Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ በፌስቡክና በዩቲዩብ ገንዘብ የሚሸቅሉ አክቲቪስት ተብዬዎች ጉዳይ ነው፡፡ ከአንድ የጦር ጄኔራል ወይም ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን የተገኘ አስተማማኝ መረጃ ነው እያሉ የሚያወናብዱት አደገኛ ድርጊት ካልቆመ፣ ለብሔራዊ ደኅንነታችንም ሆነ ለሁላችንም ሰላም ፈታኝ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥም መረጃውን ለእነዚህ ኃላፊነት የማይሰማቸው ሸቃዮች የሚያቀብሉ የሚሊተሪና የሲቪል ባለሥልጣናት ካሉም፣ ድርጊታቸውን ቆም ብለው በማሰብ መታቀብ ይኖርባቸዋል፡፡ ካልሆነ ግን በአገር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት አደገኛ ስለሚሆን በሕግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ በተለይ የወታደራዊ ዘመቻዎች ውሎ በአግባቡ ተሰድሮ በመደበኛ ሚዲያዎች የማቅረብ ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑ እየታወቀ፣ በዘፈቀደ ለእነዚህ ግለሰቦች መረጃ መልቀቁ የሚቀጥል ከሆነ መንግሥት ራሱ ተጠያቂ መሆን አለበት እላለሁ፡፡ በዚህ መነሻ ከዚህ በፊት የባለሥልጣናትን ስም እየጠሩ ሲያወናብዱ ስለሚታወቁ ሰዎች አንዳንድ ገጠመኞችን ላካፍላችሁ፡፡  

በሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ ዘመን ሁሌም ድንቅና ግርም የሚለኝ አንድ ጉዳይ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ሰብሰብ የሚሉባቸው የመዝናኛ ቦታዎች አንዳንድ ሰዎች ያጋጥሟችኋል፡፡ ድንገት አንድ ጉዳይ ይነሳና በዚያ መነሻ፣ ‹‹እከሌና እከሊትን እኮ አውቃቸዋለሁ፡፡ እንዲያውም ዛሬ ምሳ አብረን ነው የበላነው፡፡ በጣም ከመቀራረባችን የተነሳ ሚስጥር ሁሉ እንጋራለን…›› ይሉዋችኋል፡፡ ‹‹እከሌ›› የጦር ጄኔራል ወይም ‹‹እከሊት›› ሚኒስትር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የተለየ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስፈራራት ሲፈልጉ፣ በሚሊተሪም ሆነ በሲቪል ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ስም ከለላ በማድረግ ለማመን የሚያዳግቱ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ፡፡

አንድ ጊዜ አንዱ ውስኪ ቤት እየጠጣ የአንድ ታዋቂ ሚኒስትር ስም በማንሳት፣ ‹‹ትናንት ሸራተን አብረን ኩርቫይዘር ስንጠጣ ነው ያመሸነው…›› ይላል፡፡ በሰውየው ንግግር በጣም የተገረመ ሰው፣ ‹‹ከማን ጋር?›› ይለዋል ለማጣራት ፈልጎ ነው፡፡ የሚኒስትሩን ስም እንደገና ይጠራለታል፡፡ ሰውየው በጣም ተናዶ ስለነበር፣ ‹‹በቃህ! እሱ እንኳን አልኮል ለስላሳ መጠጥ እንኳ አይጠጣም፡፡ አንተም በቅጡ የማታውቀውን ስም እያነሳህ አፍህን አትክፈት…›› ሲለው ሹልክ ብሎ ወጥቶ ይሄዳል፡፡ አጋጣሚ ባገኘ ቁጥር የታዋቂ ሚኒስትሮችንና ወታደራዊ ሹማምንትን ስም እየጠራ ብዙዎችን ሲያሸማቅቅ የነበረ አጭበርባሪ ከዚያ በኋላ ድርሽ ሳይል ቀረ፡፡ አንዳንዴ እኮ ደፋር አያሳጣን ያስብላል፡፡

እኔ ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት በርካታ ሰዎችን ታዝቤያለሁ፡፡ የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ አንዱ ቢሮዬ ይመጣና ስፖንሰርሺፕ ይጠይቀኛል፡፡ እኔ በኃላፊነት የምመራው መሥሪያ ቤት እሱና ቢጤዎቹ ለሚያዘጋጁት በዓል 200 ሺሕ ብር በስፖንሰርሺፕ እንዲሰጥ ነው ጥያቄው፡፡ ይህንን ገንዘብ ለሠራተኞቻችን በቦነስ መልክ ብንሰጥ ምን ያህል የተቀደሰ ተግባር እንደሆነ በሚገባ ስለማውቅ እንደማይቻል እነግረዋለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ሰውየው ቴአትር ጀመረ፡፡ ‹‹እኛ እኮ የኢሕአዴግና የመንግሥት ደጋፊዎች ስለሆንን ብዙ ድርጅቶች ቃል ገብተውልናል፡፡ የእናንተ ድርጅት ይህንን ገንዘብ ቢሰጥ መንግሥት በጥሩ ዓይን ያየዋል፣ ተጠቃሚም ትሆናላችሁ…›› ሲለኝ ደሜ ፈላ፡፡ ስለዚህ መናገር ነበረብኝ፡፡ ‹‹ሰማህ በአገራችን ውስጥ መለመድ ያለበት በጥገኝነት ሀብት መሰብሰብ ሳይሆን፣ ሕግና ሥርዓት አክብረው እየሠሩ ማደግ ነው፡፡ አይቻልም ስልህ እሺ ብለህ መሄድ እንጂ፣ እንዲህ ዓይነቱን ርካሽና ተራ ወሬ መዘብዘብ አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ውጣ!›› ስለው ተንሿኮ ሄደ፡፡

የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የፖለቲካ ድርጅትን፣ የታዋቂ ግለሰቦችን፣ የሀብታሞችን፣ ወዘተ. ስም እየጠሩ የሚያጭበረብሩ አሁንም በርካቶች ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ደግሞ መጠጥ ቤቶች፣ ሬስቶራንቶች፣ መዝናኛ ሥፍራዎችና መሥሪያ ቤቶች አካባቢ አይጠፉም፡፡ አሁን አሁን በከተማችን ታዋቂ የሆኑ መጠጥ ቤቶች የእነዚህ ግለሰቦች መናኸሪያ እየሆኑ ናቸው፡፡ እነዚህ መጠጥ ቤቶች በተለይ ንፋስ አመጣሽ ወጣት ሀብታሞች ውስኪና ቮድካ የሚጎነጩባቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ በተለያዩ ምክንያቶች እጅ መንሻ ሰጥተው ላጋጠማቸው ችግር መፍትሔ የሚፈልጉ ሰዎች መቃጠሪያ ናቸው፡፡ በስም ተጠቃሚ የሆኑ ሹማምንትም ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የድርሻቸውን ይሰበስባሉ፡፡ እነሱ ስለማይሳካላቸው ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› ለሚባሉ ተላላኪዎች ባለጉዳዮችን ያስተላልፋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት የሚጸየፉ ኩሩ ኢትዮጵያውያን አንጀታቸው እያረረ ይቃጠላሉ፡፡

ባለፈው ሰሞን አንደኛው ውስኪ ቤት ተገኝቻለሁ፡፡ አራት ሆነው ‹‹ጎልድ ሌብል›› ጠርሙስ ውስኪ አስወርደው ከሚጎነጩት መካከል አንዷ ሴት ናት፡፡ በአነጋገሯ ፈጠን፣ በአስተያየቷ ደፈር፣ በአጠጣጥዋ ጠንከር ያለች ናት፡፡ የሲጋራ አያያዝዋና አጫጫስ ቄንጧ ልዩ ነው፡፡ በየመሀሉ በተደወለላት ወይም ራሷ በደወለች ቁጥር የታዋቂ ሰዎች ስም ይነሳል፡፡ ‹‹በእኔ ይሁንብህ ወይም ይሁንብሽ›› በታጀበው አነጋገሯ በሚጠሩት ታዋቂ ሰዎች አማካይነት ጉዳያቸውን እንደምታስፈጽም በድፍረት ትናገራለች፡፡ ስልኳን አንስታ መነጋገር በጀመረች ቁጥር ሁላችንም እንድንሰማ ድምጿን ከፍ አድርጋ መሆኑ ገበያ ፍለጋ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ ገበያው ደግሞ የፈረደበት መሬት ነው፡፡ ብሔርና መሬት ድርና ማግ የሆኑባት ኢትዮጵያ ውስጥ የደላላው ብዛት አይጣል ነው፡፡

የዚችን ሴት ድፍረት ሲታዘብ የነበረ አንድ የማላውቀው ሰው፣ ‹‹ይቅርታ እዚህ አገር ማፈር ቀረ እንዴ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብልኝ፡፡ ‹‹ይኸው እንደምታየው ነው…›› አልኩት፡፡ ‹‹የእኔ ወንድም በየደረስክበት እኮ ማንም እየተነሳ የባለሥልጣን ወይም የታዋቂ ሰው ጓደኛ መሆኑን ይነግርሃል፡፡ ይኼ በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳቅቅ ተግባር ነው…›› ብሎኝ ሒሳቡን ከፍሎ ውልቅ አለ፡፡ ከጎኔ የተቀመጡ ሁለት ሰዎች በሴትዮዋ የድፍረት ንግግር መነሻ ወግ ይዘዋል፡፡ አንደኛው፣ ‹‹በዚህች ሴትዮና በዩቲዩብ በሚያደነቁሩን ደላሎች መካከል ያለው ልዩነት ሊገባኝ አልቻለም፡፡ እዚህ መሬት ላይ ያሉት ሌቦች የባለሥልጣን ተላላኪ ሆነው የአገር መሬት ይደልላሉ፣ የድርሻቸውን እየዘገኑ ውስኪ እየጠጡ ሌሎችን ያድናሉ፡፡ ዩቲዩብ ላይ ያሉት ደግሞ መሬት ላይ ካለው እውነታ ያፈነገጠ ሐሰተኛ መረጃ እየጋቱን፣ ምንጮቻቸው ስም አይጠሬ ባለሥልጣናት መሆናቸውን ይነግሩናል፡፡ መንግሥት የሚባለው ጉድ ደግሞ የሚሰርቁና ሐሰተኛ መረጃ የሚያሾልኩ ባለሥልጣናቱን መግራት አቅቶት መጫወቻ አድርጎናል፡፡ ሕግ ቢከበር ኖሮ የማንም መጫወቻ አንሆንም ነበር…›› እያለ ሲናደድ ይህ ጉዳይ ሁላችንንም የሚመለከተን መሰለኝ፡፡ ጎበዝ ዝምታው ይብቃና በቃ እንበል እንጂ!

(አረጋ ጫንያለው፣ ከሳር ቤት)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...