Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​​​​​​​በየዓመቱ የሚያሻቅበው የተማሪዎች የትምህርት ክፍያ

በዘንድሮው የኑሮ ውድነት የማያማርር የለም፡፡ በእርግጥም አማራሪ ነው፡፡ ገበያው ከአቅም በላይ ሆኗል፡፡ የዜጎች ገቢ ግን አልጨመረም፡፡ በተለይ በደመወዝ የሚተዳደሩና ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ዜጎች በወቅታዊው የዋጋ ንረት ተረትተዋል፡፡

ኑሮው ጣራ ነክቶ የእነሱ ገቢ እዚያው ባለበት ቆሟል፡፡ ኑሮው እንዲህ ተወደደ፣ ገበያው አልቀመስ አለ፣ እየተባለ ባለበት ወቅት የቤት ኪራይ ዋጋና የተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያም ያለ ልኬትና ያለ ምጣኔ እየናሩ መሄዳቸው መድረሻችን የት ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ደግመን ደጋግመን እንድንጠይቅ ያደርጋል፡፡

በተደጋጋሚ እንደተገለጸው አሁን ላለንበት የዋጋ ንረት የደረስነው በአንዴ አይደለም፡፡ ወደ ሁለት አሠርት ለሚጠጋ ጊዜ በአናት፣ በአናቱ እየጨመረ የመጣ ነው፡፡ ይህ እውነት የሚያስማማ ቢሆንም፣ ችግሩ ከታወቀ በኋላ ቢያንስ ንረቱ ከፍ እንዳይልና ጫናው እንዳይበረታ ያለመደረጉ ችግሩን አብሶታል፡፡ በዚህ ጉዳይ መፍትሔው ላይ አለመድከሙ ያመጣው ችግር ወቅታዊውን የዋጋ ንረት ከየትኛውም ጊዜ በላይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ወደ መደብር ሄደን የምንገዛቸው ትንንሽ ዕቃዎች ሳይቀሩ ዋጋቸው ጣራ ነክቷል፡፡ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችም በየጊዜው የሚወጣላቸው ዋጋ የእያንዳንዱን ሸማች ደጃፍ አንኳኩቷል፣ አማርሯል፡፡  

በወቅታዊው የዋጋ ንረት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በተለያየ መንገድ መግለጽ ይቻላል፡፡ ይህ የሸማቹን አቅም እያደከመ ያለው የኑሮ ውድነት የመፍትሔ ያለህ እየተባለ ባለበት ወቅት፣ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶች ለወላጆች እየደረሰ ያለ መልዕክት ደግሞ ነገሮችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል፡፡

አብዛኞቹ የግል ትምህርት ቤቶች ለ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የሚያስከፍሉትን ክፍያ ዋጋ እንደሚጨምሩ አስታውቀዋል፡፡ በግል ከሰማሁት አነስተኛ የዋጋ ጭማሪው 30 በመቶ ነው፡፡ አንድ ተማሪ እስካሁን በወር 2,000 ብር ይከፍል ከሆነ በትምህርት ቤቶቹ አዲስ ዋጋ ሥሌት መሠረት ከዚህ በኋላ 2,600 ብር ይከፍላል ማለት ነው፡፡

ይህ እንግዲህ አነስተኛ የተባለው የዋጋ ጭማሪ መጠን ነው፡፡ 40 በመቶ፣ 50 በመቶ እና 60 በመቶ የጨመሩ እንዳሉም እየተነገረ ነው፡፡ እንግዲህ አሁን ባለው የዋጋ ንረት እየተፈተነ ያለ ሸማች እንዲህ ያለ የትምህርት ቤት ዋጋ ጭማሪ ሲመጣበት ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያቅትም፡፡ እችላለሁ ያለ ሊከፍል ይችላል፡፡

የአብዛኛው ወላጅ ስሜት ግን በዚህ የኑሮ ውድነት ይህንን የትምህርት ቤት የዋጋ ጭማሪ መቋቋም ከባድ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ አንዳንዶችም የተደረገውን ጭማሪ ለመሸፈን የሚያስችል አቅም እንደማይኖራቸው በማመን የመንግሥት ትምህርት ቤት አስገባለሁ ወደሚል እየሄደ ነው፡፡ የመንግሥቱም ትምህርት ቤት ከተገኘ ማለት ነው፡፡

