Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ​​​​​​​እንደ ዳማከሴ ዓይነት ተቋማትን በሁሉም መስክ ያብዛልን!

​​​​​​​እንደ ዳማከሴ ዓይነት ተቋማትን በሁሉም መስክ ያብዛልን!

ቀን:

በገብረ እግዚአብሔር ወንዳፈረው መኩሪያ (ኮሎኔል)

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ክብርና ዕውቅና የነበረው የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች፣ አቶ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ባደረባቸው ከፍተኛ ጥላቻ በ1983 ዓ.ም. በድንገት እንዲበተን ማድረጋቸው አይረሳም። የገነት ጦር ትምህርት ቤት የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመት ለመዘከር በ1998 ዓ.ም. በጦር ኃይሎች መኮንኖች ክበብ በተደረገው ስብስባ ላይ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በክብር እንግድነት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹በጦር ኃይሎች ክፍል ስም፣ በእናት ክፍልና በጦር አካዳሚ ስም የተለያየ ማኅበር መኖሩ መልካም ነው፡፡ ሆኖም ሁሉንም የሚወክል አንድ የመከላከያ  ቬተራንስ አሶሴሽን ቢቋቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ከማግኘቱም በላይ፣ ዕርዳታና ድጋፍ ለማድረግም አመቺ ይሆናል፤›› ባሉት መሠረት፣ የቀድሞ የጦር ኃይሎች ከፍተኛና ጄኔራል መኮንኖች ተስባስበው በመነጋገር ይህን አሶሴሽን መሥርተዋል።  

ዋናው ዓላማ በአገራችን የመከላከያ ተቋም ገብተው የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል በውትድርና ሙያ ያገለገሉና አሁንም በማገልገል ላይ ለሚገኙ አባላት ጭምር፣ በዕድሜ ጣሪያና በተለያዩ ምክንያቶች ከሠራዊቱ በክብር ሲሰናበቱ መሰባሰቢያ ማዕከል በማዘጋጀት ተገቢውን ክብርና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ በሙያቸው አገልግሎት ሊሰጡ በሚችሉበት መስክ እንዲሠሩና በቀሪ ዘመናቸው የተመቻቸ ሕይወት እንዲኖራቸው፣ ታሪካቸውን በግንባር ከተሳተፉ አባላት ሁነኛ ምስክርነት መመዝገብና ተበታትነው የሚገኙትን ሰነዶች በማስባስብ፣ በስማ በለውና ባልዋሉበት ግንባር የሚቀርቡ ጽሑፎችን በማረም ትክክለኛና ያልተዛባ የሠራዊቱን አኩሪ ታሪክ መጻፍና ለመጪው ትውልድ ማቆየት፣ በዚህም ሒደቱ ሳይቋረጥ ለዘለዓለም የሚቀጥል የመከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን እንዲኖር ማድረግ ነው።

ከመከላከያ ጋር የምናደርገው ትግል 15 ዓመት ሙሉ አልቆመም፡፡ በዚህ ሒደት በርካታ መሥራች አባላት በሕይወት የሉም፡፡ ይህ ሠራዊት በማናቸውም ጊዜ በእናት አገር ጥሪ ግንባር ቀደም ተሰላፊ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በኦጋዴንና በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል በተደረጉ ውጊያዎች አስመስክሯል፡፡ ከዚያም በላይ በኢትዮጵያዊነቱም ቢሆን ዓለም የቸረውን ዝናና ክብር ሊነፈገው አይገባም፡፡ አሁን በአገልግሎት ላይ የሚገኘውም ሠራዊት አባላት የአሶሴሽኑ አባል መሆን እንዳለባቸው የሠለጠነውን ዓለም ተሞክሮ ደጋግመን አስረድተናል፡፡ ሊገባቸው ወይም ሊያዳምጡን አልፈለጉም፡፡ አለበለዚያም በሠራዊቱ ላይ ወያኔ ያለውን ጥላቻ በሆዳቸው ይዘዋል ማለት ነው።  

በሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ጡረታ አያገኙም፡፡ አብዛኞቹ ለአገር ክብር የከፈሉት መስዋዕትነት ተረስቶ ራሳቸውን አዋርደው በልመና ኑሮ መጠለያ አጥተው በየጎዳናው ወድቀው ቀርተዋል፡፡ በሚመለከተው አካል ተጣርቶ መብታቸው እንዲከበር፣ ከወቅታዊ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጋር የተገናዘበ የጡረታ ክፍያ ማሻሻያም እንዲደረግና በቂ የሕክምናና ሌሎች አገልግሎት እንዲያገኙ፣ አሶሴሽኑ ከተቋቋመበት ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። 

አቶ መለስ ዜናዊ  የነበረውን የጡረታ አዋጅ በማናለብኝነት በመጣስ 20/45 በሚል ባወጡት አዲስ ሕገወጥ መመርያ ከ90 በመቶ በላይ ጡረታ ወይም ዳረጎት እንኳን ሳያገኙ ሜዳ ላይ ተበትነዋል፡፡ የሚገርመው ጉዳይ ግን የጡረታ መዋጮ ሳይከፍሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፈለው የጡረታ መዋጮ ሁሉም የወያኔ አባላት ጡረታ እንዲያገኙ ተድርጓል። 

ሠራዊቱ ባቋቋመው ጦር ኃይሎች ሆስፒታል እንኳን ከጥቂት ጄኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች በስተቀር ሕክምናም ተከልክለናል፡፡ በጦር ሜዳ በአብዛኛው ጉዳት የደረሰባቸው ግን መስመራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት መሆናቸው ይታወቃል። የኢትዮጵያ ሠራዊት የደረሰበት ግፍና በደል አሁንም አለማብቃቱን ከዚህ በላይ በአጭሩ እንደ መግቢያ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ በቅርቡ በኤፍኤም 97.1 በሚተላለፍ የሬዲዮ ፕሮግራም ዳማከሴ ስለሚባል የሕክምና አገልግሎት ስለሚሰጥ ማዕከል ማስታወቂያ ይነገር ነበር፡፡ በአጋጣሚ ልጄ ይህን መልዕክት እያደመጠች ከመሆኗም በላይ፣ አራት ኪሎ የሕክምና ማዕከሉ ካለበት በቅርብ ርቀት ላይ ነበረች፡፡ ለቀድሞ ጦር ኃይሎች አባላት ነፃ የሕክምና ድጋፍ እንደሚሰጡ ስማች። በተላለፈው ማስታወቂያና በተነገረው የስልክ ቁጥር ስትደውል አጠገቧ መሆኑን ተረዳች፡፡ ወዲያውኑ ወደዚያው ሄዳ አባቴ እንዲረዳ እፈልጋለሁ በማለት አስመዘገበችኝ፡፡ በስልክም የሆነውን ነገረችኝ፡፡ በምዝገባ ቅደም ተከተልና በወረፋ ስለሚሆን እነሱ ይደውሉልሃል አለችኝ፡፡ በጣም ገረመኝ ማመን ከበደኝ፡፡

ይህን ጉዳይ በአገራችን እንዲህ በነፃ እንርዳ የሚሉ ኢትዮጵያውያን ወይስ የውጭ ዜጎች በማለት ከራሴ ጋር ተሟገትሁ፡፡ በመጨረሻም በሰጠችኝ ስልክ ስደውል እውነትም ተመዝግቤያለሁ፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ እኛ እንደውላለን ተባልኩ ከትህትና ጋር፡፡ ከሳምንታት ቆይታ በኋላ እንደተባለው ከዳማከሴ ነው ተራዎ ስለደረሰ ነገ መጥተው ሕክምና ይጀምሩ ተባልኩ፡፡ 

በርካቶች የጦር ኃይሎች አባላት በሕመምና ደጋፊ በማጣት በችግር ተጠብሰው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ከ15 ዓመት በላይ ከመከላከያ ጋር የምናደርገው ትግል አሁንም አላቋረጥንም፡፡ ኢትዮጵያዊ መንግሥት ሲኖር እንታወሳለን በሚል ተስፋ ሳንቆርጥ ዓላማውን ለማሳካት ጥረታችን ይቀጥላል። እንደ ዳማከሴ ዓይነት ተቋማትን በሁሉም መስክ ያብዛልን።

የዳማከሴ ፊዚዮቴራፒ ሕክምና ማዕከል የሚሰጠው አገልግሎት ከጭንቅላት እስከ እግር መርገጫ ድረስ ያሉትን የሰውነት መጋጠሚያዎች፣ የነርቭና ጅማት፣ እንዲሁም ከእነዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሕመሞችን በዘመናዊ የሕክምና መሣሪያ በመታገዝ ማስወገድ ነው። በተጠራሁበት ዕለት ወደዚያው አመራሁ፡፡ ማዕከሉ እንደ ደረስኩ ሪሴፕሽኒስቷ አቀባበል አደረገችልኝ፡፡ የሕመም ዓይነትና የሚሰማበት ቦታ የሚያሳይ በቻርት የተደገፈ ዝርዝር የሚገልጽ ቅጽ እንድሞላ ተስጠኝ፡፡ የሚሰማኝን ሕመም ቦታና ሕመሙን በቅጹ ከሞላሁ በኋላ መልሼ ለሪሴፕሽኒስቷ ስጠሁ፡፡ ሐኪሙ ወደ የሚቀጥለው ክፍል ይዞኝ ገብቶ ቃለ መጠይቅ ካደረገልኝ በኋላ ለሰባት ቀናት ሕክምና እንደሚሰጠኝ ተነገረኝ፡፡

ወዲያውኑ የአንድ ሰዓት ሕክምና፣ እንዲሁም የ15 ደቂቃ የአካል እንቅስቃሴ አደረግሁ፡፡ አንድ ቀን እያሳለፍኩ እንደምመጣና የአካል እንቅስቃሴም ሳይቋረጥ በቤት ውስጥ መሥራት እንዳለብኝ ተነገረኝ፡፡ ሰውነቴ ቅልል ብሎኝ ዝለል ዝለል እያስኘኝ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡ በጣም ደስተኛ ሁኜም ዋልኩ። በዚሁ ሁኔታ አንድ ቀን እያሳለፍኩ ለሰባት ቀናት ሕክምናውን ተከታተልኩ፣ የሐኪሞቹ ትህትና የሚደነቅ ነው፡፡

የሚገርመው ከአሥር ያላነሱ ክፍሎች ዙሪያውን አሉ፡፡ የሚታከሙ ስዎችም ምንጊዜም አሉ፡፡ ቦታው ፀጥ ያለና እንደ ሌሎች ሕክምና ጣቢያዎች የሰው ግርግር የማይታይበትና ንፁህ መሆኑ አስደስቶኛል። በየጊዜው ይህን ዕርዳታ የሚያደርገው ሰው ማን ይሆን እያልኩ በሄድኩ ቁጥር አስባለሁ፣ ሐኪሙንም ጠየቅሁ፡፡ ድርጅቱ የማን እንደሆነና ለምንስ ነው የነፃ ድጋፍ አገልግሎት በተለይ ለቀድሞ ጦር ኃይሎች አባላት የሚስጠው በማለት ጠየቅሁት፡፡ የመጨረሻውን ሕክምና ጨርሼ ልወጣ ስል ሪሴፕሽኒስቷን ይህንኑ ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ‹‹ኑ! እንሂድ!›› አለችኝ፣ ተከተልኳት፡፡ ለካስ እዚያው ውስጥ ነበር ቢሯቸው፡፡ ‹‹አቶ ሰሎሞን እባላለሁ!›› አሉኝ፣ ስሜን ነገርኳቸውና ተቀመጥኩ፡፡

ይህን በጎ ተግባር ለቀድሞ ጦር አባላት የሚያደርግ ወታደር የነበረ ወይም የወታደር ልጅ፣ ከራቀም የሚወደው ወታደር ዘመድ የነበረው፣ አልያም በሙያው የተሳካለት እግዚአብሔር የባረከው መሆን አለበት የሚል ግምት ነበረኝ አልኩ፡፡ ወጣ ገባ እያሉ እንደሚሠሩ አጭር መልስ ሰጡኝ፡፡ ስለአገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን አነሳሁባቸው፡፡ ‹‹ከ15 ዓመት በላይ የተቋቋመ ማኅበር የመከላከያ ድጋፍ በማጣቱና በእኛም አቅም ማነስ ምክንያት የተፈለገውን ዓላማ ማሳካት አልቻልንም፣ በጋዜጣ ደጋግመን ለማስተዋወቅ ሞክረናል…›› አልኳቸው፡፡ ‹‹ታዋቂ ሰዎችን ማግኘት አለባችሁ፣ ብቻችሁን መወጣት አዳጋች ነው፡፡ በሬድዮና በቴሌቪዥን፣ እንዲሁም በኤፍኤም ሬዲዮ ማስተዋወቅ ይኖርባችኋል…›› የሚል ሐሳብ ሰጡኝ፡፡ ‹‹ጥቆማውን በሙሉ ለመፈጸም እሞክራለሁ…›› አልኳቸው፡፡ በዚሁ ከፍ ያለ ምሥጋና አቅርቤ እንደምንገናኝ ተስፋ በማድረግ ተለያየን።

ወደፊትም እንደ ዳማከሴ ዓይነት ለአገር አሳቢ ድርጅቶችና በጎ አድራጊዎች ትኩረት ካልሰጡ፣ ቀሪዎቹ የቀድሞ ጦር አባላት በዕድሜና በጤና ችግር ምክንያት ብዙ እንደማይቆዩ ይገመታል። እንዲህ ዓይነት ደጋግ ሰዎችንና ተቋማትን እግዚአብሔር ያብዛልን።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...