የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ አመራርና አሠራር እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ባንኩ ተዘፍቆበት ከነበረው ችግር እንዲወጣ እያደረገው ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ የሚገልጹትም፣ የባንኩን ችግር ለማቃለል የተወሰዱ ዕርምጃዎች ለውጥ እያመጡ ስለመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ከፊቱ ብዙ ሥራ ይጠብቁታል፡፡
እንደ አቶ አቤ ገለጻ፣ ባንኩ ወደፊት ፈተና ይሆንበታል ብለው የሚጠቅሱት እያደገ ከመጣው የባንክ ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ እየታየ መሆኑና ለዚሁ የሚመጥን ቴክኖሎጂ መገንባት ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን ነው፡፡
ከዚህ ውጪ ባንኩ ከነበረበት ችግር ለመውጣት የወሰዳቸውና እየወሰዳቸው ያሉ ዕርምጃዎች ወደፊትም ይተገበራሉ ተብለው የሚጠበቁ አዳዲስ አሠራሮች ባንኩን የወደፊት አቅጣጫ መልካም ያደርጋል ተብሎ ይታመናል፡፡
ይህም እንቅስቃሴው ባንኩን በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአኅጉር ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችለውን አቅም እንዲያገኝ የሚረዳው ስለመሆኑም
የውጭ ባንኮች ቢገቡ ባንኩ ተወዳዳሪ ሊሆን ይችላል ወይ? እንዲሁም ባንኩን ሪፎርም ለማድረግ በቅርቡ የተቀጠረው ዓለም አቀፍ አማካሪ ኩባንያ የሚሠራው ሥራ ባንኩን ወዴት ያደርሳል? የሚል ጥያቄዎች ቀርበውላቸው የሰጡት ምላሽም ይህንኑ ያመለክታል፡፡
እንደ ተግዳሮት ሊሆን ይችላል የተባለው የባንኩ ትራንዛክሽን በየጊዜው እያደገ መምጣትና ቀጣይ የባንክ ዕርምጃን በተመለከተ እንዲሁም የባንኩን የብድር አሰጣጥና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በተመለከተ የሰጡት ምላሽ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ከአራት ትሪሊዮን በላይ የገንዘብ እንቅስቃሴና ቴክኖሎጂ
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው የ2013 የሒሳብ ዓመት ከአራት ትሪሊዮን በላይ የገንዘብ ተንቀሳቅሷል፡፡ ለዚህም የባንክ ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመር እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ በመሆኑም የበለጠ በቴክኖሎጂ በመታገዝ አገልግሎቱን ማሳደግ እንደሚገባው አመላክቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ሊገጥም የሚችለው ፈተና ከዚሁ ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ ጋር የተጣጣመ ቴክኖሎጂ እንዲተገበር ማድረግ ነው፡፡ ውድድርም ከዚሁ ጋር ይያያዛል፡፡
ቴክኖሎጂውን ማዘመን የግድ ይላል፡፡ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የቢዝነስ መጠኑ በጣም በዝቷል፡፡ የባንክ ትራንዛክሽንና ቴክኖሎጂ አንዳንዴ ይኼን መሸከም የሚያቅተው ጊዜ አለ፡፡ ትራንዛክሽኑ እየጨመረ ነው፡፡ በአንድ ዓመት የባንኩ ተቀማጭ 140 ቢሊዮን ብር ሲደርስ፣ አዲስ የተቀማጭ ሒሳብ የከፈቱ በአንድ ዓመት ወደ 6.4 ሚሊዮን ደንበኞች ናቸው፡፡ ይህም አጠቃላይ የባንኩን ደንበኞች ቁጥር አሳድጓል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የባንኩ ደንበኞች በብዛት ዲጂታል እየተጠቀሙ መሆኑ ዓምና ወደ አራት ትሪሊዮን ብር እንዲንቀሳቀስ አድርጓል፡፡ ይኼ የገንዘብ እንቅስቃሴ በጣም ብዙ ነው፡፡
