በአፋር ክልል በቀጠለው ጦርነት ምክንያት ምግብና ሌሎች ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ወደ ትግራይ ለማድረስ መቸገሩን የዓለም የምግብ ድርጅት ገለጸ፡፡
የዓለም የምግብ ድርጅት ዋና ኃላፊ ዴቪድ ቤስሌይ ይፋ እንዳደረጉት፣ ወደ ትግራይ ክልል ምክብና ሌሎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ቁሶችን የጫኑ 170 ተሽከርካሪዎች አፋርን ማለፍ ተቸግረው ቆመዋል፡፡
የዓለም የምግብ ድርጅት በትግራይ ክልል ውስጥ ባሉት መጋዘኖች የተከማቸ የምግብ ዕርዳታ ከመጪው ከዓርብ ሐምሌ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ባዶ እንደሚሆን ገልጸው፣ ‹‹በአፋር ጦርነት ምክንያት ለመቆም የተገደዱት ተሽከርካሪዎች በአስቸኳይ እንዲያልፉ ሊደረግ ይገባል፣ ሰዎች እየተራቡ ናቸው፤›› ሲሉ ጥሪ አድርገዋል፡፡
መንግሥት ማክሰኞ ሐምሌ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ለሰብዓዊ ዕርዳታ ሲል የወሰነው የተናጠል የተኩስ አቁም በሕወሓት ትንኮሳ ክልል እየገጠመው እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ከተኩስ አቁም ውሳኔው ባለፈ መንግሥት በትግራይ በሚገኙ መጋዘኖች አራት መቶ ሺሕ ኩንታል ስንዴና 2.5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ተደራሽ እንዲሆን ማድረጉንም ጠቁሟል፡፡
‹‹በትግራይ የሚገኙ ዜጎቻችን ደኅንነት ያሳስበናል›› ያለው መግለጫው፣ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በተለይም በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሕወሓት በአፋር በኩል የሚያደርገውን ትንኮሳ እንዲያቆም ግፊት ሊያደርጉ ይገባል ሲል ጥሪውን አቅርቧል፡፡