቃርኖ ያላቸው ወገኖች ጭምር በአገር ጉዳይ አቋማቸው ተመሳሳይ ነበር፡፡ ጭቆናው የመደብም ይባል የብሔር ‹‹ዞሮ ዞሮ መዝጊያው ጭራሮ›› እንደሚባለው በአገር ጉዳይ ግን ቀልድ አልነበረም፡፡ የዚህ ዘመን ትውልድ በእጅጉ ሊረዳው የሚገባው ጉዳይ፣ ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር አለመኖሩን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ ሲደራደሩ አይታወቅምና የአገራቸው ዋልታና ማገር ኢትዮጵያዊያን ራሳቸው ናቸው፡፡ የአገራቸው ተስፋም በእጃቸው ላይ ስለሆነ፣ የውጭ ጣልቃ ገቦች መሣሪያ ላለመሆን መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ታሪካዊ ጠላቶች አድፍጠው የሚጠባበቁት የኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ መፋጀት ስለሆነ ጥንቃቄ ያሻል፡፡

የኢትዮጵያ ተስፋ በልጆቿ እጅ በመሆኑ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ለአገራቸው ሰላም፣ ዕድገት፣ ዴሞክራሲና ተሰሚነት በአንድነት መቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞች ወይም ፍላጎቶች ቢኖሩ እንኳ የአንድ ወገን የበላይነት ለማግኘት ሲባል ብቻ፣ የአገር ሰላም ማደፍረስ በፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ የውጭ ጣልቃ ገቦች በዲፕሎማሲ ከሚያደርሱት ጫና በተጨማሪ፣ በውክልና ጦርነት ሳይቀር እጃቸውን እያስረዘሙ አገር ለማዳከም መነሳታቸው ይታወቃል፡፡ በተለይ በታላቁ የህዳሴ ግድብና በቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካዊ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ምክንያት፣ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የተለያዩ ኃይሎች ተሠልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ይህንን የሴራ ጥልፍልፎሽ በመገንዘብ አገራቸውን መታደግ አለባቸው፡፡ የውጭ ጣልቃ ገቦችን ፍላጎት በመረዳት፣ ዕይታን ሰፋ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ሌሎች የውጭ ኃይሎች ምን እንደሚፈልጉ አብጠርጥሮ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት በውጭ ኃይሎች የደረሱባትን ጫናዎች በማወቅ ለዚህ ዘመን የሚመጥን ቁመና ላይ መገኘት የግድ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ የሚታወቀው ለአገሩ ነፃነት በሚያደርገው ተጋድሎ መሆኑን ታሪክ ከበቂ በላይ መዝግቦታል፡፡ ኢትዮጵያውያንም በአገራቸው ህልውና  እንደማይደራደሩ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ የአገር ጉዳይ የተወሰኑ ቡድኖች ወይም ስብስቦች ሳይሆን የመላው ሕዝብ ጉዳይ ስለሆነ፣ ማንም እየተነሳ አገርን እንዳሻው ማድረግ ወይም ማፍረስ አይችልም፡፡ አገር የመላው ሕዝብ አንጡራ ሀብት ናት የሚባለው፣ የሁሉም ነገር ሉዓላዊ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ በመሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ በታሪኩ የሚታወቀው፣ አገሩን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች ሲጠብቅና ደሙን አፍስሶ የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍልላት ነው፡፡ ለዚህ ምስክር መቁጠር ሳያስፈልግ ታሪክ የከተባቸውን ድርሳናት ማገላበጥ በቂ ነው፡፡ አቶ እከሌ ወይም ወይዘሮ እከሊት በተደሰቱና ባኮረፉ ቁጥር፣ የኢትዮጵያን ዕጣ ፋንታ መወሰን አይቻላቸውም፡፡ አገር ረቂቅ በሆኑ ማኅበራዊ መስተጋብሮችና የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች ላይ የተገነባች መሆኗን እየዘነጉ፣ ነጋ ጠባ ስለመፍረስና ስለመበተን የሚያላዝኑ አሉ፡፡  ከጎጥና ከጎራ አስተሳሰብ መላቀቅ ስለማይፈልጉ አገር እያዳከሙ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ይጋብዛሉ፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን በማስተባበር የአካባቢውን ሰላም በማስከበር ብሔራዊ ደኅንነቷንና ጥቅሟን ለማረጋገጥ መትጋት እየቻለች፣ በረባ ባልረባው ሰላሟን እያናጉ ቀውስ መፍጠር ጠላትነት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚያምርባቸው ተባብረው አገር ሲገነቡ እንጂ፣ ለውጭ ጣልቃ ገቦች አገራቸውን ሲያጋልጡ አይደለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ውስብስቡን የኢትዮጵያ ችግር ለመፍታት የአገር ፍቅር፣ ዕውቀት፣ ብስለት፣ ቅንነትና ሰፋ ያለ ዕይታ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ጫፍ ድረስ በታሪኩ የሚታወቀው ለአገሩ ባለው ጥልቅ ፍቅርና ተወዳዳሪ በሌለው አስተዋይነቱ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ፀጋ የያዘን ሕዝብ አንድ ላይ አስተባብሮ መምራት ከተቻለ ለጣልቃ ገቦች ክፍተት እንደማይፈጠር የዘመናት ተጋድሎዎች ውሎ ህያው ምስክር ነው፡፡ ሕዝባችን ዘመናትን አብሮ ሲሸጋገር የኖረው በጋራ አገሩን ሲጠብቅ ነው፡፡ ይህንን ጠንካራ ሕዝብ ይዞ ለልማት ማሠለፍ ቢቻል ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያ የምድር ገነት ትሆን ነበር፡፡ ባለመታደል ግን ኢትዮጵያ የድህነት፣ ከዚያም አልፋ ተርፋ የረሃብና የጠኔ ተምሳሌት ተደርጋለች፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አሳፋሪ ውርደት ውስጥ ለመውጣትና በአደባባይ ቀና ብሎ ለመራመድ፣ ከኋላቀር አሳፋሪ ድርጊቶች መገላገል ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን ለጠላት የሚያጋልጣት ጦርነት በመቀስቀስ አቅላቸውን የሳቱ ከንቱዎችና ተከታዮቻቸው ድርጊታቸውን ይመርምሩ፡፡ የውጭ ጣልቃ ገቦች የሚፈልጉት እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች እንዲስፋፉና ኢትዮጵያ እንድትዳከም ስለሆነ፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ይቁሙ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩ ወደ ዴሞክራሲና ዕድገት እንድትገሰግስ ይፈልጋል፡፡ ይህ ፍላጎት በስኬት መከናወን የሚችለው ሰላም ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ሰላም የሚሰፍነው ግን የአገር ጉዳይ ተዋንያን ሙሉ ተሳትፎ ሲታከልበት ነው፡፡ አንዱ እየገነባ ሌላው የሚያፈርስ ከሆነ ሰላም አይኖርም፡፡ ሰላም በሌለበት ደግሞ ዴሞክራሲም ዕድገትም አይታሰቡም፡፡ የአገር ህልውናም ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ ከጠባብ የቡድን ጥቅም በላይ አገር የምትባል የጋራ ጎጆ መኖሯን የዘነጉ ወገኖች፣ ከዜሮ ድምር ፖለቲካ ካልተገላገሉ የአገር ህልውና ችግር ይገጥመዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ልጆቿ የጋራ እናት እንድትሆን ጥርስን ነክሶ ከመታገል ይልቅ፣ የጽንፈኝነት ፖለቲካ ውስጥ ተወሽቆ አገርን ለማተራመስ መሞከር የማይወጡት አዘቅት ውስጥ ይከታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዕይታ የተጋረደባቸው ኃይሎች የማንነትና የግዛት ትንቅንቅ በመጀመር የአገርን ተስፋ እያጨፈገጉ ነው፡፡ የጋራ የሆኑ ጉዳዮችን የተወሰኑ ወገኖች ለማድረግ የሚደረገው መሯሯጥና አጉል ጀብደኝነት የአገርን ህልውና እየተፃረረ ነው፡፡ ልዩነትን አክብሮ ለአገር መፃኢ ዕድል ከመጨነቅ ይልቅ፣ ለውጭ ጣልቃ ገብ ኃይሎች ቀዳዳ መፍጠር አገርን ማዳከም ነው፡፡

የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በቅጡ ሊያስቡበት የሚገባው ዋነኛ  ጉዳይ፣ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ ሕገወጥነትን ማምከን መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው እንዲረጋገጥ፣ በሕገወጥ ድርጊት ውስጥ መሳተፍ የሕግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትልባቸው፣ በሕግ ዋስትና ያገኙ መብቶች በተግባር ሥራ ላይ እንዲውሉላቸው፣ በነፃነት የፈለጉትን እንዲደግፉ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ በአገራቸው ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑና አገራቸው እንድትመነደግ ጠንክሮ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ፈንታ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ሲነግሡ የሚጎዱት ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ አቅመ ደካሞችና ንፁኃን ወገኖች ናቸው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ባጋጠሙ ግጭቶች ሰለባ የሆኑት እነዚህ ምስኪን ወገኖቻችን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊና ታላቅ አገር ሆና ሳለ በስግብግብነት ስሜት ቀውስ የሚቀሰቅሱ ለጠላት ጥቃት የሚያመቻቹ አደብ ይግዙ፡፡ሕዝብ ስም እየነገዱ አንፃራዊ ሰላሙን ወደ ግጭት በመቀየር አገሩን ማተራመስ በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም፡፡ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የውጭ ኃይሎች ከመቼውም ጊዜ በላይ እየፈተፈቱ ያሉት፣ ውስጣዊ ጥንካሬን በማዳከም አገራዊ አንድነትን ለማላላት ከፍተኛ ተንኮል ስለተፈጸመ መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡ አሁንም ከዚህ አደገኛ ድርጊት በመታቀብ፣ የውጭ ጣልቃ ገቦች በኢትዮጵያ ላይ እንዲፈነጩ ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

በንጉሥ ወዳጅነው ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...