በቴክኖሎጂ ዘርፉ ብዙ መሠራት እንዳለበት ያሳያል፡፡ በቀን እስከ አራት ሚሊዮን ትራንዛክሽኖች (ግብይቶች) ሲስተሙ ያስተናገደበት ቀን አለ፡፡ አንድ ሚሊዮን አካባቢ ትራንዛክሽን እንዲያውም አነስተኛው መጠን ነው ማለት ይቻላል፡፡ እናም አራት ሚሊዮን ሲደርስ ሲስተሙን የሚያንቀጠቅጥ ግዙፍ ትራንዛክሽን እየሆነ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው በቀን ይኼን ያህል ሰው የባንኩን ሲስተም ነክቷል ማለት ነው፡፡ ይኼ ሲስተሙ ላይ በጣም ከባድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ግዙፍ መጠን ያላቸው ባንኮች የራሳቸውን ኮር ባንኪንግ አደራጅተው ነው የሚያስተዳድሩትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ወደዚያ መግባት አለበት፡፡ አሁን ከአቅራቢዎች የሚገዛው ሲስተም ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አይሆንምና እኛ የራሳችን የምንለው ሲስተም እንዘረጋለን፡፡ ይህ ትልቅ ፈተና ቢሆንም በጣም እየሰፋ ያለውን የዲጂታል ባንኪንግ ተጠቃሚ ለሰከንድ አገልግሎቱ እንዳይቋረጥበት ለማድረግ ከፊታችን ትልቅ ሥራ ይጠብቀናል፡፡ ለአንድም ሰከንድ ትራንዛክሽኑ እንዲዘገይ አንፈልግም፡፡ እናም ይህ ከፊታችን ያለው ፈተና ነው፡፡ እኔ ከእሱ ጋር ነው የምታገለው፡፡ ባንኩን ዘመናዊ ለማድረግና የላቀ እንዲሆን ለማድረግ ጭምር ነው ዓለም አቀፍ አማካሪ የቀጠርነው፡፡ ይህ ከተሠራ ባንኩን ከነበረበት ወደ ሌላ ከፍታ ያሳድገዋል፡፡ ባለን ነገር መቀጠል አንችልም፡፡ አሁን በምንሠራበት ሲስተም፣ ሥርዓተ ሒደት ቢዝነስ ኦፕሬሽን ሜካኒዝም የወደፊቱን ተግዳሮት ልንጋፈጥ አንችልም፡፡ ትልቁ የባንኩ ፈተናና ትልቁ ችግር ተደርጐ ሊወሰድ የሚችለውም ይኼ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ለምሳሌ ብድርና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ላይ አሉ የሚባሉ ችግሮች በጣም ጥቃቅን ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ (ቢዝነስ) ተግዳሮቶች ጋር በጥቅሉ ሲነፃፀር እነዚህ በቀላሉ የሚፈቱ ይመስለኛል፣ አስቸጋሪ አይደሉም፡፡
ሪፎርሙና የአማካሪ ድርጅቱ ሥራ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2013 የሒሳብ ዓመት ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ባንኩን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ ለማድረግና አጠቃላይ የባንኩን አወቃቀር ለመቀየር በዘርፉ አንቱ የተባሉ አማካሪዎችን በማወዳደር መቅጠሩ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ውሳኔ ባንኩ በአገር ደረጃ ተወዳዳሪነቱንና ቀዳሚነቱን በማስጠበቅ ተመራጭ ባንክ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በአፍሪካ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ ቢያንስ በአፍሪካ ደረጃ አካባቢያዊ እንቅስቃሴ እንዲኖረን ለማስቻል አማካሪ ድርጅቱ የሚሠራው ሥራ ይጠበቃል፡፡ ጐረቤት አገሮች ላይ ቅርንጫፎች አሉን፡፡ ግን በደንብ አሳልጠን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አቀናጅተን ውጤታማ የማድረግ ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ እነርሱም እዛው ቁጭ ብለው እንደ አንድ ንዑስ ክፍል ይሠራሉ፡፡ አላገናኘንም፡፡ ከዚህም አልፎ ባንኩ ቀደም ብሎ በውጭ አገሮች ቅርንጫፎች ኖረውት ኮርስፖንዲንግ ባንኪንግ ሪሌሽን (የአገናኝ ባንኪንግ ግንኙነቶች) በራሱ የሚያስተዳድርበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ምኞት አለ፡፡ ባንኩ ወደዛ ደረጃ እንዲወጣ ነው የሚፈለገው፡፡ አሠራሩ በጣም አዋጭ ሆኖ ዘመናዊ አሠራርን በቀላሉ እንዲቀበልና ያሉትን ችግሮች ቀርፎ ለደንበኞች ከጊዜው ጋር የሚሄድ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ለማድረግ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ውድድርን ማሸነፉም ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በቴክኖሎጂ፣ በአሠራር፣ በሰው ሀብትና የሠራተኛ ጥራት መዝነው ክፍተታችንን ነግረው የምንሠራበትን ስልት (ስትራቴጂ) ሰጥተውን ጭምር ነው ኩባንያው የተቀጠረው ክፍተታችንን አርመን፣ አገር ውስጥ ላሉ ባንኮቻችንም ጥሩ ምሳሌ የሚሆን የሀብትምና የዕውቀት ማዕከል እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ በዓለም ደግሞ ተወዳድሮ የሚታይ፣ እዛ ባንክ አለ የሚያስብል በምሥራቅ አፍሪካም ከጐረቤቶቻችን ጋር ንግዱን የበለጠ ማቀላጠፍ የሚያስችል እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ዝም ብለን ተቀባይ ብቻ ሳይሆን ወደዛ ሄደን በሌላ አገር ባለ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተንም ገቢ ማምጣት የሚያስችለን ዕውቀትም ለማግኘት እንፈልጋለን፡፡ ድንበር ተሻጋሪና የጠረፍ ንግድ ሥራው አካባቢ ላይ እና መድረሻው መቆሚያ ስለሌለው እንዲህ ባሉ ሥራዎች ላይ ለመግባት አማካሪው ዕገዛ ይኖረዋል፡፡
ባንኩ በ2025 ዓለም አቀፍ ባንክ የመሆን ራዕይ ነው ያስቀመጠው፡፡ ስትራቴጂው ላይ ውይይት ጀምረናል፡፡ አሁን ከዚህም ባለፈ በተግባር የት መድረስ እንችላለን ለሚለው ስትራቴጂ በመቅረጽም እንዲያግዙን ባንኩን በተጨባጭ ካለበት ሁኔታ መዝኖ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የት መድረስ ይችላል ለሚለውም ስትራቴጂ በመቅረጽ እንዲያግዙን እንፈልጋለን፡፡ እንዲህ ላሉ ውጥኖቻችን ስኬት ነው አማካሪው የተቀጠረው፡፡
የውጭ ባንኮችና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዝግጁነት
የአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ሲስተም አሁን አገር በቀል የፋይናንስ ተቋማት ብቻ የሚንቀሳቀሱበት ነው፡፡ ይኼ ግን እንደማይቀጥል ይታሰባልና የውጭ ባንኮች ቢገቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብቃት ለመወዳደር የሚችልበት አቅም ይኖረዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ ይነሳል፡፡ የውጭ ባንኮችን ልንወዳደር የምንችልበት በርካታ እውነታዎች አሉ፡፡ የውጭ ባንኮች ቢገቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብዙ ላይፈተን ይችላል እነሱ የትኩረትና የውድድር አቅጣጫቸው ውስን ነው፡፡ በሁሉም ነገር ላይ አይወዳደሩም፡፡ እንደውም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር መወዳደር አይችሉም፡፡ የኢትዮጵያ ሀብት አንድ ቦታ ተቆልሎ የሚገኝና ተሸክመው የሚሄዱበት ዓይነት አይደለም፡፡ ትናንሽ ሳንቲም ሰብስበህ ሀብት የምታደርግበት አገር ነውና እነሱ ያንን የመሰብሰብ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ሰዎች እንደሚያስቡትም እነዚህ የውጭ ባንኮች ግር ብለው የሚገቡ አይደሉም፡፡
