Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​​​​​​​ያኑርልን!

ሰላም! ሰላም! መኖር መቼም ደግ ነው። በመቆየት ብዙ ዓየን። ያደላቸው ደግሞ ላላዩት ጭምር ያያሉ። እሱንፀጋብሎ ማለፍ ሳይሻል አይቀርም። በቀደም ሶታ ጎረምሶች፣ “ለአገራችን እኛ አለንላት” እያሉ ሲፎክሩ ልቤ ሞቀ፡፡ ጎበዝ ወጣትነት እንዲህ ይናፍቃል እንዴ? “ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም፣ እናት አገራችን የደፈረሽ ይውደም” እያሉ ሲያዜሙ በደመነፍስ አብሬያቸው ሳዜም ዕንባዬ በጉንጮቼ ላይ ወረደ፡፡ በዚህ ዕድሜ ወኔ ይነሳል እንዴ? እያልኩ በሐሳብ ስመሰጥ፣ተው እንጂ አንበርብር! የ98 ዓመቱን አባት አርበኛ አላየህም እንዴ? በዚያ በሚያስገርም ግርማ ሞገስ ፉከራውን ተቀላቅለው ሲያበቁ ወጣቶችን በጋለ ወኔ ሲያነሳሱ የት ነበርክ?” ሲለኝ ልቤ በሐሴት ውስጤ ሲዘል ይሰማኝ ነበር። ዘመን መቼም ብዙ ብዙ ምዕራፍ እንዳለው አውቃለሁ። አባቴ ኮሪያና ኮንጎ ከመዝመቱም በላይ ኦጋዴን ከሶማሊያ ወራሪ ጋር መፋለሙንም አስታውሳለሁ። እኔ ዕድሌ ሆኖ ይህ ክብር ባይደርሰኝም ብዙዎቼ አብሮ አደጎቼ ለአገራቸው ደማቸውን ማፍሰሳቸውን ምስክር ነኝ። ለአገር ክብርና ህልውና ተፋልመው ታሪክ ለሠሩ ባርኔጣዬን አውልቄ አክብሮቴን ስገልጽ፣ ታሪክ ለመሥራት ለተነሱ ወጣቶችም ሞራሌን እለግሳለሁ፡፡ እንዲህ ነው ኢትዮጵያዊነት!

ወደ መደበኛው ወጋችን ስንመለስ አንዱ ምናለ መሰላችሁ፣እንደግዲህ ይኼ ትውልድ በብዙ ነገሮች ቢተችም፣ አንዳንዴ የሚፈጽማቸው አስገራሚ ነገሮች ያስደንቁኛል።ዘመኑም ነገር ሲበሉት ቀላል፣ ሲለብሱት ቀላል፣ ሲነካኩት በቀላሉ፣ ሲያላምጡት በቀላሉ፣ ሲውጡት በቀላሉ፣ በአጠቃላይ ቀለል ቀለል ያሉ ነገሮችን የሚያመርት ቢመስለንም፣ በሌላ በኩል ይዞት የሚመጣው ከባድ ዕሳቤና ዕይታ ያስደምመኛል” አለኝ። ሐሳባችን በተለያየ መንገድ ይገለጽ እንጂ ያለው እውነት ነው። እያዩ ያለ ማየት እየሰሙ ያለ መስማት አባዜያችንም ከዚህ ጋር እንደሚያያዝ ታየኝ። የከፋ የአገር ጉዳይ ሲገጥመን ወደ አቅላችን እየተመለስን ቀናው ጉዳይ ላይ እናተኩራለን እንጂ፣ ዘና ስንል ደግሞ የምንራኮትበት ነገር መብዛቱ ንድድ ያደርገኛል። ብቻ የዚህ ዓለም የቅሌት መዝገብ የተከፈተ ቀን፣ እንደለመደብንከዓለም አንደኛ ከአፍሪካ ሁለተኛሆነን እንዳንገኝ ፀልዩ አደራ፡፡ ፀሎት መልካም ነው!

