Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሲሚንቶና የግንባታ ግብዓቶች እጥረትና የዋጋ ንረት ቸርቻሪዎችንና ተጠቃሚዎችን እንዳማረረ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሲሚንቶን ጨምሮ በሌሎች የግንባታ ዕቃዎች እጥረትና የዋጋ ንረት ሳቢያ ቸርቻሪዎችና ተጠቃሚዎች መማረራቸውን፣ አንዳንዶችም መደብሮቻቸውን እስከ መዝጋት የሚደርስ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው ተገለጸ፡፡

በሲሚንቶ ግብይት ላይ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት በሚል መንግሥት የምርቱን ተደራሽነት ለማስተካከል ያደርግ የነበረው ክትትልና ቁጥጥር ቀድሞ በነበረው የግብይት ሥርዓት እንዲፈጸም ከሁለት ሳምንት በፊት መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ሆኖም ሪፖርተር ባደረገው የሲሚንቶ ገበያ ቅኝትና ካነጋገራቸው የሲሚንቶ ነጋዴዎች እንደተረዳው በመሸጫ መደብሮች ካለመገኘቱም ባሻገር በተገኘው ሲሚንቶ ዋጋ ላይ በተስተዋለው ጭማሪ መማረራቸውን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

በዊንጌት አካባቢ ሲሚንቶ በመሸጥ የሚተዳደሩት አቶ እንድሪስ ከድር ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ሲሚንቶ አሁንም እጥረቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ የምርት እጥረቱ እንዳለ ሆኖ ሰሞኑን መንግሥት በገበያ ትስስር ያደርግ የነበረውን ክትትል ሲያነሳ፣ በምርቱ ላይ የዋጋ ጭማሪ መስተዋል እንደ ጀመረና አቅርቦትም ባለመኖሩ ይኼ ነው የሚባል ለውጥ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

አቶ እንድሪስ በአሁኑ ጊዜ ሲሚንቶ ከ700 እስከ 720 ብር እየተሸጠ እንደሆነ አስረድተው፣ ቀደም ሲል በአራት መቶ ብር ያህል ግብይቱ ይከናወን እንደነበር አስታውሰው፣ ለመጨረሻ ጊዜ ሲሚንቶ ካገኙ ከወር በላይ ጊዜ እንደተቆጠረና በዚህ ወቅት የእሳቸውን መደብር ጨምሮ በአጎራባች የሚገኙት መደብሮችም ዝግ መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡

ሲሚንቶ የሚያከፋፍሉ ወኪሎችን ከእጥረቱ ጋር ተያይዞ ስላለው ጉዳይ በተደጋጋሚ እንደሚጠይቁ የተናገሩት አቶ እንድሪስ፣ ፋብሪካዎች ከዚህ በፊት የተቀበሏቸውን የሲሚንቶ ፍላጎት ጥያቄዎች ወረፋ ሊያስተናግዱ ይገባል በሚል በመንግሥት ጥያቄ በመቅረቡ የተነሳ፣ በዚህ ወቅት የሚጫነው ሲሚንቶ በአብዛኛው ከዚህ ጋር ለተያያዘ ጉዳይ እየዋሉ ነው የሚል ምላሸ ማግኘታቸውን ያስረዳሉ፡፡

ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ሲሚንቶ አግኝተው እየሸጡ የሚገኙ ግለሰቦችም እያገኙ ያሉት ቀደም ሲል ወረፋ ደርሷቸው ካገኙ አካላት በመግዛት እንደሆነ ያስረዱት የሲሚንቶ ነጋዴው፣ ለሲሚንቶ ነጋዴው ምርቱን ሲሸጡ ከ660 እስከ 670 ብር በላይ በሆነ ዋጋ እንደሆነና በዚህም ሳቢያ ዋጋው ሊንር እንደቻለ አስታውቀዋል፡፡

የብረት ዋጋ ጭማሪ እንዲሁ በመስተዋሉ ንግዱ እያሽቆለቆለ እንደሆነ ያስረዱት አቶ እንድሪስ፣ በዚህም ሳቢያ የሰውም የመግዛት ዝንባሌ እየተመናመነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ የአንድ ዕቃ መርከስና መወደድ የሚወሰነው ከምርት ማምረት ጋር የሚገናኝ በመሆኑ፣ ፋብሪካዎች በበቂ ሁኔታ እንዲያመርቱና ከውጭ የሚገባም ከሆነ የምርት አቅርቦቱ ላይ በመሥራት ችግሩን ማቃለል እንደሚቻል፣ ነጋዴውም ምርቱ ቶሎ እንደሚተካ ስለሚረዳ በዝቅተኛ ትርፍ የሚሸጥበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር በመገናኛ አካባቢ የሲሚንቶና ሌሎች የግንባታ ግብዓቶች ሽያጭ በሚከናወንባቸው መደብሮች አካባቢ ቅኝቶችን ያደረገ ሲሆን፣ በዚህም ለወትሮው ከፍተኛ የሲሚንቶ ግብይት እንቅስቃሴ የሚከናወንባቸው አብዛኞቹ የሲሚንቶ መሸጫ መደብሮች ዝግ ናቸው፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በመገናኛ አካባቢ የሲሚንቶና የግንባታ ግብዓቶች አቅራቢ ነጋዴ እንደገለጹት፣ ከሰሞኑ በሚመለከተው አካል ሲሚንቶ ቀድሞ በነበረበት የግብይት ሥርዓት ይፈጸም ተብሎ የተነገረው በእሳቸውና በሌሎች መሰል ነጋዴዎች የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ምንም ያመጣው ለውጥ የለም፡፡ በዚህ ወቅት የሲሚንቶ እጥረት እንዳለና በተንጠባጠበ መልክ የሚገኘውም የሚቀርብላቸው ሲሚንቶ ከሚያቀርቡ ወኪሎች ሳይሆን፣ ከሌሎች ነጋዴዎች (ደላሎች) እንደሆነና ዋጋውም በእነሱ እንደሚወሰን ይገልጻሉ፡፡

ሲሚንቶ እንዲያከፋፍሉ የተመደቡ ወኪሎችን ምርቱ ለምን እንደማይቀርብ ለሚያቀርቡት ጥያቄ የለም የሚል ምላሽ እንደሚያገኙ ያስረዱት ግለሰቡ፣ በከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የገዙትንም ሲሚንቶ የሚገዛቸው ባለመኖሩ እንደተቀመጠ ነው ብለዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ሲሚንቶን አከፋፋዩ በቀጥታ ታች ላለው ነጋዴ ወይም ቸርቻሪ እንዲያቀርብ ካልተደረገ የሚለወጥ ነገር እንደማይኖር ያስረዳሉ፡፡

እንደ ሲሚንቶ ሁሉ በአርማታ ብረት ውጤቶች ላይም ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየተስተዋለ እንደሆነ የገለጹት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በመገናኛ አካባቢ የአርማታ ብረት ሱቅ ባለቤት፣ ለቤቶች ግንባታ በብዛት በሚፈለጉት ባለ ስምንት፣ አሥርና አሥራ ሁለት ቁጥር የአርማታ ብረት ምርቶች ላይ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የ80፣ የ135 እና የ195 ብር የዋጋ ልዩነት በእያንዳንዱ ምርት ላይ እንደተስተዋለ ገልጸዋል፡፡

በገላን ከተማ የመኖሪያ ቤት እየገነቡ እንደሚገኙ ለሪፖርተር የገለጹት ወ/ሮ ብዙአየሁ ኃይሌ በበኩላቸው፣ እሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ሲሚንቶ ነጋዴው በነፃ ገበያ መሠረት ይሽጥ ተብሎ ከተነገረ ወዲህ ለወትሮ ያልነበረው ሲሚንቶ በመደብሮች እየቀረበ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ዋጋው በፊት ከሚሸጥበት ከፍተኛ የሆነ ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ በግንባታ ፈቃድ አማካይነት ሲሚንቶ የማግኘት ዕድል ያገኙ ሰዎችም ለቸርቻሪዎች ሲሚንቶ በከፍተኛ ዋጋ ከመሸጣቸው ጋር ተያይዞ ለመጨረሻ ተጠቃሚው የሚደርሰው በጣም ውድ በሆነ ዋጋ እንደሆነ ገልጸው፣ የተጀመረ ግንባታን ለማጠናቀቅ በሚል እስከ 700 ብር እያወጡ በስፋት የማይታወቁ የሲሚንቶ ምርቶችን ጭምር እየገዙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የሲሚንቶና የግንባታ መሣሪያ ነጋዴዎች እንዳስታወቁት፣ የግንባታ እንቅስቃሴ በተዳከመበት በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነት ጭማሪዎች መስተዋላቸው ገበያውን አቀዛቅዞታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለወትሮው በእንቅስቃሴው ምክንያት የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው የጉልበት ሠራተኞችን ሥራ ከማሳጣቱም በላይ፣ ቸርቻሪዎችም መደብሮቻቸውን ለመዝጋት ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ እንዳደረጋቸው አስታውቀዋል፡፡

በዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ውስጥ ያለ የሪፖርተር ምንጭ እንደገለጸው ከሆነ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑ የሲሚንቶ ምርት ግብዓቶች ከውጭ አገሮች የሚገቡ ስለሆነ፣ በኢትዮጵያ ያጋጠመው የብር የመግዛት አቅም መዳከም የምርት ወጪዎችን አንሯል፡፡ በሌላም በኩል ከውጭ የሚገቡት ግብዓቶች በሚመረቱበት አገርም ዋጋ ጨምረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ፋብሪካው በኅዳር ወር ይሸጥበት ከነበረው 295 ብር ወደ 350 ብር ዋጋ ለመጨመር ተገዷል፡፡

ከማምረት አቅም አንፃር ዳንጎቴ የአቅሙን ከ92 እስከ 95 በመቶ ተጠቅሞ እያመረተ እንደሚገኝ የገለጹት ምንጩ፣ ብዙዎቹ ፋብሪካዎች ግን ላለፉት ሁለት ዓመታት የአቅማቸውን ግማሽ በመቶ እያመረቱ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ወኪሎችና ሻጮች የምርት እጥረት ማለታቸው ብዙም የሚገርም እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሪፖርተር ምንጭ እንዳስታወቁት፣ ቀድሞውንም ቢሆን መንግሥት ዋጋ የመወሰን ፍላጎት አልነበረውም፡፡ የሥርጭትና የዋጋ ቁጥጥር ኃላፊነትን ሲሚንቶ ፋብሪካዎች መውሰድ እንዳለባቸው የሚመለከተው አካል በደብዳቤ ማሳወቁን ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚሰጠውን ምላሽ ለማካተት በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት ሊሳካ አልቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች