በከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ከተሰጣቸው ደረጃ ስያሜ ውጪ መመርያ ተላልፈው ያልተሰጣቸውን የደረጃ ስያሜ በመጠቀም፣ ራሳቸውን በተለያየ መንገድ እያስተዋወቁ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡
የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ ገረሱ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ እያንዳንዱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የየራሱ የደረጃ ስያሜ አለው፡፡ ይህም ዩኒቨርሲቲ፣ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ኮሌጅና ኢንስቲትዩት ተብሎ የሚገለጽ ነው፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ደረጃ ስያሜ እንዲሁ በዘፈቀደ የሚሰጥ ሳይሆን፣ የራሱ የሆነ መመርያና ዝርዝር የመመዘኛ መሥፈርቶች አሉት፡፡
ከስድስትና ከሰባት ዓመታት በፊት መመርያ ሳይኖር የከፍተኛ ትምህርት ለመስጠት ዕውቅና የወሰዱ ተቋማት የተለያየ ስያሜ ይጠቀሙ እንደነበር ያስረዱት አቶ ታረቀኝ፣ ሆኖም በአዋጁ ላይ የተቀመጠ ጉዳይ መኖሩም አስታውሰዋል፡፡ ኤጀንሲውም እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ መመርያውን የማስፈጸም ውስንነት እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡
ከሦስት ዓመታት በፊት ኤጀንሲው በነበረበት የክትትል ክፍተት ምክንያት በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በሻሸመኔ፣ እንዲሁም በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች አንዳንድ ተቋማት ከመመርያው ውጪ ኤጀንሲው ያልሰጣቸውን የደረጃ ስያሜ በመጠቀም ራሳቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮችና በመደበኛ ሚዲያዎች ጭምር ሲያስተዋውቁ እንደቆዩ ያስታወቀው ኤጀንሲው፣ ሆኖም በዚህ ወቅት መሰል ድርጊቶች የሚፈጽሙ አካላትን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ለማስገባት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
አንድ ተቋም ከኢንስቲትዩነት አንስቶ እስከ ሙሉ ዩኒቨርሲትነት ያለውን ደረጃ የሚያገኝበት የራሱ የሆነ መመርያና ‹‹ቼክ ሊስት›› እንዳለው ተጠቁሟል፡፡ ለምሳሌ አንድ ፕሮግራም ወይም ተመሳሳይ ፕሮግራሞችን የሚሰጥ ተቋም ኢንስቲትዩት፣ ሁለትና ከእዚያ በላይ ፕሮግራሞችን ሲሰጥ ኮሌጅ እየተባለ ደረጃው እንደሚሰጥ፣ እንዲሁም ከጥናትና ምርምርና ከመምህራን ልማት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮች ሌላው በደረጃ አሰጣጡ ላይ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው ተብሏል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተሰጣቸው የደረጃ ስያሜ ውጪ ባልተፈቀደ የደረጃ ስያሜ በሚዲያ ማስታወቂያ ማሠራት፣ በተለያዩ ሰነዶችና ባነሮች መጠቀም፣ ማኅተሞችን ማሠራት የተከለከለ እንደሆነ ያስረዱት የኮሙዩኒኬሽን ዋና ዳይሬክተሩ፣ ተቋማት በዚህ አግባብ ከመሥራት ባለፈ በሚሰጧቸው የምሩቃን የትምህርት ማስረጃ ላይም መሥፈር ያለበት የተፈቀደው የደረጃ ስያሜ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ወቅት መሰል ሥራዎችን የሚያከናውኑ አንዳንድ ተቋማት እንዳሉ ያስታወቁት አቶ ታረቀኝ፣ ሆኖም ስማቸውን ጠቅሶ ለሕዝብ ይፋ ከማድረግ በፊት ማሳሰቢያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ኤጀንሲው ተቋማቱ ከወዲህ ስህተታቸውን የሚያርሙበትን ማሳሰቢያ እንዳስተላለፈ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በፊት በዚህ መንገድ አስተምረው ለምሩቃን የትምህርት ማስረጃ ያስተላለፉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰጡትን የትምህርት ማስረጃ መልሰው እንዲያስተካክሉ ይደረጋል ያሉት አቶ ታረቀኝ፣ በተለይም በውጭ ጉዞዎች ወቅት በዚህ ምክንያት የሚፈጠሩ መስተጓጎሎች ስላሉ ተማሪዎችም ይህ ዓይነቱን ክስተት በጊዜ ማስተካከል እንደሚገባቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ከማሳሰቢያ ባለፈ በድርጊቱ የሚቀጥሉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ካሉ ስማቸው ተጠቅሶ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደሚጻፍላቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ በዚህም የማይስተካከሉ ከሆነ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተሳትፈው ያፀደቁት የሥነ ሥርዓት መመርያ ስላለ ዕርምጃው በዚያ መሠረት የሚከናወን እንደሆነ አቶ ታረቀኝ አስታውቀዋል፡፡
እንደ ኤጀንሲው መረጃ ከሆነ ዩኒቨርሲቲ የሚል የደረጃ ስያሜ ያላቸው የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በቁጥር አምስት ሲሆኑ፣ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን ደረጃ አሟልተው እንዲያስተምሩ ፈቃድ ያገኙትም እንዲሁ አምስት ናቸው፡፡ የተቀሩት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በኮሌጅና ኢንስቲትዩት ደረጃ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