Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገት​​​​​​​እውነትን ቀና ብለው ለምን አናይም አሉ?

​​​​​​​እውነትን ቀና ብለው ለምን አናይም አሉ?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

‹‹ሕወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል፡፡ ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል፡፡ ይህ ሠራዊት ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ ሠራዊት ነው፡፡ በቦታው የሚገኘውም የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ነው፡፡ ሕወሓት ግን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ አገር ሠራዊት ቆጥሮ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነስቷል፡፡ በዳንሻህ በኩልም ጦርነት ከፍቷል፡፡ መንግሥት የትግራይ ሕዝብ እንዳይጎዳ በማሰብ፣ ጦርነት እንዳይፈጠር የትዕግሥቱ ጫፍ ድረስ ታግሷል፡፡ ጦርነት የሚቀረው ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ አይደለም፡፡ የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ አገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ቀዩ መስመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል፡፡ አገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ እንዲከታተል፣ በየአካባቢ ሊከሰቱ የሚችሉ ትንኮሳዎች በንቃት እንዲቃኝና ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን እንዲቆም ጥሪ አቀርባለሁ፡፡››

ይህ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ከዕኩለ ሌሊት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ያስታወቁት መልዕክት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ከመንፈቀ ሌሊት በኋላ፣ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት በኋላ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ያስታወቁትን የአገር ጉዳይ፣ የዘወትርና የዕለት ተዕለት የመንግሥት መረጃውን ከመደበኛው የመንግሥት ሬዲዮና ቴሌቪዥን የሚሰማው/የሚያገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያወቀው ከንጋት በኋላ ነው፡፡ በተለመደ አነጋገርና አቆጣጠር ረቡዕ ጠዋት፡፡ እንደ ወጉና እንደ ሕጉማ፣ እንደምናስረው ሰዓትማ፣ በተለይም ከዓለም የሰዓት ሥርዓት አቆጣጠር ጋር አቀናጅተን እንደምንሞላው የሞባይል ስልካችንማ ረቡዕ የገባው መንፈቀ ሌሊት አናቱ ላይ ነው፡፡ ከፍ ሲል ቀኑን ጥቅምት 25 ያልኩት በዚህ ምክንያትና ሥሌት ነው፡፡

- Advertisement -

እና ከላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባረዱት አኳኋን የተጀመረው ጦርነት ውስጥ ከገባን እነሆ በሐምሌ ወር አራተኛ ሳምንት መጨረሻ ላይ ዘጠኝ ወር ሆነን፡፡ ዘጠኝ ወር ሞላን፡፡ አሁን አሥረኛው ወር ውስጥ ገባን፡፡ በዚህ ዘጠኝ ወር ብዙ መከራዎች ውስጥ አልፈናል፡፡ ከሁሉም በፊትና በላይ ከፌዴራሉ ሪፐብሊክ አባላት መካከል አንዱ የትግራይ ክልል የጦርነት ቀጣና ሆነ፡፡ ጦርነት የሚያመጣው ችግር፣ ችጋርና የሰብዓዊነት ቀውስ ሰለባ ሆነ፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 62(9) እና የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 14/2/ለ ጠቅሶ፣ የትግራይን ክልል በጊዜያዊነት የሚያስተዳደር ለፌዴራሉ መንግሥት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ወሰነ፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 470/2013 ኅዳር ወር ውስጥ ተቋቋመ፡፡ ይህ ጊዜያዊ አስተዳደር ያደረገው ምክክርና ጥናት፣ እንዲሁም ያቀረበው ጥያቄ ተገልጾ፣ ‹‹… ይህ የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ ያለ ቅድመ ሁኔታ በሰብዓዊነት ላይ የተመሠረተ በተናጠል የተኩስ አቁም ከዛሬ ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት›› ማወጁን አስታወቀ፡፡ በሳምንቱ መጀመርያ ላይ ደግሞ የቪኦኤ የአማርኛው አገልግሎት እንደ ዘገበው፣ ‹‹የትግራይ ክልል ምክር ቤት ከስምንት ወራት በኋላ ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ጉባዔ ማካሄዱንና የክልሉ ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ያለፉትን ስምንት ወራት ሪፖርት፣ እንዲሁም የክረምት ወራት ዕቅድ ማቅረባቸውን›› የትግራይ ክልል፣ ‹‹ሕጋዊው መንግሥት ወደ ቦታው በመመለሱ ጉባዔው›› መጠራቱን፣ በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጦ ቆየው በየሦስት ወራት ማካሄድ የነበረበት የምክር ቤቱ ስብሰባ ሐምሌ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው ‹‹ስድስተኛው ዘመን አንደኛ አስቸኳይ ጉባዔ›› መጀመሩን ሰማን፡፡