የወላጆች ውሳኔ ምንም ይሁን ምን በዚህ ጉዳይ መጠየቅ ያለበት ጉዳይ ግን አለ፡፡ አሁን አብዛኛዎቹ የግል ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎታቸው የሚጠይቁት ዋጋ አግባብ ነው አይደለም? ከሚለው ይጀምርና እነዚህ ትምህርት ቤቶች ተቆጣጣሪ አላቸው ወይ? የሚለው ጥያቄ ይከተላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በወር በሺዎች የሚቆጠር ክፍያ የሚጠይቁ ትምህርት ቤቶች የዋጋ ትመና ምንን መሠረት ያደረገ እንደሆነ አይታወቅም፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን በየዓመቱ የሚያደርጉት ጭማሪ ልክ የሌለው ነው፡፡ ለጭማሪ የሚሰጠው አብዛኛው ምክንያትም የቤት ኪራይ መናርና መምህራን ከፍተኛ ደመወዝ መጠየቃቸው ነው፡፡ የተወሰኑ ሊከፍሉ የሚችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስላሉ የመማሪያ ዋጋን እንዲህ ባለ ደረጃ እንዲያሻቅብ የሚያደረግበት ምክንያት ሁሌም የሚገርመኝ ነገር ነው፡፡

በተከፈለው ገንዘብ ልክ ዕውቀት ይሸመታል ብሎ ማመን፣ ትምህርት ቤቶቹ የሚያደርጉት ፉክክር፣ አንዳንዴም ወላጆች ልጄን እዚህ ነው የማስተምረው ለማለት የፈጠሩት አመለካከት ብዙ ነገሮችን አበላሽቷል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ትምህርት ቤቶች በተለየ ታይተው፣ በየዓመቱ የሚደረገው ጭማሪ ምንን መሠረት አድርጎ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡

ቀድሞም ቢሆን ብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች የሚጠይቁት ዋጋ የተጋነነ መሆኑ ሳያንስ፣ ዓመት በደረሰ ቁጥር ወላጆችን እንወያይ ብሎ በመጥራት በመቶኛ እየተሠላ የሚደረገው ጭማሪ ቅጥ ካጣ ቆይቷል፡፡ በአንድ ዓመት ልዩነት 30 በመቶ፣ 50 በመቶ ጨምሩ ማለት ምን የሚሉት ነገር ነው፡፡

የትምህርት ክፍያ የዋጋ ጭማሪ ወላጆች ልጆቻቸውን ከፈለክ አስተምር ወይም አታስተምር የሚል መልዕክት ያለው ጭምር ይመስላል፡፡ ዕውቀትን እንደ ሸቀጥ የቆጠሩትም ይመስላሉ፡፡ ይህ ዕሳቤ እንዲሁ ከቀጠለ የነገ አገር ተረካቢ ዜጎችን እንዴት ማፍራት እንደሚቻል ግራ ያጋባል፡፡ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ካልተከፈለ፣ ዕውቀት መገብየት ካልተቻለና አቅም ያለው ብቻ ያስተምር የሚባል ከሆነ የዚህች አገር ወደፊት ዕጣ ፈንታ ሊያሳስበን ይገባል፡፡

የትምህርት ቤቶች አገልግሎት ክፍያ በተለየ መታየትና ቁጥጥር ሊደረግበት የሚገባ ነው፡፡ ጉዳዩ በዚህ ከቀጠለ የሚፈጥረውንም ማኅበራዊ ቀውስ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ቢቀር እንኳን አንድ ትምህርት ቤት ጭማሪ ማድረግ የሚችለው ‹ከዚህን ያህል በመቶ ያልበለጠ ነው› መባል ካልቻለ፣ እንዲሁም ይህንንም በሕግ ማስደገፍ ካልተቻለ ዘርፉ የጉልበተኞች መጫወቻ ይሆናል፡፡

አሁንም ለ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን እየተደረገ ያለውን የዋጋ ጭማሪ በማጥናት የሚመለከተው አካል ዕርምጃ ይውሰድልን፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት