‹‹ሰለሞን ባረጋ የ10,000ሜ ድልን ወደ ኢትዮጵያ መለሰ››፡፡ የሰለሞን ባረጋ ወርቃማ ድል ተከትሎ የዓለም አትሌቲክስ የገለጸበት ቃል ነበር፡፡
ሰለሞን የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳሊያ ከዑጋንዳ አትሌቶች መዳፍ ውስጥ አውጥቶ ነው ድሉን ማስገኘት የቻለው፡፡ ሰለሞን ርቀቱን ለማጠናቀቅ የወሰደበት 27፡43፡22 ደቂቃ ነው፡፡ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት በነበረው በዚህ ውድድር ሰለሞን ከዑጋንዳዊያኑ ጆሽዋ ቼፕቴጌና ኪፕሊሞ ጃኮብ ጋር ከፍተኛ ፉክክር አድርጓል፡፡ በተለይ የ5,000 እና የ10,000ሜ ክብረ ወሰን ባለቤቱ ቼፕቴጌ የእንግሊዛዊውን ሞ ፋራ ድል ለመድገም ቢያቅድም፣ ሰለሞን ግን ማፈናፈኛ እንዳሳጣው የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ሰለሞን 400ሜትር ሲቀረው በሙሉ መተማመን ደረጃ ላይ እንደነበርም ዘግበዋል፡፡
በ10,000ሜ ፍፃሜ ላይ የተሳተፉት በሪሁ አረጋዊ በ27፡46፡16 በመግባት አራተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ፣ ዮሚፍ ቀጀልቻ በ27፡50፡06 8ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡
የ21 ዓመቱ ሰለሞን ዘንድሮ ጠንካራ ዝግጅት ያደረገ ሲሆን፣ በበርካታ የግል ውድድሮች ላይ ተሳትፎ ነበር፡፡ ሰለሞን ከውድድሩ በኋላ ደስተኛ እንደሆነና ሲጠብቀው የነበረ ውጤት እንደሆነ አስረድቷል፡፡
‹‹ውጤቱ ለእኔ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ለቡድናችን መነሳሳት ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ከቤጂንግ ኦሊምፒክ በኋላ የወንዶች ረዥም ርቀት ከእጃችን ወጥቶ ቆይቷል፡፡ አበበ ቢቂላ ታሪክ በሠራበት ቶኪዮ ማስመለስ በመቻሌ ደስ ብሎኛል፤›› በማለት ሰለሞን ባረጋ ከውድድሩ በኋላ ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡
ኢትዮጵያ በ10,000ሜ ለመጀመርያ ጊዜ ወርቅ ያገኘችው በ22ኛው ኦሊምፒያድ ሞስኮ ላይ በምሩፅ ይፍጠር ሲሆን፣ በቀጣይነትም ኃይሌ ገብረሥላሴና ቀነኒሳ በቀለ በተለያዩ ኦሊምፒኮች ድሉን ተቋድሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በወንዶች 10,000ሜ ያመጣችውን ድል ሴቶቹም ይደግሙታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