ለውጭ ባንኮች ዘርፍ ይከፈት ብለው ከመግለጽ ባሻገር ያን ያህል ይመጣሉ ብዬ አላስብም፡፡ ቢመጡም አዲስ አበባ ላይ ነው መቀመጥ የሚፈልጉት፡፡ የሚወስዱብን ሥራም ውስን ነው፡፡ እነዚህ የውጭ ባንኮች አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠው ሊወስዱብን የሚችሉት ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ነው፡፡ ይህ ግን ትልቅ ጫና ሊያመጣ ይችላል፡፡ በዚህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪውን ይወስዳሉ፡፡ ከሪሚታንስም የተወሰነ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ውጪ በምንም ሊወዳደሩን አይችሉም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በእነሱ በኩል የሚገኘው ዕድል ንግዱን ሊያቀላጥፍ ይችላል፡፡ ይህም መታሰብ አለበት፡፡
በእርግጥ የእነሱ መምጣት ጫና የሚፈጥርባቸው ባንኮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በተለይ የአንዳንድ ባንኮችን ብደር እስከ 40 በመቶ ከዓለም አቀፍ ባንክ አገልግሎት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ውድድሩ ሊከብዳቸው ይችላል፡፡ በዚህ ዘርፍ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 14 በመቶ አካባቢ በመሆኑ ሊገጥሙን የሚችለው ውድድር በ14 በመቶው ቢዝነሳችን ላይ ነው፡፡ ከዚህ ላይ ግን ሌላው መታሰብ ያለበት የውጭ ባንኮች ሲመጡ ዝም ብሎ በር ወለል ተደርጎ የሚከፈት አለመሆኑን ነው፡፡ ምናልባት ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር ተጣምረው እንዲመጡ ሊደረግ ይችላል፡፡ ከዚህም ሌላ እነዚህ የውጭ ባንኮች መግባት ከፈለጉም ከአገር ውስጥ ባንኮች ላይ 10 በመቶና 20 በመቶ ድርሻ ይደረጋል፡፡ እንደው ዝም ብሎ እንደፈለጋችሁ የሚባሉ አይመስለኝም፡፡ በአጠቃላይ መግባታቸው ያን ያህል የሚያስፈራ አይደለም፡፡ ሆኖም ከእነሱ ጋር ሊያወዳድረን የሚያስችል ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ አሁንም አንዱ ዝግጅታችን ይህ ነው፡፡
ለደንበኞቻችን የተሻለ አገልግሎት ማቅረብ ከቻልን፣ ሌላው ቀርቶ ሊወስዱብን ይችላሉ ብዬ የጠቀስኳቸውን ቢዝነሶች ሳይቀር እኛም የምናገኝበት ዕድል አለ፡፡ እኛ የራሳችን ብዙ መሠረተ ልማት ተጠቅመን እንሠራለን፡፡ የሠራተኞች ደመወዝና የመሳሰሉ ብዙ ነገሮች ተመጣጣኝ ነው፡፡ ለእነሱ ዋጋው ሊወደድባቸው ይችላል፡፡ ለውድድር ስትራቴጂክ ተጠቃሚነታችን ብዙ ናቸው፡፡ ግን በአሠራራችን ቅልጥፍና ማነስ እንዳንበለጥ እነዚያን አሻሽለን ለውድድሩ ብቁ ሆነን መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡
የብድር አቅርቦት አለ?
ብድር ላይ ወረፋ የለንም፡፡ የረዥም ጊዜ ብድር አሁን ብዙ ትኩረታችን አይደለም፡፡ ምክንያቱም በቂ የረዥም ጊዜ ብድር ሰጥተናል፡፡ የአጫጭር ጊዜ ብድሮች ላይ ወረፋ የለም፡፡ መጥተው መውሰድ ይችላሉ፡፡ ቻሌንጁ የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ ነበረ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ሳናቀርብ ረዥም ጊዜ ቆይተናል፡፡ አሁን በቅርቡ የመስጠት ዕቅድ አለን፡፡