 ይኼን ሐሳብ ይዤ አዛውንቱ ባሻዬ ዘንድ ሄድኩኝ። እሳቸው ደግሞ ለአላቂው ዓመት የይቅርታ መስዋዕት እያቀረቡ ሰሞኑን ከባድ ፀሎት ላይ ናቸው።  በደህናው ጊዜ ልባቸው መንግሥተ ሰማይን ናፋቂ ስለሆነ የዚህ ዓለም ነገር በፊታቸው ከተናቀ ቆይቷል። ለእኛ ደግሞ ሌላ ነው። ‹‹እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም…›› የተዘፈነው ለምሳሌ ለእኛ ለእኛ ዓይነቱ በሁለት ልብ ለሚያነክስ ለፍቶ አዳሪ ነው። ማስጠንቀቂያውን ብሰማና የለኝም ብል ደግሞ ንፉግ፣ ቆጥቋጣ፣ ገብጋባ፣ ቋጣሪ፣ ራስ ወዳድና ብዙ ብዙ መሰል ስሞች ጀርባዬ ላይ ሲለጠፉ ይታዩኛል። እኛ ደግሞ እንደምታውቁት በል ሲለን የመለጣጠፍ ችግር የለብንም። አንስቼ ብሰጥ የማንጠግቦሽ ጉምጉምታና የእኔ ላብ መና መቅረት ስቀመጥ ስነሳ ሰላሜን ሊነሱት ነው። ይኼን እያሰብኩ አንድ ሥራ መጣ። ያበደ ዘመናዊ ባለሦስት ፎቅ ቪላ ይሸጣል ተባልኩ። ወዲያው ቤቱንና አካባቢውን አጣርቼ ሳበቃ ለአራት ቤት ፈላጊ ደንበኞቼ ደወልኩ። ሁለቱ አላነሱም፣ አንዱ ስልኩ አይሠራም። አንደኛውሃሎ!› አለ። የነገርኩትን ሰማ። ጊዜ ሳያጠፋ አገኘኝና ቤቱን ሄዶ አየ። ገንዘብ ይኑር እንጂ ለማየት ማን ሰንፎ!

ብታምኑም ባታምኑም የዕለቱ ዕለት 15 ሚሊዮን ብር በባንክ ወደ ባለቤቱ ከአካውንቱ እንዲዛወር አደረገ። እኔም ከድርሻዬ ላይ በመጠኑ በእጄ አፈፍ አድርጌ ሌላውን ወደ አካውንቴ እንዲያስገባው ነገርኩት። ወዲያው ያቺን ብር ወስጄ ካላበደርከኝ እያለ አማላጅ እየላከ ላስቸገረኝ ወዳጄ ሰጠሁ። አልሰጥም ብል ምን እሆናለሁ ብሎ ማሰብ ጥሩ ነዋ። ማግኘትና ማጣት እንዲህ ከፍና ዝቅ እያሰኘ የሚያስተያየን ሳያንስ፣ አንተሳሰብም ብንል ማን ሰላም አጥቶ ማን ሰላም ያድራል አይመጣም እንዴ? እሱን እኮ ነው የምላችሁ። ነገን ማሰብ ማንን ገደለ? የምን አለኝ የለኝም ማለት?’ ምሁሩን የባሻዬን ልጅ ይኼን ጥያቄ ባቀርብለት፣ይኼ ሁሉ ሰው እንዲህ ማሰብ ቢችል እንኳን በግለሰብ ደረጃ እንደ አገር የብድር ድር ላያችን ላይ ያደራብን ነበር?” ብሎ ልክ አስገባኝ። ለካ  እንደ ግለሰብ በአበዳሪነቴ ስታበይ እንደ ማኅበረሰብ ተረጂነቴን ስቼው ነበር። ይኼ ምን ይገርማል!

እናላችሁ ሰሞኑን የማስበው በገንዘብ አቅም ራስን ከመቻል በፊት በአስተሳሰብ ራስን ስለመቻል ሆኗል። የእናንተን ባላውቅም የብዙ ሰዎችን ውድቀትና ስኬት ስታዘብ ሚስጥሩ በአስተሳሰብ ራሳቸውን የቻሉና ያልቻሉ መሆናቸው ይከሰትልኛል። እኛ ደግሞ እንደምታውቁት በአለባበስ፣ በሜክአፕ፣ በምንነዳው መኪና፣ በውፍረትና በክሳታችን ነው ስንመዛዘን የምንውለው። ይኼን ትታችሁት በቀደም አንድ ቅጥቅጥ  ላሻሽጥ ደንበኛዬን እየጠበቅኩ ካፌ ተቀምጬ ሁለት ወንድማማቾች ሲነጋገሩ የሰማሁትን ላጫውታችሁ። አንደኛው ሃይማኖቱን ከረር ያደርጋል። አንደኛው ልዝብ መሆኑ ነው። በማን ዓይን? በአክራሪው ዓይን፡፡ እናም ይመክረዋል።       “አንተ እስከ መቼ ነው ዕድሜህን፣ ገንዘብህንና ዕውቀትህን አልባሌ ቦታ የምትጨርሰው? መቼ ነው ሰው የምትሆነው? መቼ ነው ወደ ፈጣሪ ፀጋ የምትመጣው? እስካሁን እኮ የኖርከው ሁሉ ከንቱ ነው…ይለዋል። ተመካሪው በትህትናና በየዋህነት፣ለእኔ ስለምታስብ እንዲህ እንደምትለኝ አውቃለሁ። ግን እኔ የራሴ የሆነ ከፈጣሪ ጋር የምገናኝበት መንገድ አለኝ። የግድ የአንተን መምሰል የለበትም። እኔንም አንተንም ፈጣሪ እኩል ነው የሚያየን። ምናልባት አንተ ጠንካራ እምነት ሊኖርህ ይችላል። እኔ ደግሞ ደካማ ልመስል እችላለሁ። ነገር ግን ሁሉንም የሚያውቀው ፈጣሪ ነው። የአንተን ምክርና ሐሳብ እረዳለሁ፣ እቀበለዋለሁ። ግን በሕይወቴ ዘመን የማደርገውን ሁሉ ማድረግ የምፈልገው በራሴ ጊዜና ውሳኔ እንዲሆን ስለምፈልግ ታገሰኝ…ይለዋል። የሚደንቅ አባባል!

ንግግሩ እየቀጠለ ቢሆንም ያኛው ግን አይሰማውም።አልገባህም፣ ዛሬ ወደ ትክክለኛው መንገድ ካልተመለስክ ከዚህ ካፌ ተነስተህ ስትሄድ ሰይጣንሲኖትራክ ተመስሎ ሊወስድህ ይችላል…ሲለው ተመካሪው በዝምታ ተነስቶ መኪናውን አስነስቶ ተፈተለከ። እኔ አልኩኝ፣እስከ መቼ ይሆን በቡድን ፍረጃ፣ በቡድን አስተሳሰብ፣ በቡድን ብያኔ ሕይወታችን እየተቃኘ ስንራብ አንድ ላይ፣ ስንጠግብ አንድ ላይ፣ ስንፀድቅ አንድ ላይ፣ ስንኮነን አንድ ላይ መሆኑ የሚያከትመው?’ ደግሞ ደግሞ አሁን በቡድን ተደራጅተንም ከቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥየዳቦ ስምማውጣት ጀምረናል አሉ። የዴሞክራሲያችንም ማነቆ ዋነኛ እንከኑ የሚጀምረው መደራጀት መሀል ይሆን እንዴ? ጥያቄ የመጠየቅ መብት ያለው ሕፃን ብቻ ነው ያለው ማን ነው? ወጥረን በሠለጠነ መንገድ ብንሟገት እኮ ለበርካታ ጥያቄዎቻችን መልሶቻችን እኛው ዘንድ ነበሩ፡፡ ወይ ነዶ!

ደግሞ በቀደም ይኼንም ያንንም እያሰብኩ ግራ ግብት ብሎኝ የሆድ የሆዴን የማጫውተው ሰው ብፈልግ አጣሁ። የባሻዬ ልጅ ሥራ፣ ሥራ እያለ ቀልቡ ከእሱ የለም። ባሻዬ የተጣላ ሲያስታርቁ፣ ቀብር ሲደርሱ ዕድሩን ሲመሩ ጊዜ አጡ። ነገሩ ዙሪያውን ባስስ ሆነብኝ። እናንተ ሆናችሁብኝ እንጂ  ሰው በሞላበት አገር ሰው አጣሁ ብሎ ማውራትም እኮ ያሳፍራል። ኋላ ዘወር ስል አንድ መጽሐፍ አዟሪመጽሐፍብሎወዳጄ ልቤየሚል አስነበበኝ። ባሻዬ፣እግዜር የሚናገርለት ሰው ቢያጣ ድንጋይ ያናግራል” የሚሉት ነገር ትዝ ብሎኝ መዥረጥ አድርጌ ከኪሴ ብር አወጣሁና መጽሐፉን ገዛሁት። ግን አታስዋሹኝ እስካሁን አላነበብኩትም። በቆምኩበት ለአንድ ዘመናዊ ስካኒያ ገልባጭ ግብይት የቀጠርኳቸውን ሰዎች እየጠበቅኩ በቆምኩበት ከልቤ ጋር ጨዋታ ያዝኩ። ከራስ ጋር ንግግር ማለት ነው!