እዚህ ይበልጥ ውስብስብና ከተገለጸው የባሰ ‹‹የተጭበረበረ› መልክ ወደያዘው የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ክልል መንግሥት ግንኙነት ውስጥ መልሰን ከመግባታችን በፊት፣ አንድ መሠረታዊና መነሻ የሆነ ሕገ መንግሥትዊ እውነትና እምነት እናንሳ፡፡ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል የሚፈልጉም፣ ሕገ መንግሥቱ መሻሻሉን ብቻ ሳይሆን ከእነ አካቴውም ሕገ መንግሥቱን የሚጠሉትና የማይፈለጉትም ጭምር፣ የጥበብ መጀመርያና የትግል መንደርደሪያ ይህ ብቻ ስለሆነ፡፡ የኢትዮጵያ የሕጎች ሁሉ የበላይ በአንቀጽ አንድ የኢትዮጵያን መንግሥት ስያሜ፣ ከስያሜ ይበልጥ ደግሞ ፍጥርጥር ይደነግጋል፡፡ ‹‹ይህ ሕገ መንግሥት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፕብሊክ በሚል ስም ይጠራል›› ይላል፡፡ ይህ ከመጠሪያ ስም፣ ከስያሜ በላይ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ነው የሕገ መንግሥቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ እንኳን (በአንቀጽ 93/4/ሐ) በጭንቅና በጥብ ወቅትም ቢሆን፣ የዚህን የስያሜ ወይም የመጠሪያ ይዘት የሚገደብ ዕርምጃ ሊወሰድ አይችልም የሚለው፡፡

እና ይህን ያህል ክብር፣ ከፍታና ጥበቃ የተሰጠው የኢትዮጵያን ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር የሚደነግገው ሕገ መንግሥት ይዘት ምንድነው? ዴሞክራሲውን (የሚመለከተውን ነገር) ለጊዜው እንተወው፡፡ ተብሎ ተብሎ ያለቀለት፣ ያሰለቸም፣ ከሁሉም የበለጠ ደግሞ ትግሉን ለውጡን አምጦ የወለደ የእሱ የይዘት ባዶነት በመሆኑ፡፡ ትግሉና ለውጡ የመጣው የአገሪቱን ሕዝቦች ልዕልና መወከል የቻለ/የተዋጣለት ሪፐብሊክ ማደራጀት ስላቃተ፣ ሕዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ወደ የሚችልበት የታወቀ መንገድ መግባት ስላልተቻለ ነው፡፡

የፌዴራላዊነት አወቃቀራችን ሀ ብሎ ሲነሳ ሕገ መንግሥቱ ትልቁን የመንግሥት ሥልጣን በማዕከላዊው መንግሥትና በክልል መንግሥታት መካከል ያደላድላል፡፡ ሁሉም፣ ሁለቱም ዓይነት መንግሥታት በሰፊው ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሕግ የማውጣት፣ ሕግ የማስፈጸምና ሕግ የመተርጎም ሥልጣን እንዳላቸው ይደነግግና ለማዕከላዊ/ለፌዴራል ወይም ለክልል መንግሥት ለብቻ የተሰጠውን፣ ለሁለቱም በጋራ የተሰጠውን፣ እንዲሁም ለማዕከላዊው/ለክልልም መንግሥት የተከለከለውን ይደነግጋል፡፡ ይህንን የየብቻና የጋራ ክልከላ ጭምር የደነገገው፣ ከዚህ ጋርም፣ ‹‹በሕገ መንግሥቱ ለፌዴራል መንግሥት በተለይ ወይም ለፌዴራል መንግሥትና ለክልሎች በጋራ በግልጽ ያልተሰጠ ሥልጣን የክልል ሥልጣን ይሆናል›› ያለውና ሕገ መንግሥቱን ያወጣው፣ በሕግና በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ከሁለቱም የመንግሥት የሥልጣን አካላት (ከክልልም ከማዕከላዊውም) በላይ የሆነ ሥልጣን ነው፡፡ ይህን ክፍፍል፣ ድልድልና ክልከላ ለየብቻ ሆነው ሊለውጡት አይችሉም፡፡

ከዘጠኝ ወራት በፊት ጀምሮ በማዕከላዊ መንግሥትና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል የተነሳው፣ ወደ ጦርነትም የተለወጠው አለመግባባት ፀብና ውዝግብ መነሻና የሥር የመሠረት ምክንያት (ውስብስቡን ችግር እንዲህ በቀላሉና አቃልሎ መናገር ከተቻለ) ይህ ፌዴራላዊ አወቃቀር ድንጋጌ መጣስና መርገጥ ነው፡፡ ይህን የመሰለ መነሻና የሥር ምክንያት ያለውን አለመግባባት፣ ፀብና ውዝግብ ወዲያውኑና እዚያው በዚያው፣ ምንም የዝግጅትና የ‹‹ሽግግር›› ጊዜ ሳይፈጅ ወደ ጦርነት የለወጠው ደግሞ አስቀድሞም ቢሆን ለሕግ፣ ለዚያውም ለሕገ መንግሥታዊ ሕግ ድንጋጌ የመገዛት ክብር ተነፍጎት የኖረው ይኼው የፌዴራል አወቃቀር ሕግ ነው፡፡ ዛሬም ያልተላቀቅነው፣ አገርን በማዳን ዘመቻው ውስጥ ጭምር ጎልቶና መፍትሔም ተደርጎ የሚሰማው የየክልሉ የ‹‹ልዩ ኃይል›› የታጠቀ ኃይል፣ የክተት ጥሪ፣ ወዘተ ሁሉ የዚህ የቆየ ሕመም ማሳያ ነው፡፡

በዋነኛነት በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥትና በአንድ ክልል አስተዳደር መካከል ያለ ችግር አድርጌ አቃልዬ፣ ምናልባትም አሳንሼ የገለጽኩትን ጉዳይ ሳነሳ፣ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ማለቴን መልሶ የማጥራት፣ እንደገና አብራርቶ ከማስረዳት ስሜትና አደራ ጋር መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ከዚህ ጋር ከላይ የገለጽኩት የቪኦኤ አማርኛ ዜና ውስጥ ‹‹ወደ ቦታው [ስለ] ተመለሰው ሕጋዊ መንግሥት›› መነሳቱን፣ እንዲሁም የዚህ ‹‹ሕጋዊ መንግሥት›› የክልልም፣ ምክር ቤትም ‹‹የስድስተኛውን ዘመን አንደኛ አስቸኳይ ጉባዔ ማድረጉን›› መነገሩን አስታውሳሁ፡፡

እነዚህን ጉዳዮች እንደ ፍጥርጥራቸው፣ እንደ አመጣጣቸውና አቀማመጣቸው፣ በየሥፍራና ቦታቸው ለመረዳትና ለመገምገም ይቻል ዘንድ አንዳንድ ለዳራ ያህል የሚያገለግሉ መረጃዎችን ማከል የሚያስፈልግ ይመስኛል፡፡ የተቻለኝን ያህል እነዚህን አንድ ሁለት ብዬ ልዘረዝር፡፡

አንደኛው ‹‹የስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ›› ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. በኋላ ምርጫ የማድረግም ሆነ ለምርጫ የመዘጋጀት ጉዳይ ከዚያ በፊት አስቀድሞ የተያዘ የቀጠሮ፣ የሞት ቀጠሮ ነገር ሳይሆን፣ ትርጉም ላለው ዴሞክራሲን የማደላደልና ለምርጫ ዝግጅት ከማድረግ በኋላ የሚመጣ አጀንዳ መሆኑን በለውጡ፣ በዓብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ፣ አሸናፊ ሆኖ፣ በኢትዮጵያውያን ሆይታና እሰይታ ብቻ ሳይሆን፣ ማንም ባላለመው የኖቤል የሰላም ሽልማት ታጅቦ መውጣት ጭምር የተወሰነ ጉዳይ ነው፣ ነበር፡፡ ይህ ዋና ጉዳይና መሠረታዊ ቁምነገር ግን የሁሉም የጋራ መግባቢያ ባለመሆኑ የአገር የሕግ ማዕቀፍ ማስተናገድ በሚችለው መጠን፣ በአገር ሕገ መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ፣ ለዚያውም ሁሉንም ነገር ክፋታችንንም፣ ጥፋታችንንም፣ ጉዳችንንም የአገር የዓለም ምድር ሰው እያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው የተወሰነ ጉዳይ ነው፡፡ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫ የተካሄደው በዚህ የክልልና የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንን ባከፋፈለና ባደላደለ ሕግና ውሳኔ መቃን ውስጥ ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት (ወይም ይህንን ጉዳይ ይበልጥ ለማብራራት በሚያገለግሉ ስሙ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት) የመንግሥቱን ፌዴራላዊነት የመጠበቅና የመመከት ግዴታውና ሥልጣኑ ውስጥ የገባው፣ የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣውን የ1995 ዓ.ም. ሕግ በሚያዘው መሠረት ዕርምጃ የወሰደው ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ነው፡፡ የትግራይ ክልላዊ መስተዳድር ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ተግባር ፈጸመ የተባለው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ይህንን አዋጅ መሠረት አድርጎ የትግራይ ክልልን በጊዜያዊነት የሚያስተዳድር ለፌዴራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም የወሰነው ከጥቅምት 24 በኋላ ጥቅምት 28 ቀን ነው፡፡ በዚህ ሁሉ መካከልና ከዚያ በኋላ ፌዴራል መንግሥት ትግራይ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ መኖሩን ማወጁ፣ ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው መሰየማቸውንም፣ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚሁ በሐምሌ ወር ከፍተኛ ፋይዳ ወይም ጠንቅ (Consequence) ያላቸው ክሶች መመሥረታቸውን ልብ ይሏል፡፡ በእነዚህ ዕርምጃዎችና ለዕርምጃዎቹ መነሻ በሆነው በተለይም በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 14/2/ለ መሠረት ፌዴራል መንግሥት የክልሉን ምክር ቤትና የክልሉን ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል አገደ፡፡ ለፌዴራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደርም አቋቋመ፡፡ በተጠቀሰው ሕግ ተፈጻሚነትና በተወሰደው የፌዴራል መንግሥት የሥልጣን አካላት ዕርምጃ መሠረት የክልሉ ምክር ቤትና የክልሉ ከፍተኛ አስፈጻሚ አካል ታግደዋል፡፡ የዚያ ክልል የሥልጣን አካል አሁን ለሁለት ዓመት (አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከስድስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ሊያራዝመው ይችላል) የሚቆየውና ተጠሪነቱ ለፌዴራሉ መንግሥት የሆነ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 479/2013 የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ነው፡፡

የኢትዮጵያ የፌዴራል አወቃቀር ድንጋጌ በአጠቃላይ ክልሎች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52/2/ሀ እንደተደነገገው ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳደር የማዋቀር፣ የሕግ የበላይነት የሠፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባት፣ ይህንን ሕገ መንግሥት የመጠበቅና የመከላከል ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡ ከማዕከላዊ መንግሥት ማዕዘን አንፃርም (በሕገ  መንግሥት አንቀጽ 51/1 ቁጥብና አጠቃላይ ቋንቋ) ፌዴራላዊና ሪፐብሊካዊ የአገርን ሥርዓተ መንግሥት የመከላከል ግዴታ ያቋቁማል፡፡ ይህ በሕገ መንግሥቱ በዚህ አንቀጽ በደፈናው የተገለጸውና ከፋም ለማም፣ አረረም መረረም በአዋጅ ቁጥር 359/95 የተብራራው የማዕከላዊ መንግሥት ለክልሎች ያለው ግዴታ ድንጋጌ የአሜሪካው ሕገ መንግሥት የአንቀጽ አራት ክፍል አራት አቻ ድንጋጌ መሆኑ ነው (የተጠቀሰው የአሜሪካው ሕገ መንግሥት ድንጋጌ ርዕስ “Protection Afforded to States by the Nation” ይላል፡፡ ደግሞም የትኛውም ስቴት/ክልል ሠራዊት/የጦር ኃይል አይኖረውም ብሎ ይከላከላል፣ አንቀጽ አንድ ክፍል አሥር ንዑስ 3)፡፡

የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ውስጥ ጣልቃ የሚገባው፣ የተገለጸውን ዓይነት ዝርዝር የጥበቃና የመከታ ሥራ የሚሠራው በአጠቃላይ በአንቀጽ አንድ የተደነገገውን የመንግሥት አወቃቀር የሚጠብቀው፣ በዚህ ሥልጣኑ አማካይነትም ክልሎች ውስጥ ጣልቃ ገብቶ የመከላከያ ሠራዊትን ማሰማራት፣ የክልሉን የሥልጣን አካላት (ምክር ቤቱንና አስፈጻሚው) ማገድ፣ ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም፣ የክልሉን ባለሥልጣናት፣ ተሿሚዎች፣ ተመራጮች ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ ድረስ ዕርምጃ የሚወሰደው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወደቀ ብሎ ሲያምንና ሲወስን ነው፡፡ ሥራ ላይ ባለው፣ ደግሞም ያኔ በ1995 ዓ.ም. በወጣው ሕግ መሠረት ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት አደጋ ላይ ወድቋል የሚባለው፣ በአንድ የክልል መንግሥት ተሳትፎ ወይም ዕውቅና ሕገ መንግሥቱን ወይም ሕገ መንግሥዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት ሲፈጠር/ሲፈጸም፣ በተለይም በትጥቅ የተደገፈ የአመፅ እንቅስቃሴ ሲደረግ፣ ከሌላ ክልል ወይም ከሌላ ክልል ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ እፈታሁ ሲባል፣ ወይም የፌዴራሉን ሰላምና ፀጥታ ማናጋት ሲመጣ ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ ፌዴራል መንግሥት ጣልቃ የገባው፣ የየክልሉን የመንግሥት የሥልጣን አካላት አግዶ ጊዜያዊ አስተዳደር ያቋቋመው፣ ወዘተ ይህ ሁሉ ተሟልቶ ነው፣ ወይም ተጣልቷል ተብሎ ነው፡፡

ከሰኔ 21 ቀን ጀምሮ ጊዜያዊ አስተዳደሩም፣ የመከላከያ ሠራዊቱም ከክልሉ ወጥቷል፡፡ ዜናውን ከቪኦኤ አማርኛው ክፍል የሰማሁት የክልሉ ‹‹ሕጋዊ መንግሥትም ወደ ቦታው ተመልሷል››፣ ወደ ቦታው ተመልሷል ተብሎም የ‹‹ስድስተኛው ዘመን [የክልሉ ምክር ቤት] አንደኛ አስቸኳይ ጉባዔ›› ተካሂዷል፡፡ ትግራይ ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት ይህን የመሳሰሉ እንስተካከላለን ብለው የሚፋለሙ ጥያቄዎችና እንቆቅልሾች ጭምር ያሉበት ቀውስ ነው፡፡

ቀውሱንና የአገራችንን ችግር በአጠቃላይ በአገር የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረትና ትጋት (ፀሎትም ጭምር) የሚያደናቅፈውና አድሮ ጥሬ የሚያደርገው ደግሞ ሕጋዊነትን፣ በሕግ መረማመድን መከራ ከሚያሳያው ችግር በላይ እውነት መጥፋቱ ነው፡፡ እውነት አለመነገሩ ነው፡፡ እውነት መሰወሩ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለምሳሌ ዘጠኝ ወራት የሞላው የጥቅምት 24 ነገር ምንድነው? ምንድነው ጥቅምት 24 የሆነው? አፍረጥርጠን፣ በማስረጃና በትረካ አብራርተን ያልተናገርነው ጉዳይ ነው፡፡ ዘጠኝ ወራት የሞላው ይህ ድርጊት በዚህ ዕድሜው የመጀመርያ ሳምንት/ምናልባትም ሳምንታት ውስጥ ተራና መደበኛ ዜናዎች ሳይቀር በሌላው ወገን የታመነ ሀቅ አድርገው ያላወሩት ይመስል፣ ዛሬ የድርጊቱ  መነሻ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ዕዝ ላይ ደረሰብኝ የሚለው›› ጥቃት ነው እየተባለ ይካዳል፡፡ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሚባለውም እውነትን ቀና ብሎ ማየት የማይፈልግና እውነት ቀና ብሎ እንዳይታይ ዋነኛው ሥራው አድርጎታል፡፡

ፈርዶብን፣ እሱም ፈርዶበት ደጋግሜ ወደ ጠቀስኩትና ምንጭ ወዳደረግሁት የቪኦኤ የአማርኛው ዜና ተመልሼ ልግባ፡፡ ዜናው እኔም ደጋግሜ የጠቀስኳቸውን ነገሮች ካወራልን በኋላ፣ ‹‹ከፌዴራል መንግሥት አስተያየት ለማግኘት በስልክና በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት አልተቻለም›› ብሎ፣ ‹‹ሆኖም…›› ብሎ ጀምሮ ያንኑ የተለመደ ‹‹አሮጌ ሸክላ›› ያሰማናል፡፡ ‹‹ሆኖም የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ጦርነት የትግራይ ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው ነው የተጀመረው…›› በማለት ሲገልጽ ቆይቷል በማለት፣ ‹‹ዜናው›› እኩልታ፣ እኩለት ተጨንቆ ግዳጁን ሲወጣ እንሰማለን፡፡ ዋናው ጥያቄ አሁንም ጦርነቱ የተጀመረው እውነትም የትግራይ ኃይሎች በግዙፉ የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው አይደለም ወይ? ተድበስብሶ የቆየው፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም በዚህ በወሬው፣ በኢንፎርሜሽኑ ዘርፍና ግንባር ሰንፎና አቅም አጥቶ እውነት ራሱ ቀና ብሎ አገር እንዳያይ፣ ለአገር እንዳይታይ ያደረገው ጥቅምት 24 ቀን ምን ሆነ? የሚለውን ጥያቄ በዝርዝና በሰፊው ሳይናገር በመቅረቱ ነው፡፡

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የሆነውን፣ ወደዚያም የወሰደውን ሁኔታና ምክንያት ትንሽ ትንሽና እስካሁን ከማንም በላይ አቀናጅቶና አፍታትቶ የገለጸልን (ለዚያውም ያገኘነውን ያህል) የካቲት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ማለትም ከሦስት ወር ተኩል ያህል በኋላ የመንግሥታቱ ድርጅት የዲቨሎፕመንት ፕሮግራም (UNDP) ኃላፊ ለአንቶኒዮ ጉተሬስ በጻፉት ማስታወሻ አማካይነት ነው፡፡ ይህን ባለ አራት ገጽ ማስታወሻ (ሜሞ) ራሱን ያወቅነው የየካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ፎሬን ፖሊሲ ጋዜጠኝነት መልካም ፈቃዱ ሆኖ ከአርዕስቱ ጀምሮ በመላው የጽሑፉ አካልና ይዘት ውስጥ ዓይን ባወጣ ወገንተኛነቱ ቁጥብና ንፉግ ሆኖ ያንጠባጠበልንን ያህል ነው፡፡

በፎሬን ፖሊሲ መጽሔት ንፉግነትና ወገንተኛነት ውስጥ ቢሆን፣ የኢትዮጵያን መንግሥት የማጥቃት ዕርምጃ በውጤትነት ያስከተለውና የቀሰቀሰው በየትም ቦታ በዓለም ላይ የጦርነት ተግባር የሚባል አፀፋዊ ጥቃት የሚያስከትል፣ የኢትዮጵያ የሰሜን ዕዝ ጠቅላይ መምርያ በሕወሓት መጠቃትና መያዝ ነው ሲል ነግሮናል፡፡ ልብ አድርጉ የዩኤንዲፒ ማስታወሻ የተጻፈው ከጥቅምት 24 በኋላ የካቲት 9 ቀን ነው፡፡ በዚያች አጭር የሦስት ወር ጊዜ ውስጥ እንኳን የመንግሥታቱ ድርጅት ማስታወሻ እውነትን አላይም ያለውን ዓለም አቀፋዊውን ማኅበረሰብ ምን እንደሚለው ይገርማል፡፡ በዚህ ረገድ ፎሬን ፖሊሲ ራሱ የጻፈውን እንዳለ አንብቡት፡፡

The U.N. agency echoed many of the Ethiopian government’s grievances, citing the “strong sentiment” that the international community is applying “double standards” in its dealing with the Ethiopian government and the renegade Tigrayan political movement. “There is no evidence of any early action taken by the international community to stem what was known to be a 2-year-old cancer in Ethiopia’s body-politic.” The memo stated.

የሚገርመው ከዚያም በላይ የሚያሳፍረኝ ይህንን ሜሞ ራሱን ፈልጎ አግኝቶ፣ አደባባይ አውጥቶ ይህንን እሪ ብሎ እየጮኸ፣ ግን የታፈነውን ሰላላ ድምፅ አንድ የትግል ግንባር ማድረግ የቻለ አቅም ማጣታችን ነው፡፡

በዚህ በያዝነውና በመገባደድ ላይ ባለው በሐምሌ ወር ውስጥ ዓቃቤ ሕግ ሁለት አዲስ ክሶችን የመመሥረቱን ወሬ ሰምተናል፡፡ እዚህን ክሶች (ወደ ዝርዝሩ መግባት የሚያስችል መረጃ፣ በራሱ በክስ ደረጃ እንኳን ማግኘት ችግር ስለሆነና ስላልቻልኩ ከዚህ በላይና ስለክሱ ስሰማ ያሰብኩት ያህል ዝርዝር ውስጥ መግባት ይቸግራል) ደጋግመን የጠየቅነውን ጥያቄና ጥቅምት 24 ቀን ምን ሆነ? ወዘተ የሚለውን ጥያቄ በሰፊውና በሥርዓት ያስመዘግባሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ይህን የምለው ከፍርድ ቤት ዋና ዋና ተግባሮች መካከል አንዱ ይህንኑ ታሪክ እንዲነገር ማድረግ፣ መመዝገብ ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ የፍርድ ቤቶች፣ በዋናውና ፊት ለፊት በሚታየው የዳኝነት ሥራቸው ውስጥ የሚገኝ ትክል (ኢንኸረንት) ተግባር ከዚህ በፊትም ሊጨባብጠን ሞካክሮ ነበር፡፡ ካመለጡ ዕድሎች ጋር አብሮ አመለጠ እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ በደርግ ዘመን የተፈጸሙትን ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች እፋረዳለሁ ብላ በወሰነችበት ወቅት የተጀመረውና በልዩ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ አማካይነት የተገለጸውና የተሞካከረው ይኼው ነበር፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች በደርግ ኢሠፓ መንግሥት አማካይነት የደረሰባቸውን አረመኔያዊ ወንጀሎች፣ የንብረትና የሀብት ምዝበራ ለመጪው ትውልድ በሀቀኛ መንገድ መዝግቦ ማቆየትና ደግሞ የዚያን ዓይነት የመንግሥት ሥርዓት እንዳይደገም ማስገንዘብና ማስተማሩ ትክክለኛ ታሪካዊ ግዳጅ መሆኑን በማመን…›› ነበር የደርግ ባለሥልጣናትን ለፍርድ ከማቅረብ አስፈላጊትን መካከል አንዱ ምክንያት፡፡ ይህ የተሳካ ስለመሆኑ አፍን ሞልቶ የሚናገር የለም፡፡ አፍን  ሞልቶ መናገር የሚቻለው ያኔ በ1983 ዓ.ም. የተጀመረው ሁሉ አለመሳካቱን ነው፡፡

እነዚህ የጠቀስናቸው አሁን በሐምሌ 2013 ዓ.ም. ፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረታቸው ክሶች በእርግጥም ይህንን ተሞክሮ ያልተሳካ የፍርድ ቤቶች ታሪክ የማስመዝገብ ተግባር ማሳካት አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ ይህ የተሳካ የታሪክ ምዝገባ፣ ወዘተ ተግባር የብዙ ነገሮች አወጣወጥ ውጤት ነው፡፡ ጥቅምት 24 ቀን ምን አምጦ ወለደው? ያን ዕለት ምን ሆነ? ወዘተ የሚለው ጥያቄ መልስ ግን ለመጪው ትውልድ ተዘጋጅቶ እስኪቀርብ ድረስ መጠበቅ የለብንም፡፡ ወይም የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክሱን መመሥረቱን ሲገለጽ እንደ ነገረን ጉዳዩን እንደ ክሱ አቀራረብ ያስረዳሉ የተባሉ 510 የሰው ምስክሮች ተሰምተው፣ የ5,329 ገጽ የሰነድ ማስረጃዎች ተጠንተው፣ ፍርድ ቤትም ውሳኔ ሰጥቶ… እስከዚያ ድረስ መቆየት የለብንም፡፡ በመንግሥት ደረጃ በአንፃራዊ ገለልተኛ ስሜትና መንፈስ ሊነገረንና ልናውቀው የሚገባ የተወዘፈ ጉዳይ ዛሬም አለ፡፡ በዚህ በከበባ ወቅት፣ በዚህ በጦርነትና በጦርነት ሁኔታ ውስጥ ያጣነውና ያጎደለን ከሁሉም በላይ ደግሞ ለመልቲው ዓለም አቀፋዊ ማኅበረሰብ ዓይን ያወጣ አድልኦ ያጋለጠን በዚህ ረገድ ያስመዘገብነው ድክመት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እኮ በዩኤንዲፒ ማስታወሻ መሠረት ደካማና አቅመ ቢስ መስሎ እስኪታይና እስኪቆጠር ድረስ ኃይል መጠቀምን እንቢኝ ብሎ ከርሞ፣ ወደ ኃይል ዕርምጃ የሄደው ተገዶ ነው፡፡ ሰሜናዊ የአገር የጦር ሠፈር ሲጠቃበት ነው፡፡ ይህ በወቅቱ የሕወሓት ወገን ራሱ ያመነው፣ ዜናም ሆኖ የተመላለሰው እውነት እንዴት አሁን፣ ‹‹የትግራይ ጦርነት የተጀመረው የትግራይ ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው ነው›› ማለት ያልተረጋገጠ ሁሌም የሚጠየቅ የመንግሥት አቋም፣ የመንግሥት መከራከሪያ፣ የመንግሥት መከላከያ ብቻ ሆኖ ይኖራል? ለዚህ ያበቃን የእውነትና የውሸት ጉዳይ ሳይሆን፣ እውነት የመናገር የመንግሥት አቅምና ችሎታ አሁንም ገና ያልተፈታና ያልተፍታታ በመሆኑ ነው፡፡             

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...