እሳትስ ይነዳል እንጨት ካልገደዱ፣ ሰው ከርሞ ይርቃል ልብ ነው ዘመዱተብሏል አይደል? ታዲያ ከብቸኝነቴ ብሶ ከልቤ ጋር ጨዋታ መያዜ ይባስ ብቸኛ አደረገኝ። ወጪ ወራጁን ስታዩት ልቡን ልብ የሚልም ጠፍቷል። እንዲያውም ካነሳነው አይቀር ሰው ልቡ የሚመክረውን ከመስማት የሰው ምክር እየሰማ መስሎኝ መከራ እየመከረ ያስቸገረው። እውነቴን እኮ ነው። ልብ ይስጠን ነው መቼም። ታዲያ አጫውተኝ ያልኩት ልቤ ከጥያቄ ጥያቄ እያስከተለ ሕመሜን አባሰው።ምነው ሰው ነፍሱ እርቃኑዋን ቀረች?’ ይለኛል።ኧረ ተወኝስለውምነው ፍቅር ቀዘቀዘች?’ ይለኛል።እኔ ምን አውቄስለውምነው እንዲህ እነ አቶ ውሸት፣ እነ ምቀኝነትና እነ ፍቅረ ንዋይ ናኙ?’ ይለኛል።ጉድ ነውእላለሁ አፍ አውጥቼ። ታዲያ ከልቤ አስጥሉኝ ብዬ አልጮህ። ለነገሩ ብንጮህም የሚጥለን እንጂ የሚያስጥለን ጠፍቷል። ወይ ልቤና እኔ!

በሉ እንሰነባበት። ግሮሰሪያችን ጢም ብላለች። አዳሜ በአዲስ ዓመት ሽልማት በተንቆጠቆጥኩ እያለ ምድረ ቀምቃሚ ይህንን ፈጣን ሎተሪ ይፍቀዋል። ይኼ ቢራ ይጠጣል። ሎተሪ ይፋቃል፣ ይጣላል። ይፋቃል፣ ይጣላል። አንዱ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ፣ ‘’እኔ ድሮም ዕድል የለሽ ነኝ…ብሎ በራሱ ይማረራል።ማን ዕድል ያለው አይተሃል?” ይለዋል ከወዲያ።ዕድል ዋዛ ነው እንዴ? ዕድለኛ ለመሆን መጀመርያ ፀንቶ በጨዋታው ሕግ መሠረት ጨዋታውን መጫወት ያስፈልጋል…ይላሉ ከባሻዬ አንድ አሥር ዓመት አነስ የሚሉ አዛውንት።አንቺ አገር…የሚለው ደግሞ መጣ። ጥንብዝ ብሎ ሰክሯል። “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” መሆኑ ነው፡፡ “አንቺ አገር የደፈረሽ ይውደም…” ሲል መፈክሩ በየአቅጣጫው አስተጋባ፡፡ ለካ ሰው ሁሉ በቋፍ ነው ያለው፡፡ የአገር ጉዳይ ሲነሳበት ይነዝረዋል መሰል!

አንዱ ሞቅ ያለው ደግሞ፣ “አንቺ አገር ዜጋሽ ቤት የለው፣ ትዳር የለው፣ ጥሪት የለው፣ ቢያመው መታከሚያ የለው፡፡ ነገር ግን እፍ ብሎ አፈርሽ ላይ እየተኛ ዕድሉን ሎተሪ ውስጥ ቢፈልግም፣ ዕጣ ፈንታው ግን ከአንቺ ጋር ስለተቆራኘ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ይጠብቅሻል…” ሲል ከዳር እስከ ዳር ፉጨትና ጭብጨባ አስተጋባ፡፡ አደባባይ አልወጣም እንጂ ስንትና ስንት አሰላሳይ፣ ፈላስፋና አርቆ አሳቢ በየቦታው አለ መሰላችሁ፡፡ ግሮሰሪ ጎራ ስትሉ እኔ ነኝ ያሉ ፕሮፌሰሮችን የሚያስንቁ ባለዘርፈ ብዙ ዕውቀት ተንታኞችን፣ በኮሜዲ ተራቀናል የሚሉ ጉረኞችን የሚያስከነዱ ልብ አፍርስ ቀልደኞችንና ተራቢዎችን እንደምታገኙ አረጋግጥላችኋለሁ፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ “አንበርብር በየፈርጁ ያሉ ኮርኳሪዎች ባይኖሩን ኖሩ ምን ይውጠን ነበር…” ሲለኝ ስሜቱ ተጋብቶብኝ “ እነሱን ያኑርልን!” እላለሁ፡፡ የማኅበረሰባችንን መስታወቶች ያኑርልን፡፡  መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት